አርብ፣ ጥር ፲ ፰ ቀን፣ ፳ ፻ ፲ ፬ ዓ. ም. (2/25/2022)
አንዱ ዓለም ተፈራ፤
ተፈጥሮ ለሰው ልጅ ካደለቻቸው አንዱ ነገር፤ ከትናንት ልምድ አካብቶ፤ ዛሬ የተሻለ የአኗኗር ዘዴ እንዲተልም ነው። ይህ ልምድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተካበተ፣ ፈጠራዎች በሂደት እያጎለበቱት፣ የሰውን ልጅ ሥልጣኔ ወደፊት ይገፉታል። የስብስብ ኑሮ ቀላል አይደለም። ብዙ የተወሳሰቡ ጉዳዮች ያካብዱታል። በተለምዶ፤ ሰዎች ተሰባስበው ሲኖሩ፤ የጋራ የሆነ ልምዳቸውን፤ ለኑሯቸው ማሳመሪያና ማስተካከያ ይጠቀሙበታል። ይህ ግን፤ ሁልጊዜ ቋሚ የሆነና ምንጊዜም እውነታን የተላበሰ አይደለም። የሰው ተፈጥሮ በሁለት አንጻራዊ ተቃራኒ ባህሪያት ተበክሎ ይሁን ወይንም ይህ የተወሳሰበ የተፈጥሮና የልምድ የኑሮ ክንውን በአዕምሯችን አንጾት፤ የስብስብ ኑሮው አንድ ወጥ አይደለም። ግለኝነት ይሄንን ያበላሸዋል። በሰዎች መካከል ባለው ግንኙነት፤ ዋናው አበላሽ ግለኝነት ነው። “ከሌሎቹ የበለጠ እኔ ማግኘት አለብኝ!” “ከሌሎቹ በተሻለ ሁኔታ እኔ መጠቀም አለብኝ!” የሚለውን የእብሪተኞችና ጉልበተኞች እምነት፤ ዛሬ በዩክሬን ላይ የታየው የፑተን ጦርነት፤ በገሃድ እያሳየው ነው። ይህ ነው የዚህ ጽሑፍ ትኩረት።
በዩናይትድ ስቴትስ ኦቭ አሜሪካ፤ በካሊፎርንያ ግዛት፣ ሲሊኮን ሸለቆ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ፤ ሳኒቬል ከተማ በሚገኘው የኩፐርቲኖ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ የወላጆች ማኅበር ሊቀመንበር ሆኜ ለአንድ ዓመት አገልግያለሁ። ይህ ትምህርት ቤት፤ በአካባቢው ካሉት ጥሩ ትምህርት ቤቶች ውስጥ፤ እጅግ በጣም ጥሩ ከሚባሉት የተሰለፈ ነው። በከተማዋና በዙሪያዋ፤ ጉግል፤ ያሁ፤ ፌስቡክ፣ አፕልና ሌሎች ትንንሽ ኩባንያዎች ማዕከላዊ መሥሪያ ቤቶቻቸውን አድርገዋል። ባገለገልኩበት ዓመት ውስጥ ትኩረት ከወሰዱት ጉዳዮች አንዱ፤ የአብሪተኛ/ጥጋበኛ (bullies) ተማሪዎች ድርጊት ነበር። ይህ ጉዳይ በጣም በትንሹ ከሚታዩባቸው አካባቢዎች ካሉት ከተማዎች በጣም ሰላማዊ የምትባለው ሳኒቬል አንዷ ናት። በዚህ ድርጊት የሚካተቱት ተማሪዎች፤ የጠቅላላ ተማሪውን ቁጥር ሰማንያ ከመቶ የሆነውን ነጮች ስለሚወስዱት፤ ከሞላ ጎደል ሁሉም ነጮች ናቸው። “እኛ ያልነው ካልሆነ!” የሚል የ“ልዩ ነን!” ስሜት ባለቤቶች ናቸው። በስፖርቱ ቦታም ሆነ በመመገቢያ አዳራሹ፤ ተቧድነው አንዳንድ ምስኪን ተማሪዎችን በጥቃቅን ጉዳዮች አሳበው ማጥቃት ይወዳሉ። በዛ ያለ ስብስብ ሲኖር አይጠጉም። ጡንቻውን ያሳበጠ ካለ ይሸሻሉ። የውሸት ክስ ሊያጠቁ በሚፈልጉት ተማሪ ላይ ይደርባሉ። አንዳንድ ነጭ አስተማሪዎች፤ ለነሱ ጉዳይ ድጋፍ ይሠጣሉ። ርዕሰ መምህሩ ኮስተር ያለ ስለነበር፤ “ጉዳዩ በወላጆች ማኅበር ይታይ!” በማለት ወደኛ ይገፋዋል። የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ አባላት፤ ይሄ የወጣትነት ጉዳይ ስለሆነ በጊዜ ይለወጣሉና እንለፈው፤ የሚል ነው ደጋግመው የወስኑት። በርግጥ አባላቱም ነጮች ናቸው። “በኔ ልምድ፤ ‘እንቁላል ቀስ በቀስ በግሯ ትሄዳለች! ይቺ ባቄላ ካደረች . . . !’” አያልኩ እርምጃ እንድንወስድ ብጎተጉትም፤ ይሄ የእብሪተኞች ድርጊት፤ ዛሬም ኩፐርቲኖ መለስተኛ ብቻ ሳይሆን፤ ከመኖሪያዬ አጠገብ በሚገኘው ተከታዩ የሆምስቴድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም አለ። ይሄን ያተትኩት፤ ይሄ የእብሪተኞች ባህሪ፤ “ከእድገትና ሰው ከመሆን ጋር የተያያዘ ይሆን፣ ይሆን!” የሚል ጉንተላ ለመጫር ነው።
ባለፈው የሃያኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ፤ “እኔ ነኝ ኃይለኛ!’ “የለም! እኔ ነኛ ኃይለኛ!” “እኔ ያልኩት መሆን አለበት!” “የለም! እኔ ያልኩት መሆን አለበት!” በማለት ሁለት አስከፊ ጦርነቶች አውሮፓን አምሰዋት ነበር። ቀጥሎ ደግሞ ሁለት ሰፈሮች ተፈጥረው፤ ምስራቅና ምዕራብ፣ ኮሚኒስትና ካፒታሊስት፣ ቅኝ ገዥዎችና ቅኝ ግዛትን ተቃዋሚዎች፣ በሚል የጥቅም ክልልን ለማበጀትና ለመጠበቅ፤ ”ቀዝቃዛው ጦርነት” ቀጠለ። የኒህ ሁለት የጥቅም ማስፋፊያ ሰፈሮች ግብግብ፤ ለብዙ አገራት ከቅኝ ገዥዎች ነፃ መውጣት ምክንያት ሆኗል። አንዱ ሰፈር አልጠቀመኝም ሲል ወደ ሌላው ሰፈር እየዘመተ፤ መንጋ የሶስተኛው ዓለም አምባገነን ሁሉ እድሜውን አራዝሟል። የሶቪየት ኅብረት መንኮታኮት ለአሜሪካ ሜዳውን ነፃ አደረገላት። አሜሪካም “የዓለም ፖሊስ እኔ ነኝ!” ብላ ተንፏለለችበት። ከቪየትናም ቀንዷን እንደተመታች ላም እየተንገደገደች ወጥታ፤ ባካባቢዋ ባሉ አገሮች፤ ማለትም ቺሊ፣ ፓናማ፤ ቦሊቪያ፣ ቬንዝዌላና ባርባዶስ፤ በጉልበት ጣልቃ ገብታ፤ የሷ ቡችላዎችን በሥልጣን ላይ አስቀመጠችባቸው። ዩጎዝላቪያን በታተነች። አፍጋኒስታን፣ ኢራቅና ሲሪያ ሳይሆንላት ቀረ። ሊቢያን አመሰች። ሶማሊያም ሞክራ አልተሳካላትም። ባጠቃላይም በየሄደችበት ሁሉ ለአገሮች ችግርን አውርሳ ሾልካ ወጥታለች። አሁንም በኛ አገር ውስጥ ጣልቃ ገብታ የምታደርገውን ሁላችን አናውቀዋለን።
ዛሬ ፑተን በበኩሉ፤ “የእብሪተኞች ሁሉ ቁንጮ እኔ ነኝ!” ብሏል። “በኔ አገር አካባቢ ያሉ አገሮች ሁሉ፤ እኔ የምላቸውን ማድረግ አለባቸው!” “የኔቶ ትብብር ውስጥ መግባት የለባቸውም!” “ከገቡ አይቀጡ ቅጣት እቀጣቸዋለሁ!” በማለት የአገሮችን ነፃነት ተጋፎቶ ቆሟል! በፋሽስቱ ጣሊያን ወራራ ጊዜ የኢትዮጵያ መሪ በተባበሩት መንግሥታት አዳራሽ ውስጥ እንደተማጸኑት ሁሉ፤ የዩክሬን መሪ ለአውሮፓ መንግሥታት የድረሱልኝ ተማፅኖ ጥሪ አቅርቧል። ነጮች ስለሆኑና በተወሰነ ደረጃ ፉክክሩ ስላለ፤ ምናልባት ትንሽ ድጋፍ ያደርጉለት ይሆናል። የዩክሬን ሕዝብ ዕልቂት ግን ተጽፎበታል። የዚህ ሁሉ ማሰሪያው፤ “ጉልበት ይሆናል እውነት!” የሚለው መርኅ ነው። ራሱ ትራምፕ በአገሩ ላይ የእብሪት ሥራ አድርጓል። በአገሪቱ ያሉ ተቋማት ጥንካሬና ጥቂት ሃቀኛ የራሱ ፓርቲ አባላት፤ አጉራ ዘለልነቱን ልጓም ባይሸብቡበት ኖሮ ጉዳቱ ከባድ ይሆን ነበር። ዛሬም የሩሲያ ሕዝብ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ፤ ፑተንን እያሳፈረው ነው። እብሪተኛ ሲያፍር ደግሞ አደገኛ ነው! በወጣትነቱ ጊዜ “ተው!” ተብሎ ያላደገ፣ ቂምን እንደጡጦ እየተጋተ ያደገ፣ የበታችነትን የኑሮው አካል አድርጎ የያዘ፣ አዕምሮው ትክክል እና ትክክል ያልሆነን መለየት ይሳነዋል። ፑትን ችግሩ ይሄው ነው። በኬጂቢ መሰሪነት ያሳደገው የቀድሞው የሶቪየት ኅብረት መፍረስ፤ አንጀቱን በልቶታል። እናም አሁንም ያን ለመመለስ ይቋምጣል። የኔቶ መስፋፋት እንቅልፍ ይነሳዋል። ጤነኛ አመለካከት ርቆታል። በአንድ ሰው ፍላጎት የዩክሬን ሕዝብ እየተሰቃዬ ነው። ታንክ በትንሽ መኪና ላይ በሮ ሲወጣ ዓየሁ! ስደተኞች፤ በተለይም ሕፃናት ሲሰቃዩ ዓየሁ። ዓለም የእብሪተኞች በረት፣ የጉልበተኞች ሜዳ መሆኗ ታዬ! የአሜሪካ እግዚዖ ማለት፤ “ከአንቺ ባል ፈስ፤ የኔ ባል ፈስ ይጥማል!” አለች እንደተባለችው ሚስት ነው። አሜሪካ ዓለምን ብቻዋን ስታምስና ግፍና ሰቆቃ በሌሎች ላይ ስታወርድ ማን ተቆጣትና ነው፣ አሁን እሷ ተቆጭ የምትሆነው!
ፊታችንን ወደራሳችን አገር ስናዞር፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ይሄው ነበር ውልደቱ፣ ዕድገቱና አሁን ያለበት ሀቅ! “እኔ ያልኩት ካልሆነ! እኔ የሁሉም የበላይ ነኝ! የኔ ዘር ወርቅ ነው! ወ.ዘ.ተ.” እናም በቅርቡ በአማራውና በአፋሩ ላይ ያዘነበው እልቂትና የንብረት ውድመት፤ “እኔ ልዩ ነኝ!” ከሚለው የእብሪት ውጥረትና የባለውለታነት አባዜ የመነጨ እምነት ነው። ዛሬም በፈረደባቸው አፋርና አማራ ላይ እልቂቱ እንደቀጠለ ነው። አሁን ሌሎች ባለተረኞች የአገሪቱን የሥልጣን ቦታ ይዘውታል። “እኔ ልዩ ነኝ!” እና “እኔ በሌሎች ኪሳራ መጠቀም አለብኝ!” የሚል አባዜ የተጠናወታቸው ሰዎች፤ አገር ማስተዳደር ቀርቶ፤ የመንደር ቡና አጣጭ ሊሆኑ አይገባቸውም።
አብሮ መኖር ማለት፤ የጋራ የሆነ ኑሮ መገንባት ነው። “በስብስብ ኑሯችን ሁላችን እኩልና አንድ ነን!” ብሎ ማመንን ይጠይቃል። ዩክሬን የሚኖሩ ሩሲያዊነት ያላቸው ዜጎች፤ ፑተንና እያወገዙት ነው። ይህ ነው አብሮ መኖር ማለት! ይህ ነው አገር መውደድ ማለት! በዚያ መሠረት ብቻ ነው አብሮ መኖር የሚቻለው። “እኛ የተለየን ነን!” “እኔ የተለየ ጥቅም ያስፈልገኛል!” የሚል ካለ፤ አብሮነት የለም። ኢትዮጵያ ከዚህ እንድትወጣ ምኞቴ ነው። በተጨባጭ በቅርቡ ይሆናል የሚል እምነት ግን የለኝም። ምኞት አንድ ነገር ነው። ተጨባጩ ሀቅ ደግሞ ሌላ ነው። ይህ ተጨባጭ እንዲሆን፤ መጀመሪያ መሠረት የሚሆነው ሕገ-መንግሥትና ለዚህ ጥብቅና የሚቆሙ ተቋማት መኖር ግድ ይሆናል። ያለን ሕገ-መንግሥት ይሄንን አያራምድም፤ ይልቁንም ተጻራሪ ነው። ትክክለኛ ሕገ-መንግሥት በሌለበት እውነታ፤ ለዚህ ጥብቅና የሚቆሙና ትክክለኛ አሠራር እንዲኖር የሚጥሩ ተቋማት የሉንም። እንኳንስ እንደኛ ባሉ ዴሞክራሲያዊ አሠራር ያልተለመደባቸው አገር ይቅርና፤ “ዴሞክራሲያዊ ነኝ! እኔ የዴሞክራቶች ሁሉ ቁንጮ ነኝ!” የሚለው የአሜሪካ መንግሥትም እያየነው ነው!
ከዩክሬን ወረራ የምንማረው ምንድን ነው? ባጭሩ፤ “ጉልበት ይሆናል እውነት!” ነው። በኢትዮጵያ፤ በትውልድ ማንነት ክልል ላይ በተመሠረተ መንግሥታዊ ሥልጣን እውነታ፤ ሥልጣኑን የያዘው ክልል አድራጊ ፈጣሪ ነው። ሌሎች ምንጊዜም ቢሆን የእንጀራ ልጆች ናቸው። ከሱማሊ ተወላጅ፣ ከሲዳማ ተወላጅ፣ ከአፋር ተወላጅ፣ ከጋምቤላ ተወላጅ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ ተወላጅ ጠቅላይ ሚኒስትር አትጠብቁ! በያዝነው የፖለቲካ ቅኝት፤ ይሄ ቅዠት ነው። ይሄን ማቆም የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ለኔ አስቸጋሪ ሆኖብኛል። ብልፅግና ይሄንን የሚያመጣ ፓርቲ አይደለም። ሌሎች፤ ይሄ ጉልበትም ሆነ ይሄ ፈቃደኝነት ያላቸው ባካባቢው የሉም። እናም በቅርቡ ይስተካከላል የሚል ጠንካራ እምነት የሌለኝ ለዚህ ነው። ይሄንን ሳሰፍር ሰውነቴን እየሰቀጠጠኝ ነው። ሀቅ ግን ወደድነውም ጠላነውም ሀቅ ነው። ብልፅግናን የሚፎካከር ሌላ ትክክለኛ ወገንና አገር ወዳድ ፓርቲ ካልተፈጠረ፤ ይሄ ሊለወጥ አይችልም። ያንን ተፎካካሪ ፓርቲ መፍጠሩ፤ አማራጭ የሌለው ግዴታ ነው። ያ ደግሞ በብዙዎች ፍላጎትና ፈቃደኝነት የተመረኮዘ ስለሚሆን፤ እኒህን የተለያዩ ፍላጎቶችና ፈቃደኝነቶች ማቀራረብና በአገር ማዳን ላይ የተመሠረተ ቅንነትን ማራመድ የመጀመሪያው እርምጃ ነው። ወገንን ማስቀደምና አገር መውደድ ማለት፤ ከእኔ ባይነት መውጣት ማለት ነው። ወገንን ማስቀደምና አገር መውደድ ማለት፤ በአገር ሕዝብ ላይ ከፍተኛ እምነትን መጣል ማለት ነው። ወገንን ማስቀደምና አገር መውደድ ማለት፤ በስብስቡ ማመን ማለት ነው። ወገንን ማስቀደምና አገር መውደድ ማለት፤ በስብስቡ ያለውን ግለሰብ እኩልነትና አንድነት መቀበል ማለት ነው። ለዚህ ዝግጁ የሆነ ፓለቲከኛ ኢትዮጵያ ውስጥ በሥልጣን ላይ አለ ወይ! ይሄን ግለሰብ ፍለጋ ብዝይ ባትሪ የሚጠይቅ ይመስለኛል፤ እናም ትልቅ ፈተና ነው።
ኢትዮጵያ የኢትዮጵያዊያን ናት። ልጆቿ ይታደጓታል።