December 28, 2021
5 mins read

ባለታላቅ ታሪክ ነኝ ኢትዮጵያዊ – እስፋው ረጋሳ

ethiopia
ethiopia

ማነህ አልክኝ?
ማነሽ አልክኝ?
በጎሳ ቋት ልትከተኝ
ከሰውነት ልታወርደኝ
ባምሳለ አምላክ የተሰራ
ስብዕናየን ልትገፈኝ
ከአራዊት መስመር ተርታ
ልታውለኝ፡ ልትፈርጀኝ
በህገ አራዊት ልታኖረኝ
በጎሳ ሽብልቅ ከወገኔ ልትለየኝ
ልታፈርሰኝ፡ ልትበትነኝ፡፡
ማነህ አልከኝ?
ማነሽ አልክኝ?
ባለታላቅ ታሪክ ነኝ ኢትዮጵያዊ
የሉሲ Hር ቀዳማዊ
ሺህ Hመናት ታሪካዊ
በአድዋ አቻ የለሽ ታሪክ ሰሪ
ለጥቁር ህዝብ የእኩልነት
የነጻነት ድል አብሳሪ።
ኤዲያ ክልልህን፣
አፍርስ አጥርህን
ቅደድ ክታብህን
ጣለው ቡትቶህን።
አገሬ ነች ኢ ት ዮ ጵ ያ
ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ
ከምስራቅ እስከ ምዕራብ
ስንዝር በስንዝር ብትለካ
አፈር ውሃ ሳር ቅጠሉ
መሬት ወንዙ እርሻ ሰብሉ
ምድር ሰማይ ከዋክብቱ
አየርና ነፋሳቱ
ወፍ አራዊት እንስሳቱ፤
ሁሉም የኔ የኢትዮጵያዊ
የድንቅነሽ ቀዳማዊ።
ኤዲያ ክልልህን
አፍርስ አጥርህን
ቅደድ ክታብህን
ጣለው ቡትቶህን።
አምላክ ሲፈጥረኝ ባምሳሉ
ሰው እንድሆን እንደቃሉ
ግና አንተ አውርደኸኝ
ክሰገነት ከከፍታ
ገፍተህ፤ ገፍተህ ከአዘቅቱ
አጣድፈኸኝ ቁልቁለቱን
በሶሥት አሥርት ስብዕናዬን የገፈፍከኝ
በጎሳ ቋት የከተትክኝ
ሰማይ ምድሬን ያጠበብክው
ኢ ት ዮ ጵ ያ ዊ ነ ቴ ን ያወረድከው
ያ ዋ ረ ድ ከ ው፤
ባጭር ዕይታ ‘ማዮፒያ’
ሰውነቴን ያሳነስከው።
ታሪክ ቅርሴ ባህል ወጌ
ጥንተ ዕምነት መሰረቴ
ክርስትና፤ እስልምና
ቤተ አይሁድ ሃይማኖቴ፤
ዜማ ቅኔ ጭፈራዬ
ህብረ ቀለም ሳለ ውበቴ፤
ከየት ነህ አልከኝ?
ከየት ነሽ አልከኝ?
ከዜግነት ክብር አውርደህ
በጎሳ ቋት የከተትከኝ
በነጭ ስሪት ከፋፍለህ ግዛ
የተንኮል ወጥመድ ያጠመድከኝ፤
የሰው ዘር መገኛ አገሬን
ኢትዮጵያን ልታፈርስ
ትልማቸውን ዳር ልታደርስ፤
አይሆንም ብያለሁ!
ኤዲያ ክልልህን
አፍርስ አጥርህን
ቅደድ ክታብህን
ጣለው ቡትቶህን
ባለታላቅ ታሪክ ነኝ ኢትዮጵያዊ
የድንቅነሽ ቀዳማዊ
አረንጓዴ ቢጫ ቀይ
ሰንደቄን ከፍ አድርጌ
ወደ ክብሬ እንድመለስ
ስብዕናዬ እንዲታደስ
በቃ አልኩኝ፤ በቃ፤ በቃ!
ኖ ሞር! ኖ ሞር!
ባለታላቅ ታሪክ ነኝ ኢትዮጵያዊ፤
የንግስተ ሳባ የማክዳ
የቅዱስ ያሬድ፤ የዮሃንስ
የምኒልክ፤ የቴዎድሮስ
የጣይቱ ክንደ ብርቱ፤
የአሉላ አባነጋ
የባልቻና አብዲሳ አጋ፤
በሰሜኑ በደቡቡ
በምስራቁ በምዕራቡ
የቀድሞና ያሁን ጀግኖች
የኔነቴ ምልክቶች፤
የሁሉም ነኝ ኢ ት ዮ ጵ ያ ዊ
የሉሲ ዘር ቀዳማዊ።
በቃ! በቃ!
ኖ ሞር! ኖ ሞር!
ከወገኔ አብሬ እንድኖር
እንደ ጥንቱ እንደ ጠዋቱ
በፍቅር ሰላም ተከባብረን
ባንተ ትብስ ባንቺ ትብሽ
መተባበር ተረዳድተን
ሁሉም ዜጋ በዕኩልነት
ፍትህ ርትዕ የሚያገኝበት
ዕንባችንን የሚያብስ
ስብራትን የሚጠግን
ህመማችን የሚፈውስ
መንግስተ ህግ አውጃለሁ!
የውድ አገሬ ኢ ት ዮ ጵ ያ ን
ውድ ሰንድቋን ክፍ አድርጌ
ለአንድነቴ እዘምራለሁ፤
ነጻነትዋን አበስራለሁ!!!

መታሰቢያነቱ፦ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት በግፍ ለረገፉት ወገኖቻችን ይሁን።

ታህሳስ 2014 ዓ ም

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop