March 20, 2022
62 mins read

ሃላፊነትና ተጠያቂነት – ጠገናው ጎሹ

accountability and Responsibility

March 19, 2022
ጠገናው ጎሹ

 ሃላፊነት (responsibility) እንደ ግለሰብ ወይም እንደ ቡድን ወይም እንደ ማህበረሰብ ወይም እንደ መንግሥት የሚጠበቅብንን ትክክለኛ ጉዳይ (ተግባር) ሁሉ ተፈፃሚ አድርገን የመገኘታችንን እና የማይጠበቅብንን እና ትክክል ያልሆነ ነገር ደግሞ አድርገን ያለመገኘታችንን አስፈላጊነት የሚገልፅ ፅንሰ ሃሳብ ነው።

 ተጠያቂነት (accountability) በሃላፊነት ተቀብለን የምንፈፅመው ወይም የምናከናውነው ጉዳይ (ሥራ) ስኬታማ ሲሆን ምሥጋና እና ማበረታቻ የሚቸረንን ያህል ሃላፊነትን በአግባቡ ለመወጣት ባለመቻላችን ለሚፈጠረው ጉድለት ወይም ውድቀት የሚቀርብብንን ትችት (ወቀሳ) ፣ የሥነ ምግባር ማስተካከያ እና ህጋዊ ወይም አስተዳደራዊ  እርምጃ   በፀጋና በቅንነት ከመቀበል  አልፎ የሚያስከፍለን ዋጋ የሚኖር ከሆነም ለመክፈል  ዝግጁዎች ሆነን የመገኘታችንን አስፈላጊነት የሚነግረን ፅንሰ ሃሳብ ነው።

እንኳንስ አገርን (ህዝብን) በሚመለከት እጅግ ታላቅ ጉዳይ የትኛውንም የጋራ ጉዳይ በሚመለከት የምንሰነዝረውን ወይም የምናቀርበውን ወይም የምንለዋወጠውን ሃሳብ (አስተሳሰብ) ከምር ከሆነ የሃላፊነትና የተጠያቂነት ስሜት እና የተግባር ውሎ ጋር ካልተቆራኘነው በስተቀር  ፈፅሞ ትርጉም የለውም  (አይኖረውም) ። ደጋግመን የመውደቃችንን ግዙፍና መሪር እውነት ደፍረን በመጋፈጥ የሚበጀንን አድርገን ለመገኘት ሲያቅተን ከሃላፊነትና ከተጠያቂነት ለመሸሽ ሰንካላ ሰበብ እየደረደርን  አያሌ ዓመታትን የማስቆጠራችን ክፉ አባዜ ያስከተለብንና እያስከተለብን ያለውን የመከራና የውርደት ዶፍ አሁንም  ይበልጥ እየተለማመድነው መጥተናል።

ከቅንነትና ከጥረት ጉድለት ሳይሆን ከቁጥጥር ውጭ የሆነ የተፈጥሮ ወይም ሰው ሠራሽ ሁኔታ ሊያጋጥም ይችላልና ሃላፊነት የተሰጠው አካል ሁሉ ሁል ጊዜና በየትኛውም ሁኔታ (necessarily all the time and in any situation) ተጠያቂ ነው (መሆን አለበት) ማለት አይደለም። ሃላፊነትና ተጠያቂነት በአግባቡ ሥራ ላይ በሚውሉበት ሁኔታ ውስጥ የሚከሰቱ ፈታኝ ሁኔታዎችን (ቀውሶችን) በፍጥነትና በስኬት ተቋቁሞ በፊት ወደ ነበረው ብቻ ሳይሆን ወደ ተሻለ ሁኔታ መራመድ ይቻላል።

የእኛ ጉዳይ ግን ከዚህ በእጅጉ የተለይ ነው በሚል ብቻ የሚገለፅ አይደለም።ለማመን በሚያስቸግር ሁኔታ አሳሳቢና አስከፊ ነው። ለገንዛ ውድቀታችን ሃላፊነትንና ተጠያቂነትን ለመቀበል የሞራልና የተግባር ብቃቱ ስለሚያጥረን  እኩይ ገዥ ቡድኖችና ግብረ በላዎቻቸው ካለማመዱን ዘመን ጠገብ ፣ አስከፊና ተደጋጋሚ  የውድቀት አዙሪት ሰብረን ለመውጣት በእጅጉ ተቸግረናል። ይህን ክፉ የውድቀት አባዜ ነገ ሳይሆን ዛሬ መረም ካልቻልን በስተቀር  እንኳን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊት እውን ለማድረግ ቀደምት ትውልዶች በዋጋ ሊተመን የማይችል ዋጋ የተከፈሉባትንና ከነችግሮቻችንም ቢሆን ለዘማናት አብረን የኖርንባትን አገር ህልውና ለመታደግ  በእጅጉ እንቸገራለን።

የሩብ መቶ ክፍለ ዘመኑን የመከራና የውርደት አገዛዝ ሥርዓት ያስቀጠሉት ተረኞች  ፈጣሪወያቻቸውንና የሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ጌቶቻቸውን (ህወሃቶችን) ከቤተ መንግሥት አስወግደው የበላይነቱን ከያዙበት እ.ኢ.አ ከሚያዝያ 2010 ወዲህ  የፈፀሙትና እየፈፀሙት ያሉት ለመግለፅ የሚያስቸግር ፖለቲካ ወለድ ወንጀል  ኢትዮጵያን ለተጨማሪ የድህነትና የሰቆቃ ምድር ምሳሌ አድርጓት ቀጥሏል ።

አዎ! ከአያሌ ዓመታት የመከራና የውርደት አገዛዝ ግዙፍና መሪር ተሞክሮ ከምር ተምሮ የተሻለ ዛሬን ለመፍጠር እና የላቀ ነገን እውን ለማድረግ ያለመቻል ውድቀት የሚመነጨው ከሃላፊነትና ከተጠያቂነት ፖለቲካ ውድቀት ነው። ነፃነትና ፍትህ እፈልጋለሁ እንደሚል ትውልድ የራሱን ሃላፊነትና ተጠያቂነት በአግባቡ ሳይወጣ ሃላፊነትና ተጠያቂነት ጨርሶ የማይሰማቸው እኩያን ገዥዎችን ሃላፊነትና ተጠያቂነት ተሰምቷቸው የመከራና የውርደት ዶፉን (ቀንበሩን) ከላዩ ላይ ያነሱለት ዘንድ የሚማፀን ወይም ተስፋ የሚያደርግ ወይም “እባክህ ልቦና ስጥልኝ” እያለ ፈጣሪውን በከንቱ የሚማፀን ትውልድ ስለ ዴሞክራሲና ዴሞክራሲያዊነት አጥብቆ ማነብነቡ (በከንቱ መፈላሰፉ/የትንታኔ ድሪቶ መደረቱ) ፈፅሞ ስሜት አይሰጥም።

ትናንት ተባበርኩ ብሎ ዛሬ እየፈራረሰ፣ ዛሬ ተደጋገፍኩ ብሎ ነገ ተጠላልፎ እየወደቀ፣ ከዓመታት መሪር ተሞክሮ ከምር ባለመማር ክፉ አዙሪት ውስጥ እየጓጎጠ፣ አስከፊ የአድርባይነት ደዌን እየተለማመደ፣ ልክ የሌለው ራስን ወዳድነትንና ፍርሃትን እንደ መልካም ዝና እና ትዕሥት እየቆጠረ (እየተረጎመ)፣ ለመግለፅ የሚያስቸግር የግፍ አሟሟትንና የቁም ሰቆቃን  (የቁም ሞትን) እየተጋተ ፣  በአስከፊ አገዛዝ ምክንያት የሚደርስበትን እጅግ አስከፊ ርሃብና ጥማት ወይም ፍፁም ድህነት  እንደ የመንግሥተ  ሰማያት መውረሻ እየቆጠረ፣  ውሸትንና ክህደትን ከመፀየፍና ከመዋጋት ይልቅ  ከርሱን ለመሙላት እስካስቻሉት ድረስ እንደ መልካም ባህል  እየተለማመደ፣ ወዘተ  ስለ ዴሞክራሲያዊትና ስለ ምትበለፅግ አገር አጥብቆ የሚደሰኩር  ወይም የሚፈላሰፍ ወይም የትንታኔ ድሪቶ የሚደርት ትውልድ ከሚገኝበት ክፉ አዙሪት እንዴትና መቼ ሰብሮ እንደሚወጣ ለመተንበይ ያስቸግራል።

አዎ!  ለዚህ ነው ይህ ትውልድ ቁማርተኛ ገዥ ቡድኖች እና ግብረ በላዎቻቸው ካዘጋጁለትና ከሚያዘጋጁለት  እኩይ አጀንዳ እና የሰቆቃ ወጥመድ ሰለባነት ጨርሶ ማምለጥ ያልተሳካለት። ለዚህ እውነትነት ደግሞ ከእኛው ከገንዛ ራሳችን ዘመን ጠገብ (አያሌ ዓመታት) እጅግ አስከፊ ሁለንተናዊ የውድቀት አዙሪት በላይ መረጃም ይሁን ማስረጃ ፍለጋ ርቀን መሄድ አያስፈልገንም።

አዎ! እርግጥ ነው የእኩያን ገዥ ቡድኖች ሃላፊነትና ተጠያቂነት አልባነት ፈፅሞ ማነፃፀሪያ አይገኝለትም ።እነዚህ ሸፍጠኛና ጨካኝ ተረኞች ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን በፍፁም ታማኝነት ባገለገሉበት እኩይ ሥርዓታቸው የፈፀሙት አስከፊ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል አልበቃቸው ብሎ በዚህ በአራት ዓመታት የተረኝነት አገዛዛቸው የፈፀሙትና እየፈፀሙ ያሉት አሰቃቂ ወንጀል “የፍፁም ድህነትና ተመፅዋችነት ተምሳሌት ከመሆን ለመላቀቅ ያቃታቸው  ኢትዮጵያዊያን ምነው ይህን ይህን ያህል እርስ በርሳቸው አጨካከናቸው ?” የሚል እጅግ ፈታኝ የሆነ የምንነትና የማንነት ጥያቄ ደቅኖብናል። እኛም ፈተናውን ተጋፍጠን ከተዘፈቅንበት አስፈሪ አዙሪት ሰብሮ ለመውጣት አስፈላጊውን ሁሉ ከማድረግ ይልቅ የምንመርጠው ጥያቄውን መሸሽ ወይም ሰንካላ ሰበብ መደርደር ሆኖ ቀጥሏል። የእነዚህ እኩያን ገዥ ቡድኖች ሰለባ ነኝ ወይም ነን የሚል ትውልድ እንደ ትውልድ መሠረታዊ ዓላማውንና ግቡን ጨርሶ በማይዘናጋ  ፣ በቅጡ በተደራጀ፣በአግባቡ በታቀደ  ፣ በተቀነባበረ  እና ዘላቂነት ባለው  የጋራ ትግል ነፃነቱን ለማስከበርና እጣ ፈንታውን ለመወሰን  ባለመቻሉ ለደረሰበትና እየደረሰበት ላለው ሰቆቃና ውርደት ተጠያቂነትቱና ሃላፊነቱ  የገንዛ ራሱም ነው።  ዘመን ጠገቡ የመከራና የውርደት  አገዛዝ ማቆሚያ እንዳይገኝለት  ማድረግ ብቻ ሳይሆን እንዲያውም በአስከፊ ሁኔታ እንዲቀጥል ካደረጉት (ካስቻሉት)  ዋነኛ ምክንያቶች አንዱም ይኸው ከምር በሆነ የሃላፊነትና የተጠያቂነት ቁመና እና አቋም  ላይ ለመገኘት ያለመቻል ስንኩልነት ነው።

እንኳንስ ትልቁን አገራዊ ተልእኮ (ሥራየትኛውንም ተልእኮ (ሥራበሃላፊነት  ተቀብሎ ለማከናወን ግልፅና ቀጥተኛ የሆነ ዓላማና ግብ፣ ግልፅና የማያሻማ የአስተሳሰብ ምንነትና እንዴትነት  የሞራል ልእልና  የሥነ ምግባር ጥራትና ብቃት  ፅእኑ የሆነ መርህ  ዓላማንና ግብን እውን ከማድረግ ሂደት ጋር እየተፈተሸ ሥራ ላይ የሚውል ስትራቴጅ  ግልፅና የማያሻማ ፕሮግራምና ፖሊሲ  ግልፅና ውጤት ተኮር የሆነ  እቅድና የአፈፃፀም ስልት እና እነዚህንና ሌሎች አስፈላጊ ግብአቶችን ወደ ተግባር የሚተረጉም ድርጅታዊ ሃይል መኖርን የግድ ይላል ። እነዚህን መሠረታዊ ጉዳዮች ከምር ተቀብለን ለመፈፀምና ለማስፈፀም ሲያቅተን የሃላፊነትንና የተጠያቂነትን ምንነትና እንዴትነት ስተናልና ቆም ብለንና አደብ ገዝተን ራሳችንን መመርመር ይኖርብናል። ያለዚያ ሃላፊነትና ተጠያቂነት ጨርሶ ፖለቲካዊ ተፈጥሯቸውና ተሞክሯቸው ያልሆነ እኩያን ገዥ ቡድኖችና ግብረ በላዎቻቸው መሳቂያና መሳለቂያ ቢያደርጉን ጨርሶ ሊገርመን አይገባም።  አዎ! ሃላፊነትና ተጠያቂነት የጎደለው ወይም የሌለው ህዝባዊም ሆነ ድርጅታዊ ንቅንናቄ ወይም እንቅስቃሴ ክስተቶችና ስሜታዊነት የሚያጠቃቸው በመሆኑ ጨርሶ ወንዝ አያሻግሩም። የእኩያን ገዥ ቡድኖችና የግብረ በላዎቻቸው የግፍና የውርደት አገዛዝ ፍፃሜ ከማግኘት ይልቅ እጅግ አስከፊና አስፈሪ ሆኖ የቀጠለውም ለዚህ ነው። ከገንዛ ራሳችን ውድቀት ለመሸሽ የሰበብ ድሪቶ እየደረትን ለመቀጠል ካልፈለግን በስተቀር ለዘመናት የዘለቀውና አሁንም በአስከፊ ሁኔታ የቀጠለው ግዙፉና መሪሩ የፖለቲካችን እውነት ይኸው ነው።

የስያሜና የአድረጃጀት ቅርፅ ለውጥ በማድረግ ብቻ የመከራና የውርደቱን ሥርዓተ ፖለቲካ ፈፅሞ ሃላፊነትና ተጠያቂነት በሌለበት እና ይበልጥ አስከፊ በሆነ ሁኔታ  እንዲቀጥል ያደረጉትን   ተረኛ ኦህዴዳዊያንን/ኢህአዴጋዊያንን/ብልፅግናዊያንን እውነተኛ ለውጥን እውን ሊያስደርግ በሚችል የሃላፊነትና የተጠያቂነት ስሜት እና ተጋድሎ  ከመታገል ይልቅ ”  በሃላፊነትና  በተጠያቂነት አምላክ አትግደሉን ፣ አታስገድሉን፣ አታገዳድሉን፣ አታሳዱን ፣ አታሰድዱን ፣ በርሃብና እርዛት አለንጋ አታስገርፉን ፣ ወዘተ “   እያሉ ከመማፀን የባሰ ትውልዳዊ ውድቀት የለም።

የአድርባይነት ልክፍተኞችን  ስግብግብና ሞራለ ቢስ ባለ ሃብት ተብየዎችን  ራሳቸውን ብቻ ሳይሆን አገርንም ያዋረዱ ተፎካካሪ ተብየ  ፖለቲከኞችን  ሃይማኖታዊ እምነትን ለወንጀኛ የፖለቲካ ሥርዓት መሣሪያነት አሳልፈው የሰጡ እርጉማን ወገኖችን ፣ የሽምግልናን እሴት በአፍ ጢሙ የደፉ ሽማግሌ ተብየዎችን  የመማርን እውነተኛ ትርጉምና እሴት በአስከፊ ሁኔታ ያጎሳቁሉ የምሁራን ደናቁርትን  በጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ በሰከሩ (ባበዱ) ቁማርተኞች አኩይ ( መርዘኛ) ፕሮፓጋንዳ  ናላቸው (አእምሯቸው) የጦዘ ልጆቹ የገንዛ ንፁሃን ወገኖቻቸውን በአሰቃቂ ሁኔታ እየገደሉ በአስከሬናቸው ሲሳለቁ  ከምር ለመገሰፅ  ወይም ለመቆጣት ወኔው ሲከዳው ከሃላፊነት ለመሸሽ ሰንካላ ምክንያት የሚደረድር   ወላጅ ተብየን  ከእኔ ወዲያ የነፃነትና የፍትህ አክቲቪስትነት ላሳር ነው ሲለን ኖሮ ስትለን ኖራ  በአስከፊ ሁኔታ የቀጠለው የሰቆቃና የውርደት ፖለቲካ ሥርዓት  አገልጋይ (አሽቃባጭ)  የሆነን/የሆነችን አክቲቪስት ተብየን  ከእኔ ወዲያ ለህዝብ የኖረና አገልጋይ ላሳር ነው በሚል ያዙኝና ልቀቁኝ ሲል ቆይቶ /ስትል ቆይታ ለዘመናት የዘለቀውና አሁንም በንፁሃን ሰቆቃና ደም የጨቀየው የተረኞች አገዛዝ ባለሟል የሆነውን/የሆነችውን ወራዳ የኪነ ጥበብ ሰው ተብየን ፣ ወዘተ  በግልፅ ፣በቀጥታና በአግባቡ ለመተቸት እና በቃችሁ ለማለት ሃላፊነት የሚገደው ትውልድ ዴሞክራሲንና ዴሞክሲያዊነትን መመኘቱ ቅዠት እንጅ እውነት ሊሆን አይችልም።

አዎ! ይህ ትውልድ “ለውጥ መጣ” በሚል ዳንኪራ ረግጦ ሳያበቃ ይኸውና ከሦስት ዓመታት በላይ   እናት ምድሩ ለንፁሃን ልጆቿ (ዜጎቿ) ምድረ ሲኦል ሆና እንድትቀጥል እያደረጓት  ያሉትን እኩያን  ተረኛ ገዥ ቡድኖች  ትርጉም ባለው የጋራ ትግል ስሜትና ተግባራዊ  ንቅናቄ  በቃችሁ ለማለትና ለማስቆም አሁንም አልተሳካለትም። ለዚህ እጅግ አስክፊ የውድቀት አዙሪት ዋነኛ ምክንያቶች ከሆኑት አንዱ የሥርዓት ለውጥን ከምር በሆነ የሃላፊነትና የተጠያቂነት ስሜት እና የተግባር ውሎ  እውን  ከማድረግ ይልቅ እራሱን በጎሳና  በጎጥ የፖለቲካ ማንነት ከረጢት ውስጥ ወሽቆ አቅሉን (አእምሮውን) በሚያስት የስሜታዊነት መንፈስ የመክነፉ ልክፍት መሆኑን ለመረዳትና ለማስረዳት የተለየ እውቀት ጨርሶ አይጠይቅም።

ስለ እውነት በእውነት መነጋገር ካለብን ይህ ትውልድ የሃላፊነትና የተጠያቂነት ተፈጥሮውም ሆነ ተሞክሮው ፈፅሞ የሌላቸውን እኩያን ገዥ ቡድኖች ከተቻለ አደብ ገዝተው ወደ ትክክለኛው ሰብአዊነት እንዲመለሱ ካልሆነ ግን ገለል እንዲሉ ለማስገደድ አልተሳካልንም። እነዚህን ሃላፊነትና ተጠያቂነት ፈፅሞ የሌላቸው የአገር ደመኞች (ነቅርሳዎች) በማስወገድ  ነፃነትን፣ ፍትህን፣ እኩልነትን፣ ሰላምንና የጋራ እድገትን እውን ከማድረግ ይልቅ የመከራና የውርደት ዜናን እየተለማመደ የመሄዱ መሪር እውነታ በእጅግ አስፈሪ ነው።

በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን የገዥዎች ሴራና ግፍ እንደተጠበቀ ሆኖ የኢትዮጵያ ፈተና የመሠረታዊ እውቀት ድህነት የቅንነት እጦት፣ መንግሥት የሚባለው አካል እንደ መብት ሰጭና ነሽ ሃይል አድርጎ የማመን ፣ የመብትን ምንነት እና እስከ ምንነት በቅጡ ያለማወቅ ፣ የዴሞክራሲያዊ አርበኝነትና የጀግንነት እሴቶች መጎሳቆል  የመልካምና የጠንካራ ፖለቲካ እሴቶችን በቃል (በዲስኩር) እንጅ መሬት ላይ ፈልጎ ለማግኘት ያለመቻል   ከክስተቶች  የትኩሳት መጠን ጋር የመሞቅና የመቀዝቀዝ አባዜ ፣ ከተደራጀና ዘላቂነት ካለው ተግባራዊ ትግል ይልቅ የአደባባይና ሌሎች  አጋጣሚዎችን እየጠበቁ ስሜት “ማስተንፈስን”  እንደ ስኬት በመቁጠር ራስን የመሸንገል  የእሥር  ወይም የአፈና ምክንያት የሆነውን ሥርዓተ ፖለቲካ ከሥሩ ነቅሎ ለመጣል ከመታገል ይልቅ በየተራ እየታሰሩና እየታፈኑ “ፍቱልንና ልቀቁልን” የሚል ሰሚ አልባ ጩኸት የመጮህ  የሰማያዊ ተልእኮውን በምድር ላይ ካለው መሪር እውነታ  ጋር አጣምሮ ማስኬድ የሚችል የሃይማኖት መሪነትና አስተማሪነት ድርቀት (እጦት)  የህዝብን የለውጥ ፍላጎት ወደ መሬት አውርዶ እውን የሚያደርግ የፖለቲካ ምህዳር (አውድ)  አለመኖር   እና ክፉዎች በመርዘኛ የፖለቲካ አስተሳሰባቸው ያሳበዱትንና የገንዛ እናቶቹን ማህፀን በስለት (በቢላዋ) ዘንጥሎ የሚፎክረውን አሳዛኝ ወጣት ትውልድ ተው ብሎ የሚቆጣ ወላጅና ሽማግሌ  ፈልጎ ለማግኘት ያለመቻል ፈተና ነው።

ይህንን ግዙፍና መሪር ሃቅ ተቀብለን ተገቢውን ማድረግ ሳንችል እግዚኦ ማለታችንን የሚሰማ እውነተኛ አምላክ የሚኖር አይመስለኝም። የማይሰማው ጨካኝ ሆኖ ሳይሆን ከሌሎች ፍጡራን ሁሉ በተለየ ማንነትና ምንነት የፈጠረበትን ምክንያትና ዓላማ በተገቢው ሁኔታ ስኬታማ ለማድረግ ባለመፈለጋችን ወይም ባለመቻላችን መሆኑን ለመረዳት የቲዎሎጅም ሆነ የዓለማዊ እውቀት ልሂቅ መሆንን የሚጠይቅ አይመስለኝም።

ከረቂቅ የማሰቢያ አእምሮ እና ከብቁ አካል ጋር የፈጠረን ክፉውን በመፀየፍና  እና በጎውን ግን በመሻትና በማድረግ ሂደት ውስጥ አምላካዊ እገዛውን ስንጠይቀው ፈጥኖ የሚደርስልን መሆኑን ቃል  በመግባት እንጅ ሃላፊነታችንን ባለመወጣታችን በሚደርስብን መከራና ውርደት ምክንያት ለምናሰማው እግዚኦታ ሃላፊነቱን በመውሰድ አይመስለኝም።  እንዲህ አይነት አምላክ  አለ የምንል ከሆነም በራሳችን ጭንቅላት ውስጥ የምንፈጥረው እንጅ እውነተኛ አምላክ አይሆንም።  ከሃላፊነትና ከተጠያቂነት ጋር የፈጠረው ሰብአዊ ፍጡር ሃላፊነቱንና ተጠያቂነቱን የተለያየ ሰንካላ ሰበብ በመደርደር እየሸሸ ” ምነው ተውከኝ” የሚል የፀሎትና የንስሃ ጩኸት ቢጮህ እና ጩኸቱ ባይሰማ የሚገርም አይመስለኝም። የምፅአት ምልክት የሚሆንም አይመስለኝም ። ኢትዮጵያዊያን በመሆናችን ብቻ ሳይሆን በክርስቶስ አምሳል የተፈጠርን ሰብአዊ ፍጡሮች በመሆናችን በዚህች ምድር (ዓለም) ላይ በነፃነት፣ በፍትህ፣ በሰላም፣ በመልካም ህይወት (አኗኗር) ፣ ወዘተ እንኖር ዘንድ የተሰጠንን ታላቅ ሥጦታ ከምር በሆነ የሃላፊነትና የተጠያቂነት ስሜትና ተግባር እውን ለማድረግ እያቃተን ከአስከፊና ተደጋጋሚ የውድቀት አዙሪት ጋር የመለማመዳችን ክፉ ልማድ ልንፀየፈውና በቃን ልንለው ይገባል። ለዚህ ደግሞ ከምር የሆነ ሃላፊነትንና ተጠያቂነትን ለመሸከም ፈቃደኛና ዝግጁ መሆንን ይጠይቃል ።

ለዓመታት ሲዋሽ (ሲቀጥፍ)  አያሌ ንፁሃን ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት በገንዛ አገራቸውና ቀያቸው የአሰቃቂ ግድያና የቁም ሰቆቃ ሰለባዎች  ሲሆኑ በብዙሃን መገናኛ መስኮት ብቅ ብሎ ሃዘኑን ሳይገልፅ ሲቀር  አገር ለልጆቿ (ለዜጎቼ) ምድረ ሲኦል በሆነችበት መሪር ሁኔታ ውስጥ ስለ ጠፉት የመንገድ ዳር የተክል አበባዎች እንቅልፍ ማጣቱን ሲነግረን፣ በሸፍጠኛና ጨካኝ አገዛዙ ምክንያት  ለብዙ ዓመታት ወደ ኋላ በመንሸራተት ላይ የምትገኘውን አገረ ኢትዮጵያ ከ30 ዓመታት በኋላ ከሁለት ሃያልን አንዷ ትሆናለች ብሎ ሲሳለቅብን ፣  ቤተ እምነትና አማኞች እርሱ  በሚመራው ገዥ ፓርቲና መንግሥት በሚታገዙ ሃይሎች ተቃጠሉና ወደሙ ሲባል “… ወደ ፊትም ሊወድሙና ሊቃጠሉ ይችላሉ”  ብሎ ሲያላግጥ ፣  ከእርሱና ከግብረ አበሮቹ በስተቀር ብዙሃኑ ህዝብ የእለት ህይወቱን ማሸነፍ ባልቻለበትና በብዙ ሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች ከገንዛ ቀያቸው ተፈናቅለው የርሃብና የበሽታ ሰለባ በሆኑባት ሁኔታ ውስጥ ሽንኩርትና ቅቤ ከበዛበት ምግብ ይልቅ ይህንን ቅጠል በጨው ውሃ ነክራችሁ ተመገቡ ብሎ ሲሳለቅ  ፈጣሪን በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበሰበሰና የከረፋ ሥርዓቱ ተባባሪ በማድረግ እርሱ ፍታና እሰር ስላለኝ ነው” ብሎ ሲያላግጥ ፣ እና ከሰሞኑ ደግሞ በስልክ በሚያዝዛት ብርቱካን ሚዴቅሳ አፅዳቂነት በህገ ወጥ መንገድ መመረጡ አልበቃ ብሎ  በጉባኤ ተብየው መድረክ ላይ ተመራጭና አስመራጭ በመሆን “ከአብይ የተሻለ የለም ወይም አለ የምትሉ እጃችሁን አውጡ” በማለት በዴሞክራሲ እና በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ሲሳለቅ ሃላፊነትና ተጠያቂነት ፈፅሞ የማይሰማው ሰው ጠቅላይ ሚኒስትር በሆነበት የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ሃላፊነትና ተጠያቂነት የተሞላበት ቁጣን ወይም በቃን ባይነትን ለማየት አለመቻላችን በእጅጉ አሳፋሪና አስፈሪ ነው።

ከዘመን ጠገቡና እጅግ አስከፊው የፖለቲካ አስተሳሰብና የሞራል ዝቅጠት ሰብረን  ለመውጣት ያለመቻላችን አንደኛውና ዋነኛው ምክንያት ሃላፊነትንና ተጠያቂነትን የምንረዳበትና ተግባራዊ የምናደርግበት ሁኔታ በእጅጉ የተንሸዋረረ  መሆኑ ነው። በእውነተኛ የጋራ (አገራዊ ወይም ህዝባዊ) ዓላማና ግብ ላይ የተመሠረተ እና ይህንኑ መልካም ሥራ እውን ሊያደርግ በሚያስችል የሃላፊነትና የተጠያቂነት ስሜት የማይመራ የነፃነትና የፍትህ ፍለጋ ጨርሶ ስሜት አይሰጥም።

የአገራችን የፓርቲ ፖለቲካ ታሪክ ከፅንሰ ሃሳብነት አልፎ ራሱን በድርጊት መግለፅ ከጀመረበት ከ1950ዎቹ መጨረሻና ከ1960ዎቹ መግቢያ ጀምሮ የመጣንበት የግማሽ ምእተ ዓመት እጅግ አስከፊ ደጋግሞ የወመውደቅ አዙሪት በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመንም ትምህርት ሊሆነን አልቻለም።

ከዘመናት ሁለንተናዊ ቀውስ ተምረን ከዛሬ ሦስት ዓመታት በፊት የተፈጠረውን ወርቃማ  የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ አጋጣሚ ከምር በሆነ የሃላፊነት፣ የተጠያቂነትና የባለቤትነት ስሜት  ለታለመለት ግብ ከማብቃት ይልቅ በተረኝነት መንበረ ሥልጣን ላይ ለወጡ ሸፍጠኛና ሴረኛ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች አሳልፈን በመስጠታችን ምክንያት  እየሆነ ወይም እየተፈፀመ ያለው ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ጤናማ ህሊና ያለው ሰው ከሚገምተው በላይ ነው ።

ይህ እጅግ ተደጋጋሚና አስከፊ ውድቀታችን ያስከተለብን ሁለንተናዊ ቀውስ ራሳችንን የመከራ አዙሪት ሰለባዎች ከማድረጉም በላይ የዓለም ከንፈር መምጠጫ ፣ መሳቂያና መሳለቂያ አድርጎናል። ይህ ትውልድ በሃላፊነትና በተጠያቂነት ስሜት እና በመርህና በዓላማ ፅዕናት ላይ የተመሠረተ ትግል በማካሄድ የባለጌዎችንና የጨካኞችን ሥርዓት ለማስወገድ ከምር እስካልታገለ ድረስ የመከራና የሰቆቃ ዜና አስነጋሪና ተቀባይ ወይንም አልቃሽና አስለቃሽ ሆኖ ይቀጥላል ።

አዎ! ንፁሃን ወገኖቹ በሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖች ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ምክንያት የገንዛ አገራቸው ምድረ ሲኦል ስትሆንባቸው ሌላው ቢቀር በአደባባይ ወይም በመንገድ ላይ ወጥቶና እጅ ለእጅ ተያይዞ “የመከራውና የሰቆቃው ዘመን በቃኝ !” የሚል የጋራ ድምፁን ለማስተጋባት የተቸገረ (ወኔው የከዳው) ትውልድ ስለ ነፃነትና ፍትህ የሚተነትነውና የሚያስተነትነው ትንታኔ ፈፅሞ ስሜት አይሰጥም።

እራሳችንን ከምር በሆነና ዘላቂነት ባለው የሃላፊነትና የተጠያቂነት ስሜት አነሳስተን፣ አንቅተን፣ ተደራጅተንና አደራጅተን፣ የምቀኝነቱንና የክፋቱን ጅኒ (እኩይ ባህሪ) ተቆጣጥረን፣ ለይምሰልና በይምሰል የመኖሩን (መኖር ከተባለ) ክፉ አባዜ በቅጡ አድርገን፣ ከክስተቶች ትኩሳት ጋር ከመሞቅና ከመቀዝቀዝ ይልቅ ከምናልመው መልካም ግብ በሚያደርሰን ፅዕኑ መርህና ፕሮግራም ላይ አተኩረን ፣እና ለዚህም የሚሆን አቅድና ስልት ነድፈን ፣ ወዘተ በመታገል ለዚህ ዘመን የሚመጥን የፖለቲካ ሥርዓት እውን ከማድረግ ይልቅ ሃላፊነትና ተጠያቂነት ተፈጥሯቸውና ተሞክሯቸው ያልሆነውን ባለጌና ጨካኝ ገዥዎችን ከመጎናበስ (ከመማፀን) የከፋ የትውልድ ውድቀት የለም።

ሃላፊነትንና ተጠያቂነትን በተላበሰ ሁኔታ የገንዛ አገራችንን አገረ ዴሞክራሲ ፣ አገረ ሰላምና አገረ እድገት ለማድረግ የሚያስችል የሞራልና የተግባር ልእልና ባለቤቶች እንደሆንና ሆነንም እንደምንዘልቅ ለማሳየት ሳንችል ወይም የምር ጥረት ሳናደርግ በዓለም የፖለቲካ ጨዋታ ሂደት ውስጥ በብሔራዊ ጥቅም ስም ጣልቃ ገብነት አዲስ ክስተት ይመስል የውጭ መንግሥታትን “እጃችሁን አንሱልን” እያልን መፎከር እና መማፀን ይበልጥ ከንፈር መምጠጫ፣ መሳቂያና መሳለቂያ ያደርገን እንደሆነ እንጅ ከበሬታንና መፈራትን ጨርሶ አያተርፍልንም።

የገንዛ አገራችን በመፈራረስ አደጋ ላይ እንድትሆን ያደረጓትን ባለጌ፣ ሴረኛ፣ ፈሪና ጨካኝ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኛ ገዥ ቡድኖችንና ግብረ በላዎቻቸውን በአልገዛም ባይነት ትግል አደብ ማስገዛት ወይም ማስወገድ ሲያቅተን የውጭ መንግሥታትን ማውገዝና መራገም ምን የሚሉት አገር ወዳድነት እንደሆነ በእውን ለመረዳት ያስቸግራል።  ለሩብ ምእተ ዓመት በህወሃት አሽከርነት በህዝብ ላይ የመከራና የውርደት ዶፍ ሲያወርዱ የነበሩ እና  ከ2010 (እኢአ) ወዲህ ደግሞ  እጃቻቸው በአያሌ ንፁሃን ዜጎች ደምና የቁም ሰቆቃ ይበልጥ የተዘፈቁ ተረኛ ገዥ ቡድኖች ሃላፊነትንና ተጠያቂነትን ከምር ወስደው ትውልድን (አገርን) ከመከራና ከውርደት ይታደጋሉ ብሎ ከመጠበቅ የከፋ ትውልዳዊ የሃላፊነትና የተጠያቂነት ዝቅጠት የለም።

የግልና የቡድን ፍላጎት (ጥቅም) እጅግ ሥር በሰደደበትና ዋነኛ ገዥ ሃይል ሆኖ በቀጠለበት እና ይህንኑ በሚመጥን የሃላፊነትና የተጠያቂነት ስሜትና ተግባር የሚታገልና የሚያታግል የፖለቲካም ሆነ የሲቪክ ሃይል በሌለበት አገር ውስጥ ዴሞክራሲያዊት አገርን እውን ማድረግ ይቻላል በሚል ተስፋ ማድረግ ቅዠት ካልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?  በዚህ አኳኋናችን እንኳን ዴሞክራሲያዊት አገር ገዥዎቻችን ካለማመዱን የመከራ የውርደት ቀንበር ጋር የሚኖርባት አገር ባትኖረን ለምን ይገርመናል?

ለዘመናት የመጣንበትንና አሁንም የተረኛ ቁማርተኞች (ኦህዴዳዊያን/ኦነጋዊያን) የበላይነት በሰፈነበት  የብአዴናዊያን (የአማራ ብልፅግናዊያን) አሽከርነት ወይም ወራዳነት ይበልጥ አስከፊ በሆነ መልኩ በቀጠለበት  ራሳቸውን ተፎካካሪ ብለው የሚጠሩ የፖለቲካ ፓርቲ መሪ ተብየዎች ተለጣፊነት ወይም የፖለቲካ አመንዝራነት በተንሰራፋበት በመርህና በዓላማ ላይ ፀንቶ መቆም አቅቷቸው ከክስተቶች የትኩሳት መጠን ጋር ልጓም በሌለው ስሜት እየነጎዱ የባለጌና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች መሣሪያዎች የሆኑ ክቲቪስት ተብየዎች ያዙንና ልቀቁን በሚሉበት  በኪነ ጥበቡ አንቱ እንደሚሰኙ ይተርኩልን የነበሩ ወገኖች በፖለቲካ አመንዝራነት ተጠልፈው በወደቁበት  የመከረኛው የኢትዮጵያ ህዝብ አይንና ጆሮእንደሆኑ ሲነግሩን  የነበሩ ጋዜጠኛና ተንታኝ ተብየዎች  እራሳቸውን ይበልጥ ሴረኛና ጨካኝ  ኢህአዴጋዊያን (ብልፅግናዊያን) ፍርፋሪ አሳልፈው በሸጡበት  ተስፋ ለምናደርገው የሰማያዊው ዓለም በምድር ላይ ከምናደርገው የፍትህ/የነፃነት/የሰብአዊ መብት/የእድገት/የሥልጣኔ ተጋድሎ  የተነጠለና በአየር ላይ የሚንሳፈፍ አንዳች አይነት ምትህት ይመስል ሁሉን ነገር “በፖለቲካ አያገባንም” አይነት የአስተሳሰብ ስንኩልነት ውስጥ የሚርመጠመጠው  የሃይማኖት መሪና ሰባኪ ቁጥር ቀላል ባልሆነበት ፣  ወዘተ ግዙፍና መሪር እውነታ ውስጥ  የእውነተኛ ለውጥ ሃላፊነትንና ተጠያቂነትን ፈልጎ ማግኘት ይቸግራል።

በየጎሳውና በየጎጡ እየነጣጠሉ በማናቆር በመግደል በማስገደልና በማገዳደል የፖለቲካ ቁማርተኝነት የተለከፉ እኩያን ገዥ ቡድኖችን  ድል ነስቶ የሚበጀውን የጋራ የሆነ ሥርዓት እውን ለማድረግ የራሱን ድርሻ በሃላፊነትና በተጠያቂነት ስሜት ለመወጣት የሚችለውን የጋራ ጥረት ለማድረግ የተሳነው ትውልድ የነገ ባለተስፋ ሊሆን ከቶ አይቻለውም። ይቻለኛል ካለም ቅዠት እንጅ እውነት አይሆንም። ያለ ዴሞክራሲያዊ አርበኝነት ተጋድሎ እውን የሚሆን ተስፋና ምኞት ወይም የነፃነትና የፍትህ ሥርዓት ፈፅሞ የለም ። ወደፊትም አይኖርም ።

ክርስቶስም “የራሳችሁን ጥረት ስታደርጉ (በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባርም ስተገኙ) ያኔ እኔም ጥረታችሁን እባርከዋለሁ” ብሎ ማስተማሩን እንጅ “በተግባር አልባ እግዚኦታችሁ ፈተናን ድል ትነሳላችሁ” ብሎ አለማስተማሩን ለመረዳት የቲዎሎጅ ሊቅነትን አይጠይቅም።  ዴሞክራሲ ማለት የብዙሃኑ መልካም ፈቃድና ምርጫ የሚተገበርበት፣ የንዑሳኑ መብት በእኩልነት የሚከበርበት፣ የሰብአዊ መብት የማይሸራረፍበት፣ ፍትህና ነፃነት የሚሰፍንበት፣ ሁሉም ተሰማምቶ ለሚያወጣው ህግና ደንብ ተገዥ የሚሆንበት፣ ሰላምና መተሳሰብ የሚኖርበት፣ የጋራ ብልፅግና (እድገት) ያለማቋረጥ የሚታይበት፣ ፣ ወዘተ ማለት ነውና  የሰማያዊው ህይወት ምንነትና እንዴትነት (ሚስጥር) እንደ ተጠበቀ ሆኖ ክርስቶስም ወደ ዚህች ምድር መጥቶ ከዚህ የተለየ ወይም የሚፃረር ትምህርት አለማስተማሩን ለመረዳት የቲዎሎጅ ወይም የገሃዱ ዓለም ፈላስፋነትን አይጠይቅም ።

በእውነት ስለእውነት ከተነጋገርን የሃይማኖት መሪዎች ፣ ምሁራን፣ ሰባኪዎችና አስተማሪዎች ከፈጣሪ የተሰጣቸውን ተልእኮ እና ከህዝብ የሚጠበቅባቸውን አደራ በሚመጥን የሃላፊነትና የተጠያቂነት መንፈስ እየተወጡ አይደለም ብሎ መተቸትን እንደ ክብረ ነክና ሃጢአት እንዲቆጥር የተደረገ ማህበረሰብ የጨካኞችን ግፍ መቀበልን ከሞት በኋላ ተስፋ ለሚያደርገው ህይወት እንደ ስንቅ ቆጥሮ ቢቀበለው ከቶ የሚገርም አይደለም።

ለዚህም ነው  የብልፅግና ወንጌል “ነቢያት” ለንፁሃን ዜጎቿ (ልጆቿ) ምድረ ሲኦል ያደረጋትንና እያደረጋትን ያለውን የወንጀለኞች ሥርዓት መሪ የሆነውን ጠቅላይ  ሚኒስትር “እግዚአብሔር  ቤተ መንግሥት ገብቶ ከአንተ ጋር  መንበርህ ላይ ተሰይሟልና ማንም ምንም ቢልና ምንም ቢሆን አትፍራ” የሚል እጅግ ጭካኔና ድፍረት የተሞላበት ትንቢት ሳይሆን ቅዠት ሲቃዡ የምንታዘበው። ፈጣሪን የአስከፊ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ተባባሪ  ሲያደርጉት “ነውር ነው” ለማለት ቢያንስ የሞራል አቅም የሚሳነው ትውልድ ዴሞክራሲን መሻቱ ባዶ ተስፋ (ቅዠት) እንጅ እውነተኛ ራዕይ አይደለም።

የሃላፊነትንና  የተጠያቂነትን ትርጉምና  እሴት አውቆ የማሳወቅን ብቻ ሳይሆን አድርጎ የማሳትን  ታላቅ  ተልእኮ  መወጣት የነበረበት ተምሬያለሁና ተመራምሬያለሁ የሚለው  የህብረተሰብ ክፍል የመሆኑ ጉዳይ የሚያወዛግበን አይመስለኝም።

ምሁርና ልሂቅ የምንለው የህብረተሰብ ክፍል እንኳንስ እንደ እኛ አይነት እጅግ አብዛኛው ህዝብ በጎሳ/ቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች የከፋፍለህ ፣ የገድለህ፣ የአጋድለህ እና የአደንቁረህ ግዛው አገዛዝ ሰለባ በሆነበት አገር በአንፃራዊነት ሰልጥኖልና ዴሞክራሲን ተለማምዷል በሚባል ህብረተሰብ ውስጥም ፖለቲካና ፖለቲከኞች ሊያሳድሩ በሚችሏቸው አወንታዊና አሉታዊ  ተፅዕኖዎች ላይ ያለው ወይም የሚኖረው ሚና በእጅጉ የጎላ ከመሆን አልፎ አንዳንዴም ወሳኝነት ያለው ነው።

ቁጥሩ ቀላል ያልሆነው የእኛ የምሁራን (የልሂቃን) የህብረተሰብ ክፍል ሚና (አስተዋፅኦ) ግን ከእውነተኛው የምሁርነት ትርጉምና እሴት አንፃር ከምር ሲገመገም የሚያኮራ ሳይሆን በእጅጉ የሚያሳፍር ነው። ይህ ደግሞ ሃላፊነትና ተጠያቂነት ባለው የምሁርነት (የልሂቅነት) እሴትና መርህ ላይ ፀንቶ ለመቆም ያለመቻል ወይም ያለመፈለግ ውድቀት ውጤት ነው። ከግማሽ ምዕተ ዓመት የመከራና የውርደት ፖለቲካ ተሞክሮ ተምሮ የተሻለ ትውልድን ለማፍራት እና በነፃነት የሚያስተናግድ ሥርዓት እውን እንዲሆን ለማድረግ ያለመቻሉ ውድቀት አልበቃ በሎ በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በምድረ ኢትዮጵያ እንኳን ይደረጋል ብሎ ለመገመት ለማሰብም የሚያስቸግሩ ፖለቲካ ወለድ ወንጀሎች ሲፈፀሙ እዚህ ግባ የሚባል የቤት ሥራ ሠርቶ ለመገኘት አልቻለም።  ይባስም ብሎ በአምሳሉ ጠፍጥፎ የፈጠራቸውንና ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን በፍፁም አሽከርነት ሲጋልባቸው የኖረውን አለቃቸውን (ህወሃትን) ከቤተ መንግሥት ፖለቲካ አስወግደው ሥርዓቱን ግን ከምንነቱና ማንነቱ  ጋር ያስቀጠሉትን ተረኛ ኦህዴዳዊያንን “የለውጥ ሐዋርያት”  ብሎ በመጥራት ከመከራው ብዛትና አስከፊነት የተነሳ የሚሰማው በጎ ቃል ሁሉ እውነት እየመሰለው የሚታለለውን ህዝብ ይበልጥ እንዲታለል  አደረገው።

ይህ ትውልድ እንደ ትውልድ የገጠመውን፣ እየገጠመው ያለውንና ወደፊትም ሊገጥመው የሚችለውን ውድቀት (ቀውስ) ከእራስ ሃላፊነትና ተጠያቂነት እያሸሸ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መናፈቁ የለየለት ቅዠት መሆኑን ተረድቶ የተሻለ ሥራ ለመሥራት እጅግ አስቸኳይና ከባድ ሥራ ፊቱ ላይ ተደቅኗልና ምርጫው የራሱ ነው። ወይ የሚበጀውን አድርጎ የነገ እጣ ፋንታውን የተቃና ማድረግ ወይም ለዓመታት በመጣበትና አሁንም በተረኞች እንዲቀጥል በተደረገው ሥርዓተ ኢህአዴግ ሥር የቁም ሙት እየሆነ መቀጠል። ሌላ አማራጭ ጨርሶ የለም።

ሴረኛ፣ ባለጌ፣ ፈሪ እና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች ከቻሉ ልብ ገዝተው ወደ ትክክለኛው የዴሞክራሲያዊ ለውጥ ሂደት እንዲመለሱ ፣ ካልሆነ ግን በነቃና በተደራጀ ህዝባዊ እምቢተኝነት እንዲወገዱ የማድረግን ሃላፊነትና ተጠያቂነት ተረድቶና ተቀብሎ መከረኛውን ህዝብ ከመከራና ከውርደት አዙሪት እንዲወጣ የሚያግዝ የምሁር (የልሂቅ) ሃይል እንዲፈጠርና እንዲጎለበት ማድረግ የግድ ነው። ይህን ችላ እያሉ ወይም  ከዚህ መሪርና ፈታኝ  አውነታ  እየሸሹ የመከራና የውርደት ትንታኔ መደረት ፈጽሞ ስሜት አይሰጥም።

ለብዙ ዓመታት ከመጣንበትና አሁንም በአስከፊ ሁኔታ ተዘፍቀን ከቀጠልንበት የሰቆቃና የውርደት ፖለቲካ ሥርዓት ሰብረን ለመውጣት ካልቻልንባቸው ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ ይኸው እጅግ ደካማ (extremely poor) የሆነው የፖለቲካ አስተሳሰብ ልማድ ነው።  በእውነት ስለ እውነት መነጋገር ካለብን የአገራዊ ቀውስ አዙሪት ያበቃ ዘንድ ተምሮ የመገኘትን ትርጉምና እሴት በሚመጥን አኳኋን ለመተርጎም ያለመፈለግን ወይም ያለመቻልን ክፉ ደዌ ሃላፊነትና ተጠያቂነት ባለው ሁኔታና ቁመና መጋፈጥ የግድ ነው።

በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን በአገራችን ለትልቅ ዓላማና ግብ ተፈፃሚነት ሲባል በተዋቀሩ ሦስቱ የመንግሥት አወቃቀር አካላት ማለትም በህግ አውጭው (the legislative) ፣ ህግ አስፈፃሚው (the executive) እና ህግ ተርጓሚው (the judiciary) መካከል ትርጉም ያለው የሥልጣን ክፍፍልና እና ሚዛናዊነት የለም። ይህ አሠራር በሰፈነበትና ሥር በሰደደበት ግዙፍና መሪር የፖለቲካ እውነታ ውስጥ እውነተኛ ሃላፊነትንና ተጠያቂነትን መጠበቅ በእራሱ ከእውነተኛ ሃላፊነትና ተጠያቂነት መሸሽ ነው ወይም የለየለት ተሸናፊነት ነው።  ሦስቱም አካላት  ወረቀት ላይ የሰፈሩ አገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የህግ አንቀፆችን የሚመዟቸውና የሚጠቀሙባቸው ገደብ የለሽ ሥልጣናቸውንና እርሱው የሚያስገኝላቸውን ጥቅም ሥጋት ላይ ይጥልብናል የሚሉትን ሁሉ ለማጥቃት ሲያስቡ ነው።  ለዚህ ነው የፍትህና የነፃነት ጥያቄ  በተነሳ ቁጥር  እየቃዡ በህዝብ (በአገር) ላይ የመከራና የውርደት ሰይፋቸውን የሚመዙት።

ለዚህ ነው ይህ ትውልድ እውነተኛ ነፃነትንና ፍትህን ከምር የሚፈልግ ከሆነ ይህን የግፈኞች ሥርዓት አስወግዶ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን እንዲሆን የማድረጉ ሃላፊነትና ተጠያቂነት የእርሱው የራሱ እንጅ የግፈኛ ገዥ ቡድኖች እና ግብረ በላዎቻቸው አለመሆኑን አውቆ የአልገዛም ባይነቱን ትግል መቀጠል ይኖርበታል ብሎ መከራከር ትክክል የሚሆነው።

 

 

ጠገናው ጎሹ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

Go toTop