ሃገራዊ ህብረታችን የሚፀናው አንዱ ስለራሱ ብቻ ሳይሆን ስለሌላውም ሲኖር ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ቡድኖች ሁሉ ወደ ውስጥ ብቻ እያዩና ግፎችን ሁሉ በብሄር ቁና እየሰፈሩ ለየራሳቸው ወየው ወየው ካሉ በህብረታችን ውስጥ መደማመጥ ይጠፋል፣ ህማምን መረዳት ይጠፋል፣ ቀስ እያለም ሃገራዊ ህብረታችን ያለ ልክ ይጎዳል።
ሁል ጊዜ ወደ ውስጥ በማየት ላይ ብቻ የተመሰረተ ፓለቲካ ስናደርግና ኦሮሞው ለኦሮሞው ብቻ፣ ትግሬው ለትግሬው ብቻ፣ አማራው ለአማራው ብቻ….. ተቆርቋሪ ሲሆን ኢትዮጵያን ህልውና እናሳጣታለን።
የማንነት (Identity politic) ትልቅ ችግር ሁሉም ወደ ማንነቱ ብቻ እንዲያይና ተቆርቋሪ እንዲሆን ማድረጉ ብቻ ሳይሆን ሌላውን ማንነት እየጎነተለ ነው ትግል ላይ ነኝ የሚለው። የብሄር ፓለቲካ ትግል የብሄርን ትግል ስለሚያሰፍን ሃገሪቱ በብሄር ትግል እረፍት የሚባል ነገር ሳይኖራት በልጆቿ መናቆር እንዲሁ ስትሰቃይ ትኖራለች። በእውኑ ይህቺ የጥቁሮች ሁሉ የነፃነት ፈርጥ ይህ ይገባታልን?
የሃገራችን ፓለቲካ የማንነት ፓለቲካን ምንነት በሚገባ አውቆ ወደ ሰለጠነ ፓለቲካ መሻገር አለበት። የማንነት ፓለቲካ የሚያራምዱ ሃይሎች መስሏቸው እንጂ ማንነት ላይ ተጥደን ፓለቲካ ስንጫወት በራሳችን ክበብ ውስጥም ማይክሮ ማንነቶች ጊዜ ጠብቀው የፓለቲካ ማልያ ለብሰው ለመጫወት ጊዜና ሁኔታ ነው የሚጠብቁት። አንድ የማከብረው አስተማሪዬ ማንነት ማለት እንደ ቀይ ሽንኩርት ነው ይለኝ ነበር። ቀይ ሽንኩርት አንዱን ሽፋን ስትልጠው ሌላ ሽፋን ከስር ይወጣል፣ ያንን ስትልጠው ሌላኛው ክፍል ብቅ ይላል፣ እንዲህ እያለ ሽንኩርቱ ያልቃል ይላል። እውነት ነው። ማንነትም እንደዚህ ነው። ለጊዜው ማክሮ የሆኑ ማንነቶችን ፈጥረን በዚያ ላይ ፓለቲካ ብንጫወት ብቻችንን ስንሆን ደግሞ እነዚያ ማይክሮ የሆኑ የቡድኑ ልዩነቶች ወደ ማክሮ ያድጉና የግጭት እሳት እዚያው ክበብ ውስጥ ይፈጠራሉ።
ሶማሊያውያን አንድ ብሄር ናቸው። ነገር ግን ዚያድባሬ ቤተ መንግስቱን የቤተ ዘመድ መሰባሰቢያ ማድረግ ሲጀምሩና ዘመዶቻቸውን በሃብት ማደለብ ሲጀምሩ የሶማሌ ህዝብ ማይክሮ ልዩነቶች ወደ ማክሮ አደጉና ሁሉም በቤተ ዘመድና በጎሳው ታጠቀ። ጨዋታው የቤተ ዘመድ ከሆነ ማን ከማን ያንሳል በሚል ሶማሌ አያት ምንጅላቱን እየቆጠረ ብዙ ክለቦች ፈጠረ። አይዛክ የተባለው ነገድ ጠንክሮ ወጣና ተዋግቶ ተገነጠለ። ሶማሌ ላንድን ነፃ ሃገር ብሎ መሰረተ። ያ የዚያድባሬ የቤተ ዘመድ አደረጃጀት ሶማሌ ላንድን ከመገንጠል በተጨማሪ ሶማሊያን መንግስት አልባ አድርጎ ረጅም ጊዜ አኖራት። የፉክክር ደጃፍ ሳይዘጋ ያድራል እንደተባለው የሶማሌ ህዝብ ያለ መንግስት ረጅም ጊዜ መከራ አየ። አሁንም ዳፋው አለቀቀውም።
እኛ ኢትዮጵያውያን ይህንን መረዳት ሊሳነን አይገባም። ከብሄር ማንነት ላይ የገነባነው ፓለቲካ ነገ ወደ ሰፈርና ቤተዘመድ ዘልቆ ሲያተራምሰን ይኖራል። ስለዚህ ከዚህ ፓለቲካ እንውጣ። ስለዚህ የኦሮሞው ተወላጅ አማራው ወገኔ ጉዳትህ ታየኝ ብሎ ህመም ይጋራ፣ አማራው ኦሮሞውን ወንድሜ ሆይ ህማምህ አመመኝ አይዞን በጋራ ችግራችንን እንወጣለን ይበል፣ ትግሬው አማራውን፣ አማራው ትግሬውን፣ ኮንሶው ኩስሜውን፣ ደራሼ ኮንሶውን፣ ያንተ ብሶት ብሶቴ ነው ወንድሜ ሆይ ና በጋራ ለሁላችን የምትሆነውን ሃገራችንን እናልማ፣ ሰላሟን እንጠብቅ ማለት ይጠበቃል። ይህ ነው ኢትዮጵያዊነት ማለት።
ባለፈው ጊዜ የጎንደር ህዝብ በየጎዳናው የሚፈሰው የኦሮሞ ወገኔ ደም ደሜ ነው የሚል መፈክር ሲያሰማ ኦሮሞው ይህንን ተቀብሎ የአማራው ደም ደሜ ነው ሲል አስተጋባ። ይህ መተሳሰብ የደም ሃረግን ፓለቲካ የገሰፀ ኢትዮጵያን ያሰበ ቅስቀሳ ነበር። ዛሬም ይህ ሊደገም ይገባል። ትግሬው የአማራው ደም ደሜ ነው ይበል። አማራው የትግሬው ደም ደሜ ነው ይበል። ኦሮሞው የሲዳማው ደም ደሜ ነው ይበል። ይህ ሲሆን ነው የእልቂት ፍላፃ የሚመክነው። ሃገር ደስ የሚላትና ትንሳኤ የምናየው። ስለዚህ ጋዜጠኛውና ፓለቲከኛው ሁሉ ከማንነት ፓለቲካና ከማንነት ጋዜጠኝነት ይላቀቅና አንዳችን ስለራሳችን ብቻ ሳይሆን ስለ ሌላውም እናስብ። ከፍ ሲል እንዳልኩት በማንነት ፓለቲካ ጊዜ ራስ (self) የምንለው ስብስብ ለብቻው ሲሆን ሌላ አካል እየተላጠ ይወጣዋል። ይህ ማይክሮ ልዩነት ወደ ማክሮ እያደገ የግጭት መንስኤ ይሆናል። ስለዚህ ሁላችን የማንነት ፓለቲካን ችግሮች ተረድተን ከዚህ ለመላቀቅ ውለን አንደር። የዚህች ሃገር አንድነት ጥንካሬ የሚለካው ከማንነት ፓለቲካ መንደር በራቅነው ልክ ነው።
እግዚአብሔር ኢትዬጵያን ይጠብቅ።