አእምሮ አሸክሞ በአምሳሉ ቢፈጥርህ፣
የሆድ ቀፈት ጋርዶህ ልቡና አልቦ የሆንክ፣
እንኳንስ ሰማዩ ላይ ሆኖ የሚያይህ፣
ምድሩም “ጉድ ነው” ብሏል ነገ የሚውጥህ፡፡
በሥራው መዝነው ብትባል ሰባኪን፣
በቀጣፊ እሰተንፋስ እንደ ትቢያ እምትበን፣
ወና ባዶ ቤት ነው መርምረው ገላህን፡፡
አሳልፎ ሰጥቶ እልፍ አእላፍ ሰማእትን፣
ሰላሳ ዓመት ከድቶህ ይሁዳን የምታምን፣
ልብህን ማን ሰልቦት ምን ነክቶት ናላህን?
አገር ስትቃጠል ሲያልቅ ዘር ማንዘርህ፣
ጀሮህን የደፈንክ ልሳንህን የዘጋህ፣
የቆረጥክ ለማለፍ አንደ ቅንቡርስ ውጠህ፣
ታልጋ ውስጥ ቀርቶ መቃበር እንቅልፍ የለህ፣
መለኮት ተሰማይ ታሪክ ተምድር ሲያሽህ፣
እንደ ጥጥ ባዘቶ አንስቶ ሲጥልህ፡፡
የምትሳሳለት ነፍስ ድሎት የሚወደው፣
እርጉዝ ስትታረድ ቅፍፍ እንኳ እማይለው፣
ተእርጅና በሽታ አንዴት ሊያመልጥ ነው፣
ሞትን በምን መስኮት ሾልኮ ሊዘለው ነው?
ሞልቶ አማይመርጉት ሆድ እያንሰፈሰፈህ፣
የማታመልጠው ሞት የሚረሳህ መስሎህ፣
ሕዝብ በእሳት ሲቃጠል ድምጥህን ያጠፋህ፣
እንደ አባ ጨጓሬ በሆድ አየተሳብክ፣
እንኳን አሕዛብን ሳጥናኤልን አስናክ፡፡
በዝምታ ድጋፍ ጭራቅ እየደገፍክ፣
ለአሳራጅ ዲያብሎስ ግብር እያስገባህ፣
ስንቱን የእግዚአብሔር ሰው አንገቱን አስቀላህ፡፡
ከንቱ ሆይ!
ህፃናት ሲሰው ደመ ነፍስ ያልጠራህ፣
ስስት ድሎት ፍርሃት እንደ ውርጭ ቀፍድዶህ፣
መኖር የቀጠልከው እንደ አህያ ታስረህ፣
መኖ እንደ አሳማዎች እየጎሰጎስክ፣
ቅንጣት እንዳትረሳ አንተም ትሞታለህ፣
ትንታ ወይ እድሜ በሽታ ሲው አርጎህ፣
ዘንግቶ እማይቀረው እንኳን ሞት አለልህ፡፡
በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
ጥር ሁለት ሺ አስራ አምስት ዓ.ም.