April 9, 2022
9 mins read

ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የተሠጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

AEUPበሠው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ጉዳት እየደረሰባቸው ላሉት ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን መንግስት አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል!!

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች ሠላምና ደህንነት መረጋገጥ ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆን እንዳለበት በፅኑ ያምናል፡፡

ወቅቱ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ በበርካታ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ተከባ ያለችበት ወቅት ነው፡፡ በተለይም በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተደረገው ጦርነት ለሀገራችን ብዙ ስጋት የደቀነ እና አሁንም የሁላችንም ልዩ ትኩረት የሚፈልግ እና ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑ ይታወቃል፡፡

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)  በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች ሠላምና ደህንነት መረጋገጥ ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆን እንዳለበት ያምናል፡፡ አሁን በስራ ላይ ያለው የኢፌድሪ ሕገመንግስት ዜጎች ከማንኛውም አይነት አደጋ እና የደህንነት ስጋት ተጠብቀው ሊኖሩ እንደሚገባ ይደነግጋል፡፡ እነዚህ ከፍተኛ ጉዳት በደረሰባቸው እና አደጋው ባንዣበበባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ በመሆኑ ዘላቂ እና የመፍትሔ ስራዎች እንዲሰራባቸው አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡

በአማራ ክልል ዋግህምራ ዞን

በአማራ ክልል ዋግህምራ ዞን በውስጡ ከያዛቸው በሰቆጣ ከተማ፣ በአበርገሌ፣ በደሀና፣ እና ሌሎች ወረዳዎች ላይ በጦርነቱ ሳቢያ ከፍተኛ የምግብ እና የመድኃኒት እጥረት አደጋ ስጋት ተጋርጧል፡፡  በአካባቢው በጦርነቱ ምክንያት የተስተዋለው የምግብና የመድኃኒት እጥረት በአካባቢው የሚኖሩ ዜጎች መቋቋም የማይችሉትን ጫና ለመቅረፍ መንግስት ለችግሩ የተሻለ ትኩረት በመስጠት አማራጭ፣ ዘላቂና ተከታታይ የሆነ የፖሊሲ አቅጣጫ ማስቀመጥ እንዳለበት እናሳስባለን፡፡

በአፋር ክልል ፈንቲረሱ ዞን አብአላ ከተማና አካባቢው

አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ከፍተኛ የሆነ ግድያና ዘረፋ ከፈፀመባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች በተጨማሪ የአፋር ክልል አንዱ ነው፡፡ ሽብርተኛው ቡድን በአፋር ክልል የፈንቲረሱ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው አብአላ እና በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎች ላይ በፈፀመው ወረራ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ በረሀብና በመድኃኒት እጥረት እየተሰቃየ ይገኛል፡፡ በመሆኑም የፌደራል መንግስቱ አስቸኳይ የሆነ መፍትሔ በማፈላለግ ለዜጎቹ እንዲደርስላቸው ስንል አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡

በአማራና ኦሮሚያ ክልል በሚገኙ አዋሳኝ አካባቢዎች

በአማራና ኦሮሚያ ክልል በሚገኙ አዋሳኝ አካባቢዎች በደራ፣ በሰሜን ሸዋ ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ራሱን ኦነግ ሸኔ በማለት የሚጠራውና ከዚህ ቀደም በምዕራብ እና ምስራቅ ወለጋ በተለያዩ አካባቢዎች ዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለው ቡድን ማንነትን መሠረት ያደረገ ከፍተኛ ጥቃትን ጨምሮ የዜጎችን ሰላም እና ደህንነት እያወከ እንደሆነ ለመረዳት ችለናል፡፡

ይሁን እንጂ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ይሄንን ችግር ተከትሎ ያወጣው መግለጫ እጅግ በጣም አደገኛ እና ኃላፊነት የጎደለው ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ገዥዎች በውስጣቸው ያለውን ልዩነት በመነጋገርና በመወያየት ለችግሩ መፍትሄ መስጠት ሲገባቸው የዜጎችን ሞትና መፈናቀል ማስቆም ሲቻል የመግለጫ ጋጋታ እያወጡ የሕዝብን አንድነት በመሸርሸር ለግጭት እና ብጥብጥ ማነሳሳት ሀገርን እና ህዝብን ይጎዳልና በአስቸኳይ ከዚህ ድርጊታቸው እንድትቆጠቡ ስንል እናሳስባለን፡፡

በደቡብ ክልል ሰገን አካባቢ ሕዝቦች ዞን አማሮና ደራሼ ልዩ ወረዳ

በአማሮና ደራሼ ልዩ ወረዳ ራሱን ኦነግ ሸኔ በማለት የሚጠራው ቡድን በኢትዮጵያ በስተደቡብ አቅጣጫ ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃትን ጨምሮ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት እያወከ እንደሆነ ተገንዝበናል፡፡

የዚህ ችግር ተጋላጭ ከሆኑት የደቡብ ክልል አካባቢዎች ውስጥ የአማሮና ደራሼ ልዩ ወረዳ ይገኙበታል፡፡ በአማሮ ወረዳ ውስጥ ደርባዬ፣ ዳልቄ እና በሌሎች ከ10 በሚበልጡ ቀበሌዎች በኦነግ ሸኔ በመወረራቸው በሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች ቤታቸውን እና ንብረታቸውን ጥለው ወደ አጎራባች ቀበሌዎች ተሰደዋል፡፡ እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ የደህንነት ስጋት ተጋርጦባቸዋል፡፡

በተጨማሪም በአጎራባች ወረዳዎች በኮንሶ ዞን በጉማይዴ ወረዳ፣ በደራሼ ወረዳ፣ ዲካያ፣ ሀይሎታ፣ ጋርጨ፣ ሉልቶ፣ መልሴ፣ ፋጩጫ፣ ባፎ ቀበሌዎች እና በሲዳማ ክልል ያሉ አንዳንድ ወረዳዎች፣ በጋሞ በቡርጂ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች በተመሳሳይ የደህንነት ስጋት  ውስጥ ይገኛሉ፡፡

 

ሌሎችን አካባቢዎችን ጨምሮ ንፁሀን ዜጎች ማንነታቸውን መሠረት በማድረግ ጥቃት እያደረሰ ያለውን የኦነግ ሸኔ ቡድን ላይ መንግስት ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ በአፋጣኝ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆን እንዳለበት እናምናለን፡፡

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) መንግስት በየአካባቢው ያሉ ችግሮች በአግባቡ በመቃኘት እና ልዩ ትኩረት የሚሹትን አካባቢዎች በአፋጣኝ ለይቶ ዜጎችን ወደ መደበኛ ህይወታቸው የሚመልስና እነዚህ አደጋዎች ተጨማሪ ስጋት እንዳይፈጥሩ እንዲሁም ለዘለቄታዊ የዜጎች ህይወት እንዲሻሻል የሚያደርጉ ፖሊሲ፣ የአሠራርና የአደረጃጀት ለውጦችን ተግባራዊ እንዲያደርግ እናሳስባለን፡፡

በተለያየ ምክንያት እየተነሱ ያሉ ግጭቶች ሕገ-መንግስታዊ ማሻሸያ ተደርጎ በአግባቡ እስኪፈቱ ህዝቡን የማረጋጋት ስራ እንዲሰራና በዘላቂነት እንዲመለስ እንዲሁም የተፈጥሮና የሰው ሠራሽ አደጋዎችን ከፌደራል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት እልባት እንዲሰጥ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡

“አንዲት ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!”
ሚያዚያ 01 ቀን 2014 ዓ.ም.
አዲስ አበባ

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop