እኛ የሰው ልጆች ብዙ የማያወዛግቡ ጉዳዮች ያወዛግቡናል። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የስፖርት እና የባሕል ሚኒስትር ባለሥልጣን የአድዋ በዓል እንደተለመደው የሚኒልክ ሀውልት በቆመበት ማዕከል እንደማይከበር ማስታውቁን ተከትሎ ሃሳቡን ከሚቃወመው አቅጣጫ ጫጫታው በዝቷል። የጫጫታው ይዘት የድል በዓሉ በተለመደው ማዕከ አለመከበር የበዓሉን ታሪካዊ ምንነት ያሳንሰዋል የሚል ነው። እኔም ስሜቱን እጋራዋለሁ። ስለሆነም ለመላው ዓለም በተለይም ለኢትዮጵያዊያን የበዓሉን ምንነት ለማስገንዘብ የምትከተለውን አጭር ጽሑፍ እጋራለሁ።
ኢትዮጵያ በጣት የሚቆጠሩ የኢምፔሪያሊዝም ወኪል አገሮች ፖርቹጋላዊው ክርስቶፎር ኮሎምበስ ሰሜን አሜሪካንን በ1492 ማግኘቱን ተከትሎ በ1494 በቶርዴሲላስ (Tordesillas) ስምምነት (treaty) ፖርቹጋል እና ስፔን የታወቀውን ዓለም (ከሕንድ እስከ ቬንዙኤላ) በመካከላቸው ከተቀራመቱ በኋላ በተለይ በ17ኛው ክፍለ ዘመን ጀምረው እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ እና የአሁኗ ኔዘርላንድ (formerly the Dutch) ዘግየት ብለው ደግሞ ኢታሊያ እና ቤልጂየም ወረራውን በመቀላቀል የእራሳቸውን የምጣኔ ሀብት (ኢኮኖሚ) ጥቅም ለማዳበር በሀገር በቀል (indigenous) ሕዝብ ላይ በፈጸሙት ወንጀል የዓለምን ታሪክ ተፈጥሯዊ ፈለግ (trajectory) እንዳይመለስ አድርጎ የቀየረ ጦራቸውን በሌሎች የደረሰው በእኔ አይደገምም ብላ የኢጣሊያንን ጦር አድዋ ላይ አንድ ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ድባቅ መታ ያሳፈረች ብቸኛዋ አገር ነች። የኢትዮጵያ ጦር ኢየምፔሪያሊዝምን ቅስም የሰበረበትን የአድዋ በዓል የምናከብረው አሸነፍን ብለን ጉራ ለመንዛት ወይም ለመመጻደቅ ሳይሆን የኢትዮጵያን ሕዝብ የሌሎች አገሮች ሀገር በቀል (indigenous) ሕዝቦች ከደረሰባቸው ሰብዐዊ ያልሆነ ውድመት ማዳን በመቻሉ ነው። የሌሎች አገሮች ሀገር በቀል ሕዝቦች በኢምፔሪያሊዝም የደረሰባቸውን ሰብዐዊ ያልሆነ ወድመት በትንሹ ለማስገንዘብ የሚከተሉትን ሦስት ዕውነቶች ያስታውሱ።
- እስከ 18ኛው ክፍለዘመን አጋማሽ ድረስ የወራሪ (ኢምፔሪያሊዝም) ወኪሎች በየሄዱበት የባሕር ዳርቻ (coastal lines) ላይ እየሰፈሩ የዓለምን የንግድ ዝውውር ከመቆጣጠር በዋናነት ቀረጥ ማስከፈል በሚያገኙት ጥቅም ተወስነው ሀገር በቀል ሕዝቦችን ሳይረብሹ ቆይተዋል።
- በ18ኛው ክፍለዘመን የእንፋሎት (steam) ቴክኖሎጂ በእንግሊዝ አገር ተገኝቶ በመላው አውሮፓ መሠራጨቱ ያስከተለው የመጀመሪያው የኢንዱስትሪ ለውጥ (1stindustrial revolution) የማምረት እና ምርትን ከቦታቦታ የማዘዋወር ችሎታን በማሻሻሉ የታላላቅ እርሻ (commercial agriculture) እና ማዕድንን እየፈለጉ እና እየቆፈሩ የማውጣት የኢኮኖሚ ዘርፎችን የዓለምን ንግድ በመቆጣጠር ከሚገኘው የቀረጥ ጥቅም የበለጠ ጠቃሚ ስላደረጋቸው ወራሪወች ከባሕር ዳርቻ ወደ መሀል አገር እየገቡ ሀገር በቀሉን ሕዝብ እየገደሉ እና እያፈናቀሉ መሬቱን በመንጠቅ የእርሻ እና የማዕድን ሥራቸውን አስፋፉ።
- በ19ኛው ክፍለዘመን ሁለተኛው አጋማሽ እና በ20ኛው ክፍለዘመን የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ የተከሰተውን የሁለተኛው የኢንዱስትሪ ለውጥ (2ndindustrial revolution) ያመጡት የብረታብረት፣ የኤሌክትሪክ እና ፔትሮሊየም ግኝት እስከዚያ ድረስ የነበሩትን የምጣኔ ሀብት (ኢኮኖሚ) እንቅስቃሴወችን የማምረት እና የማዘዋወር ዐይነታቸውን ጨምሮ በመቀየራቸው በወራሪወች አገር ብዙ ሕይወቶች ተናጉ። ለምሳሌ ብዙ ዜጎች ይሠሩበት በነበረው ሥራ ሊቀጥሉ አልቻሉም። በተመሳሳይ ጊዜ አዲሱ የኢንዱስትሪ ለውጥ በርከት ያሉ የመጣኔ ሀብት ዕድሎችን ከፍቷል። ለወራሪወችም ከታላላቅ እርሻ እና ማዕድን ቁፈራ የበለጠ ጥቅም አበረከተላቸው። ይህንን ዕድል ለመጠቀም ወራሪወች ዜጎቻቸውን በብዛት ወደቅኝ ግዛታቸው እያመጡ ማስፈር እና በምጣኔ ሀብት ዘርፍ ምርቱንም የአገር ውስጥ እና የዓለም አቀፍ ንግዱንም ተቆጣጠሩ። አፍሪካ የተወረረችው የ1885ቱን የአፍሪካ ቅርጫ (scramble for Africa) ስብሰባ (conference) ተከትሎ ነበር። ያመጧቸውን ዜጎቻቸውን ለማስፈር ከቀድሞ ወረራ ግፍ የተረፉትን ሀገር በቀል ሕዝቦች ገዱሏቸው የተረፉትንም ውስን ጥቅም ወደአላቸው ክልል ሥፍራወች (reservations) አሠፈሯቸው የቀሩትን ለእነሱ አገልጋይ ወደሆነ ዝቅተኛ ሕይወት እንዲኖሩ አደረጓቸው። እያንዳንዱን ቅኝ ግዛት ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠራቸው ቋንቋን እና ባሕልን መቀየር ጀመሩ። የአድዋ ድል ኢትዮጵያዊያንን ከዚህ ዓይነት ውድቀት ነው ያዳነው። መከበርም ያለበት ከዚሁ አንፃር ነው።
ወራሪወች በተለይ በ20ኛው ክፍለዘመን በገጠማቸው ፀረ ወረራ (anti-imperialism) ትግል ቅስማቸው እየተሰበረ የቀጥታ ቁጥጥራቸውን ቢያጡም በእጅ አዙር የሞግዚት (protectorate) እና የአሻንጉሊት (poppy) መንግሥት እያቋቋሙ መቆጣጠራቸውን ቀጥለዋል። ዓላማቸውም የንግድ እና የመዋዕለ ንዋይ (investment) ዕድሎችን መቆጣጠር ሲሆን እነዚህን ዓላማወች ለመቆጣጠር ክንዳቸውን ለማፈርጠም እንዲረዳቸው የተጽዕኖ ቀጠና (sphere of influence) ብለው የቀድሞ ቅኝ ግዛቶችን እና ሌሎችንም እያዋከቡ ይገኛሉ። ከ18ኛው የመጨረሻ ሩብ ክፍለዘመን ድረስ ያልተወለደችው አሜሪካ በአሁኑ ወቅት በዲሞክራሲ እና ሰብዐዊ መብት ሽፋን ዓለምን እያመሰች ያለችው ለዚሁ ምክን ያትነው። በኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር የምታደርገው ጥረት እና ዛሬ በዩክሬን እና በራሽያ መካከል ለሚደረገው ጦርነት ቀስቃሽነቷን መጥቀስ ይቻላል።
የአድዋ በዓል በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝ እና የወራሪ ኃይሎችን ቅስም ሰብሮ በኢምፔሪያሊዝም ለተገደሉ እና አካላዊ፣ ሥነልቦናዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ድቀት ለደረሰባቸው ሁሉ የነፃነት ጎህ የቀደደ በመሆኑ ጠቃሚነቱ ዘላለማዊ ነው። ስለሆነም የዛሬ መሪወች ባለራዕይ (visionary) መሆን እና የአድዋ በዓል የጎብኝወች መስህቦ (tourist attraction) እንዲሆን የመስህቦ ማዕከሎችን ማስፋፋት እና አከባበሩን የሚያጎሉ ገጽታወች አጠናክሮ በአገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስተዋወቅና ጎብኝወችን ማበረታታ ብልህነት ነው። ለምሳሌ የእቴጌ ጣይቱን ምስል የሚኒሊክ ሀውልት አካለ ማድረግ እና በአድዋ ጦርነት ታላቅ ሚና ለተጫወቱ አንጋፋ የጦር አበጋዞች በየትውልድ አካባቢያቸው ከታሪካቸው ጋር የተመጣጠነ ሀውልት ማቆም ለወደፊቱ ታላቅ የገቢ ምንጭ ነው።
የካቲት 22 2014 ዓ. ም. / March 1, 2022
ብርሀኑ አንተነህ