አቅራቢ:- አልማዝ አስፋ – ዘረ ሰው
Imzzassefa5@gmail.com
በይህ አደግ ጥይት – ያለቀው ቢበዛም
በይህ አደግ ምጣድ – ቢኖር የተቆላም
በይህ አደግ ጭካኔ – እግሩን አይኑን ያጣም
በይህ አደግ ክፋት – መሃን የሆነውም
የሞተው ቢበዛ – በጭንቅ የኖረውም
ይህ አደግን እናቁመው – ብለን ብንጠይቅም
መፍትሔው ከውስጥ እንጂ – ከውጭ አልሆነም::
አሁን ተረዳነው – በእርግጥ ተገነዘብን
ጆሮ ጠቢነት – ችሎታ መሆኑን
ለአገር ደህንነት – አስፈላጊነቱን::
ኢትዮጵያን ሚያስቀድም – ለአገር አሳቢ
ሰላም እኩልነት – ዲሞክራሲ ገንቢ
በውስጡ ያደገ – በይህ አደግ ግቢ
ለውጡ አስፈለገው – ጥሩ ጆሮ ጠቢ::
አንበርክኮ ኖሮ – ወኔነት ያጠፋ
ጨለማ ሸፍኖን – ያጣንበት ተስፋ
ይህ አልነበር እንዴ – የይህ አደግ ገረፋ?
እናቶች ሲያለቅሱ – ለፈጣሪ ምህረት
ስንመኝ የኖርነው – ስናሰማ ፀሎት
ጆሮ ጠቢነቱ – ያመጣው ውጤት
የተፈለገ አይደል – የይህ አደግ ውድቀት?
ለፈጣሪ ምህረት – እናቶች ለምነው
በጠበቀ ፀሎት – ተማፅነን የኖርነው
የይህ አደግን ውድቀት – እኛ የፈለግነው
በጆሮ ጠቢነት – ውጤት ያገኘነው
እስከሆነ ድረስ – ችግሩ ምንድነው?
በአንድ ስርዓት ውስጥ ማደግ – ከሆነ አስከሳሽ
በአንድ ስርዓት ውስጥ መኖር – ከሆነ አስወቃሽ
መስራትም ክሆነ – ከኃጢአት የማያሸሽ
ከ110 ሚሊዮን አይኖር – ነፃ ሚሆን ጭራሽ::
ሰገብጋባ ሆኖ ሳይኖር – የተደላደለ
ጆሮ ጠቢ ሆኖ – ሰውን ካልበደለ
በጆሮ ጠቢነት – ለውጥን ካበቀለ
ይህ አደግ ከዙፋን – ከተፈናቀለ
እሰየው ብንለው – ምንስ ችግር አለ?
መቃወም ሸጋ – ለማምጣት መሻሻል
ሚዛናዊ ሲሆን – እድገትን ይረዳል::
ግን ዝም ብሎ መቃወም – ለመቃወም ተብሎ
ለአገር ጥቅም እንዳልሆነ – ያሳያል ጎልጉሎ::
እኛ ሳንሆን ፍፁም – ፍፁም ሳናደርገው
ሰው መሆኑን ተረድተን – ካለ ምናግዘው
ከጎኑ በመቆም – በጥሩ ስራው
አይዞህ በርታ እንበል – ለጆሮ ጠቢው::
እንተ ጆሮ ጠቢ – ስልጣንን ለያዝከው
ለአገር አንድነት – ቆማለሁ ላልከው
ሕዝብን አቀራርበህ – ህብረት እንዲኖረው
በጋራ በመስራት – ችግሩን እንዲቀርፈው
ያ እንደሆን ጥረትህ – ጠርጣሪህ ይወቀው::
የጆሮ ጠቢው አቋም – ታላቁ ዓላማ
ጎሰኝነት ጠፍቶ – ህብረት እንዲለማ
ለአንድ ጎሳ ቆሟል – ተብሎ ሲሰማ
ሃቅ መሆኑ ተክዶ – በሃሰት ሲታማ
ነው የጠባብ ጎሰኞች – እንዲህ አይነት ግምገማ::
ግን ግብታዊ ሰዎች – ማስተዋል ተስኗቸው
ለአገር አንድነት መቆምህን – መገንዘብ አቅቷቸው
እውነትን መጨበጥ – አልታይ ብሏቸው
የምትሰራውን ስራ – እንዳልሰራህ አድርገው
በሀሰት በመክሰስ – ጎሰኛ ነህ ብለው
ኃጢአትህን አበዙ – ያልሆንከውን ዘርዝረው::
ስምህን ቢያጠፉ – የሚሉት ቢገባህ
ለቆምከው ዓላማ – ከውስጥ ለሚሰማህ
ኢትዮጵያ አገራችንን – ከችግር አውጥተህ
ሕዝቡን አቀራርበህ – አንድነት አምጥተህ
በወሬኞች ሀሜት – ቅሬታ ሳይሰማህ
እውነት ተመርኩዘህ – ሕዝብህን አቅፈህ
አገር ላትበተን – ቃል ኪዳን ለገባህ
ጆሮ ጠቢው ጏድ- ፈጣሪ ያግዝህ::
የእርስ በርስ ጥላቻ – ፍቅርን የተካበት
የእኔ ጎሳ እያልን – የምንፎክርበት
ልጅ ወልዶ ማሳደግ – ችግር የሆነበት
እንደ ማገዶ እንጨት – ሰው ሚገበርለት
ሰርተን እንዳንበላ – የሆነን እንቅፋት
ለማኝ ያደረገን – ሰላም ያጣንበት
መች ይሆን ሚቆመው – የጎሳ ጦርነት?
ለአመታት ያልተወንን – ረሃብ አስወግደህ
ከስንዴ ልመና – አገርን ገላግለህ
ሕዝብ ሶስቴ መብላት – እንዲችል አድርገህ
በጆሮ ጠቢነት – ዳብሮ ባለው እውቀትህ
ምራት ያችን አገር – ጎሰኛን አጥፍተህ::
ሲመቸው ለስልጣን – ሲሮጥ ከዲያስፖራ
አገር አገር ብሎ – ቆሞ ሲንጠራራ
ሲያስመስል ከርሞ – ለኢትዮጵያ ሚሰራ
ሳይመቸው ሲቀር – ሲገጥመው ኪሳራ
ማራመድ ማናፈስ – ጎሰኝነት ሴራ
ስንቱን ታዝበናል – ውሸቱን ሲያወራ::
ከትውልድ ወደ ትውልድ – እንባ የሚረጨውን
ያንን ደሃ እንጂ – አትስማ ኤሊቱን::
ለአገር መከታ – አስፈላጊ እውቀት
ሕዝብ ማቀራረቢያ – የህብረት ምሳሌት
ይቅር ለፈጣሪ – ሚያስጠይቅ ምህረት
በሰላም የሚያስኖር – ጠፍቶ ጦርነት
እንደዚያ ከሆነ – የስልጠናው ውጤት
አገር ይገነባል – ያ ጆሮ ጠቢነት::