ወገኖቸ በኢትዮጵያ ምድር ባለጊዜዎቹ መደመር የሚል ፍሬፈርስኪ የሆነ ፍልስፍና ፈጥረው እየሰበኩን፣ እያቀነቀኑልን እየለፈፉልን ይገኛሉ። መቸም “ዐይን የማያየው ፣ ጆሮ የማይሰማው የለም” እንዲሉ እደፈረደብን የሚሆነውን በአርምሞ መጠበቅ ነው።
እቺ ያልታደለች ሃገር የመሪዎች ላቭራቶሪ ከሆነች ሰነባበተች ደርግ “ሶሻሊዝም እና ኮሚኒዝም “ በሚል ህሳቤ አጦዘን ፣ ወያኔ “አንድ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ መፍጠር’ በሚል መፈክር አናወዘን ፣ አሁን ደግሞ የብልፅግና ፈላስፎች “ የመደመር ህሳቤ” ብለው እያምታቱን ፣ ማሰቢያችን እያነጎሉትና እያላጉን ነው።
ኢትዮጵያ በዓለም ቁጥር አንድ ፈላስፋ ተብለው የሚጠቀሱትን እንደ ፖሉቶ ፣ ሶቅራጠስና ወዘተ ያሉ የግሪክ ፈላስፎችን የሚያስከነዱ ወይም የሚገዳደሩ እንደ ታላቁ ዘርያዕቆብ ና ወልደ ህይወት ምትኩ ያሉ ባለምጡቅ አዕምሮ ያላቸው ፈላስፎች የነብሯት ሃገር እንደነበረች ታሪክ ከትቦ አስቀምጦታል።
ይህን እውነታ ለማወቅ የኢትዮጵያ የልብ ወዳጅ የሆኑትን ፣ በትውልድ ካናዳዊና በምርጫቸው ኢትዮጵያዊ ለመሆን የበቁትን የፕሮፌሰር ክላውድ ሳምነርን (1999-2012) መፅሃፍቶች በማንበብ ማረጋገጥ ይቻላል።
በዚህ አጋጣሚ ፕሮፌሰር ክላ ውድ ሳምነርን በስራቸው ምክንያት የማወቅ እድል አጋጥሞኛል። ይህም የሆነው አብዛኛውን መፅሃፋቸውን ያሳተሙ የነበረው አዲስ አበባ አሮጌው ቄራ አካባቢ በሚገኘው የንግድ ማተሚያ ቤት ስለነበር እኔም በዚህ ማተሚያ ቤት በሲኒየር አርታይነትና አራሚነት ስሰራ ስለነበር የሳቸውን ድንቅ መፅሃፍቶች የማረም ፣ የማንበብና የማስተካከል እጋጣሚውን አግኝቸ ነበር።
በአጠቃላይ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊያን የነበራቸው ፍቅር የትየለሌ ነበር። አፈሩ ይቅለላቸው ፣ ነፍሳቸውን በዐፀ ገነት ያኑርልን።
መፅሃፍ መፃፍና ማሳተም ቀላል ነገር ስላልሆነ የመደመር መፅሃፍ ምንም ሆነ ምን ታትሞ ገቢያ ላይ በመዋሉ ፅሃፊውን አለማድነቅ ግብዝነት ስለሆነ በዚህ አጋጣሚ አድናቆቴን እገልፃለሁ።
አንባቢያን ሊያውቁት የሚገባው እና እኔ ማተኮር የምፈልገው እንደ ባለሙያ (Critical Realists) መፅሃፉን ፣ ርዕሱና ጭብጡን መገምገም ላይ እንጂ መፅሃፉ ላይ ችግር የለብኝም።
ዋናው የመሞገቻ ነጥቤ :
- “መደመር” ፍልስፍና አዲስ ፍልስፍና ነው ወይስ ፍልስፍና ነው በራሱ ሊባል ይችላል ወይ?
- የሰውን ልጅ መደመር ይቻላል ወይ ?
- አንድነትና መደመር ምንና ምን ናቸው ?
በሚለው ላይ አተኩሬ እያብራራሁ
አብ ፣ ወልድ ፣ መንፈስ ቅዱስ አንድም ሶስትም ሆነው የተዋሃድት / የተደመሩት እነሱ እና እነሱ መለኮታዊ ኃይሎች ብቻ እንጂ “ለደካማው የሰው ልጅ መደመር የሚቻለው አይደለም” የሚለውን የመከራከሪያ ተጓዳኝ ህሳቤየንና
ሃተታየን በዚህ አጋጣሚ ጠቋቁሜ ህዝብ በጉዳዩ ላይ እንዲነጋገርበት አሳስባለሁ።
እንደሚታወቀው በዓለም ወደ ሳባት ቢሊዮን ሕዝብ በላይ እንደሚኖር ይታወቃል ይህ ስባት ቢሊዮን በላይ የሚጠጋ ህዝብ መንታ ሁነው የተፈጠሩት ሁሉ ሳይቀር ጎላ ያለ ወይም ጥቃቅን የሆነ ልዩነት እንዳላቸው ይነገራል።
አንድ ብርቱካንና አንድ ሙዝ ሲደመር ሁለት ብርቱካንና ሙዝ ሊሆን ይችላሉ ወይም ከተጨመቁ ቅርፊቱና ፍሬው ከተወረወረ በኋላ የተዋሃዱ ለየት ያለ ጣእም ያላቸው ጭማቂዎች ሊወጣቸው ይቻላቸዋል እንጂ ምንም ቢሆን እንድ ሁነዋል ፣ ተደምረዋል ማለት አንችልም።
ፍልስፍና ከሌላ የሰው የፈጠራ ሃሳብ ያልተኮረጀ ፣ በግለሰብ እዕምሮ አዲስ ሆኖ የተፈጠረ አፍቅሮተ ጥብብ የሚገለፅበት ፣ ተግባራዊ የሚሆን ፣ እውነትን በማሳለጥ የሰው ሕይወት በስሉጥነትና ከሚኖርበት ዓለም ጋር ተሰላስሎ ይኖር ዘንድ የሚረዳ እውቀት በውስጡ የሰደረ ፅንሰ ሃሳባዊ ፍሰት ነው ። ”lliterally, the term “philosophy” means, “love of wisdom.” In a broad sense, philosophy is an activity people undertake when they seek to understand fundamental truths about themselves, the world in which they live, and their relationships to the world and to each other.” ።
ከዚህ ተመርኩዘን ስናይ “መደመር” የሂሳባዊ ቀመር ሆኖ ሂሳቦችን ፣ ነገሮችን እስልቶ የሚያስቀምጥ ችግር ፈቺ ተጨባጥ ሳይንሳዊ ቀመር እንጂ በራሱ የቆመ አዲስ ፍልስፍና ነው ብሎ ለማስቀመጥ ያስቸግራል።
መደመር የሚባል ፍልስፍና አለ ወይ? ለሚለው ጥያቄ (Synergy) ከሚለው የሰው ልጅ ማህበራዊ ችግሮች የመፍቻ ቀልፍ እውቀት አዘል ጥበባዊ የተግባር አስተሳሰባዊ ፅንሰ ሃሳብ ተቀድቶ ወይም ተኮርጆ ተሰይሞ ከሆነ ፅሃፊው መደመር ለማለት የሞከረው: “SynergySynergy is an interaction or cooperation giving rise to a whole that is greater than the simple sum of its parts. The term synergy comes from the Attic Greek word συνεργία synergia[1] from synergos, συνεργός, meaning “working together”. ለሚለው ቃል ፍቺ የሚቀርበው ለላቀ ውጤት “በጋርዮሽ መስራት / መለወጥ” ቢባል ሊያስኬድ የሚችል ይመስላል።
ምክንያቱም በምድር ላይ አንድ ጊዜ የተደመሩ ነገሮች ተመልሰው እራሳቸውን መሆን ስለማይችሉ ። ጥቁርና ቢጫ ቀለም ከተቀላቀለ /ከተደመረ/ አረንጓዴ ይሆናል እንጂ ተመልሶ ጥቁር እና ቢጫ እንደማይሆን ሁሉ አንድና እንድ ከተደመረ ሁለት ይሆናል እንጂ ወይም ሁለትን በሁለት አካፍለህ ሌላ አካሄድ ተከትሎ አንድ ይሆናል እንጂ ወደነበረበት አንድነት ሊመለስ አይቻለውም ፣ ፍልስፍና የህይወት ማቅለያ መንገድ እንደመሆኑ ነገረ ሃሳቡ የተቆላለፈ ይሆናል።
ስለዚህ ብልፅግናና ከላይ ያሉ የተደበላለቀባቸው ጉምቱዎች አሁን እያደረጉት ያለውን “የመደመር” ህሳቤ የድንብር ጉዞ አንድነትና ልዮነት በመከባበር“ Unity respecting diversity” የሚለውን አካሄድ በአንድ የኦሮሞ ብሄር ስም የኢትዮጵያን ህዝብ ደምሮና አጣፍቶ የብልፅግና ፓርቲ የሚፈልጋትን አንዲት በምዕናብ ያለች ኢትዮጵያን ሊፈጥር አስቦ ከሆነ “ በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ” እንደሚሉት እንዳይሆንበት እንሰጋለን / እየሆነበትም ነው።
ስለዚህ በሳይንሱም ሆነ በፍልስፍናው “መደመር” የሚል የቁም ትርጉም ያለው ፍልስፍና የለም። እንዲያው በአቦ ሰጥና በምርቃና የተቀመረ ሊተገበር የማይችል የተኮረጀ ህሳቤ ነው እንላለን።
ከዚህ በተጨማሪ የተለያየ አስተሳሰብ ፣ ቁመና ፣ ሙያ ፣ የአኗኗር ዘየ፣ ባህል ፣ ቱፊት ፣ቋንቋ ወዘተ ያለውን ህዝብ እንደ ቁሳቁስ መደመር ይቻላል ወይ ለሚለው ? መልሱ አይቻልም ነው። የሰውን ልጅ ልዮነቱን ጥብቀህ በማቀራረብ፣ በማግባባት ፣ በጋራ እንዲሰራና እንዲኖር አድርገህ የጋራ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ታደርገዋለህ እንጂ እንደ ሂሳብ ስሌት በምዕናባዊ ቅዥት ልትደምረው መሞከር ከመጨፍለቅ ተልይቶ አይታይም።
ሌላው የአንድነትና የመደመርን ህሳቤ ማደበላለቅ የበለጠ ወደ አዘቅት የሚያማራ ይሆናል። በተፈጥሯዊ ሆነ በማህበራዊ እንቅስቃሴዎችና መስተጋብሮች የተከሰቱ የሰፉ ልዩነቶችን በትምህርት ሆነ የጋራ ተጠቃሚነትን በማስረፅ አንድነትን ማምጣት ይቻላል። ለምሳሌ ያህል ኢትዮጵያዊ መሆን ከጉዳቱ ይልቅ ጠቀሞታው ከፍ ያለ ሰለሆነ ፣ መሰል የጋራ እሴቶችን ፣ በእውነታ የተሰደሩ ታሪኮችን ፣ ቱፊቶችንና ተሞክሮዎችን በማስረፅ አንድነትን ማምጣት ይቻላል። ነግር ግን “ደመረ” ከሚለው ቃል ተነስተን በኃይልም ሆነ በቅዥት የማይጨበጥን ግዑዝ ፅንሰ ሃሳብ እየለፈፉ አንድ ማህበረሰብና ሃገር ለመፍጠር መፈራገጥ አልፈነው ወደ መጣ ነው የጋርዮሽ ሥርዓት እንደ መመለስ ነው እንላለን።
የእነብልፅግ ፓርቲና መሪዎች የምዕናቡ የማይጨበጠው የመደመር ህሳቢያቸው ትንሽ ፣ ትንሽ የመመስልና የቅቡልነትን መልክ እንዲያገኝ በመካከላቸው ፣ በፓርቲያቸው እና በግለሰብ ደረጃ በጋር የተናበበ የአንድነት አካሄድ ቢኖራቸውና ቢያሳዮን መልካም ነበር። ከአፋቸው የሚወጣው የቃላት መወራወር ሆነ ተግባራቸው ፣ መላ ሕዝቡን በጋራ ለማቆም የማያስችል ከመሆኑ ባሻገር የእለት እለት ውሉዋቸውና ድንፋታቸው ፍንትው አድርጎ ያሳያል።
ሕዝብ በየቦታው እየታረደ ፣ እርስ በእርሱ ታስቦበት ማህበረሰቡ በብሄር ፅንፍ እንዲከፋፈል እየተደረገ፣ ከኢትዮጵያዊነት ፍልስፍና ፣ እሴት ፣ ባህልና እውነታ ውጭ በስማ በለው ፣ በእውሸት የመሪዎች ትርክትና ግፊት በድንጋይ ሕዝብ እየተወጋገረ “መደመር” የሚል የለበጣ ህሳቤ ማስተጋባት “ ደሮን ሲያታልሏት በመጫኛ ጣሏት” ከሚለው ጥቅስ ያልተለየ ፋይዳ ቢስ ህሳቤ ፣ ፌዝና ተረት ተረት ነው እንላለን።
ከተዘራ አሰጉ
ከምድረ እንግሊዝ።