October 7, 2022
49 mins read

 ኢትዮጵያና የፖለቲካ ፓርቲዎቿ – ኤፍሬም ማዴቦ

Efrem Madebo 1ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected])

ፖለቲካ፣ፓርቲና ዉክልና የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ዋልታና ማገር ናቸው። ዲሞክራሲ የዜጎችን ፖለቲካዊና ማህበራዊ ተሳትፎ የግድ የሚል ሥርዓት ነው፣ ተሳትፎ ሲባል ግን ዜጎች ሁሉ ቁጭ ብለው በአገራቸው ወይም በአካባቢያቸው ጉዳይ ይወስናሉ ማለት አይደለም። ዛሬ ዓለም በደረሰበት የዲሞክራሲ ዕድገት ደረጃ አገራዊ ዉሳኔዎች የሚወሰኑት በውክልና ነው። እኛ ዜጎች በምንኖርበት የፖለቲካ ማህበረሰብ ውስጥ መንግስት እንዲያሳካልን የምንፈልገው የየራሳችን ፍላጎት አለን፣ በዲሞክራሲ ዉስጥ እነዚህን የተለያዩ ፍላጎቶች ጠቅልለውና በፖሊሲ መልክ ነድፈው መንግስታዊ ምላሽ እንዲያገኙ ትልቁን ሚና የሚጫወቱት የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው።

ኢትዮጵያ ውስጥ የምርጫ ቦርድ እውቅና ያላቸው ከ45 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉ ይነገራል። ነገር ግን ብዙዎቹ ፓርቲዎች መንግስት ባስነጠሰው ቁጥር የመግለጫ ጋጋታ ከማውጣት አልፈው የፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድ ማህበረሰብ ዉስጥ መስራት የሚገባቸውን ስራ አንድ አራተኛውን የማይሰሩ ፓርቲዎች ናቸው። የ3ሺ አመት ታሪክ አላት ተብሎ በሚነገርላት ኢትዮጵያ ዉስጥ ፓርቲና የፓርቲ ፖለቲካ ታሪክ ገና የአንድ ሰው ዕድሜ አላስቆጠረም። ኢትዮጵያ ዉስጥ እንደ አሸን የፈሉት የብሔር ፓርቲዎች “አንድ ሰው አንድ ድምፅ” የሚለው ቁልፍ የዲሞክራሲ መርህ አገራችን ዉስጥ እንዳይኖር ያለፈው ሥርዓት ጠፍጥፎ የሰራቸው አጃቢ ፓርቲዎች ናቸው። እነዚህ በተቋቋሙበት መሰረታዊ አላማም ሆነ በድርጅታዊ አቅማቸው ደካማ የሆኑ ፓርቲዎች መኖራቸው የሚታወቀው ቁጥራቸው ሲነገር ነው እንጂ በሚሰሩት ስራ አይደለም።

ኢትዮጵያ ውስጥ አንዳንዶቹ ፓርቲዎች ባልና ሚስት በሊቀመንበርነትና በገንዘብ ያዥነት የሚመሯቸው ፓርቲዎች ናቸው፣የአንዳንዶቹ ፓርቲዎች መሪዎች የሚተዳደሩት ከምርጫ ቦርድ በሚገኝ ገንዘብ ነው፣አንዳንዶቹ ፓርቲዎች ደግሞ ቢሯቸውም መኖሪያ ቤታቸውም አንድ ላይ ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎችን አስመልክቶ በቅርቡ ከምርጫ ቦርድ አካባቢ የተሰማው ዜና አንገት የሚያስደፋ ነው። አንድ በምርጫ ቦርድ ተመዝግቦ የሚንቀሳቀስ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤን ሲያካሄድ የጉባኤ አባላት ማሟላት አቅቶት የፓርቲው አባላት ናቸው ብሎ አበል እየከፈለ ወደ ጉባኤ ያመጣው የጎዳና ተዳዳሪዎችን እና በልመና ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎችን ነው። ፖለቲካችን ምስቅልቅሉ የወጣ የዕብድ ጨዋታ የሆነው የፖለቲካውን መድረክ የሚቆጣጠሩት እንዲህ አይነት ደካማና አሳፋሪ ፓርቲዎች ሰለሆኑ ነው።

የኢትዮጵያ ፓርቲዎች በፖለቲካ ሥርዓቱ ዉስጥ መጫወት ያለባቸውን ሚና እንዳይጫወቱ የሚያደርጉ መዋቅራዊ መሰናክሎች አሉ፣ ለምሳሌ፣ አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ፓርቲዎች ግልፅ የሆነ ርዕዮተ ዓለም የላቸውም፣ ጥራትና ወጥነት ያለው የፖሊሲ አማራጭ የላቸውም፣ ከምርጫ ግዜ ውጭ በስራ ሊገለጽ የሚችል ድርጅታዊ መዋቅር የላቸውም፣ ፓርላማ ውስጥ የተቀናጀ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል አቅም ያላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሉም፣አንዳንዶቹ ፓርቲዎች ቢሯቸውም መኖሪያ ቤታቸውም አንድ ላይ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ የምትገኝበት ዝቅተኛ የኤኮኖሚ ዕድገት ደረጃና ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለው የምርጫ ሥርዓት በፓርቲዎቹ ማንነትና (Party Identity) ድርጅታዊ ጥንካሬ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያደርጋሉ። የፖለቲካ ፓርቲ ማለት ምን ማለት ነው?

የፖለቲካ ፓርቲ ማለት – ተመሳሳይ ርዕዮተ ዓለም፣ ዓላማና ግብ ያላቸው ግለሰቦች ተሰባስበው ፖለቲካዊ፣ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ አስተሳሰባቸውን በፖሊሲ መልክ ቀርጸው በሚኖሩበት ማህበረሰብ ዉስጥ ለማስፋፋትና፣ መንግስት በሚቀርጻቸው አገራዊ ፖሊሲዎች ላይ ተፅዕኖ ከማድረግ ጀምሮ የፖለቲካ ሥልጣን እስከመያዝ ድረስ በአንድ አገር ማህበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ህይወት ዉስጥ ቁልፍ ሚና የሚጫወት የዲሞክራሲ ተቋም ነው። የፖለቲካ ፓርቲ- ዜጎች ፖለቲካዊና ስነልቦናዊ እሴቶቻቸው ተቋማዊ መልክ እንዲይዙና በሚኖሩበት ማህበረሰብ ዉስጥ እንዲሰራጩ የሃሳብ ፍጭትና ትግል የሚያደርጉበት የውክልና ዲሞክራሲ ተቋም ነው።

አገራችን ኢትዮጵያ በአንድ በኩል እንዲህ ዓይነት ሥራ የሚሰሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሌሉባት በሌላ በኩል ደግሞ ጠንካራ ፓርቲዎች እንዳይኖሩ ብዙ ሥራ የተሰራባት አገር ናት። እኔን የሚገርመኝ ኢትዮጵያ ውስጥ ጠንካራ ፓርቲዎች አለመኖራቸውና የሥርዓተ-ፓርቲያችን ዕድገት ደረጃ አሁንም እንጭጭ መሆኑ አይደለም። እኔን የሚገርመኝ አሁን ያሉን ፓርቲዎች እባካችሁ እደጉ ተብለው ሲለመኑ “ትንሽነት በስንት ጣዕሙ” ማለታቸው ነው። ለመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስራ ምንድነው?     

የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደማንኛውም ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ክስተት በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ የሚኖሩበት የራሳቸው የሆነ ምክንያት አላቸው። የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህንን ለህልውናቸው መሠረት የሆነውን ምክንያት የሚገልጹት በማህበረሰብ ውስጥ በሚሰሩት የአጭርና የረጂም ግዜ ሥራ ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚኖሩበት የፖለቲካ ሥርዓት ውሰጥ ለመሳተፍ፣ የህዝብን ጥቅምና ፍላጎት ለመወከልና ዲሞከራሲያዊ ሥርዓቱን ለማጎልበት በመጀመርያ እነሱ እራሳቸው በእግራቸው መቆም መቻላቸውንና እናደርጋለን ብለው ለህዝብ የሚገቡትን ቃል የመፈጸም ችሎታ እንዳላቸው ማረጋገጥ አለባቸው፣ ይህንን ለማድረግ ደሞ በአይን የሚታይ ስራ መስራት አለባቸው። የፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድ አገር ፖለቲካዊና ማህበራዊ ህይወት ውስጥ የሚጫወቱት ሚና እጅግ በጣም ብዙ ነው፣ የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው-

 

የፖለቲካ ፓርቲዎች . . .

  • በምርጫ ይወዳደራሉ፣ ምርጫ አሸንፈው መንግስት ይመሰርታሉ
  • በህግ አስፈጻሚውና በህግ አውጪው አካል ውስጥለህዝብ ጥብቅና ይቆማሉ
  • መንግስት ለሰራውና መስራት ሲገባው ላልሰራው ስራ ተጠያቂ እንዲሆን ያደርጋሉ
  • ህዝብ የዲሞክራሲን ልምድና ባህል እንዲለማመድ ያደርጋሉ
  • በብሔራዊና በአካባቢ ደረጃ የህዝብን ጥቅምና ፍላጎት ይወክላሉ
  • ብሔራዊፖሊሲና ፕሮግራም ይነድፋሉ
  • የፖለቲካመረጋጋት ይፈጥራሉ
  • የአገርመሪዎችን ኮትኩተው ያሳድጋሉ
  • ተቃውሞዎችንናየሐሳብ ልዩነቶችን ያደራጃሉ፣ ያቀነባብራሉ
  • ለዜጎች የመረጃ ምንጭ በመሆን ያገለግላሉ

 

ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ህጋዊ እውቅና አግኝተው የሚንቀሳቀሱ ከ45 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ፣ ለመሆኑ ስንቶቹ ናቸው እነዚህን ከላይ የተጠቀሱትን ስራዎች መስራት በሚችሉበት መልክ የተደራጁት? ስንት ፓርቲዎች ናቸው ትርጉም ያለው ራዕይ፣ተልዕኮ፣ ግብ፣ የፖለቲካ ፕሮግራም፣ መተዳደሪያ ደንብ፣ ስትራቴጂያዊ ዕቅድና የአጭርና የረጂም ግዜ የስራ ዕቅድ ያላቸው? ኑሮውን ኖረውለት የማያውቁትንና አንድም ቀን ለችግሮቹ መፍትሄ አግኝተውለት የማያውቁትን ብሔር እንወክላለን ከሚሉ የዘር ፓርቲዎችና፣ መኖራቸውን ለማሳወቅ የመግለጫ ጋጋታ ከሚያወጡ ፓርቲዎች ውጭ፣,ኢትዮጵያ ዉስጥ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በሚኖርበት የፖለቲካ ማህበረሰብ ውስጥ መስራት የሚገባውን ስራ ሲሶውን ለመስራት የሚሞክሩ ፓርቲዎች ቁጥር ከሁለትና ሶስት አይበልጥም።የሚገርመው ኢትዮጵያ ውስጥ ማህበረሰቡም የፖለቲካ ፓርቲዎችን ስራ በሚገባ ስለማይረዳ፣የፓርቲዎችን ጥንካሬ የሚለካው በሚያወጡት የመግለጫ ቁጥር ነው። እኛ ኢትዮጵያዊያን የምንገነባው ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ጥንካሬ፣ጥራት፣ጥልቀትና ስፋት ካሉን የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥራትና ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ሥርዓተ-ፓርቲ ጥንካሬ ጋር በቅርብ የተያያዘ ነው። ስለዚህ የፖለቲካ ፖርቲዎቻችን መሰባሰብ፣ መጠናከርና አገራዊ መልክ መያዝ ለነሱ ብቻ የምንተወው ስራ ሳይሆን የእያንዳንዳችን ስራና ሃላፊነት መሆን አለበት።

ባለፉት ሰላሳ አመታትና ዛሬም ጭምር ኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት አገር ናት እየተባለ ይነገራል፣ ነገር ግን በደርግና በህወሓት ዘመንም ዛሬ በ2015ም ኢትዮጵያ የአንድ አውራ ፓርቲ አገር ናት። በደርግ ዘመን ኢሠፓ፣ በህወሓት ዘመን ኢህአዴግ፣ ዛሬ ደግሞ ብልፅግና ፓርቲ የአገሪቱ አውራ ፓርቲዎች ናቸው። አውራ ፓርቲ ሲባል በፖለቲካ ሥርዓቱ ውስጥ አንድ ፓርቲ ብቻ ነው ያለው ማለት አይደለም። በፖለቲካ ሥርዓቱ ውስጥ ብዙ ፓርቲዎች ሊኖሩ ይችላሉ። የፓርቲ ሲስተሙን “አውራ” የሚያሰኘው አንድ ፓርቲ በፓለቲካ ሥርዓቱ ውስጥ ካሉት ፓርቲዎች ጋር እየተወዳደረ በተከታታይ እያሸነፈ ለረጅም ዓመታት የፖለቲካ ሥልጣን ይዞ መቆየት ሲችል ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አውራ ፓርቲ ግን ከዚህም የዘለለ ነው፣ዛሬም ያለውና ከ1983-2020 ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው አውራ ፓርቲ ከመንግስት ጋር እጅና ጓንት የሆነ በድርጅታዊ አቅሙና በኃብቱ የተቀሩት ሃምሳ ፓርቲዎች ተዋህደው አንድ ቢሆኑ አጠገቡ የማይደርሱ ግዙፍ ፓርቲ ነው።

በአንድ አገር ውስጥ መድበለ ፓርቲ ሥርዓት አለ ሲባል በፖለቲካ ሥርዓቱ ውስጥ ብዙ ፓርቲዎች  አሉ ማለት ብቻ አይደለም። በአንድ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት አለ ሲባል፣ በፖለቲካ ሥርዓቱ ውስጥ ሁለትና ከሁለት በላይ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ውድድር ያደርጋሉ፣ ደሞም በምርጫ የተወዳዳሩ ፓርቲዎች ሁሉ ቢያሸንፉ ብቻቸውን ወይም ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የጥምር መንግስት መስርተው አገር መምራት ይችላሉ ማለት ነው። ከዚህ በተጨማሪ በአንድ አገር ውስጥ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት አለ ሲባል፣ በምርጫ ተወዳድረው መንግስት መመስረት የሚያስችል የምክር ቤት መቀመጫ ማሸነፍ ያልቻሉ ወይም በጥምር መንግስት ውስጥ መካተት ያልቻሉ ፓርቲዎች በሥልጣን ላይ ያለውን መንግስት ተጠያቂ ማድረግ የሚችሉና በሚቀጥለው ምርጫ የማሸነፍ ዕድል ያላቸው ፓርቲዎች ናቸው ማለት ነው። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫ አሸንፈው ብቻቸውን መንግስት የመመስረት አቅም ያላቸው ፓርቲዎች ስንት ናቸው?

ብልፅግና ፓርቲ በፋይናንስ፣በድርጅታዊ አቅሙና በአባላት ብዛቱ ከሌሎቹ ፓርቲዎች ጋር ሲወዳደር፣ ሌሎቹ ፓርቲዎች ተደምረው የብልፅግናን አስራ አምስት ከመቶ አይሆኑም። ብልፅግና ፓርቲ በድርጅታዊ አቅሙ እንዲህ ጠንካራ ሊሆን የቻለው ከሌሎች ፓርቲዎች የተሻለ አመራር፣ የተሻለ የሰው ኃይል፣የላቀ  ራዕይና ርዕዮተ ዓለማዊ ጥራት ኖሮት አይደለም። የብልፅግና ፓርቲ ጥንካሬ የሚመነጨው ፓርቲው ከኢህአዴግ ከወረሰው መንግስትንና ፓርቲን ለይቶ ካለማየት ባህል ነው። ብልጽግና ፓርቲ ምን ያክል ግዙፍ እንደሆነ ለማወቅ አራት ኪሎ የሚገኘውንና በፌዴራል ፖሊስ የሚጠበቀውን የፓርቲውን ጽ/ቤትና የሌሎቹን ፓርቲዎች ጽ/ቤቶች ማወዳደር ይበቃል።

በዲሞክራሲ ወደፊት በገፉና ጠንካራ ሥርዓተ-ፓርቲ ባለባቸው አገሮች ዉስጥ የአውራ ፓርቲ መኖር ግዜያዊ ክስተት ነውና ጉዳት የለውም። እንደ ኢትዮጵያ አይነቱ አውራ ፓርቲ ግን በአገራችን የሥርዓተ ፓርቲ ዕድገት ውስጥና ባጠቃላይ በዲሞክራሲ ጅምራችን ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋልና ካሁኑ ሊታሰብበት ይገባል። መንግስትና ፓርቲ በማይለያዩበት የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ አውራ ፓርቲ በዲሞክራሲ ስም ምን ያክል ዲሞክራሲን ሊጎዳ እንደሚችል የ2013ቱ ምርጫ በግልጽ አሳይቶናል። ጠንካራ ፉክክር ይታይበታል የተባለው የ2013ቱ ምርጫ በአንዳንድ አካባቢዎች ለምሳሌ፣ ኦሮሚያ ውስጥ እንኳን ፉክክር ሊታይበት፣ ኦሮሚያ ውስጥ የተካሄደው የአንድ ፓርቲ የምርጫ አውደ ርዕይ እንጂ ምርጫ አይደለም። በሌሎች አካባቢዎችም ቢሆን፣ በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት በመላው አገሪቱ ያለምንም እንከን ቅስቀሳ ማካሄድ የቻለው ብልፅግና ፓርቲ ብቻ ነው። የሌሎች ፓርቲዎች ተወዳዳሪዎችና ደጋፊዎች ተንከራተዋል፣ ተደብድበዋል፣ ታስረዋል። የተገደሉም አሉ። ለምሳሌ፣ ቢሾፍቱ ውስጥ የኢዜማውን ግርማ ሞገስን እንገድልሃለን ብለው የዛቱበት ሰዎች በጥይት ተኩሰው ገድለውታል፣ቤንሻንጉል-ጉሙዝ ውስጥ ደግሞ የአብን ዕጩ ተወዳዳሪ በምርጫ ዘመቻው ወቅት መሳሪያ በታጠቁ ሰዎች ተገድሏል። እነዚህን ሁለት የዲሞክራሲ ሰማዕታት ማን ገደላቸው የሚለው ጥያቄ ግን አሁንም መልስ አላገኘም . . .  ነገሩ የጠፋን በሬ ከሰረቀው ሌባ ጋር ማፋለግ ነውና ወንጀለኞቹ የግርማ ሞገስና የብርሃኑ አስፈራው ገዳዮች የሚገኙም አይመስልም። በ2013ቱ የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች የተቃዋሚ ፓርቲ ዕጩ ተወዳዳሪዎችንና ደጋፊዎችን ያዋከቡት፣ የደበደቡትና ያሰሩት ለምን የማይባሉ የክልል፣ የዞንና የወረዳ የመንግስት ባለሥልጣኖች ነበሩ።

በውክልና ዲሞክራሲ ዉስጥ ፓርቲና ዲሞክራሲ የማይነጣጠሉ ክስተቶች ናቸው። በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ዲሞክራሲ ሳይኖር የፖለቲካ ፓርቲ ሊኖር ይችላል፣ ፓርቲዎች የሌሉበት ዲሞክራሲ ግን የለም። የፖለቲካ ፓርቲዎች የአንድን ማኅበረሰብ ፖለቲካዊ፣ ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፍላጎት አቀናጅተው በፖለቲካው አድማስ ውስጥ ከአንዱ ጫፍ ወደሌላው ጫፍ የሚያንሸራሽሩ መንኩራኩሮች ናቸው። አገራችን ኢትዮጵያ በነጋ በጠባ መግለጫ ከማውጣት ባሻገር የሚወክሉትን ህዝብ መንኩራኩር ሆነው የሚያገለግሉና፣ አገራችን ኢትዮጵያ ዛሬ የምትገኝበትን እጅግ በጣም አሳሳቢ ሁኔታ በውል የሚረዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያስፈልጓታል። እንዲህ አይነት ፓርቲዎች እንዲኖሩን ህዝብ፣ መንግስት፣ ምርጫ ቦርድና የፖለቲካ ፓርቲዎች የየራሳቸውን ሃላፊነት መወጣት አለባቸው።

ህዝብ- በአንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ውስጥ ማህበረሰቡን ከመሪዎቹ፣ ከተወካዮቹ፣ ከተለያዩ የፖለቲካ ሥርዓቱ አካላትና ከፖሊሲ አርቃቂዎች ጋር የሚያገናኘው መንገድ የሚገነባው በዜጎች ፖለቲካዊ ተሳትፎና ከተሳትፎው በሚወጣው ድምፅ ነው። የዜጎች ድምፅ ነውና ተደምሮ የህዝብ ድምጽ የሚሆነው፣የአንድ ግለሰብ ዜጋ ድምፅ ከሌለ የህዝብ ድምጽ ብሎ ነገር የለም። ስለዚህ በየትኛውም ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ትልቁና መሰረታዊ የሆነው የፖለቲካ ጅምር ግለሰብ ወይም ዜጋ ነው። ዜጎች እየተፈላለጉ ከሚገናኙበትና በሚኖሩበት ማህበረሰብ ውስጥ ኤኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ አስተሳሰባቸውን ከሚያሰርጹበት የተለያዩ ተቋሞች ውስጥ አንዱና የመጀመሪያው የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው። የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ ሥርዓቱ የዜጎችን ጥያቄ እንዲመልስ ማድረግ የሚችሉት ዜጎች በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በሚያደርጉት ተሳትፎ መጠን ነውና፣ የኢትዮጵያ ህዝብ መብቱን የሚያስከብሩለት ፓርቲዎች እንዲኖሩ ከፈለገ የዜግነት መብቴንና ነጻነቴን ያስከብሩልኛል ብሎ የሚተማመንባቸውን ፓርቲዎች በተለያየ መልኩ መደገፍ አለበት።

ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ዕድገትና ጥንካሬ ባጠቃላይ የዲሞክራሲ መስከንና መረጋጋት ካለህዝባዊ ተሳትፎ የሚታሰብ አይደለም። ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ተሳትፎ ከሚያደርባቸው ተቋሞች ውስጥ አንዱና ዋነኛው የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው። የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚኖሩት ለህዝብ ነው፣ የሚያኖራቸውም ህዝብ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ መንግስትን ለህዝብ ተጠያቂ ማድረግ የሚችሉና የህዝብን ጥቅምና ፍላጎት ትርጉም ባለው መልኩ መወከል የሚችሉ ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲኖሩ ከተፈለገ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ልህቃን፣ ምሁራን፣ ገበሬውና ሰራተኛው የፖለቲካ ፓርቲዎች አባል መሆንና የፓርቲ ግዴታቸውን መወጣት አለባቸው። ዜጎች የፓርቲዎችን የኤኮኖሚ፣ የፖለቲካና ማህበራዊ ፖሊሲዎች አንብበው አስተያየት መስጠት አለባቸው፣ ፓርቲዎች በሚያዘጋጇቸው ስብሰባዎች፣ ውይይቶችና አውደ ርዕዮች ላይ መሳተፍ አለባቸው። በአንድ አገር የሚኖር ዜጋ ሁሉ  የፖለቲካ ፓርቲዎች አባል መሆን ላይችል ይችላል፣ ነገር ግን እያንዳንዱ ዜጋ በፖለቲካ ፕሮግራሙ የሚደግፈውን ፓርቲ በበጎ ፈቃደኝነት፣ በሃሳብ፣በቴክኒክ፣ በቁሳቁስና በፋይናንስ መደገፍ ይችላል። እንደዚህ አይነት ህዝባዊ ተሳትፎ ሲኖር ነው ፓርቲዎቻችን የሚያድጉትና አገራችንን የሚያሳድጉት።

መንግስት- በብዙ አገሮች ውስጥ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔሮች ባለበቸውና ለዲሞክራሲ አዲስ በሆኑ አገሮች ውስጥ መንግስት የፓርቲዎችን ዕድገትና ጥንካሬ የሚያበረታቱ የተለያዩ ዕርምጃዎች ይወስዳል። ለምሳሌ፣ ሩሲያ ከኮሚኒዝም ስትላቀቅ ከወሰደቻቸው ዕርምጃዎች ውስጥ አንዱ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎቿ ከብሔር ወይም በማንነት ላይ ከተመሰረተ አደረጃጀት ተላቅቀው በብሔራዊ ደረጃ እንዲደራጁ ማድረግ ነበር። ይህንን ለማድረግ የሩሲያ መንግስት በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚቋቋሙ ፓርቲዎች  ተቋማዊ ድጋፍና ማበረታቻ ሰጥቷል። የኢትዮጵያ መንግስትም ዛሬ እንደ አሸን የፈሉት ደቃቃ ፓርቲዎች ወደ ትልቅ አገራዊ ፓርቲነት እንዲለወጡና የኢትዮጵያ ሥርዓተ-ፓርቲ ዕድገት እንዲፈጠን የተለያዩ ተቋማዊ ዕምጃዎችን መውሰድ አለበት።

ኢህአዴግን አፍርሰው ብልፅግና ፓርቲን የመሰረቱ የብልፅግና መሪዎች ኢህአዴግን እንዳፈረሱ ከኢህአዴግ የወረሱትን ጎታች ባህልም ከራሳቸው ላይ አፈራርሰው መጣል አለባቸው። የኢትዮጵያ መንግስት፣ ፓርቲና “መንግስት” የተለያዩ አካላት መሆናቸውንና የመንግስት ንብረት፣ ቁሳቁስና ፋይናንስ ከፖርቲ ንብረት፣ ቁሳቁስና ፋይናንስ ጋር በፍጹም የማይገናኙ መሆናቸውን ማወቅ ብቻ ሳይሆን ይህንን ልዩነት ማክበርም ማስከበርም አለበት። ይህንን ልዩነት የማያከብሩና የመንግስትን ንብረት፣ፋይናንስና ቁሳቁስ ለፓርቲ ስራዎች የሚጠቀሙ የመንግስትና የፓርቲ ባለሥልጣናት ህጋዊ ዕርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል። የምርጫ ቅስቀሳ በሚኖርበት ግዜም ሆነ በሌላ በማንኛውም ግዜ፣ በግብር ከፋዩ ገንዘብ የሚተዳደር የትኛውም የፌዴራልና የክልል መንግስታት ተቋምና አገልግሎት ሰጪ ድርጅት በገዢው ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ምንም ልዩነት አለማድረጉን የኢትዮጵያ መንግስት ማረጋገጥ አለበት። ባጠቃላይ የኢትዮጵያ መንግስት በሚወስዳቸውም በማይወስዳቸውም ዕርምጃዎች ለፖለቲካ ፓርቲዎችና ለሥርዓተ-ፓርቲ ዕድገት ድጋፍም ዋስትናም መስጠት አለበት።

ምርጫ ቦርድ- ኢትዮጵያ ዉስጥ አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች አገራዊ አጀንዳ የሌላቸው ትናንሽ የብሔር ፓርቲዎች ናቸው። እነዚህ ትናንሽ ፓርቲዎች ወደ ትላልቅ አገራዊ ፓርቲነት እንዲለወጡ ምርጫ ቦርድ የተለያዩ ተቋማዊ ዕርምጃዎችን መውሰድ አለበት። ምርጫ ቦርድ ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንደየአመሰራረታቸው አገራዊ (National-Party)፣አካባቢያዊ (Regional-Party) እና የብሔር ፓርቲ (Ethnic-Party) በሚል በሶስት ደረጃ ከፋፍሎ በየደረጃው የሚገኙ ፓርቲዎች ከምርጫ ቦርድ የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ማሟላት የሚገባቸውን መስፈርት በግልፅ ማስቀመጥ አለበት። ለምሳሌ፣ አንድ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚደራጅ ፓርቲ አንደኛ- ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት 547 የምርጫ ወረዳዎች ውስጥ በአርባ በመቶዎቹ ዉስጥ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ማቅረብ መቻል አለበት፣2ኛ – ምርጫ ቦርድ በሚያወጣው ቀመር መሰረት አንድ አገራዊ ፓርቲ ከአማራና ከኦሮሚያ በተጨማሪ በሌሎች አራት ክልሎች ውስጥ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ማቅረብ መቻል አለበት። እነዚህን ሁለት መስፈርቶች የማያሟላ ፓርቲ፣ አንደኛ- በአገራዊ ፓርቲነት መመዝገብ መቻል የለበትም፣ ሁለተኛ- ከምርጫ ቦርድ ምንም አይነት የገንዘብ ድጋፍ ማግኘት የለበትም።

አገራዊ ፓርቲ ነኝ የሚል ፓርቲ በሁለትና ሦስት ክልሎች ብቻ እየተወዳደረ አገራዊ ፓርቲ ነኝ ማለት መቻል የለበትም። እንዲህ አይነቱ ህግና መመሪያ ለብሔርና ለአካባቢ ፓርቲዎችም መውጣት አለበት። ባጠቃላይ ምርጫ ቦርድ ኢትዮጵያ ውስጥ ትልልቅ አገራዊ ፓርቲዎች እንዲፈጠሩ ወይም አሁን ያሉት ትናናንሽ ፓርቲዎች ወደ ትልልቅ አገራዊ ፓርቲ እንዲያድጉ የሚያበረታታ ተቋማዊ እርምጃ መውሰድ አለበት። የእንደዚህ አይነት ህግና ደንብ መኖር ትናንሽ ፓርቲዎች እየተሰባሰቡ ወደ ትላልቅ ፓርቲነት እንዲለወጡ ያስገድዳል፣ድርጅታዊ አቅም ያላቸው ፓርቲዎች እንዲፈጠሩ ያደርጋል፣ የአገሪቱን ሥርዓተ-ፓርቲ ያሳድጋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ በተመለከተ ምርጫ ቦርድ ጠንካራና ተከታታይ ክትትል ማድረግ ከሚገባቸው ስራዎች አንዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የገንዘብ ገንዘብ የሚሰበስቡበት መንገድ፣ የገንዘብ ምንጭና የገንዘብ አጠቃቀም ነው። የፓርቲ ፋይናንስን በተመለከተ ደሞ አገራችን ውስጥ ትልቁ ችግር ገዢው ፓርቲ ብልፅግና የመንግስትን ንብረት፣ ቁሳቁስና ፋይናንስ ከፓርቲ ንብረትና ፋይናንስ ለይቶ አለማየቱ ስለሆነ፣ ምርጫ ቦርድ በገዢው ፓርቲ የፋይናንስ ምንጭ ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር ማድረግ መጀመር አለበት። የፓርቲ ገንዘብ አሰባሰብን በተመለከተ ሌሎች ፓርቲዎች ማድረግ የማይችሉትን የገነዘብ አሰባሰብ ዘዴ ገዢው ፓርቲም እንዳይችል ምርጫ ቦርድ ቁጥጥር ማድረግ አለበት። ለምሳሌ፣ የብልፅግና ፓርቲ አባላት የሆኑ የፌዴራልና የክልል መንግስት ሰራተኞችና ማንኛውም ከግብር ከፋዩ ህዝብ በተገኘ ገንዘብ የሚተዳደር ተቋም ሰራተኛ፣ የፓርቲ አባልነቱን ግዴታ የሚወጣው ሰራተኛው በፈለገው መንገድ ነው እንጂ፣ በምንም አይነት መንገድ የፓርቲ መዋጮ እንደ ግብር ከሰራተኛው ደሞዝ ላይ መቆረጥ የለበትም። ብልፅግና ፓርቲ የመንግስትን ተክለሰዉነትና ድርጅታዊ አቅም ተጠቅሞ ከተለያዩ የማህበረሰብ አካላት በተለይ ከንግዱ ማህበረሰብ ላይ ገንዘብ የሚሰበስብበት መረን የለቀቀ አሰራርም በአስቸኳይ መቆም አለበት። ከዚህ በተጨማሪ የምርጫ ቅስቀሳ በሚኖርበት ግዜም ሆነ በሌላ በማንኛውም ግዜ፣ በግብር ከፋዩ ገንዘብ የሚተዳደር የትኛውም የፌዴራልና የክልል መንግስታት ተቋምና አገልግሎት ሰጪ ድርጅት በገዢው ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ምንም ልዩነት አለማድረጉን ምርጫ ቦርድ ማረጋገጥ አለበት።

 

ፓርቲዎች- ኢትዮጵያ ዉስጥ ሥልጣን ከያዘው ፓርቲ የተሻለ አማራጭ መሆን የሚችሉ ፓርቲዎች እንዲኖሩ፣ በድርጅታዊ ብቃታቸውና በሃሳብ ጥራታቸው ገዢውን ፓርቲ ለሚሰራቸውና መስራት ሲገባው ላልሰራቸው ስራዎች ተጠያቂ ማድረግ የሚችሉ ፓርቲዎች እንዲፈጠሩና የኢትዮጵያ ፓርላማ ኢትዮጵያን ወደፊት የሚያስፈነጥር ትክክለኛ የተቃውሞ ፓለቲካ የሚገለጽበት መድረክ እንዲሆን ከተፈለገ፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች የራሳቸውን የቤት ስራ መስራት አለባቸው። የተሰነጣጠቁና ታማኝነታቸው ለአንድ ብሔር ብቻ የሆነ ፓርቲዎች ፓርላማ ዉስጥም ሆነ ከፓርላማ ዉጭ አገርን የሚጠቅም ስራ ቀርቶ እንወክለዋለን የሚሉትን ብሔርም የሚጠቅም ስራ መስራት አይችሉም። ስለዚህ ዛሬ እንደ አሸን የፈሉት ፓርቲዎቻችን ከብሔር ማንነታቸው ተላቅቀው መነጋገር፣ መሰባሰብና ወደ ትልቅ አገራዊ ፓርቲነት መለወጥ ይኖርባቸዋል። የብሔር ፓርቲዎች የኔ ነው የሚሉትን ብሔር ብቻ እየወከሉ የሚደረግ አገራዊ የምርጫ የእያንዳንዱን ብሔር አባላት ቁጥር የሚነግረን “ህዝብ ቆጠራ/ Census Census” እንጂ በምንም አይነት  “ምርጫ/Election” ተብሎ ሊጠራ አይችልም። ፓርቲዎቻችን ወደ ትልቅ አገራዊ ፓርቲነት ተለውጠው የብልፅግናን አውራ ፓርቲነት መቅጨት የሚችል አቅም ካልፈጠሩ፣ ብልፅግና ፓርቲ እንደ ሜክሲኮው ተቋማዊ አብዮታዊ ፓርቲ ከግማሽ ምዕተ አመት በላይ በተከታታይ ምርጫ እንዲያሸንፍ ከማገዝና እነሱም መግለጫ እያወጡ በቋሚ ተቃዋሚነት ከመቀጠል ውጭ፣ ምርጫ አሸንፈው የፖለቲካ ሥልጣን መያዝ ቀርቶ፣ ድምጻቸው እንዲሰማ የሚያደርግ የፖርላማ ወንበር ማሸነፍም አይችሉም።

ማጠቃላያ  

የህዝብን ልቦና የሚገዛ ርዕዮአተ አለማዊ አቋም፣ህዝባዊ መሠረትና አስተማማኝ ድርጅታዊ አቅም ያላቸው ፓርቲዎች በሌሉባት ኢትዮጵያ ዉስጥ ፖለቲካ የጥቂት ግለሰቦችና የተለያዩ ፍላጎት ቡድኖች መጫወቻ መድረክ ከመሆን አልፎ ለአገር የሚፈይደው ፋይዳ የለም። ዛሬ አገራችን ውስጥ በግልጽ የምንመለከተው ይህንኑ አሳዛኝ ሁኔታ ነው። ኢትዮጵያ አገራቸው ያለችበትን ሁኔታ ተረድተው እየተናበቡ የሚሰሩ ልህቃን፣በማህበረሰብ ውስጥ ያለውን ሃላፊነት ተገንዝቦ ይህንን ሃላፊነቱን ለመወጣት የሚጣጣር ምሁርና የርዕዮተ ዓለም ጥራትና ድርጅታዊ ጥንካሬ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች የሌሉባት አገር በመሆኗ፣ የዛሬዋን ኢትዮጵያ ፖለቲካ መድረክ የተቆጣጠሩት “የነደወሉን ተጫኑ” ሸቃዮች፣ የፌስቡክ አርበኞች፣የዩቲዩብ ወናፎችና የሰፈር ጉልቤዎች ናቸው። አገር እስከማፍረስ ድረስ የዘለቀውን የዘር ፖለቲካ በቃ ለማለት፣ ኢትዮጵያ አገራዊ ራዕይ ያላቸው ፓርቲዎችና ጠንካራ ሥርዓተ- ፓርቲ ያስፈልጋታል። ካሁን በኋላ ኢትዮጵያን ካለዲሞክራሲ፣ ዲሞክራሲን ካለ ትክክለኛ ውክልና፣ ትክክለኛ ውክልናን በዜግነት ላይ ከተመሰረተ ፖለቲካ ውጭ፣ፖለቲካንና ውክልናን ደግሞ አለማችን ዛሬ ከደረሰችበት የዲሞክራሲ ዕድገት ደረጃ ከፖለቲካ ፓርቲ ውጭ ማየት አይቻልም።

ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ብሔሮች መኖራቸው፣ የተለያየ ቋንቋ መነገሩና የተለያየ ባህልና ሃይማኖት መኖሩ በራሱ ችግር አይደለም፣ ችግር ሆኖም አያውቅም። ነገር ግን የአገራችን የፖለቲካ ሥርዓት ከእነዚህ የተለያዩ ማንነቶች ውስጥ በአንደኛው ለምሳሌ በብሔር ላይ ተመስርቶ ሲገነባና፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በእነዚሁ ልዩነቶች ላይ ተመስርተው የፖለቲካ ሥልጣን ሲጨብጡ የአገር አንድነት አደጋ ላይ ይወድቅና ጠንካራ የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመገንባት የሚደረገው ጥረት ዋጋ ያጣል። በተለይ ኢትዮጵያን በመሳሰሉ በብሔር፣ በቋንቋ፣ በባህልና በሃይማኖት በተከፋፈሉ አገሮች ውስጥ እያንዳንዱ ማህበራዊ፣ኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ጥያቄ የብሔርና የጎሳ ቅርፅ ስለሚይዝ፣ በተከፋፈሉ ማህበረሰቦች ውስጥ የሚደረጉ የፖለቲካ ውድድሮች ስሌት ‹‹አሸናፊው ሁሉንም ይወስዳል›› በሚል የ‹‹ባዶ ድምር ጨዋታ›› ውጤት ላይ የተመሰረተ ይሆንና ፖለቲካ የአሸናፊና የተሸናፊ ጨዋታ ይሆናል።

“በተከፋፈለ ማኅበረሰብ” ውስጥ በተለይ የማንነት ፖለቲካ በነገሰባቸው አገሮች ውስጥ በምርጫ ወቅት የፖለቲካ ተዋንያኑ ህዝብን በቀጥታ በሚመለከቱ አካባቢያዊ ጉዳዮች፣ በትልልቅ አገራዊ ጉዳዮችና በርዕዮተ ዓለም ላይ ያተኮረ ቅስቀሳ ሲያካሄዱ አይታዩም። እንዲያውም ‹‹በተከፋፈለ ማኅበረሰብ›› ውስጥ የብሔር ፖለቲካ ተዋንያን ደጋፊዎቻቸውን የሚቀሰቅሱት በብሔርና በጎሳ ቃና በታጀበ ቅስቀሳ ነው። የዚህ በብሔርና በጎሳ ቅኝት የተቃኘ ጨዋታ ውጤት ደግሞ አሸናፊነቱን መልቀቅ የማይፈልግ ‹‹አሸናፊ›› እና ተሸናፊነቱን መቀበል የማይፈልግ ‹‹ተሸናፊ›› ስለሆነ የፖለቲካ ሥርዓቱ ሁሌም በእነዚህ ሁለት ተፃራሪ ኃይሎች መካከል በሚካሄዱ ግጭቶች እየተናጠ ይኖራል። ዛሬ አገር ውስጥም ውጭ አገርም በብዙ የኢትዮጵያ ፖለቲካ መድረኮች ላይ ስለ ወደፊቱ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት ሲነገር፣ ፖለቲካችን ከብሔር ማንነት ተላቅቆ በዜግነት ላይ መመስረት አለበት የሚለው ድምፅ በተከታታይ የሚሰማው ህወሓት የገነባው የብሔር ፖለቲካ የብዙዎችን ቤት ስላፈረሰው ነው። የዚህ ጽሁፍ ጸሃፊም የፖለቲካ ፓርቲዎቻችን አደራጀጃት ከብሔር ማንነት መላቀቅ አለበት ብሎ የሚሞግተው የብሔር ማንነትና ፖለቲካ ተጋብተው አንድ ላይ ሲኖሩ አገር መበተን እንደሚችሉ ስለሚረዳ ነው።

ዜግነትና ፖለቲካ ሲጋቡ የሚመሰረተው ትዳር የቤተሰቡን አባላት በግለሰብ ደረጃም ሆነ በቡድን ሁሉንም እኩል ይመለከታል፣ለሁሉም አባላቱ እኩል ነጻነት፣ መብትና ግዴታ፣ የትምህርት፣የጤናና የስራ ዕድል ይሰጣል፣ ሁሉንም በፍትህ መነጽር እኩል ይመለከታል። በዚህ ትዳር ውስጥ ልዩ ልጅ፣የእንጄራ ልጅ፣የቤት ልጅና የማደጎ ልጅ ብሎ ነገር የለም። የዜግነት ፖለቲካ በፖለቲካ ሥርዓቱ ውስጥ ያለውን እያንዳንዱን ዜጋና የወል ስብስብ በእኩልነት ያቅፋል እንጂ፣ እንደ ብሔር ፖለቲካ የኔ ነው እያለ ከሌላው ለይቶ የሚያሽሞነሙነው፣ ወይም የኔ አይደለህም ብሎ የሚያገለው ግለሰብም የወል ስብስብም የለውም። አድሎና አግላይነት በሌለለበት ወይም እያንዳንዱ ዜጋና የወል ስብስብ አጠገቡ ካለው ዜጋና የወል ስብስብ ጋር እኩል ነኝ ብሎ በሚያምንበት የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ደሞ ሰላምና መረጋጋት የየቀኑ ኩነት እንጂ እንደ ዛሬዋ ኢትዮጵያ ህዝብ በየቀኑ ቤተክርስቲያንና መስጊድ የሚሄድለት ጉዳይ አይሆንም። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ከምንም ነገር በላይ ያጣነው ሰላምና መረጋጋት ነውና፣ ለሰላምና መረጋጋት ኖሮን ፊታችንን ወደ ልማትና ዕድገት ማዞር ከፈለግን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የዜግነት ፖለቲካ ግዴታ እንጂ አማራጭ አይደለም። የዜግነት ፖለቲካን የምንፈልግ ከሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎቻችን አደረጃጀት ከማንነት መላቀቅ አለበት፣ ይህ እንዲሆን ደሞ ህዝብ፣መንግስት፣ ምርጫ ቦርድና የፖለቲካ ፓርቲዎች የየራሳቸውን ዕርምጃ መውሰድ አለባቸው።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
Go toTop