ቀን ያጎደለው በቀን ሲተካ
ያኔ ነው ልብ የሚረካ
ንጋት አይሉት ጨለማ
ጭጋግ አይሉት ዳመና
ያዝ ለቀቅ የሚል ያለየለት
ምን ሊመስል ነው የቁርጡ ዕለት
ድብልቅልቅ ያለ አተላ
ገና በድፍድፉ የተበላ
የቆላ ማሩን በጋን ጥሎ
ብቅል ከጌሾ አስመጥኖ
አትረፍርፎ ስለአበላው
ጥጋቡ አልቻልህ ቢለው
ፊቱ ወርዝቶ ጉንጩን ሞላው
ያ ገበሬም እጀ ሰፊው
ምንም ተርፎት ሣያቀናው
በሬው ሙቶ ቢያከስረው
የልጅ ቀለቡን አናረው
ግራ ተጋብቶ መላ ቢያጣ
ለዘር ያስቀመጠውን አወጣ
አንድ ዕፍኝ ዘር ቢዘራው
የጎደለውን በቀን ሞላው
ቀን ያጎደለው በቀን ሲተካ
ያኔ ነው ልብ የሚረካ