ይህንን አውቃለሁ !…
( የግጥሙ ደራሲ መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ )
ሰዎች ሁላችን…
ሥጋን እንወዳለን…
ሥጋን እናፈቅራለን…
ለሥጋ እንሞታለን…
ለሥጋዬ ለዘመዴ… ሁሌም እንላለን።
ከቶ ምን ይሆን ይህ ሥጋ ማለት ?
በዘር፣በቋንቋ በጎሣ ተቧድኖ የሚሞትለት ?
…………………………….
ይህንን አውቃለሁ…
ይኽ የሰው ሥጋ ይለያል ከከብት
በአዋዜ አጥቅሰው አይመገቡት።
የእንስሳን ስጋ ነው የሰው ልጆች ምግብ
ይህንን ይገነዘባል በሰውነቱ ያለ ፣ እነደ አውሬ የማያስብ፡፡
እርግጥ ማንም ያውቃል…
ከብት ታርዶ፣ ሥጋው ተበልቶ፣በውዛ እየበራበት የሚሰቀለው በየሉካንዳ ቤቱ
ሰው ገዝቶ እንዴያነክተው ነው፣ እዛው ከሉካንዳ ወይ ወስዶ ከቤቱ፡፡
……………………………
እርግጥ ነው፤ አለሰማሁም …
ከቶም አላየሁም…
የሰው ሥጋ ታርዶ ባይቀርብ ለገበያ
ሲሆን ግን አውቃለው በሰብቅ ፣የእንጀራ መብያ
ለብዙሃኑም የቡና ማህበርተኛ ፣ይሆናል የሰው ስጋ ቁርስ
ተነስቶ የሚቦጨቅ…ሺ ጊዜ የሚነሳ የሚጣል.. ደሞም የሚታፈስ፡፡
………………………..
ይህንን አውቃለሁ፣
ሰው ለእንሥሣ ሥጋ፣ ባልትና እየሰጠ
ጣፍጦ እንዲገባ በበልተናው ጣእሙን እያጣፈጠ
ክትፎ፤ጎረድ፣ጎረድ፤ቁርጥና ዱለት
ምንቸት፣ ቀይ ወጥ፣ አልጫ- ፍትፍት
ቅቅል፣ ጥብሥ፣ ክትፎ፣ ምላሥና ሰንበር
አውቃለሁ…እጅ እያስቆረጣሚ ሆኖ
እየተጎረሰ፣ በአፍ ገብቶ በከርስ እንደሚቀበር።
……………………………
ይህንን እውቃለሁ …
የስጋን ሥጋነት
የእንሥሣን … ከብትነት
የስጋውን…መብልነት።
ይህንን ማንም ያውቃል፣እኔም አውቃለሁ…
ግና ጥቂት ሰው ነው ፣የስጋን ክቡርነት በጥልቅ የሚረዳወ
በመንፈሣዊ ጥበብ ተክኖ ሥጋውን ከሐጥት የሚጠብቀው፡፡
ይህንን አውቃለሁ…
የህ የእኛ የነፍስ ልብሥ …ከሰማይ እንደመጣ
በክብር እንደሚኖር ነፍሳችን እሥክትወጣ።
ሰው ከሞተ በኋላ ልብሱ ሬሳ እንደሚባል
ሥጋው ለዘላለም ከአፈር እንደሚቀላቀል።
ይሁን እንጂ ተራ ሞች…
በህይወቱ ሣለ የፈጣሪ ቤተመቅደስ መሆኑንን ይዘነጋል
በስጋው እየተደሰተ በሐጥያት ይኖራል ፡፡
በሐጥያትም ይከብራል፡፡
……………….
ይህንን አውቃለሁ
ብዙ ሰው ክቡሩነቱን ፈፅሞ እንዳልተረዳ
ዋጋ የከፈለለትን እያሳዘነ፣ እንደሚኖር፣ራሱን እየጎዳ።
ማነው የሚረዳው ሰው “ህዋዊ ” ፍጥረት እንደሆነ
እንደፕላኔት ፣እንደከዋክብት፣እንደጨረቃ በምድር ገዝፎ እንደገነነ ።
የተከበረ ታላቅ ፍጡር መሆኑን ባለማወቁ፣ይኖራል ሰው፣ሰውን እያሳዘነ ።
በሆድ፣ለሆድ ለስጋ ምቾት በመኖር ግላዊ ደሥታን እያቀነቀነ።
እንሆ ለሦሥት ሺ ዘመን ኖሯል የህዋው አካልነቱን እንደረሳ
ዛሬም ይኖራል፣በአልጠግብ ባይነት በእብሪት እያገሳ ።
የራሴ ዜጋ ፣የራሴ ጎሣ ፣የሚለውን ብቻ በማቀፍ
የእኔን ቋንቋ አይናገርም ብሎ ሌላውን በመንቀፍ
ሁሌ፣ሥጋዬን፣ዘሬን ፣ጎሳዬን፣ቋንቋዬን ብሎ
ለሥጋው ምቾት የመንፈሥ አንድነቱን ጥሎ
ከጥንት እሥከዛሬ ሥጋዬ ዘመዴ እያለ
በአውዳሚ መሣሪያው ብዛት እየፎለለ
ሥለሥጋ፣ ለሀብትና ንብረት ሁሌም እየተጨነቀ
ወገኔ፣የአገሬ ዜጋ የማይለውን እያደቀቀ ፤፡
ይህንን አውቃለሁ ! …
ሰው ያለማወቁን እንደማያውቅም እረዳለሁ።
ሀ ሲል ከላይ ከአርያም እንደመጣ
ከሄዋን መሐፀን እንደወጣ
አዳም እነደሆነ አባቱ
ፈፅሞ በመዘንጋቱ…
በመራቅ ከመንፈሳዊ እውቀት
መዳረጉን ለሥጋ እስር ለህሊና ውድቀት።
………………………………..
ይህንን አውቃለሁ !
የምናዋድደው ይህ ሥጋ …
እያየን እኮ ነው ፣ነፍሳችንን ሲወጋ።
በዘርና በጎሣ ሰውነታችንን እየለካ ?!
ሥጋን በማግዘፍ በቅድስናላይ እያስካካ
ክቡሩ ሰውነት ተቆጥሮ እንደእንሥሣ ሥጋ
ሰው በሰው ላይ ማድረሱን ቀጥሎል እየተቧደነ በመንጋ።
…………………………………………..
ይህንን አውቃለሁ !
ሰው ሁሌ ቢበላ የከብት ሥጋ
አወፍሮ ይዳርገዋል እንጂ ለህመም፣ለአደጋ
ጥቂቱን ያጋድለዋል እንጂ ይህ የሥጋ ጥጋብ
በማይረባ ትርኪ ምርኪ፣ በሰበብ ና አሥባብ።
የከብት ሥጋ መብላት ከብት አያደርግም…
የከብት ሥጋ ሥለ በላ ሰው ማሰቡን አያቆምም፡፡
ህሊና የሚበላውን ዓይነት የእንስሳ ሥጋ ሆኖ አያውቅም።
ይህንን አውቃለሁ …
ሰው መሆኑን ለዘነጋ…
ሰው መሆኑን እንዲረዳ
ዛሬም እፀልያለሁ፡፡
……………………………
አመሰግንሃለሁ።
ፈጣሪዬ ሆይ ቸሩ የእኔ አምላክ
(እየሱስ ክርስቶስ )
አንተ ፍፁም ነህ ፣እኔ ባልሆን ልክ።
የልቤን ፀሎት ፣ፈጣሪዬ ሰምተህ
በማሥተዋል ሞላኸኝ ፣ በጥበብ አሥታጥቀህ ።
ህሊናዬ እንዳይዋዥቅ ፣በመንፈሥህ ገዝተህ…
በፍቃድህ አደርገህኛል የሃሳብህ መልዕከተኛ
ሰለፍቅር እና እውነት እንድፅፍ ዘወትር ሳልተኛ።
በአንተ መሪነት ዘወትር እውነትን ፅፌያለሁ
ለዚህም ውለታህ… አመሠግንሃለሁ ።
ማስታወሻ
እነዚህ ሁለት ግጥሞቼ ታህሣሥ 26/2013 ሌሊት፣8:30 ላይ ፈጣሪዬ ከእንቅልፊ ቀሥቅሶኝ የፃፍኳቸው ግጥሞቼ ናቸው። በፈጣሪ ቁጥጥር ውሥጥ የተገጠሙ…። በዛው ሌሊት 10:43 ላይ ግጥሞቹ ተጠናቀቁ። እናም ” የገና ሥጦታ ለአንባቢዎቼ ለምን አላደርጋቸውም ?” አልኩና ዛሬ “እንሆ በረከት ! ” አልኳቸዋ !
እንኳን ለጌታችን ለመድሃኒታችን ለእየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፡፡