ምርጫ ቦርድን እንዳሻቸው የሚያስደንሱት የገዢው ቡድን ሹማምንት፣ በዘንድሮው ምርጫ እንደለመዱት በቀላሉ አታለውና አጭበርብረው ማለፍ እንደማይቻላቸው የተገነዘቡ ይመስላል፡፡ ለዚህም ነው፣ በቀደሙት ምርጫዎች ህወሓት/ኢህአዴግ ተቃዋሚዎች ምርጫ ጥለው ወጥተው በአለም እንዳያሳጡት፤ የተለያዩ የማባበያና የማግባቢያ መንገዶችን የማይሳተፉ ፓርቲዎች እንዲሰረዙ የሚያደርግ ድንጋጌ አስቀምጦ ነበር፡፡ የዘንድሮው ምርጫ ግን ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ለተላተመው ገዢው ቡድን ግዙፍ “ናዳ” ይዞ እንደመጣ ያፈጠጠ ሀቅ ሆኗል፡፡ ይህንን የተገነዘበው ገዢው ቡድን፣ ባልተለመደ ሁኔታ ሀቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫ 2007 እንዳይሳተፉ የማከላከል እርምጃ በመውሰድ ላይ ይገኛል፡፡
ህወሓት/ኢህአዴግ፣ የ2007 ምርጫን ከጅምሩ ለማጭበርበር የተጠቀመበት ስልት ሁለት መንገዶችን የተከተለ ነበር፡፡ የመጀመሪያው፣ በምርጫው ሂደት ህዝብን ያነቃሉ ያላቸውን ጋዜጠኞችና ጦማሪያንን በማሰር እንዲሁም ተአማኒነት እያተረፉ የነበሩ የሚዲያ ተቋማትን የመዝጋት ሂደት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በምርጫው እንቅስቃሴ የህዝብን ቀልብ ይገዛሉ ያላቸውን እና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መሀከል መቀራረብን ለማምጣት የሚተጉ ወጣት ፖለቲከኞችን የማሰር እርምጃ ነው፡፡ ህወሓት፣ ከላይ የተጠቀሱትን እርምጃዎች ቢወስድም፤ የነፃነት ትግሉ ከመዳከም ይልቅ በተባበረ ክንድ በህዝባዊ እንቢተኝነት ጨቋኙን የህወሓት ኢህአዴግ አገዛዝ ለማስወገድ ወደሚያስችል ህዝባዊ ንቅናቄ ከፍ ብሏል፡፡
በዚህ ሂደት የተደናበረው ገዢው ቡድን፣ ፓርቲዎችን ከምርጫ ብቻ ሳይሆን ከአጠቃላይ የፖለቲካው ሜዳ ለማስወገድ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ አንድነት ፓርቲ እና መኢአድ፣ በህወሓት የተሸረበባቸውን ሴራ ለማክሸፍ በተደጋጋሚ ጠቅላላ ጉባኤ ቢያካሂዱም፤ ምርጫ ቦርድ አላየሁም አልሰማሁም ማለትን መርጧል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ፣ የምርጫ ቦርድን ኢ-ፍትሀዊነት በአደባባይ በመቃወም፣ ቦርዱ የጠራቸውን ስብሰባዎች ረግጦ በመውጣቱ ይቅርታ እንዲጠይቅ፤ ህወሓት በምርጫ ቦርድ ሹምባሾች በኩል ትዕዛዝ እስከማስተላለፍ ደርሷል፡፡ ሰማያዊ፣ ይቅርታ ለመጠየቅ ፍቃደኛ ባለመሆኑም፤ “የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ” እንደተሰጠው ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡ ይህ የህወሓትና የምርጫ ቦርድ የዕውር ድንብር እንቅስቃሴ የሚያስተላልፈው መልዕክት አለው፡፡
ህወሓትና ምርጫ ቦርድ ምን እያሉን ነው?
ህወሓት/ኢህአዴግ፣ የመንግስትነት ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ ጠንካራ የለውጥ እንቅስቃሴ እንደተደረገበት በብዙዎች የሚታመነው ምርጫ 97 ነው፤ በወቅቱ ህወሓት “ህዝብ ይመርጠኛል፣ ጠንካራ ተቃዋሚ የለም” በሚል የተሳሳተ ምልከታ፤ በአንፃራዊነት የፖለቲካ ምህዳሩን ገርበብ በማድረጉ የለውጥ ኃይሎች የገዢውን ቡድን መንበር ለማነቃነቅ በቅተው ነበር፡፡ ሆኖም ህወሓት/ኢህአዴግ፣ ከምርጫ 97 በኋላ ባወጣቸው ቀፍዳጅ ህጐች፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የምርጫም ሆነ የፓርቲ ፖለቲካ እንዳይሰራ አድርጓል፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና አመራሮችን ህዝብን ለማሸበር ባወጣው ህግ አስታኮ አስሯል፡፡ ሃቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎችንም ወደ ተለጣፊ ፓርቲነት አውርዷል፡፡ ይህ ድርጊት፣ ፓርቲዎች እራሳቸውን በብቁ የሰው ኃይል፣ በገንዘብና በቁሳ-ቁስ በማደራጀት ጠንካራ ተቋማዊ መሰረት ፈጥረው የአገዛዝ ስርአቱን ለማስወገድ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንዲመክን ገዢው ቡድን ተግቶ እንደሚሰራ ነው፡፡
እነዚህ ሁሉ ድምር ሁኔታዎች፣ የነፃነት ትግሉ የፓርቲ ፖለቲካ ላይ ብቻ መንጠልጠል እንደሌለበት የሚያመላክቱ ከመሆናቸውም በላይ፤ ህወሓት/ኢህአዴግ እና ምርጫ ቦርድ የአፈና ስርዓቱ የሚቀየርበት መንገድ የምርጫና የፓርቲ ፖለቲካ ትግል እንዳልሆነ በአስር ጣታቸው ፈርመው በማረጋገጥ ላይ ናቸው፡፡
ከለውጥ ሀይሎች ምን ይጠበቃል?
የነፃነት ትግል፣ በፓርቲም ያለ ፓርቲም የሚካሄድ መሆኑን እንዲሁም ነፃነት በአንድ ወጥ ቀኖናዊ የትግል ስልት ብቻ የሚተገበር አለመሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ነፃነትን ያጐናፅፈናል፣ ባልነው በየትኛውም የትግል ስልት መሳተፍም ስህተት የለውም፡፡ ሆኖም በሀገራችን ካለው ነባራዊ እውነታ አንፃር ህወሓት ያነበረውን የአገዛዝ ስርነት ለማስወገድ፣ ህዝባዊ እምቢተኝነት ብሎም አብዮት የለውጥ ኃይሎች ተገፍተው እየገቡበት ያሉ የትግል ስልቶች ናቸው፡፡
ህዝባዊ እምቢተኝነትም ሆነ አብዮት፣ የተሳኩ እንዲሆኑ ሁሉም የለውጥ ሀይሎች በአንድ አላማ ስር መሰባሰብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በነፃነት ትግል ውስጥ የአይዲዮሎጂና የትግል ስትራቴጂ ልዩነቶች ትኩረት ሊያገኙም አይገባም፡፡ በህወሓት የአገዛዝ ስርአት ላይ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን የጀመሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማስተባበር፤ ህዝባዊ እንቢተኝነትን ማቀጣጠል ከለውጥ ኃይሎች የሚጠበቅ የቤት ስራ ነው፡፡
ምርጫ ቦርድ፣ በራሱ ጊዜ የትግሉን እንቅስቃሴ አጡዞታል፤ ሀቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎችንም ከምርጫ የማስወጣትና በማስጠንቀቂያ የማሸማቀቅ ሙከራዎችን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ አሁን ያለው ብቸኛ አማራጭም በህዝባዊ እምቢተኝነት ህወሓት መራሹ ስርዓት፤ ግብአተ-መሬቱ የሚፈፀምበትን ዕልህ አስጨራሽ ትግል ማስጀመር ብቸኛው አማራጭ እየሆነ ነው፡፡