November 24, 2021
1 min read

እምቢ በይ ኢትዮጵያ! – በላይነህ አባተ

በቋንቋ ቢላዋ ሰውቶ ሊመትርሽ፣
ጉልቻ ጎልቶ ጠባብሶ ሊውጥሽ፣
ዛሬም እንደ ድሮው ምዕራብ ሲያሴርብሽ፣
እምቢ በይ ኢትዮጵያ ደሞ እንደልማድሽ!

እንደ አምስቱ ዘመን የፋሽሽት ወረራ፣
ዓለም ሲያድምብሽ ሲዶልት ተባንዳ፣
አሻፈረኝ በይ እምቢ በይ እማማ፣
ጠንክረሽ መክቺ የእጅ አዙር ወረራ!

ጃሎ በል ራስ ደጀን ዘራፍ በል ጭላሎ፣
አመዳሚት ፎክር ሸልል ጮቄ ባቱ፣
ባንዳን ተፊት አርገው ሊወሩህ ሲመጡ፡፡

ደፍርስ ተከዜ ወንዝ አዋሽና ጊቤ፣
እንቆቆ ሁን ዓባይ ባሮና ሸበሌ፣
ተባእድ ተሻርኮ ሲጠጣህ ከሀዴ፡፡

ምድሪቱ እሾህ ሁኝ ባንዳ የማይረግጥሽ፣
ሰማዕቱ ጴጥሮስ እንዳስጠነቀቀሽ፡፡

ሴቷን መቀነቷን ወንድ ቀበቶ አስጣጥቀሽ፣
ዲያቆኑን እምቢልታ ቄስ ታቦት አሲዘሽ፣
እምቢ በይ ኢትዮጵያ እንደ ጥንት ታሪክሽ!

በላይነህ አባተ ((abatebelai@yahoo.com)
ህዳር ሁለት ሺ አስራ አራት ዓ. ም

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop