ከልጅነት እስክ እውቀት
የንግስና ቅዥትህን
ልታሳካ ስትዋትት
ስትባዝን ስትቃትት
ስታምታታ ስታሳስት፤
በማሳመን ወይ ማጭበርበር
“ፍልስፍና”ህ የመደመር
ስትቀባጥር ስትደሰኩር
እርካብ ረግጠህ
መንበር ወጥተህ
ላሞችህን ሳር አብልተህ
ወደ ገደል ስትጨምር፤
በኢትዮጵያና በልጆችዋ
መከራ ግፍ የምታወርድ
የምታስወርድ፤
ለሽመልስ ላባዱላ
ማኪያቨሊ ካሊጉላ
መጥፎ ጨካኝ
ህጻን በላ
ባይን ጥቅሻ ትእዛዝ ሰጥተህ
የሪፐብሊክ ቅዠትህን
በወገን ደም
በወገን ዋይታ
የምትተጋ ልታምዋላ፤
መከረኛው ህዝባችንን
በአራቱም ማዕዘናት
በአንድነት የኖረውን
ኢትዮጵያዊነትን
ማተቡ አርጎ
ሺህ ዘመናት የኖረውን
አብሮ በልቶ፤ አብሮ ጠጥቶ
አብሮ ኖሮ፤ አብሮ ሞቶ
ለክብሩና ላንድነቱ
ሰንደቅና ነጻነቱ
በአንድነት የቆመውን
አንድነቱን ልትፈታ
ከጡት አባት ካሳዳጊህ
ከዚያ ጨካኝ ባንዳ መለስ
ተቀብለህ ዱላ ሪለይ
ዳር ልታደርስ
ውድ ኢትዮጵያን እንድታፈርስ፤
በቀን ብርሃን ኢትዮጵያዊ
መሢህ ሆነህ የሐሣዊ
ህዝባችንን የምትመግብ
በአደንዛዥ ባዶ ቃላት
አእምሮ ልብ የምትሰልብ፤
በጭለማ ኦሮሙማ
ከሽመልስ ካባዱላ
ከነአዳነች ከነኡማ
ስትዶልት ስትስማማ
ካፈጣጠር ካስተዳድግ?
ርህሩህነት የጎደለህ
የወገን ስቃይ ስደት ሞቱ
የሰት ወንዱ ትልቅ ትንሽ
የህጻናት ያዛውንቱ
ረሃብ ጥማት ግፍ እልቂቱ
ቅንጣት ታህል ያልገደደህ
ሰው ለመሆን ያልተቻለህ
ለመሆኑ አንተ ማነህ?
በአራቱ ማዕዘናት
የሚሊዮኖች መፈናቀል
የሺዎች እርድ
እንዲያው ከቶ
ግድ ያላለህ
ለመሆኑ አንተ ማነህ?
እንደ ሮማው ንጉስ ነሮ
ሮማ ስትነድ ተደስቶ
በቫየሊን የዘመረው
በመቶዎች እንደዋዛ
በጨካኞች ተጨፍጭፈው
የወገን ዋይታ ልብ መድማት
እንዳች ፍጹም ግድ ያልሰጠህ
ጅል አድር ባይ
ባምስት ኮከብ
በሸራተን አስኮልኩልህ
የርካብ መንበር ሲመት በዓል
ልታከብር ልበ ድንጋይ ያደረገህ
ማነህ አንተ ለመሆኑ?
ድንቁርናህ ሞልቶ ፈሶ
ባታውቀውም ባይገባህም
ያነሳሀው ያጋጨህው
ለሲመትህ የተሞላው
ብርጭቆው ላይ የተቀዳው
ወይን መስሎህ፤ ወይን አይደለም
የህጻናት ያዛውንቱ
ትልቅ ትንሽ ወንድ ሰቱ
ደም እንባ ነው
ስትጎነጨው ሚያሰክርህ
እንደ ጥላ ሚከተልህ
የዕድመ ልክ ክፍያህ ነው፤
ልብ ካለህ ልብ ብትል
ከሐዋርያው የጳውሎስ ቃል
ከገላትያን መልእክቱ
አንድዋን ሐረግ ብታስተውል
ጊዘው ይርዘም ይጠር እንጂ
የዘራህውን እንድታጭድ
ቅዱስ ቃል ነው
የሚሆን ግድ፡፡
ከፈለቀ አለሙ
መጋቢት 2013