February 10, 2023
24 mins read

ሕገወጥነትና ብልግና የነገሰባት የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ “ብልጽግና” ኢትዮጵያ ወደ የት እያመራች ነው? – አክሎግ ቢራራ(ዶር)

ክልፍ አራት

የዚህ ሃተታና ምክረ ሃሳብ ዋና ዓላማ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን የገጠማት የሕገ መንግሥት ቀውስ (Constitutional and governance crisis) በራሱ በጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ አሊና በመሰረቱት የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ የዘውግ ጽንፈኞች እብሪተኛነት፤ ተተኪነትና ሙሉ የበላይነት ሴራ የተጠነሰሰ መሆኑን መላው የኢትዮጵያ፤ የአፍሪካና የዓለም ሕዝብ  እንዲያውቀውና ይህች ታሪካዊ አገር ከማትመለስበት ደረጃ ላይ ከመድረሷ በፊት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሕግን አክብረው፤ ሌሎች ሕግን እንዲያክብሩ ግፊት እንዲያደርጉ ለማሳሰብ ነው።

በዛሬው ቀን የኢትዮጵያ የበላይ ፍርድ ቤት ለቅዱስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን አቤቱታ የወሰነው ፍርድና ተገንጣዩና አመጸኛው አካል የሕግ እውቅና የለውም ያለው ተስፋ የሚሰጥ እርምጃ ነው። የሕግ አስፈጻሚው የጠቅላይ ሚንስትሩ መንግሥት ይህን ውሳኔ የማክበርና የማስፈጸም ሃላፊነት አለበት።

ችግሩ ግን በቀላሉ መፍትሄ የሚያገኝ አይመስለኝም። በዘውግና በቋንቋ የማይታረቁ ልዩነቶች ላይ የተመሰረተ ሕገ መንግሥትና በማንነት ላይ ብቻ የተዋቀረ የአስተዳደር ስርዓት ኢትዮጵያን ወደማትወጣው ብሄር ተኮር ግጭት፤ እልቂትና ጦርነት እንደሚያሸጋግራት ባለፉት ሰላሳ የኢህአዴግ/ብልጽግና ዓመታት ተመልክተናል። ህወሃት ያቀጣጠለው የእርስ በእርስ ጦርነት ለ600,000 ወገኖቻችን እልቂት፤ ለአስር ቢሊየን ዶላር የኢንቨስትመንት ውድመት ምክንያት ሆኗል።

ኢትዮጵያ ልጆቿን እያፈነች፤ እያሳደደች፤ እየበላች፤ ወጣቶቿን እያማከነች፤ ተቋሞቿንና ቅርሶቿን እያፈረሰች፤ የሰራችውን ፋብሪካና ሌላ መሰረተ ልማት እያወደመች፤ ከተሞቿን፤ ቤተ ክርስቲያኖቿን፤ ገዳሞቿን፤ ሞስኮቿን እያቃጠለች፤ ውንብድናን፤ ሌብነትን፤ አድልዎን፤ ሙስናን እየፈቀደች ልትበለጽግ አትችልም። ብድር፤ የውጭ እርዳታ እነዚህን ሊተካቸው አይችልም።

የዐብይ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ራሱ ካላከበረ ሌላው የሕግ የበላይነትን ሊያከብር አይችልም። እንዲያውም ሕገ-ወጥነት እየተባባሰ ይሄዳል። ዛሬ የምናየው ሕገ-ወጥነት የነገሰ መሆኑን ነው።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ማናቸው?

ቅንነት፤ ሰብእነት ካለው ኢትዮጵያዊ ምክርና ገንቢ የሚነሱ አማራጮችን የማያስተናግዱ፤

ሁሉን እኔ አውቃለሁ የሚሉና ራሳቸውን የማይፈትሹ፤

ማንንም ተቃዋሚ የሚዘልፉ፤ ትእቢተኛና ጉረኛ፤

ቀጥተኛነትን እንደ ደካማነት የሚተቹ፤

መንፈሳዊ ነኝ ቢሉም ቅሉ፤ ኢ-ፍትሃዊ ባህሪ የሚያሳዩ፤

በሥልጣን የበላይነት እንጅ በሕግ የበላይነት የማያምኑ፤

የአምባገነን ዝንባሌ ያላቸው፤

ሁሉንም ማህበረሰባዊና መንፈሳዊ ችግሮች በወታደራዊ ኃይል እፈታለሁ የሚሉ፤

በመንግሥት ሃላፊነትና ተጠያቂነት የማያምኑ፤

“እኔ ብቻ አሻግራችኋለሁ” የሚሉና ቃላቸውን ከሚሰሩት ጋር ያላጣመሩ፤ ያላገናኙ መሪ ናቸው።

በመሬት ላይ የሚታየው ሃቅ

ዛሬ የኦሮምያ ፖሊስ፤ ልዩ ኃይል፤ ደህንነት በጋራ ሆነው ለሚያካሂዱት እጅግ በጣም ለሚዘገንና አገር አፍራሽ ለሆነው የንጹሃን እልቂት፤ የኦርቶዶክስ ተዋህድዶ ቤተክርስትያን መሪዎች፤ አባቶች፤ ምእመናን እልቂት፤ ድብደባ፤ ውርደት፤ እስራት፤ ማሳደድና የቤተክርስቲያኗ ንብረት ውድመት የመጀመሪያው ተጠያቂ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ናቸው። ሌላው ቀርቶ ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሰረት ተዋህዶ በሚቀጥለው እሁድ ሰላማዊ ሰልፍ ስትጠራ፤ ለናንተም ሆነ ለአፈንጋጩ፤ ለብሄር ጽንፈኛውና ህገወጡ ቡድን ፈቃድ አንሰጥም የሚል ውሳኔ የተደረገው በጠቅላይ ሚንስትሩ የደህንነት የበላይ አካል መሆኑ በራሱ እሳቸውን ተጠያቂ ያደርጋቸዋል። እጃቸው እንዳለበት አልጠራጠርም።

በንጹሃን ወገኖቻችን ላይ፤ በተለይ በአማራውና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋህዶ አባቶች፤ ምእመናን፤ ወጣቶች ላይ የሚካሄደውን ጭካኔ ማየቱ በቂ ነው። በሻሸመኔ የተጨፈጨፉትን ወጣቶች ማጤን በቂ ነው። መንፈሳዊ አባቶችን እንዴት እንደሚያዋርዷቸውና እንደሚያዋክቧቸው ማየት በቂ ነው። ከዚህ በታች የሚታየውን ቪዲዮ ማየት በመላው ኢትዮጵያ ያንዣበበውን አደጋ ክብደትና ጥልቀት እንድናጤነው ይረዳናል።

https://t.co/KjBg22U6Td

(https://twitter.com/TayeNani/status/1623392587670335489?t=OdMdXoy2wppG9apTJ5lJjQ&s=03

ጠቅላይ ሚንስትሩን፤ ሽመልስ አብዲሳን፤ የፌደራል መንግሥቱን ካቢኔ አባላት የምጠይቃቸው እነዚህን መንፈሳዊ አባቶች እንደዚህ ለማዋረድ ያስቻላችሁ ልብና መርህ ሰብአዊ ነው ወይንስ እንስሳዊ? የሚል ነው። ክጭካኔው ከእንሰሳም በላይ አልካይዳ፤ ቦኮ ሃራም፤ አልሸባብ፤ ግራኝ፤ ዮዲት ጉዲት መሰል ነው። “እግዚዖ “ እንበል።

በንጽኋን ዜጎች ላይ የሚካሄደውን ተከታታይ ግፍ፤ በደል፤ ኢ-ሰባዊ ሁኔታ ስገመግመው ኢትዮጵያ ከውድቀት አፋፍ ላይ ናት ወደሚል ድምዳሚግ ይገፋኛል።

በተከታታይ ስገመግመው፤ ዛሬ ኢትዮጵያ የደረሰችበትን ጫፍ ሳጤነውና ኢትዮጵያ ወደ የት እያመራች ነው ብየ ራሴን ስጠይቅ፤ በትእቢተኛነት የተበከሉት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ አሊ በሕግ የበላይነት ሆነ በፍትህ  አያምኑም። ወደ አሜሪካ መጥተው በነበሩበት ወቅት፤ እኔም ሆነ ሌሎች ተስፋችን ከፍ ያለ እንደ ነበረ ታሪክ ይመሰክራል። እኔም “ጠቅላይ ሚንስትሬ ነዎት ያልኩበት” መሰረታዊ ምክንያት ዘረኛው፤ ጠባብ ብሄርተኛው፤ ሙሰኛው ህወሃት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ያካሄደውን ግፍና በደል በማጤንና ኢትዮጵያን የሚመጥን ፍትሃዊ ስርዓት ይመሰራትል በሚል ተስፋ ነበር። ከእነዚህ መካከል በዘውግና በቋንቋ ልዩነቶች ላይ የተመሰረተው ሕገ መንግሥትና የአስተዳደር ስርዓት ሊቀየር ይችላል የሚል ምኞትም ነበረኝ።

ቃልን ያለማክበሩ ክስተት

“ኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያዊንት ሱስ ነው። ስንኖር ኢትዮጵያዊ፤ ስንሞት ኢትዮጵያ። እመኑኝ እኔ አሸጋግራችኋለሁ። የቀን ጅቦችን” እንታገላቸዋለን ወዘተ የሚሉት ትርክቶች ሲደጋገሙ ስሰማ የተሻለ ሁኔታ ይፈጠራል የሚል ግምት ነበረኝ። አብዛኛው የኢትዮጵያና የዓለም ሕዝብም የተማረከው በነዚህና መሰል ንግግሮች ነበር።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ሥልጣን ከያዙበት ጀምሮ በተከታታይ የሆነው ሃቅ የሚያሳየው ግን አጅግ በጣም የሚዘገንን ብሄር ተኮር ሰብአዊ እልቂት፤ ውንብድና፤ የእርስ በእርስ ጦርነት፤ ፍጹም የሆነ ሕገወጥነት፤ ከህወሃት የባሰ አድልዎ፤ ሌብነት፤ ዘረፋ፤ ሙስናና፤ ኢ-ሰባዊነት ወዘተ ነው።

የአገራዊ/ብሄራዊ/ኢትዮጵያዊ ተቋማት ውድመት

በአገራዊ፤ ብሄራዊ፤ ኢትዮጵያዊ ተቋማት መስፈርት ስመራመረው ደግሞ ከኢትዮጵያ አየር መንገድና ከኢትዮጵያ ተዋህዶ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን እምነትና ሲኖድ ውጭ የኢትዮጵያ ተቋማት ከስመዋል ለማለት ይቻላል። ሕገወጥነት፤ ሽብርተኛነት፤ ዘውጋዊነት፤ ብሄርተኛነት ነግሰዋል። አገራዊ/ብሄራዊ/ኢትዮጵያዊ ተቋማትን እያፈረሱ ክልላዊና ዘውጋዊ ማድረግ የተለመደ ሆኗል።

ጦርነቱ ለምን ተካሄደ?

በህወሃትና በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ጥምር ኃይሎች መካከል የተካሄደው የሁለት ዓመታት የሚዘገንን እልቂትና ውድመት በፕሪቶሪያ/ናይሮቢ ስምምነቶች መሰረት እየተፈታ ነው ተብሎ ተነግሮ፤ ኢትዮጵያውያንና መላው ዓለም የጥምቀትን በዓል ካከበሩ/ካከበርን በኋላ ባልታሰበ ፍጥነት የኦሮሞ ጽንፈኞች ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ “አገር ነው” ብለው የጠሩትን የኢትዮጵያን ተዋህዶ ቤተክርስትያንና ሲኖድ በሁለት ከፈሉት። ዋናው አገር አቀፍ፤ ሁሉን አሳታፊ የሆነው ተቋም እንዲፈርስ ተመቻቸ። ለዚህና ለሌች ሕገወጥ ክስተቶች የመጀመሪያው ተጠያቂ ዐብይ አህመድ ናቸው። የስለላውን፤ የፌደራል ፖሊሱን፤ የብሄራዊ መከላከያ ኃይሉን፤ የፌደራል ባጀቱን፤ የውጭ ግንኑነቱን መረብ ሁሉ በበላይነት የሚቆጣጠሩት እሳቸው ናቸው። እሳቸው የማያውቁት አስኳል ጉዳይ አይታሰብም።

የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ተቋም ለማፍረስ ለምን ተፈለገ?

የኦርቶዶክሱን መከፋፈልና ንትርክ፤ የተከተለውን እልቂትና ውርደት ሁኔታ ጠቅላይ ሚንስትሩ አባብሰውታል። እንዴት? ህገወጥ የሆነውን ቡድን በመተቸት ፋንታ፤ “የኔን መንግሥት አያገባውም፤ ችግሩ በድርድር ይፈታ” ብለው ተናገሩ። ወገንተኛነታቸውን፤ ከፋፋይነታቸውንና መሰሪነታቸውን አሳዩ ማለት ነው።

አብይ የረሱት አንድ ክስተት አለ። የምእራብ አገሮች የራሳቸውንና የህወሃትን “መንግሥት” አቻ በአቻ አድርገው ሲያቀርቡ ለምን ተቿቸው? ለምን እኛም እንድንተች ቀሰቀሱን? በአንድ ራስ ሁለት ምላስ የሚሉት ይህንን ነው። ዐብይ የሚናገሩትን ለማመን አልችልም። የተናገሩትን በድርጊት አያሳዩም (Abiy Ahmed does not walk the talk). ለዚህ ነው የማይታመኑት፡፡

ዐብይና ህወሃት የተስማሙበትን የውስጥ አጀንዳ ማንም አያውቅም። የሚታመን አጀንዳ ግን አይደለም። የአፋሩን፤ የአማራውን፤ የኤርትራውን ጥቅምና ደህንነት አይወክልም። በዘላቂነት ስመለከተው የአማራው፤ የአፋሩ፤ የትግራዩና የኤርትራው ወንድማማች/እህትማማች ሕዝብ እየተሸወደ ነው።

ህወሃት የሰላምና የትጥቅ መፍታት ውል ከፈረመ በኋላ በቅርቡ በመቀሌ የሚሰብከውን አስጊ ፕሮፓጋንዳ ስሰማ ህወሃት እንደ ገና ወደ ሌላ ጦርነት እያመራ ይሆን ወይ? ብየ ራሴን ጠይቄ ነበር። ጌታቸው ረዳ ትግራይ የራሱ ኦርቶዶክስ ተቋም ያስፈልገዋል ሲል ከኦነጋዊያን፤ ከዐብይ ብልጽግና ፓርቲ ጋር የመሰረተውን ምስጢራዊ ግንኙነትና እቅድ ያሳያል።

የተጠያቂነት ክፍተት እንዴት ተከሰተ?

ጊዜ የሚወስድ መሆኑ ባይካድም፤ የህወሃት መሪዎችና ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ለተጨፈጨፉት የአፋር፤ የአማራ፤ የትግራይ ወገኖቻችን ተጠያቂ እንደሚሆኑ አልጠራጠርም። ከ600,000 ሺህ በላይ የሚገመት ሕዝብ ተገድሏል። ከአስር ቢሊየን ዶላር በላይ የሚገመት ኃብት ወድሟል። ለዚህ ተጠያቂው ማነው?

የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት ሕግን የማስከበር አቅምና ብቃት ይዳከም፤ አይዳከም ባላውቅም፤ ህወሃት ግን ከመስመሩ ፍንክች ያለ አይመስለኝም። አሁንም  የኤርትራ፤ “የአማራ ልዩ ኅይልና ፋኖ ከትግራይ መውጣት አለበት” እያለ ነው። ትርጉሙ ከወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ጠለምትና ራያ ማለቱ ነው። ይህ ሌላ ጦርነት እንዲካሄድ ማመቻቸት ይመስላል። ይህ ሁሉ ሲሆን የዐብይ አህመድ አጀንዳ ምን እንደሆነ አናውቅም። “ምታ በዝምታ ተባለ” እልቂት ተካሄደ፤ ተስማማ በዝምታ የሚለውስ ፋይዳውም ምን ይሆናል?

የህወሃት ጠብ ጫሪነት እንዳለ ሆኖ፤ በአሁኑ ወቅት እኔን የሚያሳስበኝ እልቂት በአጣየ፤ በሸዋ ሮቢት፤ በጅብ ውሃና አካቢዎች የሚካሄደው የለየለት የአማራ እልቂትና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ተቋም፤ መሪዎች፤ አባቶችና አባላት ላይ የሚካሄደው ኢ-ሰብ አዊና አገር አፍራሽ ግጭት ነው።

አንድ ሊካድ የማይቻል ሃቅ አለ። ይኼውም፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ሥልጣን ከያዙ በኋላ በኣነዚህ አካባቢዎች እልቂት ተካሂዷል፤ ኃብትና ንብረት ወድሟል፤ አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል። ሻሸመኔ፤ አጣየ፤ ሸዋ ሮቢት፤ ምእራብ ወለጋ፤ ቤኒ ሻንጉል ጉሙዝ ወዘተ።

የዐብይ መንግሥት የመጀመሪያ ሃላፊነት ምንድን ነው?

የመጀመሪያው የመንግሥት ሃላፊነት በእነዚህ አካባቢዎችና በወለጋ የሚካሄደውን እልቂት ማስቆም ነው። የፖለቲካ ፈቃደኛነት ካለ ይቻላል። ፈቃደኛነት እንደሌለ ግን ግልጽ ነው።

ባለፉት አምሳ ዓመታት የዘውግ ፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ተባባሪ ወይንም አጋር ምሁራንና ልሂቃን በሕዝብ ስም እየማሉና እየተገዘቱ ያላደረጉት አማራጭ ጉዞ በግልጽ ይታያል። ይኼውም፤ ፍትህን ዋና መርህ አድርጎ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ማገናኘትና የሕዝብን ድምጽና ግብዓት ሳይሰለቹ ማስተናገድ፤ ወደ ፖሊሲ መቀየር፤ ለሕዝቡ እውነተኛ አገልጋይ መሆንና ተጥሪነት/ሃላፊነት ማሳየት ነው። እብሪተኛነት አያዋጣም።

የታጠቀ ኃይል ብቻውን የሕዝብን እምቢተኛነት ሊገታው ይችላል?

ከደርግ በላይ የታጠቀ ኃይል አልነበረም። ሕዝቡ በገፍ ሲነሳበትና በቃ ሲል ግን የእምቧይ ካብ ሆኗል። የዐብይ መንግሥት ከዚህና አብጦና ታጥቆ ከነበረው፤ በሕዝብ እምቢተኛነት ወደ መቀሌ ሄዶ ከመሸገው ከህወሃት መንግሥት እብሪተኛነት ሊማር ይችል ነበር፤ አልተማረም፤ የሚማርም አይመስለኝም።

እኔ እስከማውቀው ድረስ፤ አብዛኛው የኦሮሞ ሕዝብ ከአማራ፤ ከትግራይ፤ ከሶማሌ፤ ከወለይታ ወዘተ ሕዝብ ጋር አልተጣላም። የአማራ ሕዝብ ከኦሮሞ፤ ከጉራጌ፤ ከትግራይ፤ ከሶማሌ፤ ከአፋር ወዘተ ሕዝብ ጋር አልተጣላም። በሕዝብ ስም ጥላቻ አለ ብለው ኢትዮጵያዊያን ለተከታታይ እልቂትና ሁከት የዳረጓት የኢትዮጵያ የፖለቲካ መሪዎች፤ ተባባሪ ምሁራን፤ ልሂቃንና ሌሎችን የፖለቲካ ነጋዴዎች ማን ተጠያቂና ሃላፊ ያደርጋቸዋል? ዐብይ አሕመድ የዚህ ጉዞ መሪ ሆነዋል። እባከዎ ለህሊናዎ ተገዢ በመሆን ይጸጸቱ (Please consider repentance and seek forgiveness).

ይህ ተግዳሮት ሊፈታ የሚችልበት እድል ሕዝብን ሳይሰለቹ በማሳተፍና በማማከር እንጅ ምክንያት እየፈጠሩ ግጭቶች እንዲቀጥሉ በማድረግና ትችት የሚያቀርበውን ሁሉ በማሰር አይደለም። ዜጎች የሚጠይቁት ፍትህን ነው። የኑሮ ውድነት እንዲሻሻል ነው። ሕግ እእንዲከበር ነው። ሌሎቻችን ስንት ስው ቢታሰር፤ ስንት ሰው ቢሞት “በቃ” ለማለት እንደፍራለን? የሚለውን ጥያቄ ራሳችሁ መልሱት። የአጣየ፤ የሻሸመኔ ወዘተ ሕዝብ ስንት ጊዜ ይጨፍጨፍ? ለማን ጥቅም?

ይህንን ክፍል ለማጠቃለል፤

የኦርቶዶክስ እምነትን ለመከፋፈል የሚደረገው ከዘውጉ የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነት ሴራ ሊለይ አይችልም። ፓስተር ዮናታን የተባለው ግለስብ ለአዲሱ ዓመት የሚመኘውን ሲገልጽ አዳመጥኩት። “የኔ የሆኑትን እለያለሁ” አለ። ወይ ጉድ፤ በእምነትም እንደዚህ ያለ እብደት ይሰማል? አልኩ። “አዲስ አበባ ኬኛ፤ ወለጋ ኬኛ፤ ሰሜን ሸዋ ኬኛ፤ ወሎ ኬኛ፤ ጎንደር ኬኛ፤ አክሱም ኬኛ፤ ኦርቶዶክስ ኬኛ” ከሆነ የሚቀጥለው ፤ ኢትዮጵያ ኬኛ ይሆን ብየ ራሴን ጠየቅሁ። ገና መልስ የለኝም፤ ግን አቅጣጫው ይታየኛል። የዐብይ የድብቅ አጀንዳ አያምርም የምለው ለዚህ ነው። ይህንን አደገኛና አገር አፍራሺ ሁኔታ የመታገል ሃላፊነት የሁላችንም ነው።

 

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድን ላሳስብ የምፈልገው እሳቸውና መንግሥታቸው ሕግን እንዲያክበሩና እንዲያስከብሩ፤ ተገንጣይና ተቋም አፍራሽ የሆኑትን ግለሰቦች ለፍርድ እንዲያቀርቡና የሚካሄደውን ውንብድና እንዲታገሉ ነው።

በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ የምንኖረውን ኢትዮጵያዊያንና ወዳጆቻቸውን አደራ የምለው ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንና ሲኖድ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንድንሰጥ ነው።

የሕግ የበላይነት ይከበር!

ሰብ አዊ መብት ይከበር!

ይቀጥላል

February 10, 2023

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
Go toTop