ስሙኝማ እናንተዬ፡-
ጀሮዬ ካላከራከረኝ በስተቀር እመት አዳነች አቤቤ ከየትኛው ተቋም እንደሆነ ለማረጋገጥ ግድ ባይሰጠኝም የሕግ ሙያ እንዳጠኑ በጨረፍታ ሲወራ የሰማሁ መሰለኝ፡፡
ከዚህ በተረፈ ዎይዘሮዋ ቅድመ-ክንትብና በተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት ሓላፊነቶች ተመድበው መስራታቸው የሚታወቅ ሲሆን ከጥቂት ዓመታት በፊት ደግሞ የሀገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ-ሕግ ሆነው እንዳገለገሉም እናስታውሳለን፡፡
ይሁን እንጂ ከተጠቀሰው የሙያ ዝግጅትና የአገልግሎት ቆይታ በተቃራኒው አልፏልፎ የሕግ ትምህርት ቤት ደጃፍ ጨርሶ የረገጡ የማይመስሉባቸውን አንዳንድ አጋጣሚዎች እያስተዋልን መጥተናል፡፡
መደበኛ ትምህርት በኦሮምኛ ቋንቋ ይሰጥባቸዋል በተባሉ አንዳንድ የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቤቶች ቅጥር ግቢ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ እያወረድን የኦሮምያን ባንዲራ በሀይል እንሰቅላለን፣ የዚህንኑ ክልል መዝሙር እናስዘምራለን፣ በሚሉ አክራሪ ወገኖችና ይህንኑ እንቅስቃሴ አጥብቀው በሚነቅፉ መምህራንና ተማሪዎች መካከል ሰሞኑን የሚታየው የርስበርስ ፍጥጫና ያልተገባ ግርግር ብዙዎችን ከልብ እያሳዘነ ነው፡፡
አሁን-አሁንማ ይህንኑ የተቃውሞ አመጽና ግርግር የተማሪዎቹ ወላጆችና ሌሎች ነዋሪዎች በስፋት እየተቀላቀሉት የመጡ ሲሆን ለፖሊስና ለጸጥታ ሀይሎች ሳይቀር ከፍተኛ ራስ ምታት ሆኖባቸዋል፡፡
ክብርት ከንቲባዋ ግን 17ኛውን የብሔር-ብሔረ-ሰቦች ቀን ለማክበር ከታደሙበት ከሃዋሳ ከተማ ሳይነቃነቁ ወደሚዲያ ብቅ ብለው የአዲስ አበባ ህዝብ አስተዋይ ነውና ልጆቹን ይምከር በማለት በስላቅ የታጀበ አስተያየት ከርቀት ሲሰጡ ተደምጠዋል፡፡ ይልቁንም ይህ ጉዳይ የከተማው ህዝብ አጀንዳ እንዳልሆነ ገልጸው በአንዳንድ ወገኖች አለአግባብ እንደሚቀነቀነው የኦሮሞ ባህል በአዲስ አበባ ህዝብ ላይ እየተጫነ አይደለም ሲሉ በሀሰት ሊያጽናኑን ሞክረዋል፡፡
እንደእውነቱ ከሆነ በመዲናይቱ ውስጥ በሚገኙት የእንጦጦ አምባ፣ የካራማራና የአዲስ ከተማ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመታየትና ወደሌሎች መሰል ተቋማት ቀስ በቀስ በመስፋፋት ላይ ያለው ህዝባዊ ሁከት ለንጹሃን ወገኖች የአካል ጉዳትና ለየትምህርት ቤቶቹ የንብረት ውድመት ጭምር አሉታዊ አስተዋጽኦ ከማበርከቱም በላይ የመማር ማስተማሩን ሂደት ከናካቴው እንዳያስተጓጉለው ክፉኛ የሚሰጉ ዜጎች ብዙኃን ናቸው፡፡
እርሳቸው ግን የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆነው ሳለ መዲናችን ላለፉት 30 ዓመታት የኦሮምያ ክልል ርእሰ-ከተማ ሆና ስታገለግል ቆይታለች ይሉንና ይህ በበኩሉ ሕገ-መንግሥታዊ ድጋፍ እንዳለው እርግጠኝነት በጎደለው ማብራሪያቸው ሊያሳምኑን ሲውተረተሩ ተመልክተናቸዋል፡፡
ማንም ከሀገሪቱ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 49 ድንጋጌዎች በቀላሉ እንደሚረዳው አዲስ አበባችን ራሷን የቻለችና ሕገ-መንግሥታዊ ህልውና ያላት ከተማ ነች፡፡ የከተማዋ ከንቲባም ተጠሪነቱ ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤትና ለፌደራሉ መንግሥት ነው፡፡ እመት አዳነች የሚያውቁት የቅርብ አለቃ ግን በካድሬነት አሰልጥኖና በእጩነት አቅርቦ ለያዙት ወንበር ያበቃቸውን የብልጽግና ፓርቲ፣ በተለይም የኦሮምያውን ክንፍ ብቻ ይመስላል፡፡
እነሆ በከንቲባነት ይመሯት ዘንድ ቃለ-መሃላ ፈጽመው በይፋ የተረከቧት ይህቺው እድለቢስ ከተማ እርሳቸው ብቻ ባነበቡት ሕገ-መንግሥት መሰረት የኦሮምያ ክልል ዋና ከተማ ናት፡፡ ስለሆነም የተጠቀሰው ክልል ባንዲራ ሊሰቀልባትና መዝሙሩ ሊዘመርባት ይገባል፡፡ አፈጻጸሙም ቢሆን በግዴታ ጭምር መሆን አለበት፡፡
በመሰረቱ አዲስ አበባ እንደፌደራሉ ሕገ-መንግሥት አቀራረብ ከሆነ ዋና ከተማ መሆን ይቅርና የኦሮምያ ክልል ክፍልና አካል እንኳን አይደለችም፡፡ አዳነች በአደናጋሪ ድምጸት የሚያወሩልን ስለኦሮምያ ሕገ-መንግሥት ከሆነ ደግሞ ይህ ማእቀፍ ተፈጻሚነቱ በዚያው ክልል የግዛት ወሰን የተገደበ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
ከዚህ ጥሬ ሀቅ ስንነሳ ታዲያ እንደርሳቸው የተማረና የተመራመረ ብቻ ሳይሆን በመንግሥት ተሹሞ ህዝብን እንዲያገለግል የመዲናዋን መክፈቻ ቁልፍ የተረከበ ቱባ ባለሥልጣን ይቅርና የሕግ ሀ/ሁን የቆጠረ ማንኛውም ተራ ዜጋ አዲስ አበባ ውስጥ የአንድ ክልል ባንዲራ በተናጠል ተለይቶ ይሰቀል፣ መዝሙሩም ይዘመር ብሎ እንዴት በዚህ ደረጃ በአደባባይ ደፍሮ ሊሟገት እንደሚገባ ለመረዳት ፈጽሞ አዳጋች ይሆናል፡፡
ይህ መቸም ሌላ ሳይሆን ጫፍ የረገጠ የበታችነት ስሜት ከመነሻው አርግዞ ቅድመ-ልደት የጨነገፈው አቋም መሆን አለበት፡፡
በዚህ ጸሃፊ አስተያየት ዎ/ሮ አዳነች ቀልደኛ ሴት ናቸው፡፡
ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ችግረኛ ተማሪዎችን በምገባ ፕሮግራም እንዲታቀፉ አድርገን ስለምንመግብላችሁ ብትወዱም ባትወዱም የኦሮምያ መዝሙር በትምህርት ቤቶች ውስጥ መዘመሩን ይቀጥላል ሲሉ በአንድ ወገን እየዛቱ በአሁኑ ወቅት ከተማችንን በማተራመስ ላይ ያሉት ዖ.ነ.ግ-ሸኔ፣ ጽንፈኛው ፋኖና በስም ያልጠቀሷቸው ምእራባውያን ሀይሎች ናቸው በማለት ወዲያውኑ ከገዛ ራሳቸው ጋር በቀጥታ ሲላተሙ አንዳች ሀፍረት የሚሰማቸው አይመስልም፡፡
ነገሩ የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም መሆኑ ነው፡፡
እመት አዳነች ከወራት በፊት በአንድ ሌላ መድረክ ላይ ተገኝተው ትግራይን አንድ ነጻና ሉኣላዊት ሀገር ለማድረግ ካስፈለገ እኮ መላዋን ኢትዮጵያ ማተራመስ ወይም ማፍረስ አይገባም ሲሉ የቱን ያህል እንዳስደመሙን አይዘነጋም፡፡
ሴቲዮዋ በዚያ ዝነኛ ዲስኩራቸው ራሳቸው የቀረጹትን የሕገ-መንግሥቱን አንቀጽ 39 ተጠቅመው በሠላም ከኢትዮጵያ ይገነጠሉ ዘንድ የትግራይ ወገኖቻችንን በአደባባይ እስከመምከር የሄዱበት ርቀት በአንዳንድ ደጋፊዎቻቸው ዘንድ ከአይን ያውጣሽ ያስባላቸውን ያህል በተቺዎቻቸው ዘንድ ደግሞ አይንሽ ለአፈር ሲያሰኛቸው እንደሰነበተ ፈጽሞ አንረሳውም፡፡