የዚህ ጽሑፌ ዓላማ፣ ዛሬ በመንግሥትና በተፋላሚ ወገኖች መካከል እየተደረገ ያለው ግጭት በተወሰኑ ቡድኖች የተቀሰቀሰ እንጂ፣ የሕዝቦች ግጭት አለመሆኑን ለማመልከት ነው። እንደዚሁም፣ የውጭ ኃይላት ለግጭቱ ዘላቂ መፍትሔ ሊያገኙልን እንደማይችሉ ለማሳሰብና በራሳችን ተማምነን ይህንን ቤተሰባዊ አለመግባባትን ራሳችን እንፍታው ብዬ ለመጠቆምም ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንዶቹ በግልጽ፣ ሌሎቹ ደግሞ በድርጊት፣ “ይቺን አገር አፍርሰን አዲሲቷን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በጋራ እንፈጥራለን” እያሉ አገር ማፍረስን እንደ ተቀዳሚ ዓላማ አንስተው ሲጽፉና ሲናገሩ እየተስተዋለ ስለሆነ፣ አገር ማፍረስ ውድ ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑንም በሂደት ለማስረዳት ነው የምጥረው። ያ እንዳለ ሆኖ፣ ወያኔ ዳግመኛ እንዳይለምደው አይቀጡ ቅጣት መቀጣት አለበት ከሚሉና፣ ዓቢይ ዛሬውኑ ሥልጣን መልቀቅ አለበት ከሚሉ ወገኖች የተቃውሞ ድምጽ እንደሚገጥመኝ አውቃለሁ። ይሁን! ሃሳቤን መግለጼ፣ እንደ ሰው ልጅ መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቴ ሲሆን፣ እንደ አንድ ዜጋ ደግሞ ግዴታዬ ነው። ያ እንዳለ ሆኖ፣ የተለየ አስተሳሰብ ካላቸው ወገኖቼ ጋር ደግሞ ቅን ውይይት ለማድረግ ዝግጁ ነኝ።
ከአገር ማፍረሱ እንቅስቃሴ ብጀምር፣ በዘመናችን ብዙ አገራት ሲፈርሱ አይተናል። በአውሮፓ አገር የተከሰቱ መፍረሶች በአብዛኛው በምዕራቡና ምሥራቁ ዓለም መካከል ለሰባ ዓመት ሲካሄድ የነበረው የአይዲኦሎጂ ልዩነት ያስከተለው የቀዝቃዛ ጦርነት ውጤት ሆኖ በምዕራቡ ዓለም አሸናፊነት የተጠናቀቀው ክስተት ነው። ከአውሮፓ ውጪ የተከሰተው የአገር መፍረስ ሂደትም የተቀሰቀሰው የምዕራባውያንን (በተለይም የአሜሪካን) ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ሲሆን፣ የተጠናቀቀውም በነዚሁ በምዕራባውያን አሸናፊነት ነው።
ሶቪዬት ኅብረት የፈረሰው በምዕራቡ የተቀነባበረ የሰባ ዓመት ትግል ምክንያት ነው። ኅብረቱ ከፈረሰ በኋላ ደግሞ 15ቱ የኅብረቱ አባላት (አብዛኞቹ ዩክሬይንን ጨምሮ ድሮ ያልነበሩ) የየራሳቸውን ነጻ አገር መሥርተው ሕይወት ቀጠለ። ሕዝቡም ደግሞ በአብዛኛው ፈልሶ በውጭ አገር ስደተኛ ሆኖ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ አላስቸገረም። ሩሲያ ጊዜያዊ የኤኮኖሚ ችግር ቢያጋጥማትም፣ የአዲሶቹን ጎረቤት አገራትን የሰው ኃይል በመጠቀም ቀስ በቀስ አገግማ ኤኮኖሚዋንም በተፈለገው ደረጃም ባይሆን ሕዝቦቿን ከረኃብና ከስደት አድናለች።
ዩጎዝላቪያ በምዕራቡ ዓለም የተቀነባበረ የማፍረስ ትግል አጄንዳ ምክንያት ከአስከፊ የርስ በርስ ጦርነት በኋላ ፈረሰች። ዩጎዝላቮቹ (ስድስቱም ሬፑብሊኮች) “ያደጉ አገራት” ስለነበሩና ሕዝባቸውም የተማረ በመሆኑ፣ ስደተኛ ሆነው በሄዱባቸው አገራት ሁሉ እንደ ተፈላጊ ሠራተኛ ኃይል ተቆጥረው ተወሰዱ። ምዕራብ አገራት ተቀራመቷቸው ማለት ይቻላል። እኔው ራሴ በሂደቱ የተካፈልኩበት፣ የተባባሩት መንግሥታትም ከመደበኛው አሠራሩ ውጪ፣ በየሳምንቱ በሺዎች የሚቆጠሩትን ዩጎዝላቮችን ያላንዳች ችግር ወደ አውሮፓና አሜሪካ ስንልካቸው ትዝ ይለኛል። ዩጎዝላቪያም ፈርሳ በቦታው ስድስት ነጻ አገራት ሲፈጠሩ፣ አዲሶቹን አገራት መልሶ በማቋቋሙ ላይ የዓለም አቀፉ ማሕበረ ሰብ በመተባበር ይደግፏቸው ስለነበር ከጦርነቱ በኋላ ማህበረሰባዊ እንጂ፣ ጉልህ የሆነ ኤኮኖሚያዊው ችግር አልገጠማቸውም።
ምዕራባውያን አገራት ሆን ብለው ለየራሳቸው ብሔራዊ ጥቅም ከማለት ያፈረሷቸውና ዳግመኛም እንደ አገር እንዳያንሠራሩ ተደርገው የወደሙና እስከ ዛሬም ተመልሰው አገር መሆን ያቃታቸው ከአውሮፓ ውጪ ከሚገኙ አገራት መካከል ኢራቅ፣ ሶማሊያ፣ ሶሪያና ሊቢያ ይጠቀሳሉ። እነዚህ አገራት የነበረው ማኅበራዊ ትስስራቸው በማያዳግም ሁኔታ ስለ ተበጣጠሰ፣ የትናንቱ ሰላማቸው ሕልም ሆኖ ዛሬም በርስ በርስ ውጊያ እየተናጡ ነው።
ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ እነዚህ አገራት ሲፈርሱ በሬዲዮም ሆነ በቴሌቪዥን ይሰማና ይመለከት ነበር። አገራችን ፈርሳ የነዚህ የፈረሱ አገራት ተመሳሳይ ዕጣ እንዳይጋጥማት ከመፍራት የተነሳ፣ ሰሚ አጣ እንጂ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሥጋቱን እየገለጸ ነው። አንዳችም የውክልና መብት ሳይሰጣቸው “ወክልንሃል” የሚሏቸው የፖሊቲካ ድርጅቶች፣ ፓርቲዎችና አክቲቪስቶች እንዲሁም ጽንፈኛ ምሁራን ይህንን የሰፊውን ሕዝባችንን ሥጋት ከምንም ሳይቆጥሩ አገሪቷን አፍርሰን “ለሁሉም የምትመች ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን” እንደ ገና በአዲስ መልክ እንገነባለን ሲሉ ይደመጣሉ። የምንትዋብን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም የሚለው ተረት ከምን እንደ መነጨ የገባቸው አይመስለኝም። ሁለት ነገሮች ያሳዝኑኛል። የመጀመርያው፣ ለዘመናት ከፋም ለማም በፍቅር እንኳ ባንከንፍ እንደ ጥሩ ጎረቤትማማች አብረን መኖራችን እንዳልነበር ተቆጥሮ፣ “ይቺ አገር ካልፈረሰች ሰላም አይገኝም” ብለው በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የሚለፍፉ መኃይማን ምሁሮቻችን፣ አክቲቪስቶቸና የፖሊቲካ ድርጅቶች መኖራቸው ነው። ሁለተኛው ደግሞ፣ ይህንን ወቅታዊ ቀውሳችንን በሠለጠነና ሰላማዊ በሆነ መንገድ በግልጽ ተወያይተን አገር በቀል የአለመግባባቶችን መፍቻ ዘዴዎችን በመጠቀም ፈንታ፣ የአሜሪካና የአውሮፓ መንግሥታት ጣልቃ ገብተው አደራድረውን ለችግራችን መፍትሔ እንዲያገኙልን ያለ መታከት መትጋታችን ነው።
ምናልባት ያሁኑ ትውልድ ባለፈው የመቶ ዓመት ታሪካችን ውስጥ ከምዕራብ አገራት ጋር የነበረንን ግንኙነት በደንብ አልተረዳው ይሆናል። አሜሪካና አብዛኞቹ የአውሮፓ መንግሥታት አገራችን ሁለት ጊዜ በጣሊያን፣ ከዚያ ደግሞ ሶማሌ አንድ ሶስተኛ አገራችንን ስትወር፣ ፍትሓዊ የሆነውን የአገራችንን ኅልውና ለማስጠበቅ ስናደርግ የነበረውን የመከላከል ጦርነት ማገዝ ይቅርና፣ በግልጽ ከጠላታችን ጋር ወግነው ሲወጉን ነበር። ሙሶሊኒ ኢትዮጵያን ሲወርና አጼ ኃይለ ሥላሴ ወደ ጄኔቫ ሄደው በመንግሥታቱ ሕብረት ላይ ንግግር ሲያደርጉ፣ መላው የማሕበሩ አባል መንግሥታት የስብሰባው ተካፋዮች፣ ጠረጴዛውን እየደበደቡ የስብሰባ አዳራሹን በጩኸት በማወክ ንጉሡ እንዳይናገሩ ሲከለክሉ፣ ለኢትዮጵያ ያገዘች ብቸኛ አገር ሶቪዬት ኅብረት ነበረች። ይባስ ብሎም ሙሶሊኒ አዲስ አበባን እንዲይዝ በቃል ማበረታታት ብቻ ሳይሆን በግልጽ ደብዳቤ ጽፋ ድጋፏን የገለጸችላትና፣ ዚያድ ባሬ ኢትዮጵያን ሲወርር፣ በገንዘባችንን የገዛነውን የአውሮፕላናችንን መለዋወጫ መሣርያ እንኳ ከልክላ ለአስከፊ ጥፋት የዳረገችን ይችው ዛሬ “ሰላም እንድታሰፍንልን ጣልቃ እንድትገባ” አንዳንዶች የሚማጸኗት አሜሪካ ነበረች። እንደ ገና የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ፣ በአድዋም ሆነ በማይጨው ከጎናችን የቆመውና፣ የራሱን ወታደሮችና አማካሪዎች ብቻ ሳይሆን መሣርያ ሳይቀር ሰጥቶን እና የኩባና የየመን ወታደሮችን አስተባብሮ አገራችንን ከሶማሊያ ወረራ ያዳነን ሶቪዬት ኅብረት ነበር። መረሳት የሌለበት ታሪካዊ ሓቅ ስለሆነ ነው ያነሳሁት!
እንደ አገር መፍረስ እጅግ በጣም አስፈሪ ነገር በዚህች ምድር ላይ ያለ አይመስለኝም። አብዛኞቹ ከላይ የጠቀስኳቸው አገራት ሲፈርሱና መፍረሳቸው ያስከተለውንም ማኅበራዊ ቀውስ ከቅርብ ሆኜ ያየሁ ስለሆነ፣ አያድርስና ኢትዮጵያን የማፍረስ ሂደትና ከፈረሰችም በኋላ ሊከሰት ስለሚችለው ሁኔታ መገመት እምብዛም አይከብደኝም። አንድ አገር ሲፈርስ ሂደቱ እጅግ አስከፊ የሆነ የርስ በርስ መገዳደልን፣ መፈናቀል፣ ማሰቃየት፣ ዘርን ማጥራት ወይም ማጥፋት ድረስ የሚያስኬድና ኅሊናችን እንኳ መገመት ከሚችለው በላይ የሆነ የጭካኔ ድርጊትን የሚያካትት መሆኑን ከሙያዬ ጋር በተያያዘ ምክንያት ከላይ የተጠቀሱት አገራት አብዛኞቹ ሲፈርሱ በቦታው ተገኝቼ የታዘብኩት ነገር ነው። አገር ፈረሰ ማለት፣ መላው ብሔራዊ መዋቅር (ፖሊስ፣ ፍርድ ቤት፣ መከላከያ ሠራዊት፣ ቢሮክራሲው፣ እድሩና ወርኃዊ ማሕበሩ፣ ሰንበቴው፣ የዓርብ ስግደቱና የእሁድ ጸሎቱ ወዘተ) ሁሉ ፈረሰ ወይም ተዛባ ማለት ነው። እነዚህ መዋቅሮች ሲፈርሱ ደግሞ “አዲሲቷን አገር ተስማምተን እንፈጥራታለን” የሚለው አባባል ባዶ ተረት ይሆናል። ከፈረስክ በኋላ የለህም። በቃ የለህም። ስለሌለህ ደግሞ ምናልባት በወዲያኛው ዓለም እንጃ እንጂ በዚህ ምድር ላይ ለመነጋገር አጋጣሚውንም መድረኩንም አታገኝም።
ሌላው ዘወትር የፖሊቲካ “ተንታኞቻችን” ደጋግመው የሚያሰሙት ግን ደግሞ ምንም ጥልቀት የሌለው “ዓቢይ መሄድ አለበት” የሚለው መፈክር ያኔ ተማሪ ሆነን “የአክሊሉ ካቢኔ ይውረድ” ብለን ቁርጠኝነታችንን ለመግለጽ ደግሞ በድንጋይ የአንበሳ አውቶቡሶችን መስታወት ስንሰብር ያስታውሰኛል። የተለያዩ ሁኔታዎች ተገጣጥመው የአክሊሉ ካቢኔ ሲወርድ፣ እንኳን እኛ ገና ተማሪዎቹ ይቅርና፣ በውጭ አገር ደረጃ በፖሊቲካ ዕውቀታቸው ይመለክባቸው የነበሩ ምሁሮቻቻችን እንኳ አክሊሉን ተክተው የፖሊቲካ ሥልጣኑን ለመረከብ ዝግጁ ስላልሆኑ፣ በወቅቱ የተደራጀ መዋቅር ለነበረው የመከላከያ ሠራዊት የሥልጣን ወንበሩን አስረክበን እንደገና “ደርግ ይውረድ” ብለን ደግሞ መጮህ ጀመርን። ያዘጋጀነውና ደርግን ሊተካ የሚችል የፖሊቲካ ኃይል ስላላዘጋጀን ለጊዜው የተደራጀ ኃይል የነበረው ወያኔ መጥቶ የፖሊቲካ ሥልጣን ወንበሩን ወሰደው። እንደ ገና ደግሞ፣ “ወያኔ ይውረድ” ብለን አገር አቀፍ እንቅስቃሴ ጀመርን። በለስ ቀንቶን፣ ወያኔን ስናወርደው፣ ያዘጋጀነው የፖሊቲካ ኃይል ስላልነበር፣ የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ፣ ያልታሰበና የማናውቀው ዶ/ር ዓቢይ ያገራችን መሪ ሆኖ ብቅ አለ። ዛሬ ዞር ብለን ብንገመግመው፣ የኅብረተሰብ ታሪክ የራሱ ቦይ ስላለውና የታሪክ አጋጣሚ ስለሆነ ብቻ ነው እንጂ፣ መንግሥቱ ኃ/ማርያም ሆኑ መለስ ዜናዊ፣ አቶ ደሳለኝ ኃ/ማርያምም ሆኑ ዶ/ር ዓቢይ አሕመድ፣ ከማንኛውም ኢትዮጵያዊ የበለጡ ፖሊቲከኞችና ኢትዮጵያን ሊመሩ የሚችሉ ብቸኛ መሪዎች ናቸው የሚል ዕብደት አይከጅለኝም። አገሪቷ ከነሱ የተሻሉ ፖሊቲከኞችና መሪዎች እንዳሏት አንዳችም ጥርጥር የለኝምና። ለማለት የፈለግሁት፣ ዛሬ “ዓቢይ ይውረድ” ከማለት ባሻገር፣ እሱ ሲወርድ አገሪቷን የሚመራ ተተኪ ሳናዘጋጅ ዝም ብለን “ይውረድ” ማለቱ ካለፈው ስሕተታችን አለመማር ይመስለኛል።
የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አቋም፣
ዛሬ አገራችን ያለችበትን ሁኔታ ከኛ ይልቅ የውጭ አገር ዲፕሎማቶች የበለጠ የተረዱት ይመስለኛል። በግሌ ከማውቃቸውና ከማነጋግራቸው የምዕራብ አገራት ዲፕሎማቶች ጋር ከማደርገው ውይይት አንድ የማስተውለው ነገር ቢኖር፣ አንዳቸውም የዶ/ር ዓቢይን ከሥልጣን መውረድ አይደግፉም። በዚያው ልክ ደግሞ፣ ወያኔ በምንም ተዓምር ተመልሳ የፖሊቲካ ሥልጣን እንድትይዝ አይፈልጉም። ነጥባቸው፣ ዛሬ አገሪቷ እንደዚህ በየብሔሩ ጽንፈኞች ተከፋፍላ ባለችበት ሰዓት፣ የሁሉንም ወገን ተዓማኒነት ሊያገኝ የሚችል ሌላ መሪ ማግኘት አይቻልም የሚለው ነው። መቶ በመቶ የምስማማበት ነጥብ ነው። ዶ/ር ዓቢይን አስገድዶ “ሕዝቡ የሚፈልገውን እንዲያደርግ” እምቢ ካለ ደግሞ፣ ከሥልጣን ለማውረድ የሚቻለው የሁለቱ ታላላቅ ብሔሮች (የኦሮሞና የአማራ) ፖሊቲከኞችና አክቲቪስቶች እንዲሁም ምሁሮች ጥምረት ሲፈጥሩ ብቻ ነው የሚል እምነት ስላለኝ። በዛሬው የኢትዮጵያ ሁኔታ ደግሞ ይህ ሊከሰት የማይችል ባዶ ሕልም ነው። ጥምረቱ ካልተፈጠረ ደግሞ፣ የአማራም ሆነ የኦሮሞ ፖሊቲከኞች የፈለገውን ያሕል በተናጠል ቢደራጁ፣ ዶ/ር ዓቢይን ከፖሊቲካ ሥልጣን ወንበር ለማውረድ አይችሉም። ዶ/ር ዓቢይም ሆነ የዓለም አቀፉም ማኅበረሰብ ይህንን ጠንቅቀው ያውቃሉ።
የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ እንድትፈርስም በጭራሽ አይፈልጉም። የአውሮፓ ኅብረትና የአሜሪካ መንግሥት በዚህ ላይ አንድ ዓይነት አቁም ነው ያላቸው። አገርን የማፍረስ ልምድም ሆነ የፈረሰ አገር ሊያደርስባቸው የሚችለውን ጉዳት ጠንቅቀው ስለሚያውቁ፣ ኢትዮጵያ ከፈረሰች በቀጠናው የሚከሰተው የጸጥታ ሁኔታ እጅግ በጣም ያሳስባቸዋል። ሁለት ዋና ምክንያቶችን ብቻ ለመጥቀስ ያህል፣
ሀ) የኢትዮጵያ በየርስ በርስ ጦርነት መፍረስ ሊያስከትል የሚችለው የሰዎች መፈናቀልና መሰደድ እጅግ በጣም ያሳስባቸዋል። የኢራቅ፣ የሶርያና የሊቢያ ሕዝቦች ቁጥር ተደምሮ የኢትዮያን ስለማያክል፣ አያድርስና የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመሰደድ ከተገደደ፣ እንኳን አህጉራችን ይቅርና የአውሮፓ ኅብረት አገራትም ተባብረው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩትን የኢትዮጵያን ስደተኞችና ተፈናቃዮች ማስተናገድ አንችልም ብለው ስለሚያስቡ፣ እና
ለ) ኢትዮጵያ ከፈረሰች፣ ዛሬ መተላለፍያ አጥቶ በሶማሊያ ውስጥ ታጥሮበት ያለው አልሻባብ፣ ኢትዮጵያና ጎረቤት አገሮችን በቀላሉ መቆጣጠር ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያም አልፎ፣ ሱዳንና ሳህልን አቆራርጦ እስከ ማግሬብ አገራት ድረስ በመዝለቅ፣ ከአልካይዳና ከቦኮ ሓራም ጋር ጥምረት ፈጥሮና አሕጉራዊ ኃይል ሆኖ የምዕራብ አገራትን ብሔራዊ ጥቅም ሊነካ ይችላል ብለው ስለሚፈሩ ነው።
ሌላ ልናስብበት የሚገባን ጥብቅ ጉዳይም አለ። ምክንያቱ በባይገባኝም፣ ምሁሮቻችን ሳይቀሩ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም አቅጣጫ እየተፈጸሙ ያሉትን አጠቃላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች (የጦርነትና የዘር ማጥፋት/ማጥራት ወንጀልን ጨምሮ) ሲያነሱና ወንጀለኞቹ ለፍርድ እንዲቀርቡ ሲያሳስቡ፣ ፍትሕ የሚገኘው ከዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ወይም የተባባሩት መንግሥታት ለዚሁ ጉዳይ ብሎ ከሚያቋቁመው የጦርነት ወንጀል ፍርድ ቤት (Tribunal) ይመስላቸዋል። አዎ! የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዩጎዝላቪያን፣ የሩዋንዳን፣ የሴራሊዮኔንና የካምቦዲያን የጦርነት ወንጀል ፍርድ ቤት አቋቁሞ ሁላቸውንም ባይሆን ብዙ ወንጀለኞችን ለፍርድ አቅርቧል። የጸጥታው ምክር ቤት ዛሬም ከተስማማበት የኢትዮጵያን ጉዳይ ብቻ የሚዳኝ ተመሳሳይ የጦርነት ወንጀል ፍርድ ቤት ሊያቋቁም ይችላል። ሌላው ደግሞ ተስፋ የምንጥልበትና የፍትሕ ቋት አድርገን የምናየው የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ወንጀለኞቹን ለፍርድ ያቀርባል የሚለው ነው። ለታማሚ፣ ሁሉም መድኃኒት ይመስለዋል እንደሚሉት ዓይነት ነው። እስቲ እነዚህን “ሊሆኑ የሚችሉትን” (possibilities) በአጭሩ እንመልከታቸው፣
ሀ) የተመድ ልዩ የጦርነት የወንጀል ትሪቡናል የሚቋቋመው በጸጥታው ምክር ቤት ነው። ከዘጠናዎቹ በተለየ መልኩ አምስቱ የምክር ቤቱ ኃያል አገራት (veto powers) ደግሞ በሁለት ጎራ በተከፈሉበት በዛሬው ሁኔታ የአምስቱን አገራት ስምምነት አግኝቶ ልዩ ትሪቡናል ማቋቋም ተግባራዊ ሊሆን አይችልም። ሩሲያና ቻይና እስካሉ ድረስ በዛሬ ሁኔታ የኢትዮጵያን መንግሥት ጥቅም ሊነካ የሚችል አንዳችም ውሳኔ በጸጥታው ምክር ቤት ሊተላለፍ አይችልምና።
ለ) እንዳለፉት ዘመናት መንግሥታት የጦርነት ወንጀል በፈጸሙ ቁጥር (የዩጎዝላቪያ፣ የሩዋንድ፣ የሴራሊዮን እና የካምቦዲያ) መሰል ትሪቡናሎችን ማቋቋሙ ጠቃሚ መስሎ ስላልታየ፣ ሁሉንም ዓይነት የጦርነትና ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀሎችን መርምሮ እንዲፈርድ ተብሎ በአዲስ መልክ የተቋቋመው የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት (Iinternational Criminal Court – ICC) ሥልጣን ደግሞ የፍርድ ቤቱን ኮንቬንሽን በፈረሙትና ባጸደቁት አገራት ላይ ብቻ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ውሉን ፈረመ እንጂ ስላላጸደቀ፣ ፍርድ ቤቱ በኢትዮጵያ መንግሥት ባላሥልጣናት ወይም ተጓዳኝ ግለ ሰቦች ላይ አንዳችም ሕጋዊ ሥልጣን አይኖረውም።
ሐ) ሌላው ሁላችንም ለችግራችን ደራሽ አድርገን የምናየው ደግሞ “ጥርስ አልባውን” የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን (United Nations High Commissioner for Human Rights) ነው። ለምሳሌ፣ በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጸሙ የጦርነትና ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንዲመረምር የተቋቋመው የምክር ቤቱ ዓለም አቀፍ የኤክስፔርቶች ቡድን ባለፈው ሳምንት “በርቀት ምርመራ” የደረስኩበት ነው ብሎ ለኮሚሽኑ ባቀረበው ዘገባ እንዳመለከተው፣ ኤክስፔርቶቹ ከአዲስ አበባ ውጪ የትም እንዳይንቀሳቀሱ የኢትዮያ መንግሥት እንደ ከለከላቸውና፣ የጂቡቲና የሱዳን መንግስታትም ኤክስፔርቶቹ የትግራይ ስደተኞችን ኢንተርቪዉ ለማድረግ እንዳልፈቀዱላቸው በግልጽ አስቀምጠዋል። ስለዚህ፣ ያቀረቡት ዘገባ ለአንዳንድ የምዕራብ አገራት የፖሊቲካ ሸቀጥ መጠቅለያ ለማዋል ካልሆነ በስተቀር፣ በተፋላሚ ወገኖቹ ላይ የሚያደርሰው አንዳችም ጫና አይኖርም። ሆኖም ግን ኮሚሽኑ አንዳች ውሳኔ ላይ ቢደርስ እንኳ፣ የኢትዮጵያን መንግሥትና የትግራይ ክልላዊ መንግሥትን ማውገዝና መገዳደሉን አቁመው አለመግባባታቸውን በድርድር ጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ ከመጠየቅ አያልፍም። በርግጥ አገራት በተናጠል ወይም በቡድን ሆነው፣ ሰብዓዊ እርዳታን ያላካተተ ኤኮኖሚያዊ ማዕቀብ በኢትዮጵያ ላይ ሊጥሉ ይችላሉ። ይህ ደግሞ ጊዜያዊ ከመሆኑም በላይ ይህ ነው የሚባል ኤክስፖርት ለሌላት ደሃ አገር ጫናው ከባድ አይሆንም።
ወገኖቼ! አለመጀመር ነው እንጂ፣ አንዴ ከተጀመረ በጦርነት ውስጥ ሰብዓዊነት የለም። በመጀመርያ ደረጃ፣ የሰው ልጅ በሙያው ሠልጥኖም ይሁን ተገዶ ወደ ጦር ሜዳ የሚሄደው የሰውን ልጅ እንጂ እንስሳን ለመግደል አይደለም። ይህ ሁሉ የእናት/አባት አገርን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ፣ ተገንጣዮችን ለመደምሰስ፣ ጁንታውን ለማጥፋት፣ ፋሺስቱን ለመቅጣት ወዘተ የሚባሉ ሃረጎች ዝም ብሎ ደጋፊን ለማብዛት ነው እንጂ፣ የማንኛውም ጦርነት ዓላማ የሰውን ልጅ ገድሎ “ቀድሞ የታቀደን ዓላማ” ከግብ ለማድረስ ነው። የዓለም አቀፉ ማኅበረ ሰቡም ተስማምቶበት ያጸደቀው የጦርነት ሕግ (Humanitarian Law) መግደልን ሕጋዊ አድርጎ፣ የአገዳደሉን ሁኔታ ነው በዝርዝር ያስቀመጠው። ከዚህ ከሕጉ ውጭ ያለው ግድያና ጥፋት ነው እንግዲህ የጦርነት ወንጀል ተብሎ አድራጊዎችን በብሔራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ፍ/ቤት ተጠያቂ የሚያደርጋቸው። ሕጉን እስከ ተከተለ ድረስ ግን፣ የአንድ ተዋጊ (ወታደር) ጀብዱ የሚነገርለትና ሹመት የሚያገኘው በገደላቸው ሰዎች መጠንና፣ “ወገኖቹን ለማዳን” በሚያደርገው የመከላከል ብቃት ነው።
በቦታው ተገኝቶ አስፈላጊውን ሙያዊ ምርመራ አድርጎ የተጨበጠ መረጃ ያቀረበ አካል ባይኖርም፣ ከላይ ባስቀመጥኩት ምክንያት፣ በዚህ በተያያዝነው የርስ በርስ ጦርነት ሂደት ውስጥ መጠነ ሰፊ የሆኑ ወንጀሎች ተፈጽመዋል የሚል እምነት አለኝ። በተለይም በሁለቱ ወገኖች የተሰለፉት ጠብመንጃ አንጋቾች በከፍተኛ የወታደራዊ አካዳሚ ወይም ካዴት ማሠልጠኛ ገብተው የጦርነትን ደንቦች የመሳሰሉ መደበኛ ወታደራዊ ትምህርት በበቂ ያልተቀበሉና መሣርያ መፍታትና መገጣጠም እና አነጣጥሮ ከመተኮስ ያለፈ ብቁ የሆነ ሙያዊ ሥልጠና የሌላቸው ናቸው ብዬ ስለምገምት፣ በጦርነት ሕግ የተከለከሉትን የወንጀል ድርጊቶች አይፈጽሙም ብሎ መገመት ከባድ ነው። ወንጀል ደግሞ በማንኛውም ምድራዊ ሕግ የተኮነነ ነውና አድራጊዎቹ ያላንዳች ማመንታት ለብሔራዊ ፍርድ ቀርበው ተገቢውን ቅጣት ማግኘት አለባቸው። “ብሔራዊ ፍርድ ቤት” ያልኩት ሆን ብዬ ነው። ከላይ በዝርዝር ባስቀመጥኳቸው ምክንያቶች፣ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጸሙትንና እየተፈጸሙ ያሉትን የጦርነትና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ጥልቅና የማያዳላ ምርመራ አድርጎ ለፍርድ የማቅረብ ግዴታ ያለበት የኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ መሆኑን ለመጠቆም ነው። ተግባራዊ ሊሆን ይችላል ወይ የሚለው ተገቢ ጥያቄ እንዳለ ሆኖ!
ለመደምደም ያህል፣
በአገራችን እየተካሄደ ያለው የርስ በርስ ግጭት ነው። ግጭቱ ግን በመንግሥትና ከመንግሥቱ ጋር በማይስማሙ በተደራጁ የፖሊቲካ መዋቅሮች መካከል እንጂ፣ በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል አይደለም። አዎ ሕዝቡ በቡድኖቹ ግፊት ወደ ጦርነቶቹ ተገፍቶ ገብቷል። ከዚያ ባለፈ ግን በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል አንዳችም ቅራኔ አልነበረም፣ የለምም። የርስ በርስ ግጭት ነው ያልኩበትም ምክንያት፣ ዛሬ የፌዴራሉን መንግሥት ከሚወጉት ቡድኖች መካከል “ከኢትዮጵያ ተለይቼ የራሴን አገር አቋቁማለሁ” የሚል ቡድን ስለሌለ ነው። ቡድኖቹ እያነሱ ያሉት “በሕገ መንግሥቱ በተደነገገው መሠረት ራሳችንን በራሳችን እናስተዳድር” ነው። ይህ ደግሞ የዲሞክራሲ ጥያቄ ስለሆነ ጦር የሚያማዝዝ ጉዳይ መሆን አልነበረበትም። “ራስን በራስ ማስተዳደር” ደግሞ የሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ፣ ዛሬ በግልጽ ነፍጥ አንግተው መንግሥትን የሚወጉ አካላት ጥያቄ ብቻ አይደለም። ሳያድለን ቀርቶ ግን፣ አለመግባባቶችን በሠለጠነ መንገድ ተወያይቶ የመፍታት ባህል ስላልነበረንና እንዲኖረንም ጥረት ስለማናደርግ፣ ለጊዜው ያለን ብቸኛውና የለመድነው መፍትሔ “ጠላትን ማድቀቅና ማውደምን” ተያይዘነዋል። የሚያሳዝነው ግን፣ በዚህ “ጠላትን ለማውደም ወይም ለማድቀቅ” በሚደረገው የርስ በርስ ጦርነት ሂደት ውስጥ፣ ከማንኛውም ወገን የሚሞቱና የሚፈናቀሉት ኢትዮያዊያን ሲሆኑ፣ የሚወድመውም ንብረት የኢትዮጵያ ሕዝቦች አንጡራ ሃብት ነው። ለዚህም ነው የርስ በርስ ጦርነት ሽንፈት እንጂ፣ አሸናፊ የለውም የሚባለው!
ወገኖቼ! የምናጠፋውም የምንጠፋውም እኛው ነን። ይኸ “አንድ ወታደርና አንዲት ጥይት እስኪቀረን ድረስ እንዋጋለን” የሚለው ፊውዳላዊ አባባል ይቅርብን። ኢትዮጵያውያን ከጠፉ በኋላ ኢትዮጵያ አንድ ግለሰብ ብቻ ይዛ እንደ አገር ልትቀጥል አትችልም። ይህ ሃቅ ነው። ስለዚህ መገዳደሉን ትተን፣ በሠለጠነ መንገድ ተወያይተን ለመስማማት፣ ካልሆነም ደግሞ እስከነልዩነታችን በሰላም አብሮ ለመኖር እንሞክር። ከሁሉ በላይ ደግሞ ይህ በውጭ ኃይል ላይ መተማመኑን እርግፍ አድርገን እንተው። ለኛ ከኛ በላይ መድኃኒት አቀባይ ሊኖር አይችልም። አገር በቀልና ዘመን ዘለል የአለመግባባቶች መፍቻ መድኃኒቶች ደግሞ በያንዳንዱ ብሔር ዘንድ አለን። የውጪው ኃይላት ደግሞ እሳት አቀብለውን እኛ ስንቃጠል ከዳር ቆመው ይሞቁን እንደው እንጂ፣ አንዳችም ነገር ሊፈይዱን እንደማይችሉ ከምን ጊዜውም በላይ መረዳት አለብን። ለዚህ ትልቁን ሚና ሊጫወት የሚችለውና አስፈላጊውን ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችለው የተማረው ክፍል ስለሆነ፣ እባካችሁ እስቲ ሰከን ብለን፣ የርስ በርስ ጦርነቱ ቆሞ፣ ዜጎች እንዳይገደሉና እንዳይፈናቀሉ የሚረዳ ሃሳብ ላይ እንወያይ። በተለይም በውጪ አገር ሰላምና መረጋጋትን እያጣጣምን የምንኖር ምሁራንና አክቲቪስቶች ለዚህ ቅዱስ ሥራ ተቀዳሚውን ሚና እንጫወት። ልክ እንደምንኖርባቸው አገራት ምሁራንና ፖሊቲከኞች፣ እኛም አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት እንሞክር። በትምህርቱ ዓለም የተጎናጸፍነውን ልቀት ለጽንፈኝነት ሳይሆን፣ አገራዊ ችግራችንን በውይይት ለመቅረፍ እንጠቀምበት። ፈጣሪ ይተባበረን!
******
ጄኔቫ፣ መስከረም 27 ቀን 2022 ዓ/ም