July 10, 2024
3 mins read

የሱዳን የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር በሚል ስም ይንቀሳቀስ የነበረው በዃላ ላይ የኢሕአፓ መሰናዶና የፖለቲካ ትምህርት ቤት

SESUይህ በሱዳን ፣እምዱርማን ከባቢ ከምንኖርባቸው ሁለት ቤቶች በአንዱ የምንኖረው የፖለቲካ ጥናትና ውይይት ስናካሂድ በነበረበት ወቅት ነው።በእያንዳንዱ ቤት ከ16 በላይ ወጣት ይኖር ነበር፣በዚህ ፎቶ ከሚታዩት መካከል አምስቱ በትግል ሜዳ መሰዋታቸውን ሰምቻለሁ ከነዚህም መካከል በውጊያ ደፋርና የጋንታ መሪ የነበረችው  ስመኝ(ድላይ)፣ጌታቸው ሚደቅሳ(ጃፈር)፣ መኖር መሞቱ ያልታወቀው በለጠ አመሃ(ገብሬ) የሜዳ ስማቸውን የማላቀው አባተ፣ ዮናታንና፣ጥበቡ ይገኙበታል።ቆስለው በህይወት ከተረፉት   መካከል ተቀባ ጀርመን መኖሩን ስሰማ ፣ስለሽና ሙሉነህ ዋሲሁን አገርቤት ገብተው ሲኖሩ ስለሽ በህመም መሞቱን ሰምቻለሁ፤ ሙሉነህ ግን ሐረር ይኖራል

እሬትም ይጥማል

በማናውቀው ቋንቋ በማናቀው አገር፣
ካገራችን ወጥተን ተሰደን ስንኖር፣
አንድ ላይ በመሆን የኑሮ ሸክሙ አይከብደንም ነበር።

ሳቅና ጨዋታው ቀልድና  ተረቡ፣
ያላማ ጽናቱ የትግል ሃሳቡ፣
እያበረታታን የትግላችን ግቡ፣
ያለንን ተካፍለን በመተሳሰቡ ፣
አልበታተነንም መቼገር መታረዝ መጠማት መራቡ

የተጋሩት ነገር ባንድ ላይ ተጋግዘው፣
እሬትም ይጥማል የሚጎመዝዘው።
ፍቅር ባለበት ቤት እራብም ጥጋብ ነው፣
ፍቅር ባለበት ቤት ሕመምም ጤና ነው

በጋራ ከሆነ ክፉም ሆነ ደጉ፣
መራራው ይጥማል ጣፋጭ(ስኳር) ሳያደርጉ።

ለአምባገነን ሥርዓት ያልተንበረከከ፣
ግፍን ተጠይፎ ጠላቱን ያወከ።

ሙሉ ቤተሰቡን ሚስት ልጁን ጥሎ፣
አገርና ወገን ይበልጣሉ ብሎ።

ደህና ደመወዙን ቤት ንብረቱን ትቶ፣
ሁሉንም የሆነ ትግል ሜዳ ገብቶ፣
አንድ ህይወቱን ሰጥቶ፣አካሉን ተጎድቶ
ታሪኩ ይነገር አይቅር ተዘንግቶ።

በትግል ሜዳ ላይ ለሞት ተሰልፈው፣
ፎክረው ጨፍረው እንደሞላለት ሰው፣
እራብ ውሃ ጥሙን ብርድ ሃሩሩን ችለው፣
አንዱ አንዱን ለማዳን በሞት ላይ ተራምደው፣

ያስተሳሰራቸው ሁሉን እንደዘመድ፣
የዓላማ ጽናት ነው፣
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ነች፣
ኢትዮጵያዊነት ነው የቃል ኪዳን ገመድ።

ለእኔ ብቻ ማለት ሰው ከተጠዬፈ፣
ኢትዮጵያ ማድ ነች የተትረፈረፈ፣
ለሁሉ ምትበቃ ከራስ ሆድ ባለፈ።

መትረዬስ ቢተኮስ ቦምብ ቢወረወር፣
የማያፈገፍግ ከቶ ማይሸበር፣
ሲረሸን መዘመር፣ሲታገል መፎከር
በሃገር በወገኑ የማይደራደር፣
ያ ነው የእኔ ትውልድ ታሪኩ ቢነገር።
አገሬ አዲስ

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop