ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ውጭ ጉዳይ ምኒስትሩን፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙን፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ኃላፊን እና የፌድራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነርን ከኃላፊነት አንስተዋል። በዛሬው ሹም ሽር እና ሽግሽግ ማን ተሹሞ ማን ተሻረ?
_____________________
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ምኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው፣ የመከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አደም መሐመድ፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ደመላሽ ገብረ ሚካኤል እና የፌድራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር እንደሻው ጣሰው ከኃላፊነታቸው ተነሱ። ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም. አዳዲስ ሹመቶች ሰጥተዋል።
ውጭ ጉዳይ ምኒስትር የነበሩት ገዱ አንዳርጋቸው ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን የጠቅላይ ምኒስትር ጽህፈት ቤት ዛሬ ይፋ አድርጓል። በምትካቸው ደመቀ መኮንን ከምክትል ጠቅላይ ምኒስትርነታቸው በተጨማሪ የውጭ ጉዳይ ምኒስትርነት ሥልጣንን ደርበው እንዲሰሩ ተሾመዋል። አቶ ገዱ ከዛሬ ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብሔራዊ የደህንነት አማካሪ ሆነው ተሾመዋል።
ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ሲገደሉ የኢትዮጵያ የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም ሆነው የተሾሙት ጄኔራል አደም መሐመድ ከኃላፊነት ተነስተዋል። ምክትላቸው የነበሩት ጄኔራል ብርሀኑ ጁላ የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም ሆነዋል። ባለፈው ሳምንት ጥሪ ተደርጎላቸው የኢትዮጵያን ጦር የተቀላቀሉት ሌቴናል ጄኔራል አበባው ታደሰ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሆነዋል።
የብሔራዊ መረጃ እና ደሕንነት አገልግሎትን በዋና ዳይሬክተርነት ሲመሩ የቆዩት አቶ ደመላሽ ገብረሚካኤል ሌላው ከኃላፊነት የተነሱ ባለሥልጣን ናቸው። በኦሮሚያ ክልል እና በፌድራል ፖሊስ ኮሚሽን በከፍተኛ ኃላፊነት የሠሩት ደመላሽ የብሔራዊ መረጃ እና ደሕንነት አገልግሎትን እንዲመሩ የተሾሙት ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ከተፈጸመው የከፍተኛ ባለሥልጣናት ግድያ በኋላ ነበር።
በምትኩ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አቶ ተመስገን ጥሩነህ የብሔራዊ መረጃ እና ደሕንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሆነዋል። አዲሱ የብሔራዊ መረጃ እና ደሕንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ተመስገን ጥሩነህ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው የተሾሙት ሐምሌ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ነበር። ተመስገን ክልሉን የመምራት ኃላፊነት የተረከቡት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) በባሕር ዳር ከተማ ከተገደሉ በኋላ ነው። ከዚያ በፊት የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብሔራዊ ደሕንነት አማካሪ ሆነው አገልግለዋል።
በዛሬው ሹም ሽር እና ሽግሽግ አቶ ደመላሽ የፌድራል ፖሊስ ኮሚሽነር ሆነው ተሾመዋል። በውሳኔው መሰረት የፌድራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር እንደሻው ጣሰው ከኃላፊነት ተነስተዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ዛሬ ባካሔደው ስብሰባ በአቶ ተመስገን ምትክ የክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የነበሩትን አቶ አገኘሁ ተሻገርን ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ ሾሟል።
SOURCE: DW (Deutsche Welle’) Amharic