February 18, 2023
27 mins read

ከራሳችን መሪር እውነታ ጋር ከመላተም ክፉ አባዜ አልወጣንም!

February 18, 2023

ጠገናው ጎሹ

የመፈላሰፋችንና የመጠበባችን ምሥጢር ወደ መሬት ወርዶ በሚታይና በሚጨበጥ ተግባርና ውጤት ካልተተረጎመ የምድራዊውም ሆነ ተስፋ የምናደርው ከሞት በኋላ ህይወት ከባዶ ምኞት ወይም ተስፈኝነት ጨርሶ አያልፍም ። በሌላ አገላልለፅ ሆኖና አድርጎ በመገኘት ምሳሌነት (አርአያነት) የማንኖረው ምድራዊም ይሁን  ሰማያዊ ተልእኮ   የውድቀት  አዙሪት ሰለባ ከመሆን ፈፅሞ አያልፍም። በመንበረ ሥልጣን ላይ እየተፈራረቁ በመከረኛው ህዝብ ላይ የመከራና የውርደት ዶፍ ለሚያወርዱ እኩያን ገዥ ቡድኖች   ምቹ  ሁኔታ ከፈጠሩላቸው ውድቀቶቻችን መካከል አንዱና ዋነኛው ይኸው ነው። ለዚህ ደግሞ ለዘመናት ከመጣንበትና ከአራት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ለማመመን ቀርቶ ለማሰብም በእጅጉ በሚከብድ ሁኔታ ከቀጠልንበት የገዛ ራሳችን ግዙፍና መሪር እውነታ የተሻለ ማሳያ ፈፅሞ የለም።

እንደ መንደርደሪያ ይህንን ካልኩ ወደ ዋናው  ሂሳዊ  አስተያየቴ ልለፍ፦

” የየራሳችሁን የሳንቲም ማጠራቀሚያ ግዙና አሥር፧ አሥራ አምስትና ሃያ አምስት እያላችሁ አጠራቅሙ”  አብይ አህመድ ይህንን የተናገረው ለመሠረታዊው መብቱና  ፍላጎቱ ፀር የሆነውን ሥርዓት በአግባቡ ታግሎ ከማሸነፍና ነፃ ከመውጣት ይልቅ የኑሮውን ክብደት አልቻልኩምና ትንሽ ሳንቲም ይጨመርልኝ የሚል የመማፀኛ አቤቱታ ላቀረበው አስተማሪ (መምህር) ነው።  እንዲህ አይነት ወራዳና አዋራጅ ስላቅ ሲነገረው እንኳን ነውር ነው ለማለት ከአንገቱ ቀና ብሎ ለማየት ድፋርነት የጎደለው አስተማሪ  እንዴትና መቸ ከዚህ ክፉ የውድቀት አዙሪት እንደሚላቀቅ ለመገመት ያስቸግራል።

ABIY ERKUS SEW 1

“ይህን ቅጠል በጨው አጣፍታችሁ ብሉት ። ሙዝ በዳቦም ብሉ ” ይህ ደግሞ የኑሮው ውድነት መሠረታዊ ለሆው በህይወት የመቆየት ዋስትና የሆነው የምግብ  እጥረት በከፍተኛ ደረጃ ላጠቃው መከረኛ ህዝብ የሰጠው ምላሽ (ምክር) ነው። ህዝብም ለምን በመከራችን ትሳለቃለህ ብሎ ከምር ከመቆጣትና ለመብቱ ከመታገል ይልቅ የሰው ልጅ ከቶ ሊታገሰው ከማይችለው መከራናውርደት ጋር ይበልጥ እየተለማመደ ከቁም ሙትነት ወደ የመቃብር ሙትነት የሚለወጥበትን እለት ይጠብቃል።

መሠረታዊ ፍላጎታቸውና ዓላማቸው ከምር ሃይማኖታዊ ሳይሆን ሃይማኖቱንም በእኛ ክልል ( አዲስ አበባን/ፊንፊኔን)  ጨምሮ ያለው ሁሉ የእኛና የእኛ ብቻ በመሆኑ ቁጥጥሩም  በእኛና በእኛ ሥር እንዲሆን ግድ ነው  ለሚል አስቀያሚና አደገኛ  ዘመቻ ያዘጋጃቸውን የቤተ ክህነት አልባሳትና ቆብ የለበሱ ቡድኖችን ወደ ሥራ ካሠማራ በኋላ ህሊናቸውን ለፍርፋሪ ለቃሚነት አሳልፈው የሰጡ ሚኒስትሮች ተብየዎችን ሰብስቦ ” አንዳችሁም እጃችሁን ብታስገቡ ዋ!” ሲላቸው መስማትና እነርሱም እንደ ምስኪን ተማሪ በድንጋጤ ማስታወሻ ቢጤ ሲሞነጫጭሩ ከማየት የከፋ የህሊናን የሚያም ነገር የለም።

አገርና ህዝብ ከዘመን ጠገቡና በእጅጉ አሳፋሪና አስፈሪ ከሆነው የውድቀት አዙሪት  ሰብሮ ለመውጣት ይችሉ ዘንድ  ተገቢውን ሃይማኖታዊ ተልእኮ ለመወጣት የተሳናቸው አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች “ባህር ማዶ ለታቀደ ፕሮጀክት (የገዳማ ምሥረታ) ያላችሁን ሁሉ በመስጠት የበረከቱ ተሳታፊ ሁኑ”  የሚል ዘመቻ ሲያካሂዱ መታዘብ  ምነው የቅድሚያ ቅድሚያ የሚባል ነገር አናውቅም እንዴ? የሚል ጥያቄ ቢነሳ ፈፅሞ ድፍረት ሊሆን አይችልም።  ዘመቻው በመሠረተ ሃሳ ብ ተገቢ ወይም አስፈላጊ መሆኑ ባያጠያይቅም አገር ቤት እየሆነ ካለው አጠቃላይ ሰቆቃ (total disaster) የከቅድሚያ ቅድሚያ አሰጣጥ አንፃር ሲገመገም ግን ፈፅሞ አሳማኝነት የለውም።

ለዚህ ነው “እዚህ ያለው ወገን ብቻ ነው የሚገድህን? አሜሪካ ያለው ወገንህ አይገድህምን?” የሚለው ድራማዊ አቀራረብ ብዙም ሚዛን የሚደፋ ነው ብሎ ለመቀበል የሚያስቸግረው።እናም በዚህ ረገድ ያለው ከፍተኛ ጉድለት እልህ አስጨራሽ የጋራ ተጋድሎ ያስፈልገዋል።

በህወሃት የበላይነት ሥር ሆነው ለዘመናት ሲገድሉና ሲያስገድሉ ከቆዩት እና ከአራት ዓመታት ወዲህ ደግሞ መከራውንና ውርደቱን እጅግ በከፋ ሁኔታ እያስኬዱት ካሉት ኦህዴዳዊያን/ ኦነጋዊያን/ኦሮሙማዊያን ጋር በመላላስ ወይም በመተሻሸት ፈጣሪን እውነተኛ ነፃነትና ሰላም ውለድ እያሉ እግዚኦ ማለት ፈፅሞ የትም አያደርስም ።

ሸፍጠኛው፣ ሴረኛውና ርህራሄ ቢሱ (ማህፀኗ በስለት ለተዘነጠለው እናት አዝናለሁ ያላለውና የማይለው) አብይ አህመድ ከሰሞኑ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ የፖለቲካ ወለዱ ወንጀል ተውኔት ሰለባዎች የሆኑትን የሃይማኖት መሪዎች ሰብስቦ “ለህዝቡ እኛ እንሰዋለን። እናንተ ለወንጌል ተሰው። ምን አገባችሁና ነው ለህዝብ የምትሰውት? የእናንተ ዓላማ ሌላ ነው “ ሲል ተሳልቆባቸዋል።

ይህ ሲሆን ምነው ይሀን ያህል? ብሎ አለመጠየቅና በእውነት ስለ እውነት ለመጋፈጥ ወኔ ማጣት እንኳን ብዙ እውቀትና ተሞክሮ አለኝ ለሚል የሃይማኖት መሪ ለማነኛውም ሚዛናዊ ህሊና ላለውና እውነተኛ የሃይማኖት ነፃነት ፈላጊ ሰው ፈፅሞ አይመጥንም።

እውነተኛው አምላክ እንደ እረኝነታችሁ መንጋዎቻችሁን (ህዝቤን) ጠብቁ ነው ያለው ። “ለህዝብ (ለሰዎች) ደህንነትና መብት ግድ የማይለው ሃይማኖት ሌላ ምን ዓላማ  አለውና ነው ዓላማችሁ ሌላ ነው እስከ ማለት የደረስከው?  በፈጣሪ አምሳል ለተፈጠረ የሰው ልጅ በተለይም ደግሞ የመከራና የውርደት ቀንበር ተሸካሚ  የሆነውን ምእመንና በአጠቃላይ ኢትዮጵያዊ ሰው ከመታደግ በላይ ዓላማ ያለው የትኛው መንገድ (ተግባር) ነው?  ከዚህ የሚበልጠው የፅድቅ መንገድስ የትኛው ነው? ለንፁሃን ምእመናንና በአጠቃላይ ለንፁሃን የአገር ልጆች መስዋእት መሆንን ለአንተና ለመንግሥትህ ብቻ የሰጠ ወይም የሚሰጥ ምድራዊና ሰማያዊ ተልእኮና ህግ የትኛው ነው? ምነው ይህን ያህል ትእቢትና ንቀት?” ብሎ አግባብነት ያለው ቁጣ የማይቆጣና  በአገር መሪ ነኝ ባይነቱ በንፁሃን ላይ ለሆነው ሁሉ አዝኛለሁና አዝናለሁ ያላለንና የማይልን ሰው በግልፅና በቀጥታ ለመገሰፅ ወኔው የሚያንሰው የሃይማኖት መሪ ስለ የትኛው ፅድቅና ኩነኔ ወይም መንፈሳዊነትና ኢመንፈሳዊነት እንደሚያስተምር ለመረዳት ያስቸግራል። ከባድ የውድቀት አዙሪትም ነው።

እንዲያውም በተቃራኒው “ለካስ የሙሴ ድንቅ መንፈስ በአብይ ውስጥ ተደብቆ ነበረ” የሚል አይነት ሙገሳ ነው የታዘብነው። የሃይማኖት መሪዎች  ቢያንስ አራት ዓመታት  –

ሙሉ ካየነውና ከሰማነው ከአብይ ፖለቲካዊና ሞራላዊ ዝቅጠት (የለየለት አታላይነት) እውነታ አንፃር ምን ማለቱ እንደሆነ ለመጠየቅ እንዴት የሞራል አቅም ያንሰናል?  ተብለው ሲጠየቁ “ጥሩ ሲሠራ ማመስገን ፣ ሲሳሳት ደግሞ መውቀስ “ የሚለውን እጅግ አጠቃላይ እውነታ አራት ዓመታት ሙሉ አገሪቱን በገዛ ልጆቿ ደምና መከራ እንድትጨቀይ ካደረገው የአብይ አገዛዝ ጋር እያነፃፀሩ ሊያሳምኑን ይሞክራሉ። ታዲያ ይህን ክርስቶስ ከሞተለት ታላቅና የተቀደሰ ተልእኮ ጋር እንዴት ማቀራረብ ይቻላልየሚቻል አይመስለኝም።

ከጎሳ/ከቋንቋ አጥንት  ስሌት  የፖለቲካ ንግድ እናተርፋለን ባይ ገዥ ቡድኖች እጅግ ጨካኝ የፖለቲካ አቋምና ቁመና ምክንያት አያሌ ቁጥር ያላቸው ንፁሃን ወገኖች በአሰቃቂ ሁኔታ የመገደላቸው አስከፊ ሁኔታ በቀጠለበት ፣  አያሌዎች በአካልና በአእምሮ  ህመም በሚሰቃዩበት፣  አያሌ ቁጥር ያላቸው ህፃናትና አረጋዊያን መፈጠራቸውን ጠልተው የመቃብር ሙት መሆንን በመረጡበት ፣ አገራቸውና ቀያቸው ወደ ምድረ ሲኦልነት ተለውጠውባቸው የፈጣሪና የወገን ያለህ  የሚል የሰቆቃ ድምፅ የሚያሰሙ ወገኖች ቁጥር  በብዙ ሚሊዮኖች እየተቆጠረ ባለበት በዚህ እጅግ አስከፊ (painfully tragic) ወቅት “ባህር ማዶ ለጀመርነው ገዳማዊና ታሪካዊ ኢንቨስትመንት/ፕሮጀክት በብዙ ሚሊዮኖች ያስፈልገናልና ለሃይማኖታችሁ መስፋፋት ስትሉ አሁንኑ ሁለገብ ድጋፍ አድርጉልን” በሚል ዘመቻ ላይ መጠመድ እውነተኛ አምላካዊ ጥሪ ይዘት ያለው አይመስለኝም።

መከረኛው ህዝብ ከዘመናትና በተለይም ደግሞ ከአራት ዓመታት ወዲህ እንኳን ለማመን ለማሰብም በሚከብድ ሁኔታ ከቀጠለው ፖለቲካ ወለድ የመከራና የውርደት ዶፍ ነፃ ይወጣ ዘንድ በአግባቡ አንቅቶ፣ አደራጅቶና አንቀሳቅሶ የሚያታግለው የፖለቲካም ሆነ የሲቪል ሃይል (አካል) ባለመኖሩ የሆነውንና እየሆነ ያለውን መሪር እውነታ ለመረዳት የማይፈልግ ወይም የሚሳነው ፊደል የቆጠረ (ተምሬያለሁ የሚል) የአገሬ ሰው የራሱን ውስጠ ነፍስ (ህሊና) መመርመር ይኖርበታል።

የመንፈሳዊ ተልእኮኳቸውና ዓላማቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ሰብአዊ መብትንና የህግ የበላይነትን በተመለከተ ከሌሎች የሲቪል ተቋማት (civil institutions) የሚበልጥ እንጅ የማያንስ ሚና ያላቸው ወይም ሊኖራቸው የሚገቡ የሃይማኖት ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት ለመወጣት ባለመቻላቸው የሸፍጠኛ፣ ሴረኛና ጨካኝ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ሰለባዎች ሲሆኑ ከመታዘብ የከፋ የውድቀት አዙሪት ያለ አይመስለኝም።

ይህ የውድቀት አዙሪት (vicious cycle of failure) አልበቃ ብሎ ከሰሞኑ ደግሞ በገዥዎች ቤተ መንግሥት ውስጥ የተተወነው እጅግ አስቀያሚ ተውኔት  በመንበረ ሃይማኖቱ መድረግ ላይ ሲተወን እያየንና እየታዘብን ነው።  ቅንና አስተዋይ ህሊናን በእጅጉ ያቆስላል!

መከራንና ውርደትን እየተለማመደ ሳይኖር ኖርኩ ብሎ ራሱን እንዲያታልል የተፈረደበትን መከረኛ ህዝብ ከሁሉም በላይ የሆነ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ ከማገዝ ይልቅ በተለያዩ ማህበራዊና ሥነ ልቦናዊ ችግሮች ምክንያት ለሚከሰቱ አሉታዊ ውጤቶች ተገቢ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ተቋማት (አካላት) ባሉበት ምድረ አሜሪካ አሁንኑ የገዳም ፕሮጀክት እውን አድርጌ አገልግሎት ካልሰጠሁ  በሚል ዘመቻ መጠመድ እንኳን ለመንፈሳዊ ለዓለማዊ ህሊናም የሚመጥን አይደለም።

በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን የሩብ ምዕተ ዓመቱ ይቅርና በአራት ዓመታት ውስጥ እጆቻቸውና ህሊናዎቻቸው እጅግ ለመግለፅ በሚያስቸግር ሁኔታ በንፁሃን ደምና የቁም ሰቆቃ ለተጨማለቁ ፖለቲከኞች (ገዥ ቡድኖችና ግብረ በላዎቻቸው) ርካሽና አደገኛ አስተሳሰብና አካሄድ ደጋግሞ ሰለባ እየሆኑ ስለ ሰላም፣ ስለፍቅር፣ ስለ ስኬታማ የምድር ላይ ህይወት እና ስለ ሰማያዊው ፅድቅ መስበክን ብቻ አሜን ብሎ የሚቀበል እውነተኛ አምላክ የሚኖር አይመስለኝም።

እውነተኛው አምላክ እስከ መስዋዕትነት ፀንተን እንቆማለን የሚለውን ሃይለ ቃል ወደ ደርጊት ለመተርጎም  ከምር የሚጥር ፍጡሩን (ሰውን) ነው ከምር የሚያደምጠውና የሚያግዘው ። በሥልጣናቸው ተመክተው በተገዥዎቻቸው ላይ ጨካኝ እርምጃ የሚወስዱትን ገዥዎች “ህዝቤን ልቀቁ” ብሏል እያልን የምንሰብከውን ሃይለ ቃል  በግልፅና በቀጥታ ለመናገር ለመናገርና ለመነጋገር አለመድፈር ምን ማለት እንደሆነ የየራሳችንን ህሊና መመርመር ይኖርብናል።

ታላላቅ የምንላቸው አገርና ሃይማኖት እጅግ አሳፋሪና አስፈሪ በሆነ የወድቀት አዙሪት ተተብትበው በሚገኙበት ግዙፍና መሪር እውነታ ውስጥ  ሆነን የቅድሚያ ቅድሚያ   ትኩረትን  ጨርሶ ግምት ውስጥ  ባላስገባ ሁኔታ የገዳም ምሥረታና ልማት ፕሮጀክት ላይ መጠመድና ሌሎችም ይህንኑ እንዲከተሉ መማፀን  ትክክል ነው ብሎ ለመቀበል ያስቸግራል።

እንደዚህ አይነት አስተያየት መሰንዘር እንደ ፀረ ገዳም  ወይም ኢሞራላዊነት  ወይም የሃይማኖት መሪዎችን እንደ መዳፈር የሚቆጥር ሰው ካለ መመርመር ያለበት የራሱን የህሊና ጤንነት (ሚዛናዊነት) ነው።

አዎ! እንደ እኛ አይነት ለዘመናት የዘለቀና አሁንም እጅግ አስከፊና አስፈሪ በሆነ ሁኔታ የቀጠለ መከራና ውርደት መናኸሪያ ለሆነችና እየሆነች ላለች አገር ከሁሉም በፊት የቅድሚያ ቅድሚያ ሊሰጠው በሚገባ አገራዊ ጉዳይ ላይ አካልተረባረብን ድረስ አሁን በያዝነው ከክስተቶች ትኩሳት ጋር በሚሞቅና በሚቀዘቅዝ ግልብ ስሜታዊነት ጨርሶ የትም አንደርስም።

የትግላችን ቅድሚያ ቅድሚያ መሆን ያለበት በወንጀለኞች ሥርዓተ ፖለቲካ ከፉኛ የተጎዱትን ወገኖችን ከመርዳት ጎን ለጎን ሥርዓቱን ከነመርዙ ነቅሎ መጣልና ለሁሉም ዜጎቿ የምትበጅ ዴሞክራሲያዊት አገርን እውን ማድረግ ነው።

አዎ! በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን እጅግ ክቡር የሆነውችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ቤተ ክርስቲያን (እምነት) የኦሮሙማ (ኢትዮጵያን በተረኝነት መቆጣጠርና መዝረፍ ካልቻልን ኦሮሚያ የምትባል የኩሽ አገር እንመሥርታለን የሚሉ አደገኛ ቅዠታሞች) መፈንጫ ስበሆነችበት እና ይህንን ክፉና አደገኛ ቅዠት በቅጡ (በአግባቡና በማይናወፅ አቋምና ቁመና) ማስትናገድ አቅቷቸው በእጅጉ የሚዋዥቁ የሃይማኖት መሪዎችን እያስተዋልን ባለንበት በዚህ እጅግ አስከፊና አስፈሪ ወቅትና ሁኔታ ውስጥ ባህር ማዶ ለጀመርነው  ገዳማዊ ኢንቨስትመንት (ፕሮጀክት”) የቅድሚያ ቅድሚያ ካልሰጠን ሞተን እንገኛለን ማለት እንኳንስ ለቅዱስነት (ለመንፈሳዊነት) ለዓለማዊ  ማንነትና ምንነትም  ፈፅሞ አይመጥንም!

እያልኩ ያለሁት ባህር ማዶ ሃይማኖታዊ ተቋምና ለዚሁ የሚያግዝ ልማትና አገልግሎት አያስፈልግም አይደለም። እንዲህ አይነቱ  አስተሳሰብ ደምሳሳና እንጭጭ መሆኑን ለመረዳት የሃይማኖትም ሆነ የዓለማዊ እውቀት አዋቂነትን አይጠይቅም ።

እያልኩ ያለሁት በህወሃት መራሹ አገዛዝ ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን በሆነውና ከአራት ዓመታት ወዲህ ደግሞ የተረኝነቱን የቤተ መንግሥት ፖለቲካ ታይቶና ተሰምቶ በማያውቅ ግዙፍና መሪር ሁኔታ እያስቀጠሉ ባሉት የዚያው ሥርዓት ውላጆች  ምክንያት አገሩ ምድረ ሲኦል የሆነችበትን መከረኛ ህዝብ አሜሪካ ካለው ችግር ጋር ማነፃፀር ፈፅሞ ትክክል አይደልምና  የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት ምንነትን በአፍ ጢሙ ደፍተን አናንብበው ነው።

በብዙ ዓመታትና በብዙ መስዋእትነት የተገነባች የሃይማኖት ተቋም በገዛ ራሷ እኩያንና ጨካኝ ገዥ ቡድኖችና ግብረበላዎቻቸው  እንዳልነበረች እንድትሆን እየተደረገች ባለችበት እጅግ መሪርና ግዙፍ እውነታ ውስጥ እየጓጎጥን ለባህር ማዶ ገዳምና ገዳማዊ ፕሮጀክት እኩል ወይም ቅድሚያ ካልሰጠሁ የሚለውን ዘመቻችን እንኳንስ ለመቀበል ለማሰብም በእጅጉ ያስቸግራልና አደብ እየገዛን ብንችል ወደ ፊት በፍጥነት መገስገስ ቢያንስ ግን በቅጡ መራመድ ይኖርብናል።

በጎሳ/በቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች እየተደረሰ፣ እየተቀነባበረና እየተዘጋጀ የሚሰጣቸውን ተልእኮ ለማስፈፀም በተንቀሳቀሱና በሚንቀሳቀሱ ጳጳሳት ተብየዎች አማካኝነት በቤተ መንግሥቱ  ፖለቲካ እና በመንበረ ሃይማኖቱ መካከል የሚደረገው እጅግ የወረደና አዋራጅ ኦርኬስትሬሽን (ተውኔት) በአስቸኳይ ሊገታ ይገባል። የዚህ ርካሽና አደገኛ  የፖለቲካ ድራማ ሰለባ መሆንን እንደ ሃይማኖታዊ እምነት ጥንካሬ መነሻና መድረሻ መቁጠርን ከምር  መፈተሽ ይኖርብናል። አዎ!   በግልፅና በቀጥታ  መናገርና መነጋገር የእውነትና የፅድቅ እንጅ የህፀፅና የኩነኔ መንገድ እንዳልሆነ ለመረዳት ቅንና አስተዋይ ህሊናን እንጅ የተለየ እውቀትን አይጠይቅም ።

ፈጣሪ ቃልን ወደ ተግባር ከመተርጎም ጋር እንጅ ከባዶ ቃል (መነባንብጋር  ከቅንነት ጋር እንጅ  ከሸፍጠኝነት ጋር ፣ከአርበኝነት ጋር እንጅ ከባንዳነት  ከእውነተኛነት ጋር እንጅ ከሃሰተኝነት ጋር  ከትህትና ጋር እንጅ ከትዕቢተኝነት ጋር  ከሰብአዊ ፍጡርነት ጋር እንጅ ከዘረኝነት  ጋር  ከባለ መርህነት ጋር እንጅ ከመርህ አልባነት ጋር  ከአዳኝነት ጋር እንጅ ከገዳይነት ጋር  ከሞራላዊነት ጋር እንጅ ከሞራለ ቢስነት ጋር  ከወድቆ መነሳት ጋር እንጅ የውድቀት  ቁራኛ  ከመሆን  ጋር  ጉዳይ  የለውምና ልብ ያለው ልብ ይበል!

+

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

ትላንት አንድ ወዳጀ ደውሎ “አሳየ ደርቤን” ታውቀዋለህ ወይ” አለኝ፡፡ እኔም አላውቀውም አልኩት፡፡ ኢንጅኔር “ኡሉፍ” የተባለ ሰው የዛሬ ሰባት ዓመት ያሰራረውን ጥልቀትና ስፋት ያለውን ዘገብ አቅርቦታልና አዳምጠው አለኝ፡፡ እኔም “ጉድሺን ስሚ ኢትዮጵያ–ከባድ አደጋ

ተቆርቋሪ የሌላት ኢትዮጵያ – አክሎግ ቢራራ (ዶር)

ወገኖቸ፤ ለጊዜው ትችቱን እናቁምና ለወገኖቻችን እንድረስላቸው፡፡፡ በቤተ አማራ ወሎ ቡግና የተከሰተው ርሃብ ጉዳት ቀላል አይደለም፡፡ ለወገን ደራXኡ ወገን ስለሆነ እባካችሁ ህሻናትን እናድን፤ ለግሱ፡፡ ጦርነት ያመክናል፤ ተከታታይ ጦርነት አረመኒያዊነት ነው፡፡ ጦርነት ካልቆመ የረሃቡ

እግዚኣብሔር ግን ወዴት አለ?

ልዩ ቆይታ ከገዱ አንዳርጋቸው ጋር ! – “ዐብይ ቂም የያዘ የነጣቂ መንግስት መሪ ነው”/ “አማራ እየተዋጋ ያለው ሰላምን ፍለጋ ነው” – ክፍል አንድ ልዩ ቆይታ ከገዱ አንዳርጋቸው ጋር ! –

“ፋኖ የበለጠ ይደራጃል ወደ ኋላ አይልም!”/ “የትግራይን ህዝብን ይቅርታ ጠይቂያለሁ” “ፋኖ በናፍቆት እየተጠበቀ ነው” ገዱ አንዳርጋቸው (ዶ/ር)

December 28, 2024
ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር) (ታህሳስ 19፣ 2017) December 28, 2024 መግቢያ እንደተነገርን ኢትዮጵያን “ከዕዝ ወይም ከሶሻሊስታዊ” ኢኮኖሚ አላቆ ወደ “ ነፃ ገበያ ኢኮኖሚ” እንድትሸጋገር ከተደረገ ይኸው ከ31 ዓመት በላይ ሊያስቆጥር ነው። በጊዜው ስልጣንን የተቆናጠጠው የህወሃት አገዛዝ

ሁለ-ገብ ለሆነ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ዕድገት መሰረት የሚጥል ህግ፣ ወይስ የኢትዮጵያን ሀብት የሚያዘርፍና ህዝብን አቅመ-ቢስ የሚያደርግ አዲስ የባንክ ህግ- ከኒዎ-ሊበራሊዝም ወደ ባሰ ኒዎ-ሊበራሊዝም የዝቅጠት ጉዞ!

ልዩ ቆይታ ከገዱ አንዳርጋቸው ጋር ! – “ዐብይ ቂም የያዘ የነጣቂ መንግስት መሪ ነው”/ “አማራ እየተዋጋ ያለው ሰላምን ፍለጋ ነው” – ክፍል አንድ

ልዩ ቆይታ ከገዱ አንዳርጋቸው ጋር ! – “ዐብይ ቂም የያዘ የነጣቂ መንግስት መሪ ነው”/ “አማራ እየተዋጋ ያለው ሰላምን ፍለጋ ነው” – ክፍል አንድ

December 27, 2024
የሲቪል ማህበረስብ ድርጅቶች ባለስልጣን፤ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከልን (EHRDC) “ገለልተኛ ባለመሆን ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጭ ተንቀሳቅሰዋል” በሚል ምክንያት ማገዱ ገለጸ። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል (EHRDC)

መንግስት ኢሰመጉ እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከልን አገደ፤ የታገዱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቁጥር አራት ደረሷል

December 26, 2024
Go toTop