July 7, 2024
ጠገናው ጎሹ
ብዙ መልካም የለውጥ አጋጣሚዎች በአሳዛኝ ሁኔታ እንዲጨነግፉ ያደረግንበት የፖለቲካ ማንነታችን (ታሪካችን) መሪር ትምህርት ሆኖን አሁንም ሌላ መልካም እድል እጃችን ላይ እንዳይጨነግፍ (እንዳይመክን) ከምር የምንፈልግ ከሆነ ይህንን በእጅጉ አስቸጋሪ (ፈታኝ ) የሆነ ጥያቄ በአግባቡና በወቅቱ ለመመለስ ፅዕኑና የማይታጠፍ ዝግጁነትን ግድ ይለናል።
የመከረኛው የአገሬ ህዝብ መሠረታዊና አንገብጋቢ ጥያቄ የዜግነት እና የብሔረሰብና የቡድን መሠረታዊ መብቶች የሚከበሩባት ዴሞክራሲያዊት አገር እውን እንድትሆንለት እንጅ በየመንደሩና በየቋንቋ ክልል ተከልሎለት አትድረሱብኝ ብቻ ሳይሆን የእኔ ሰዎች ያልሆናችሁ ያለምንም ጥያቄ ለቃችሁ ካልወጣችሁ በሚል ለመግለፅ የሚያስቸግር ኢሰብአዊ ድርጊት እንዲፈፀም በሚያደርግ የእኩያን ገዥ ቡድኖች ሥርዓት ሥር ሆኖ የመከራና የውርደት ዶፍ ሰለባ ሆኖ ለመኖር አልነበረም ። ግን ሆነ ። ከሆነም ይኸውና ከሦስት አሥርተ ዓመታት በላይ ሆነው።
ሰብአብዊ ፍጡርነትን ከመሠረታዊ የሰብአዊና የዜግነት መብቶቹ አውርደውና አዋርደው የጎሰኝነትና የመንደርተኝነት ፖለቲካ (the politics of tribalism and parochialism) ሰለባ ባደረገው የሩብ ምእተ ዓመት ህወሃት መራሽ ሥርዓት ውስጥ የፍፁም አሽከርነት ሚና የነበራቸው ኢህአዴጋዊያን ከስድስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በኦህዴዳዊያን/በኦነጋዊያን የበላይነት እና ወራዳነት በማይሰለቻቸው ብአዴናዊያንና ደህዴናዊያን ታማኝ አሽከርነት የመከራውንና የውርደቱን ስፋትና አስከፊነት እንኳንስ ለማመን ለመስብም በሚከብድ ሁኔታ ቀጥለውበታል ።
ለሩብ ምዕተ ዓመት በህወሃት ጠርናፊነት ሥር ለቆየው እጅግ መርዘኛና አደገኛ የጎሳ አጥንት ስሌት ሥርዓተ ፖለቲካ በፍፁም አሽከርነት (የሰው ሥጋ ለባሽ መሣሪያነት) ሲያገለግሉ የነበሩት የኦህዴድ/ኦነግ ፖለቲከኞች ህዝብ በእኩያን የህወሃት ፖለቲከኞች ላይ ከነበረው ምሬትና ጥላቻ የተነሳ የተቀጣጠለውን እና ነገር ግን በአሳዛኝ መልኩ ከግልብ ስሜት ያላለፈውንና በአብይ አህመድ የቅጥፈት፣ የሴራ፣ የሸፍጥ፣ የብልግና እና የጭካኔ ፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ የተጠለፈውን የተቃውሞ እንቅስቃሴ በወቅቱና በአግባቡ ተረድቶ ከምር የሆነ የእርምት እርምጃ የሚወስድ የፖለቲካ ድርጅት (አካል) ባለመኖሩ እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ማህበረሰብ ወይም እንደ ህዝብ ከሰብአዊ ፍጡርነት በታች በሚያወርድ ፖለቲካ ወለድ የመከራና የውርደት አዙሪት ውስጥ እንደተዘፈቅን ቀጥለናል።
ፈጣሪያቸው፣ አሳዳጊያቸውና አዛዣቸው የነበረው ህወሃት የሰጣቸውን ኢህአዴግ የየሚል ስያሜ ይዞ መቀጠሉ ያሰቡትንና የተዘጋጁበትን በተረኝነት ሁሉን የመጠቅለል እጅግ ሴረኛ፣ ሸፍጠኛና አረመኔያዊ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖልቲካ ዓላማቸውን ሊያበላሽባቸው እንደሚችል ሲያውቁ “አዲስ” ስያሜ ማወጅ የግድ ነበር። ለዚህ ደግሞ እምነታችን ነው ከሚሉት የብልፅግና ወንጌል በመውሰድ ለአገራዊ መከራና ውርደት ተጠያቂ የሆነውንፓርቲቸውን ብልፅግና ብለው ሰየሙት። ብልፅግና የሚለውን ፅንሰ ሃሳብም በእጅጉ አጎሳቆሉት። እናም ነገረ ሥራቸው ሁሉ በማጭበርበር ( በማታለል) እና በእኩይ ተውኔት ተጀምሮ ወደ ጣረሞታዊ የፖለቲካ ተውኔት ሊያመራ እንደሚችል ግልፅና ግልፅ ነበር። አሁን እየታዘብን ያለነውም ይህንኑ ሃቅ ነው።
የእኩይ ዓላማ ማስፈፀሚያ የሆነውን የፖለቲካ ፓርቲያቸውን በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በተፈጠረና እንዲስፋፋ እየተደረገ በመጣ የብልፅግና ወንጌል ሃይማኖታዊ እምነት (“ክርስቲያንነት”) ስም ሰይመው የሸፍጥ፣ የሴራ፣ የእኩይና የጨካኔ አገዛዛቸውን የተቀደሰ እንደሆነ ሲሰብኩንና ሊያሳምኑን ሲሞክሩ ነገረ ሥራቸው ከሰው አልፎ ፈጣሪንም የሚጋፋ በመሆኑ ቢያንስ አደብ እንዲገዙ የሚያደርግ የመሠረታዊ ለውጥ ሃይል (ድርጅት) መፍጠርና ማጎልበት ብንችል ኑሮ የሆነውንና እየሆነ ያለውን የመከራና የውርደት ስፋትና አስከፊነት ሲሆን በማያዳግም ሁኔታ እናስወግደው ቢያንስ ግን ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን ማድረግ እንችል ነበር። አሁንም ያንን እድል ካበላሸነው እኩያን ገዥ ቡድኖች አሁን ያሉበት ጣረሞታዊ የፖለቲካ ተውኔት ይበልጥ ህይወት ዘርቶና ጎልብቶ የመከራውንና የውርደቱን እድሜ ያራዝመዋል።
ክርስቶስ ሳይቀር የተጋራውን የሰው ልጆችን ደስታና ሃዘን ወይም እፎይታና መከራ ወይም ሰላምና ሰላም ማጣት ፣ ወዘተ በዋናነት በቁሳዊ ሃብት ከሚገኝ ደስተኛነት ወይም እርካታ ጋር በማቆራኘት የወንጌልን ምንነት፣ ለምንነት፣ እና እንዴትነት ለዓለማዊ ብልፅግና (ቱጃርነት) እና ልክ ለሌለው ሰው ሠራሽ ፍላጎታቸው ማስፈፀሚያነት እያዋሉት መሆኑን አደገኛ ሁኔታ ሊያሳስበን ይገባል። እንዲህ አይነቱ ሃይማኖታዊ እምነ ትን ከፖለቲካ ጋር የማቀላቀል አደገኛ ተውኔተ ጣረሞት በወቅቱና በአግባቡ ካልገታነው በቀላሉ ወደ ማንወጣው ቀውስ ነው የምንገባው።
ከሰሞኑ የምንታዘበው የእኩያን ገዥ ቡድኖች ብዙ አፋኝና አደገኛ አዋጆችን የማወጅ፣ በምክክር ኮሚሽነርነት ስም ወራዳ ሽፋን ሰጭ የሆኑትን ኮሚሽነሮች ከቦታ ቦታ እያንቀሳቀሱ ርካሽ ፕሮፓጋንዳ የማሰራጨት፣ ካድሬዎቻቸውን እና አድርባይና ወራዳ ግለሰቦችን አሰባስበው የሰላም ካውንስል በሚል የጣረሞታዊ ተውኔታቸው አካል የማድረግ፣ መብት፣ ነፃነት ፍትህ ፣ሰላም እና የጋራ እድገት በሚጠይቅ ህዝብ ላይ ጨካኝ ሠራዊታቸውን ይበልጥ ጨካኝ እንዲሆን የማድረግ ፣ አሻንጉሊታቸው በሆነው ፓርላማ ተብየ ፊት ቀርበው የውሸት፣ የሴራ፣ የሸፍጥ፣ የዝርፊያ እና የጭካኔ ቅርሻታቸውን የማቀርሸት፣ ወዘተ የሚነግረንና የሚያሳየን ጣረሞታዊ (deeply desperate /last breathe of death) በሆነ ሁኔታ ላይ የመገኘታቸውን ግዙፍና መሪር እውነት ነው።
እናም ጥያቄው የሆነውንና እየሆነ ያለውን ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት ያሉትን መልካም ሁኔታዎች (የፋኖ እና የዓላማውና የግቡ ተጋሪ ወገኖች ሁለገብ ተጋድሎዎችን) ተጠቅመን የእኩይ ገዥ ቡድኖች ጣረሞታዊ ተውኔት ወደ ሙሉ ህልውናው በመመለስ የግፍ ሙቶችና የቁም ሞት ሰለባዎች አድርጎን እንዳይቀጥል ማድረግ የመቻል ወይም ያለመቻል ጥያቄ ነው።
ራሱንና ቤተሰቡን ለህይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን አሳጥቶ ወደ ፍፁም ድህነት እንዲወርድ ያደረደው የባለጌዎች፣ የሙሰኞችና የጨካኙ አገዛዝ መሆኑን አሳምሮ የሚያውቀው ምሁር የህብረተሰብ ክፍል ቢያንስ እጆቹን ወደ ሰማይ ዘርግቶ ጎዳና ላይ ወይም አደባባይ ላይ በመውጣት “ለምን፣ እንዴትና እስከመቸ የቁም ሞት ሆኘ የመቃብር ሞቴን እጠብቃለሁ?“ በሚል ራሱን በመፈተሽ የገዥዎችን ጣረሞታዊ ተውኔት ወደ የማይቀርለት መቃብር ለመሸኘት የሚደረገውን እልህ አስጨራሽ ትግል አግዞ ለውጤት ማብቃት ይኖርበታል።
የዘመናት ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት ሰለባ የሆነውን የአገሬ ህዝብ አንቅቶና አደራጅቶ መሠረታዊው የዜግነትና የሰብአዊ መብት የሚረጋገጥበትና የሚከበርበት ዴሞክራሲያው ሥርዓት እውን ይሆን ዘንድ ግንባር ቀደሙን ሚና መጫወት የነበረበት አብዛኛው ምሁር ነኝ ባይ ራሱም በአብይና በካምፓኒው (ብልፅግና ተብየው) ተሽመድምዶ የወደቀ ዕለትና ከወደቀበት በፍጥነት ለመነሳት የተሳነው ጊዜ ነበር የመከራውና የውርደቱ ዘመን ሊረዝም እንደሚችል ግልፅ የሆነው። ለዚህ እውነትነት ደግሞ በመሬት ላይ ከሆነውና እየሆነ ካለው ግልፅና ግልፅ መሪር ሃቅ በላይ ማስረጃ ፈፅሞ የለም።
እናም ይህ ፖለቲካ ወለድ አስከፊና አሳፋሪ ሁኔታ ፍፃሜ ያገኝ ዘንድ አሁን ያለበትን ጣረሞታዊ ተውኔት ወደ የማይቀርለት መቃብር መሸኘት የነገ ሳይሆን የዛሬ የትግል ዒላማ መሆን አለበት።
የመከራውና የውርደቱ እድሜ መራዘሙ ህሊናውን የማያቆስለውና ከዚህ እጅግ አስቀያሚና አሳፋሪ የፖለቲካና የሞራል ዝቅጠት ሰብሮ ለመውጣት እና የተሻለ ነገንና ከነገ ወዲያን እውን ለማድረግ የማይፈልግ ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ የአገሬ ሰው የሚኖር አይመስለኝም። ጥያቄው የመፈለግ ወይም የመመኘት ብቻ ሳይሆን ፍላጎትንና ምኞትን ወደ ተግባር የመተርጎም ጉዳይ ነው። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ልህ አስጨራሽ የህልውና ፣የነፃነትና የፍትህ ተጋድሎ በማካሄድ ላይ ከሚገኙ ፋኖዎች/አርበኞች/ጀግኖች ጎን ተሰልፎ አስፈላጊውን ሁሉ የማድረግ ፈቃደኝነትንና ዝግጁነትን ይጠይቃል ።
ይህ ካልሆነ የእኩያን ገዥዎችን ጣረሞታዊ የፖለቲካ ተውኔት ወደ የማይቀርለት መቃብር ሸኝቶ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትንና ዴሞክራሲያዊት አገርን እውን ማድረግ አይቻልም።