“አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም” እንዲሉ አሁን ኢትዮጵያን እየመሩ ያሉ አንዳንድ ባለስልጣናት “ ከድንጋይ ላይ ውሃ ቢያፈሱት መልሶ እንቦጭ” እንዲሉ የሥልጣኑ ኮረቻ ዘለዓለማዊ መስሏቸው እውነታን ፣ ታሪክንና ቱፊትን በመፃረር ከሕዝብ ጋር መጣላትን፣ መቃቃርን ፣ ሕዝብ ማበሳጨትንና መናናቅን ሥራየ ብለው ይዘውታል።
ምን ይባላል “ ካለፈው የማይማር እሱ እራሱን እንዳጠፋ ይቁጠረው” የሚባል አባባል አለ። ዘሃር ወጦላቸው ኢትዮጵያን እየመሩ ያሉ ባለስልጣኖች “አያ በሬ ሆይ ሳሩነን አይተህ ገደሉን ሳታይ” እንዲሉ ከሕዝብ ጋር እልህ ተጋብተው ፣ ህዝብን ከማዳመጥ ይልቅ በምዕራባዊያን ጉግ ማንጉጎች የማይጨበጥ ተስፋ በመስከር ፣ በቁርጥ ፣ በውስኪና በሙስና በመንፈዝ ውሃ የማይቋጥር ውሳኔ ለመወሰን ተፍ ተፍ እያሉ ይገኛሉ።
ለነገሩ አንዳንዶቹ ለአቅመ ታላቅዋን ኢትዮጵያ የምታክል ሃገር የመመራት ደረጃ ሳይደርሱ ሥልጣኑ ኮረቻ ላይ ፊጥ ያሉ በመሆኑ “እንደሰናኦር ግንብ” ገንበኞች ቋንቋቸው ተደበላልቆባቸው የሚይዙትና የሚጨብጡት ጠፍቶባቸው የሚናገሩት ግራ የሚያጋባ ፣ የተፈላለሰና ሕጋዊ መሰረት የሌለው ነው ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ብልህ ነው ፣ ቀና ስትሆንለት ቅና ይሆንልሃል ፣ ክፉ ፣ መሰሬና ሃገር አማሽ ከሆንክ ፈረንጆቹ “ Silence is a language ‘ዝምታ ቋንቋ ነው’” እንደሚሉት የኢትዮጵያ ሕዝብ ገደሉ ጫፍ እስክትደርስ ድረስ ዝም ይልሃል ፣ ገደሉ አፋፍ ዳር ስትደርስ ግን አንድ መቶ አስር ሚሊዮኑ ህዝብ የህዝብ ድምፅና ክንድ ከጠብመንጃ በላይ ኃያል ነውና “ሆ” ብሎ ወደ ገደሉ ገፍቶ አፈር ያለብስሃል ፣ ይደበልቅሃልና አፈር ድሜ ያበላሃል ። ይህም በታሪክ ያየነው ነው።
“ግፉ ከአፍ እስከ ገደፉ “ ሲደርስበት “ይቅርታ ፣ እንታረቅና የማሪያም መንገድ” ስጥኝ ብትለው የማይታሰብ ነው። በሥልጣን ዘመንህ ልቡና እንዲሰጥህ ፀልዮልሃል ፣ መክሮሃልና ታገስ ብሎሃልና።
ኢትዮጵያዊው ምን ብትከፋፍለው በሃገሩ ፣ በደንምበሩ ፣ በባንዴራውና በጋራ ቋንቋው አይደራደርም።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከውጭ ወራሪ ኃይል ጋር ለሶስት ሺህ ዓመት ሲፋለም “ሃገሬ ኢትዮጵያ ካንቺ በፊት እኔን ፣ ብሰዋ አረንጓዴ ፣ ቢጫና ቀይ ባንዴራየን አልብሳችሁ ቅበሩኝ ፣ ሃገሬ ደንምበር ላይ አጥንቴ የሾህ አጥር ሆኖ ይጠብቅ ብሎ የተማማለ ሲሆን ፣ ይህን የጋራ ቱፊታዊ ቃለ ስምምነቱን የተፈራረመው ምንም የተለያየ ቋንቋ ቢናገርም በቀይ ደም በተነከረ መቃ በጋራ የመግባቢያ ቋንቋው የአማረኛ የኢትዮጵያ ቋንቋ እንደሆነ ልብ ይሏል።
አንዳንዴ የኛዎችን የቅርብ ጊዜ ሕዝብ አልሰማ ያሉ ግፈኛ መንግስታት መሪዎችን ኑዛዜ ለትውስታ እንመልከት። ጓድ መንግስቱ ኃይለማሪያም ወደ መውደቂያቸው አካባቢ የመወናጀርና የመዘላበድ ምልክቶች ይታይባቸው ነበር። በቀዝቃዛው ጦርነት /The cold war/ ምክንያት ከሶሻሊስቱ መንግስት ጋር ያላቸው ግኑኝነት ሲቀዘቅዝ ና ግራ ሲገባቸው “ቅይጥ ኢኮኖሚ/Mixed economy/” እንከተላለን ብለው ዘላበዱ ” ከዛም አልፎ ጦርና ጎራዴ እየያዙ ቴሌቭዥን መስኮት ላይ በመሰየም ሕዝብን ያስፈራሩ ፣ ያደነባብሩ ነበር። እሳቸውስ መቸም በሃገር አንድነት ፣ የጋራ ቋንቋ ፣ ደንበርና ባንዴራ ስለማይደራደሩ ነፍሳቸው ተርፏል ፣ ጓዶቻቸውም ዘብጥያ ወርደው ውርዴትን ተከናንበዋል።
ወያኔ ደግሞ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ አገዛዙ ሲያንገሸግሸውና በቃኝ ሲለው ሳይታደስና የመተካካት አካሄድ ሳይታይበት የስመ ታሃድሶና የመተካካት አዋጆችን አወጆ ነበር። መጨረሻ ተተካኩ ላለፉት አራት ዓመት “ለዐጣን የመጣ ለፃድቃን “ እንዲሉ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ሰላማዊ ሕዝብ ፣ ገበሬ ፣ ወጣት ወዘተ አስጨርሰው ፣ እርስ በርሳቸው ተራርደው ፣ የአንዳንዶችም ባለስልጣን ዕሪሳ ለክብር ቀብር ሳይበቃ አሁን ያሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።
ሰሞነኞቹ የብልፅግና መሪዎች በመስቀል አደባባይ “ በሃገራችን ጉዳይ ላይ አሜሪካና ምዕራባውያን እጃቸውን ያንሱ “ ብለው የተደናገረውን ሕዝብ እቅዥበው አሰልፈው ፣ ታንክ ፣ ሚሳየል ፣ ሰራዊትና ጀት እንዳላገለባበጡብን ሰሞኑን ደግሞ ዋሽንግተን ተከስተው ምን መርፌ ተወግተው፣ ርኩሰ ቁርባን ቀምሰው እንደመጡ አይታወቅም ይዘላብዱ ጅምረዋል ፣ “አሜሪካ ከሚወጋ ቀኘ ይወጋ” ማለት ጀምረዋል ፣ እስኪ መጨረሻውን ያሳምርላቸው።
ኢትዮጵያ ሃገራችን ኢትዮጵያዊ የጉግ ማንጉጎ ተላላኪዎችን ፣ አበሻዊ ድርቡሾችንና ምንም ዮዲት ጉዲት የይሁዳ ደም ኑሯት የታቦተ ፅዮን ከጣና ደሴት መራቅ አስቆጭቷት ብትገነፍልም ያን ሁሉ ቤተክርስቲያን ማፍረሷ አግባብ አለመሆኑ እንዳለ ሆኖ የዘመኑ ሴት ዮዱት ጉዲቶች ብቅ ብቅ እያሉ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ፣ ባንዴራዋን ለማዋረድና የጋራ መግባቢያ ቋንቋዋን አማረኛ ቋንቋ ከምድረ ገፅ ለማጥፋት እንቅልፍ አጥተው እየታተሩ ይገኛሉ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ ለሃገር ኢዮጵያ ቀናይ የሆነው የኢትዮጵያ አምላክ አለና “ህዝቤ ሆይ ፣ ኢትዮጵያ ታበፅህ እደዊሃ አበ እግዚአብሔር” እያልክ ፀልይ መልሱ የእግዚአብሔሩ ፈጣናና ምልኡ ነውና።
“እቺ ዳርዳርታ ዳቦየን ለመቀማት ነው” እንዲሉ ብልፅግና አዲስ ነጠላ ዜማ ለቋል። የጉግ ማንጉጉ ተላላኪዎች ፣ የቦኮ አራሙ ፣ የአልሻባቡ ፣ የአልቃይዳው የሕወሃት ነባር ቃል አቀባይ “አልበቃኝ ባይ ሲተፋ ያድራል” እንዲሉ ሬድዋን ሁሴን የሚባል ሰውየ እንደተለከፈ ውሻ ሰሞኑን አረፋ ማዳፈቅ ጀምሯል።
ወደ ጉዳዮ ስመጣ “ የተናገሩት ከሚቀር ፣ የወለዱት ምን ይበል” የሚባል ኢትዮጵያዊ የአነጋገር ቱፊት አለ። ትላንት ከወያኔ ጋር ሲፋለሙ በነበረበት ጊዜ የወልቃይትና የራያን ሰራዊት ከጎናቸው ለማሰለፍ ሲሉ ብልፅግናዎች “ወልቃይት በቤጌምድር ጎንደር እንዲሁም ራያ በወሎ ጥቅላይ ግዛት ስር የነበሩ ፣ በህወሃት በኃይል ተነጥቀው የተወሰዱ ናቸው፣” ብለው ማረጋገጫ ከሰጡና የሕዝብ ይሁንታን ካገኙ በኋላ እንደገና ቃላቸውን የማጠፍ ዳርዳርታ ማሳየት ጀምረዋል።
በኢትዮጵያ የመንግስት ታሪክ ውስጥ መንግስት “ ድልድይ ፣ መንገድ ወዘተ እሰራልሃለሁ” ብሎ ለሕዝብ ቃል ከገባ በኋላ በበጀት ማነስ ፣ ማሸራሸር ወይም ክፍተት ምክንያቶች ፕሮጀክቶችን ሊያጥፍ ወይም ላያሳካ ይችላል። ለዚህም ስህተቱን ይቅርታ ጥይቆ ሌላ አማራጭ በማቅረብ ከሕዝብ ጋር ይታረቃል እንጂ እንደ ብልፅግና መንግስት የሥልጣንን ዘመን ለማራዘም” ብሎ በአንድ አፍ ሁለት ምላስ” እንዲሉ በተለይ ላህላይ የተሰየሙ መሪዎች በወልቃይትና ራያ የኢትዮጵያ ጉሮሮ ፣ የልብ ትርታና ማንነት ላይ የሚያስተዛዝብ ልፈፋና ኩሸት እየፈፀሙ ያሉት አካሄድ በማንም የመንግስት ዘመነ ንግስና ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም ፣ አላጋጠመንም። ኤርትራ ከእናት ሃገሯ እዳትለያይ የደርግ መንግስት ለ17 ዓመታት ሲፋለም ፣ የአፄ ኃይለስላሴ መንግስት ደግሞ ለ22 ዓመታት ኤርትራን በብልሃት ከእናት ሃገሯ ጋር አቆይተዋቷል።
አቶ ሪድዋን ሁሴን “ ሕውሃት በኃይል ወልቃይትንና ራያን እንደ ወስደው ፣ በ21 ኛው ክፍለ ዘመን በኃይል ለመውሰድ መሞከር አግባብ አይደለም” ብለው ውሃ የማይቋጥር ከሕግ ጋር የተጣረዘ የማናለብኝነት ንግግር የቀደሞ ወዳጃቸውን ህወሃትን ለማስደሰት ሲዘላብዱ ተጠምደዋል።
ይሄ ነው የጉግ ማንጉግ ተላላኪነት ማለት ፣ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ መወሰዱን ካወቁ ሕግ አልባ የሆነውን አካሄድ አጥፎ ሕጋዊ ወደሆነ መንገድ መሄድ ሲቻል ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ለማጫራረስና ሌላ የቤት ስራ ለመስጠት መሞከር መንግስትንም ሆነ በህግ ማንጉጎች የተገዙትን አፈ ቀላጤዎች ትዝብት ውስጥ የሚጥል ከመሆኑም ባሻገር የመንግስት ሹመኞችን በምክንያታዊነት ሆነ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ለመሞገት የሚያስችል መንገድ እንዳላ ሊያውቁት የሚገባ መሆኑን ልናስገነዝብ እንወዳለን
ከዚህ ባሻገር የኢሕአዲግ እፀፀ ብዙ ህገ መንግስት ከመፅደቁ በፊት ህወሃት በብልጣብልጥነት፣ የኢኮኖሚ የበላይነት ለማግኝትና ለም መሬት በመፈለግ በኃይል የወሰደውን መሬት ህዝብ ፉርሽ ባደረገው ሕገ መንግስት እንፈታለን ማለት ጉጭ አልፊና ሕጋዊ እንዳልሆነ እንቅጩን እንነግራችኋለን።
ሕወሃት ከኢትዮጵያ ጋር መኖር ከተሳነው የወልቃይትንና የራያን መሬት እራሱ በሚመቸው መልኩ አርቅቆ ባፀደቀው እንቀፅ -39 “ የእራስን እድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል” በሚለው ህዝባዊ ቅቡልነት በሌለው አካሄድና አመክንዮ ትግራይን ከኢትዮጵያ ለመነጠል ህሳቤ እንዳለው እየታወቀ ከህውሃት ጋር “ መስመር ኃይልና” ብሎ መሞዳሞድ ከአዲነት ፣ የጉግ ማንጉጎች ተላላኪ መሆን ፣ ሃገርን መናቅ ፣ ሕዝብን ማስከፋትና ይቅር ሊያስብል ከማያስችል ወንጀል መዘፈቅ መሆኑን ከወዲሁ እንነግራችኋለን።
ነገ ሃገረ ኢትዮጵያ እነ አቶ ሪድዋን ሁሴን ለሚያጎበድዱላቸው እስላማዊና አረባዊ መንግስታት ወልቃይትን ይዞ ህወአት ከቀደም ወዳጆቹ ሱዳኖች ፣ ግብፆችና ወዘተ እንዲቀላቀል ድልድዮን ማመቻቸት ያስጠይቃል ፣ እስከ ዘር ማንዘር ሲያስረግም ያስኖራል እንላለን።
ከዚያ አልፎ ኢትዮጵያ አደጋ ላይ እድትወድቅ ፣ ለረጅም የማያባራ ጦርነት እድትዘፈቅና እድትታመስ ከአሜሪካና ከምዕራባዊያን ጋር ያደረጋችሁት የጫጉላ ሽርሽር ፣ የጫና ውሳኔና ሕዝብን ያላሳተፈ ስምምነት የትም አያደርስም ፣ ትርፉ ኪሳራ ነው።
የሞት ሞት የሚሆነው መላው የኢትዮጵያ እናቶች በመቀነታችው የቋጠሯትን ሳንቲሞች ሰባስበው ፣ መላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘቡንና ላቡን ጠብ አድርጎ የገነባውን የአባይ ግድብ አሳልፎ ለታሪካዊ ጠላቶቻችን ለመስጠት መሸረቡ “ከድጡ ወደ ማጡ” ነው የሚሆንባችሀ።
“ ኋላ ከመማመቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ” እንዲሉ የወልቃይትና የራያን የኢትዮጵያ ጉሮሮና ልብ ትርታ ምድር በፖለቲካዊ ውሳኔ እንደተወሰደ በፖለቲካዊ ውሳኔ መመለሱ የሚያዋጣ አካሄድ ነው ብለን ከወዲሁ እንመክራለን ።
የኢትዮጵያ ባለሥልጣኖች ሊገነዘቡት የሚገባው “ የቆጡን አወርድ ብላ ፣ የብብቷን ጣለች “ እንዲሉ የእነ ጉግ-ማንጉግ የአነሜሪካና መሰሎች” የላም አለኝ በሰማይ” የማይጨበጥ የተስፋ ቃላት ለሳዳም ፣ ለሊቢያ ፣ ሶሪያና መሰሎቹ ሃገር መሪዎች የእግር እሳት ነው የሆነባቸው ። ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የአማራን ታሪካዊ እርስቶች አሳልፎ ለማይገባው በመስጠት ሁለቱን ሕዝቦች በማፈናከት የሚገኝ ብልፅግና “የእምቧይ ካብ” ና እንደ እፉኝት በአንድ ምሽት የሚናድ በግፍ ደም የሚገኝ ክምችት ነው እንላለን። ይልቁንስ እውነታን ፣ ታሪክን ፣ ቱፊትንና የአብዛኛውን ሕዝብ የልብ መሻት ከግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ ወልቃይትን ወደጎንደር አማራ ፣ ራያን ወደ ወሎ አማራ መልሶ በተረጋጋ መልኩ ሃገር መምራቱ ይባጃል ፣ ይብዙሃኑን ሰላም ይጠበቃልና እንላለን።
ተዘራ አሰጉ
ከምድረ እንግሊዝ።