ክፍል አምስት
የእርስ በእርስ ጦርነት ዛሬ አልተጀመረም።
የወልቃይት ጠገዴ፤ የጠለምት፤ የዋልድባ፤ የሰቲት ሁመራ፤ የራያና አዜቦ፤ የትግራይ፤ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ደስ ያላችሁ። ሊወገድ የሚችል ጦርነት መካሄዱ አሳፍሮኛል። ሊካድ የማይችለው ሃቅ ግን የዐማራው ሕዝብ በሽብርተኛው ብድህወሓትና በኦነግ ሽኔ ተከታታይ እልቂት ሲካሄድበት ቆይቷል። ህወሓት ባወጣው ማኒፌስቶ (መመሪያ) የፋሽስቱን የጣልያን ግፍ፤ በደልና የበላይነት ተመሳሳይ ነው በማለት “የዐማራው ሕዝብ ለትግራይ ሕዝብ ዋናው ጠላት ነው” ብሎ ፈርዶበታል። ይህንን ትርክት ሌሎች የብሄር ጽንፈኞችና እንደ ኦነግ ሽኔ ያሉ ሽብርተኞች መሳሪያ አድርገው ዐማራውንና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዩን ጨፍጭፈውበታል። ይፋ አይሁን እንጅ ዐማራውን ኢላማ ያደረገ ያልታወጀ ጦርነት ሲካሄድ ከአርባ ዓመታት በላይ ሆኖታል።
ህወሓት የቀሰቀሰውን ጦርነት ጀግናው የመከላከያ ኃይል፤ ከነዋሪው ገበሬ፤ ከፋኖው፤ ከሚሊሺያውና ከሌላው አጋር ኃይል ጋር ሆኖ የሚያካሂደውን የጸረ- አመጸኞች ወይንም ሽብርተኞች፤ በተለይ ጸረ-ሰላም፤ እርጋታና ጸረ-ከሃዲነት እንቅስቃሴ አደንቃለሁ።
ይህ አላስፈላጊ ጦርነት የተጀመረው በህወሓት፤ በኦነግ ሽኔ፤ በጅሃዲስቶችና ከጀርባ ከፍተኛ ድጋፍ በሚሰጡ ኃይሎች፤ በተለይ በግብፅ መሆኑን በተከታታይ ትንተናዎቸ አሳስቤ ነበር። ኢትዮጵያን እኛ ካልገዛናትና ካልመዘበርናት የደም መሬት አድርገናት ትበተን የሚሉት ህወሓትና አጋሩ የኦሮሞ ነጻ አውጭ ወታደራዊ ኃይል (The Oromo Liberation Army/OLA) ያመጡት ጠንቅ ነው።
ወረተኛ ካልሆንን በስተቀር ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በኋላ ተራው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላምና እርጋታ ያገኘው መቸ ነው? እኔ ወጣት ከአባቴ ጋር በበቁሎው ተሳፍሬ፤ እንዳልወድቅ ወገቡን ይዠ በያካባቢው ለሰርግ፤ ለለቅሶ፤ ለልዩ ልዩ በዓል ስንዞር አንድ ሰው ሌላውን “በሕግ አምላክ” ሲለው ካለበት የማይንቀሳቀስባት አገር ነበረች–እትዮጵያ።
የደርግ መንግሥት “ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም” ብሎ ሕዝቡን ከቀሰቀሰ በኋላ የሆነውን የእኔ ትውልድ ያስታውሰዋል።
ሻቢያ፤ ህወሓትና ኦነግ የነጻ አውጭ ድርጅቶች ሆነው ደርግን ሲያስወግዱና ለሥልጣን ሲደራደሩ አብሮ የተወገደው ኢትዮጵያዊነት ነው። የገነነው ደግሞ ጠባብ ብሄርተኝነት፤ ጽንፈኝነት፤ አመጸኝነት፤ ነፍስ-ገዳይነት፤ በተራው ሕዝብ ስም ድርጅታዊ መዝባሪነት፤ የዘውግ ተረኛነት ወዘተ ነው። በሰላም፤ በፍትህ፤ በሕግ የበላይነት የሚያምኑትን ፕሮፌሰር አስራትን የገደለ ስርዓት ነው የተመሰረተው። ከሳቸው በፊት የተፈጸመውን ጭፍጨፋ፤ ግፍና በደል ችላ ብንለው እንኳን ከሳቸው በኋላ የተፈጸመውን ብንመረምረው መረጃው ብቻ አንዲት መጽሃፍት ቤት ይሞላል።
እኔ ዓለም ባንክ ሆኘ ህወሓት የሚያደርገውን ግፍና በደል በኢትዮሜድያና በኢትዮጵያን ሪቪው “እውነቱ ከፍያለው” በሚል በብእር ስም ጭምር እተች ነበር። ህወሓቶች ጭፍጨፋ ሲያካሂዱ መረጃ ሳይተው ነበር (They were silent murderers). የዓለምን ሕዝብ ያታለሉት በመለስ ዜናዊ አማካይነት እንደ ነበር አንርሳ። ዓለም ባንክ፤ አይ ኤም ኤፍ፤ የአሜሪካ፤ የእንግሊዝና ሌሎች መንግስታት ይህን ጨካኝ ሰው ከሩዋንዳው ካጋሚ ጋር የአፍሪካ “ትንሳኤ መሪዎች (Africa’s Renaissance men)” ብለው ሸልመውት ነበር።
ህወሓት ጨካኝ፤ ዘራፊ፤ ጸረ-ሰላም፤ ጸረ-ዲሞክራሲና ጸረ-ኢትዮጵያ ኃይል ሆኖ የሚሰራ ድርጅት ነው። ህወሓትና ሌሎች ጽንፈኛና ሽብርተኛ ቡድኖች የኢትዮጵያን ሕዝብ ደህንነት፤ የአገራችንን ሰላም፤ የኢትዮጵያን ግዛታዊ አንድነትና ሉዓላዊነት አይደግፉም። ኢትዮጵያ ከጠፋች ደግሞ ዲሞክራሲ፤ ልማት ወዘተ ቀልድና የፖለቲካ ንግድ ነው።
ህወሓትና የዘረጋው የጥፋት መዋቅር መፍረስ አለበት። በተመሳሳይ፤ ህወሓት የፈለፈላቸውና ያሰለጠናቸው የሽብር ምሽጎች መፍረስ አለባቸው። ኦነግ ሽኔ ሌላው መፍረስ ያለበት ድርጅት ነው።
ጠቅላይ ሚንስትር ዶር ዐብይ አህመድ ሥልጣን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ በተከታታይ የተካሄደውን አስቡት። ህወሓት የዘርፈውን ይዞ መቀሌ መሸገ። ከመሸገ በኋላ በተከታታይ ያካሄደው እልቂትን ነው። የውክልና ጦርነት አካሂዷል። እያካሄደ ነው። ወርቃማ የሆኑት እነ ዶር አምባቸው መኮነን መስዋእት ሆነዋል። ከጀርባ ሆኖ የእንሱን እልቂት፤ በተከታታይ የዐማራውንና የኢትዮጵያ ተዋህዶ እምነት ተከታዮችን እልቂት ያካሄደው ሽብርተኛ ኃይል ህወሓት ነው።
ህወሓትና ኦነግ ሽኔ ሲፈራርሱ አብሮ የሚፈርሰው ሽብርተኝነት ነው። በወለጋ፤ በቤኒ ሻንጉል ጉሙዝ፤ በጉራ ፈርዳና በሌሎች አካባቢዎች ዐማራውንና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችን ኢላማ ያደረጉ ኃይሎች ሁሉ ለመጨረሻ ጊዜ መወገድ አለባቸው። በተጨማሪ፤ ለእልቂት መሰረት የሆኑት ተቋማት መለወጥ አለባቸው (The root causes {institutional and structural} must be overhauled).
እየቀበርን ከማልቀስ ወደ መሰረታዊ ለውጥ እንሸጋገር።
ለዐማራው ሕዝብ ተከታታይ እልቂትና ብሶት ዋናው ተጠያቂ ማነው? የእልቂቱን መረብ የዘረጋውና ሕገ መንግሥታዊ ቅርጽ የመሰረተለት ማነው? ወጣቱን ትውልድ የዐማራውን ሕዝብ በጅምላ “ነፍጠኛ፤ ቀማኛ፤ ወራሪ፤ ትምክህተኛ፤ ቅኝ ገዢ” ብሎ እንዲጠላ ኢላማ (targeting it for psychological and physical assaults) እንዲሆን ያስተማረው፤ ያሰለጠነውና ያመቻቸው ማነው?
በመጀመሪያ ደረጃ ትህነግ/ህወሓት ነው። ግን ብቻውን አይደለም። ሆዳም ዐማራዎች የሚጫወቱትን ሚና መርሳት የለበንም። በተጨማሪ፤ የዐማራው እልቂት ተባባሪ ሆኖ በኦሮምያ ክልል እጅግ የሚዘገንን፤ ከእንስሳ በታች የወረደ፤ በሶርያ፤ በሊቢያ፤ በሶማልያና በሌሎች አገሮች በኣማጽያንና በኃይማኖት ጽንፈኞች እንደ ተደረገው ሁሉ፤ በኢትዮጵያም በተደጋጋሚ ህጻናትን፤ ነፈሰ ጡሮችን፤ አባቶችን፤ ሽማግሌዎችን የጨፈጨፈው ኦነግ ሽኔ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት እነዚህን ሁለት አጥፊ ድርጅቶች በስማቸው ቢጠራቸው አግባብ ነበረው። አመጸኞች/ሽብርተኞች ብሎ ይለያቸው (The Government of Ethiopia must designate the TPLF and OLF Shine as terrorist organizations).
ምን ብሎ ብሎ ይሰይማቸው? በሚለው ላይ በአንድ ቋንቋ መናገር አለብን። ልድገመው፤ ትህነግ/ህወሓትና ኦነግ ሽኔ አመጸኛ ወይንም አሸባሪ ድርጅቶች ተብለው መጠራት አለባቸው። በመጀመሪያ ደረጃ ይህን ስም በፓርላማ ውይይት አድርጎ በሕግ ማጽደቅ ያለበት የኢትዮጵያ መንግሥት ነው። ከዚያ በኋላ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ለተባበሩት መንግሥታትና ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ኦፊሻል ደብዳቤ ጽፎ እነዚህ ድርጅቶች በፈጸሟቸው ጭፍጨፋዎች፤ ውንብድና፤ ሌብነት ወዘተ መረጃ አያይዞ አመጸኛ ወይንም አሸባሪ ድርጅቶች ስለሆኑ መሪዎቻቸውና አባሎቻቸው በየተኛውም ዓለም በወንጀል እንደሚፈለጉ ማሳወቅ ያስፈልጋል።
በተጨማሪ፤ በዲያስፖራው ሆነው እነዚህን ድርጅቶች በመረጃ፤ በሜድያ፤ በገንዘብና በሌላ የሚደግፉ ሁሉ በተባባሪነት እንደሚጠየቁ ማሳወቅ ተገቢ ነው።
እነዚህ ድርጅቶች የቀን ጅቦች ብቻ ሳይሆን ከሃዲዎችም ናቸው።
ህወሓት የሚለይበት አስኳል ጉዳይ አለ። ይኼውም በመቀሌ የተመሸገው አመራር ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያን ክዷታል፤ ለጥቃት አጋልጦታል። በስሙ እየነገደ ዝነኛውንና አገር ወዳዱን የትግራይን ሕዝብ ዝቅ አድርጎታል፤ አዋርዶታል። ለድህነትና ለስደት አጋልጦታል። በሰላምና በፍቅር ከሌሎቹ ኢትዮጵያዊያን ጋር ተጋምዶ የጋራ ጠሎቶቹን፤ ድህነትን፤ ኋላ ቀርነትን፤ ስደትን፤ የውጭ እርዳታ ጥገኝነትን ለመቅረፍ የሚችልበትን ተፈጥሯዊ አቅሙን አዳክሞታል።
እኔ ህወሓት ልክ እንደ ተገነጠለ አካል፤ ምርጫ አካሄድኩ ሲል፤ በተደጋጋሚ “የፌደራሊስት ኃይሎች ተሰብሰቡ” እያለ፤ የሽግግር መንግሥት እንመስርት፤ መንግሥት የለም ወዘተ ብሎ ሲፎክር እብድነት ነው ብየ ነበር። ራሱና ለራሱ የሆነ በዘውግና በቋንቋ ተወቃቅሮ ልዩነቶችን ያጠናከረ ሕገ መንግሥትና የክልል አስተዳደር መስርቶ ሃያ ሰባት ዓመት በበላይነት ከገዛና ከመዘበረ በኋላ ሕዝብ አልፈልግህም ሲለው ምን አደረገ? አሻፈረኝ ብሎ መቀሌ መሸገ። ሲመሽግ ኪሱን ሞልቶ ነው። በመጻህፍቶቸና በብዙ ትንተናዎች እናዳሳየሁት ሁሉ፤ ህወሓት በዝቅተኛ ደረጃ ሰላሳ ቢሊየን ዶላር ሰርቋል፤ አሽሽቷል።
ወደ ሥልጣን ለመመለስ የሚፈልገውም ለሁለት ምክንያቶች ነው፤ አንደኛ የፖለቲካ የበላይነቱን ለመያዝና የወረሳቸውንን መሬቶችና ንብረቶች ደህንነት ዋስትና ለማጠናከር፤ ሁለተኛ፤ በለመደው መንግገድ ድርጅታዊ ምዝበራ ለማካሄድ። ሁለቱ አይነጣጠሉም።
ይህ ምኞት የማይሳካ መሆኑን ከተረዳ በኋላ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይበቀል” እንዲሉ በመከረኛው በዐማራው ሕዝብ ላይ የተቀነባበረ እልቂት እንዲካሄድ አደረገ። አመች ሁኔታ እየፈጠረ ከአጋሩ ከግብጽ መንግሥት ጋር፤ በአገር ውስጥ ደግሞ ከኦነግ ሽኔና ከጀሃዲስቶች ጋር የሴረኛነት ስራውን አገር አቀፍ በሆነ ደርጃ አካሄድ። ግብፅና ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ ላይ የጦፈ የዲፕሎማቲክ ውይይት ሲያካሂዱ፤ የህወሓት የሳይበር ዓለም ጽንፈኞች ግድቡ ከሚሰራ ግብፅ “ቦምብ ብታደርገው” እንመርጣለን ይሉ እንደ ነበር አስታውሳለሁ። ገና ትራምፕ ይህን ከማለታቸው በፊት። ከዚህ የበለጠ ከሃዲነት ሊኖር አይችልም።
ህወሓት የትግራይ ሕዝብ ወንድምና እህት በሆነው በዐማራውና በሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ትራምፕ ግብፅን ደግፈው ከተናገሩ በኋላ ለምን ጦርነት አወጀ? ጦርነቱ የሚያስከትለውን እልቂት ለምን ፈለገው? ለማን ጥቅም? ይህን መመለስ ያለበት የትግራይ ሕዝብ ነው። በጦርነቱ ምክንያት ለሚሞቱት ወገኖቻችንና ለሚወድመው ግዙፍ ኃብት በሃላፌንት ተጠያቂ መሆን ያለበት የህወሓት አመራርና ደጋፊዎቹ ናችው።
ኢትዮጵያ እየደማች ልትቀጥል አትችልም።
ህወሓት ጦርነት የጀመረው የትግራይና ሌሎች ክልሎች በአንበጣ መንጋ በተጎዱበት ወቅት ነው። የሰሜን እዝ ከትግራይ ሕዝብ ጎን ቁሞ አንበጣውን ተከላክሏል። የህወሓትን አረመኔነት በሌላም መስፈርት ላስቀምጠው። ዛሬ ድሃው የትግራይና ሌላው ገበሬ ምርቱን የሚሰበስብበት ጊዜ ነው። ህወሓት ወደ ጦርነት ሲሸጋገር አብሮ እንዲወድም የሚያደርገው ምርቱን ጭምር ነው።
ህወሓት ከሃዲ መሆኑን በድርጊት አሳይቷል። እኔን የሚያስጨንቀኝ፤ ይህንን ከሃዲነትና አጥፊነት እያየና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ህወሓትና አጋሮቹ ከሃዲዎችና ባንዳዎች ናቸው እያለ፤ አንዳንድ የዐማራው አክቲቪስት ነን ባዮች፤ የመከላከያ ኃይሉን መተቸት ራሱ ተባባሪነትና ውክልናን ያሳያል። በወለጋ ላይ የተካሄደው የዐማራ እልቂት የሽብር ግንባሩ ቅንብርና ድርጊት ነው።
የትግራይን ሕዝብ፤ በተለይ ወጣቱን ትውልድ የምመክረው የጥፋቱ ግንባር ቅንጅት አጋር መሆኑን እንዲያቆም ነው። በዲያስፖራው ያለው የህወሓትና የኦነግ ሽኔ ኃይሎች ደጋፊ በጋራ የሚያደርጉትን አወግዛለሁ። ከዚህ የበለጠ ክኅደትና ውርደት በኢትዮጵያ ታሪካ ታይቶና ተሰምቶ አያውቅም። ይህን ክህደትና ባንዳነት ልንቋቋመው የምንችለው የችግሩ አጋር በመሆን አይደለም። የኢትዮጵያን ሕዝብ፤ የመከላከያውን ኃይል በመደገፍ ብቻ ነው። ኢትዮጵያ ስትኖር ብቻ ነው የትግራይና ሌላው ኢትዮጵያዊ እንደ ልቡ ለመንቀሳቀስ የሚችለው፤ ተክብሮ ለመኖርና ለመስራት የሚችለው። ህወሓት የጀመረው ጦርነት ያሳርራል። የሚያሳፍረው ኢላማ ለሆነው ለዐማራው ሕዝብ ብቻ አይደለም። በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነነት ለምናምነው ሁሉ ነው።
ከርጦርነቱ ጋር አብሮ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው አስቸኳይ እርምጃ የዐማራው ክልል፤ የትግራይ አገር ወዳዶችና የፌደራል ባለሥልጣናት ጠብ ጫሪዎቹን ከተደበቁበት መንጥረው አውጥተው ለፍርድ ማቅረብ ነው። የትግራይ ክልልና ሕዝብ ከአሁን በኋላ የከሃዲዎቹና የነፍስ ገዳዮቹ ምሽግ መሆን የለበትም። በኦሮምያ ክልልም ተመሳሳይ እርምጃ መወሰድ አለበት።
ህወሓት ጭንቀት ሲገጥመው ያለ የሌለውን ኃይል፤ አጋሮቹ ጋር ሆኖ ወደ ዘረፋ፤ የእርስ በእርስ እልቂት እንደሚሰማራ አምናለሁ። በተለይ ምሽግ ወደ አደረገው ወደ ቤኒ-ሻምጉል ጉሙዝ፤ ወደ ጋምቤላ፤ ወደ ደቡብ ክልልና ወደ ኦሮምያ የሽምቅና ሌላ ጥቃቶችን ለማካሄድ ይሞክራል። ስለዚህ፤ የደህንነትና የመከላከያ ተቋማት ሕዝቡን ደጀን በማድረግ እንቅስቃሴውን ሰፊ ጉዳትና እልቂት ከመፈጸሙ በፊት ክትትል ማድረግ ይኖርባቸዋል።
ጀግናው የመከላከያ ኃይል በትግራይ የመሸገውን ኃይል ዋና መንቀሳቀሻ መሳሪያና የሰረቀውን የገንዘብ ምሽግ መስበር መጀመሩ እጅግ የሚያኮራ ድርጊት ነው። ህወሓት የለመደው ያለውን የመሳሪያና የገንዘብ አቅም ሌላው ቀርቶ በዋሻዎች መቅበር እንደሆነ አምናለሁ። ለዚህ የሚጠቅመው አገር ወዳድ የትግራይ ተወላጆችን አጋርነት መፈለግና መጠቀም ነው።
ህወሓትና ኦነግ ሽኔ ንጹሃን ኢትዮጵያዊያንን፤ በተለይ ዐማራውንና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችን ጨፍጭፈዋል። ኃብትና ንብረት አውድመዋል። እነዚህ ድርጅቶች ኢትዮጵያን ክደዋታል። ስለዚህ፤ የሁለቱም ሽብርተኛ ድርጅቶች መሪዎች በእልቂትና የእርስ በእርስ ጦረነት በመቀስቀስ ለፍርድ እንዲቀርቡ መደረግ አለበት (The leaders of the TPLF and OLA must be brought to a court of law for war crimes and for genocide).
ህወሓት፤ ኦነግ ሽኔና ጅሃዲስቶች የዐማራውን ሕዝብና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችን የሚጨፈጭፍበት እድልና አጋጣሚ ሁሉ ከስሩ መመንጠር አለበት። እነዚህ አመጸኞች/አሸባሪዎች ጠንቅ የፈጠሩት ለንጹሁ የዐማራው ሕዝብ ብቻ አይደለም። አገራችን ደም ሲፈስባትና እኛ በየቀኑ ወንድም/ እህታችን ስንቀብርና ስናለቅስ አብረን እያደከምናት የሄደነው ኢትዮጵያን ነው። አመጸኞቹ ህወሓትና ኦነግ ሽኔ እልቂቶቹን ዛሬ ሻሸመኔ፤ ነገ ጉራ ፈርዳ፤ ከነገ ወዲያ ደግሞ ቢቤኒ ሻንጉል ጉሙዝ ወዘተ እያሉ የመከላከያ ኃይሉን አቅም ሲያባክኑት አብሮ የሚባክነው የኢትዮጵያ ደህንነት፤ ግዛታዊ አንድነትና ሉዐላዊነት ነው።
ጦርነት ወደ እድል ይቀየር!
የሚካሄደው የማያስፈልግ ጦርነት እድል ፈጥሯል። ከሆነ አይቀር ይህ እድል መባከን የለበትም። ጥቂቶቹን ልጥቀስ፤
- ወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ጠለምት፤ ሰቲት ሁመራ፤ ራያና አዜቦ ወደ ዐማራው ክልል መቀላቀል አለባቸው፤
- እነዚህ አካባቢዎች ልዩ የባጀትና የባለሞያዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው በሁሉም ዘርፎች እንዲለሙ መደረግ አለባቸው፤
- እነዚህን አካባቢዎች የሚመሩት ግለሰቦች በነዋሪዎቹ የተመረጡና ሃላፊነታቸው ለነዋሪው ሕዝብ እንዲሆን አሳስባለሁ፤
- የፌደራሉ መንግሥትና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ክሕዝብ ጋር ተመካክረው በዘውግ የተዋቀረው ሕገ መንግሥትና የክልል አስተዳደር በባለሞያዎች በተጠና የኢትዮጵያዊነትን ዜግነትን፤ አብሮነትን ፍትሃዊ ልማትን በሚያጠናክር ዘመናዊ ሕገ መንትሥትና አስተዳደር አማራጭ እንዲተካ እድሉን መጠቀም ያስፈልጋል፤
- ይህ አዲስ ሕገ መንግሥትና የአስተዳደር ቅርጽ በአካባቢው የሚኖሩትን ልዩ ሉዩ የዘውግና የእምነት አባላት፤ የትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ጨምሮ በጋራ የሚኖሩበትን አዲስ ምእራፍ ይከፍታል የሚል እምነት አለኝ፤
- ከእርስ በእርስ ጦርነት ልንማር የምንችለው አስኳል ጉዳይ፤ ለዚህ እልቂትና የእርስ በእርስ ጦርነት አመቻች ሁኔታ የፈጠረው ምን አይነት የአገዛዝና የአስተዳደር ስርዓት ነው? ብየ ራሴን እጠይቃለሁ። ጣያቄ ማቅረብ በቂ አይደለም። አማራጩንም መጠቆም አስፈላጊ ነው።
ህወሓት በኢትዮጵያ የቀበረው ቦምብ መፈታት አለበት።
ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ሕዝብ እንደ አንድ ሰብሳቢ አድርጎ የሚያዛምድ ወይንም የጋራ መለያ መርህ የላቸውም። ሕገ መንግሥቱ የተከለው ቦምብ አፍራሽ ነው። የአገር ፍቅርን መለያ መስፈርት አድርጌ ላቅርብ። አገራችን ኢትዮጵያን እናፈቅራለን ካልን አብረን ማፍቀር ያለብን ሁሉንም ዜጎቿን ነው። ኢትዮጵያን ለይተን፤ ማለትም፤ መሬቷን ብቻ እናፈቅራለን ካልን፤ መሬቷንማ ግብጾችም ያፈቅሯታል፤ የዐባይን ወንዝ ለመቆጣጠር ስለሚፈልጉ እላለሁ። ህወሓትም ሆነ ኦነግ ሽኔ ኢትዮጵያን ካፈቀረ አብሮ ማፍቀር ያለበት ዐማራውን፤ ጉራጌውን፤ ሶማሌውን፤ ኦሮሞውን፤ ወዘተ ጭምር ነው። በተመሳሳይ ኦሮሞው ኢትዮጵያን አፈቅራለሁ ካለ አብሮ ማፍቀርና መቀበል ያለበት ዐማራውን፤ ጉራጌውን፤ ትግሬውን፤ ሶማሌውን፤ ወላይታውን ወዘተ ጭምር ነው። ታሪክ የሚያስተምረን ሃቅ አለ። ይኼውም፤ ህወሓትም ለመሬት እንጅ ለሕዝብ ፍቅር ደንታ የለውም። በተመሳሳይ፤ ኦነግ-ሽኔም የተከተለው መርህ ተመሳሳይ ነው፤ የሥልጣን፤ የኃብት፤ የመሬት ተተኪነት። ለተተኪነት ዋና መሳሪያ የሆነው ራሱ ሕገ መንግሥቱና የክልሉ ስርዐት ነው።
ልንክደው የማንችለው ሃቅ እንዲህ የሚል ነው። ሕገ መንግሥቱ የፈጠረው ግጭጦቶችን፤ ተተኪነትን፤ ስግብግብነትን፤ ሌብነትን፤ ከሃዲነትን፤ ጨካኝነትን፤ አንዱን ከሌላው በዘውግና በኃይማኖት ለይቶ ማጥቃትንና ማጠርን፤ አለመተማመንን፤ ቀማኛነትን፤ ውንብድናን፤ ሴረኛነትን ወዘተ። እናትን ካዝለችው ልጇ ጋር የሚገድል ወንበዴ ምን ይባላል? ድርጊቱ ከከብትነት በምን ይለያል?
የኢትዮጵያን ሕዝብ እርስ በእርሱ የሚያናክስ፤ በእርጋታና በሰላም እንዳይኖሩ፤ የሕግ የበላይነት እንዳይሰርጽ የሚያደርግ አገዛዝ ነው። በእኔ ግምገማና እምነት፤ ሕገ መንግሥቱና የክልል አስተዳደር ስርዓቱ እስካልተቀየሩ ድረስ የዐማራው ሰቆቃና ጭፍጨፋ በምንም አያቆምም። በተከታታይ የሆኑትን ልጥቀስ። ህወሓት በወልቃይት ጠገዴ፤ ጠለምት፤ ሰቲት ሁመራ፤ ራያና አዜቦ፤ ዋልድባ ወዘተ የፈጸማቸው የእልቂትና የንብረት ውድመት ወንጀሎች ወደፊት ወንጀለኞቹን፤ ሽብርተኞቹን በሃላፊነት፤ በሕግ የሚያስከስሱ ናቸው። ብዙ ሽህ ዐማራዎች ተጨፍጭፈዋል፤ እንዲሰደዱ ተደርገዋል፤ በምትካቸው ህወሓት ትግሬዎችን በመሬቶቻቸው ላይ አስፍረውበታል። ይህን የመሬት ነጠቃ፤ የዐማራው ሕዝብ ተቀብሎት አያውቅም።
ኦነግ ሺኔም በተከታታይ የፈጸማቸው ወንጀሎች ከህወሓት አያንሱም። ህወሕት የጨፈጨፈው በድብቅ ነው። ኦነግ ሽኔ ግን በይፋ ነው፤ ተባባሪዎችን እንዲመሰክሩለት እና ደጀን እንዲሆኑት እያደረገ።
ህወሓት “የፌደራሊስት ኃይሎችን” ለመሰብሰብ በሚል ስልት የሚታገለው ለምንድን ነው? ብለን መጠየቅ አለብን። በሃያ ሰባት የጭካኔ ዓመታት አምባገነናዊ አስተዳደር ስኬታማ ለማድረግ ያልቻለውን ግቡን ስኬታማ ለማድረግ መሆኑን ላሰምርበት እፈልጋለሁ። ያ የጭካኔ ዘመን ተመልሶ እንዲመጣ የሚፈልግ ግለሰብና ስብስብ ሞኝና ተላላ ነው። ትእቢተኛው ቡድን ግን ጭካኔውን እንደ ጉብዝና ነው ያየው፤ የሚዋረደውም ለዚህ ነው።
በተጨማሪ፤ በጉራ ፈርዳ፤ በተደጋጋሚ በኦሮምያ ክልል፤ በደቡብ ክልል፤ በቤኒ-ሻንጉል ጉሙዝ፤ በወለጋ፤ በአዲስ አበባና በአካባቢዋ ወዘተ እጅግ የሚዘገንኑ ዐማራውንና የኦሮቶዶክስ እምነት ተከታዮችን እልቂት ትኩረት ያደረጉ እልቂቶች ተካሂደዋል። ሁኔታው ባለፉት ሁለት ዓመታት እንደተባባሰ ዓለም አቀፍ ተቋማት ዘግበውታል። ለምሳሌ፤ ዶር ግሬገሪ ስታንቶን፤ የጀኖሳይድ ዋች መስራችና ሊቀ መንበር በዐባይ ሜድያ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፤ በመላው ኦሮምያ የተካሄደው ዘውግና ኃይማኖት ተኮር እልቂት ጀኖሳይድ መሆኑን አስምረውበታል።
ጃዋር ሞሃመድ በጽንፈኛነት፤ በአመፀኛነት የተከሰሰበት ዋና ምክንያትም ለዚህ ነው። ይህን ጭካኔ የሚያካሂዱ ጨካኞች ለምን አመጸኞች/አሸባሪዎች ናቸው ተብለው እንዳልተሰየሙ አልገባኝም።
ለመጀመሪያ ጊዜ ይህ ቃል በፓርላማ የተሰማው በወለጋ የተካሄደው እልቂት በይፋ በዓለም ከተሰራጨ በኋላ ነው። ግን፤ ወደ ፖልሲ መቀየርና የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም መሆን አለበት።
የሰኔውን ጭፍጨፋ ተከትሎ ብዙ መሰረታዊ ጥያቄዎች ለማቅረብ ይቻላል። አንዱ፤ በወለጋና በቤን-ሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተካሄደው የሚዘገንን በዐማራውና በአገው ዘውግ ላይ ትኩረት ያደረገው እልቂት ዋና ኢላማውና ግቡ ምንድን ነው? ከጀርባ ሆኖ እልቂቱንና እንደሚባለው ከሆነ በብዙ ሽህ የሚገመቱ ወገኖቻችን እንዲፈናቀሉ በመረጃ፤ በገንዘብ፤ በትጥቅና በሌላ ድጋፍ የሰጠው ኃይል ማነው? በእኔ እምነት ህወሓትና ግብፅ አሉበት። ይህ ሁኔታ በድንገት የተከሰተ ካልሆነ ለምን ቸል ተባለ? የወለጋ ሃላፊዎች፤ የቤኒ-ሻንጉልና የዐማራው ክልል፤ የፌደራሉ መንግሥት ሃላፊዎች ምን ይሰሩ ነበር? ስንት ንጹሃን እስኪጨፈጨፉ እንጠብቃለን?
የፌደራልና የዐማራው ክልል ባለሥልጣናት ወደ ቤን-ሻንጉል ጉሙዝ ሄደው ያደረጉትን ጉብኝት፤ ዘገባና ምክር እየተቀበልኩና እውቅና እየሰጠሁ፤ በተለይ ይህ ሁኔታ በምንም እንዳይደገም እያሳሰብኩ፤ ግን ይህ አካባቢ በተደጋጋሚ ለምን የእልቂት መናኸሪያ ሆነ? የሚለውን ለመገምገም እፈልጋለሁ።
የቤኒ–ሻንጉል ጉሙዝ ስትራጅካዊ ሚና ምንድን ነው?
ቤኒ-ሻንጉል ጉሙዝ ለምን መረባሪቢያና የእልቂት መናኸሪያ ሆነ? የሚለው ብዙ ጥናትና ምርምር ይጠይቃል። ባጭሩ ላቅርበው። ይህ ክልል የታላቁ የህዳሴ ግድብና የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ነው። ግብጽ አይኖቿን ካሰረፈችባቸው መካከል አንዱ ነው። ህወሓት መተከልን ከጎጃም ነጥሎ አዲስ ክልል ሲመሰርት የጸነሰው ስልት፤ አካባቢውን ከትግራይ ጋር ለማቀራረብ መሆኑን ላሰምርበት እፈልጋለሁ። ህወሓትን የተካው የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝደንት ሽመልስ አብዲሳ 37 በመቶው የቤኒ-ሻንጉል ጉሙዝ ነዋሪ ኦሮሞ ተናጋሪ ነው ሲል ምን ማለቱ ነው? መልእክቱን ማጤን አስፈላጊ ነው። ተስፋፊው ህወሓት የተመኘውን አካባቢ ሽመልስም ይፈልገዋል ቢባል ከእውነቱ የራቀ አይደለም። ለሽመልስ የምመክረው ለኢትዮጵያ የሚያዋጣት መተካካትና የመሬት ነጠቃ አይደለም። ከህወሓት አጥፊነት መማር ያስፈልጋል። የሚያዋጣው መንገድ በኢትዮጵያዊነት የዜግነት መብት ላይ የተመሰረተ የልማት መንገድ ብቻ ነው።
ቤኒ-ሻንጉል ጉሙዝ የተፈጥሮ ሀብት ባለፀጋነት ካረጋገጡት አካባቢዎች መካከል አንዱ ነው። ይህ ሰው ሰራሽ ክልል እምነበረድ፤ ብዙ ሊመረት የሚችል የወርቅ ኃብት፤ ለግንባታ ስራዎች ግብዓት የሚሆኑ ማእድኖች፤ የኃይል ማመንጫ ክምችት፤ ተጨማሪ የእሌክትሪክና የመስኖ ግድቦች፤ የጽሃይና የነፋስ ኃይል ማከማቻዎች ወዘተ እንደሚገኝበት ይታመናል። ለዚህ ነው፤ ህወሓትና አጋሮቹ ሕገ መንግሥቱን ሆነ ብለው ሲመሰርቱና ክልሎቹን ሲያዋቅሩ ለአካባቢው ሕዝብ አስበው ሳይሆን፤ በታሪኩ የተለያዩ ዘውጎች በመቻቻል የሚኖሩበትን የኢትዮጵያ አካል፤ ለምና የተፈጥሮ ኃብት ባለፀጋ የሆነውን አካባቢ፤ መተከልን ከጎጃም ክፍለ ሃገር በመንጠቅ አጠቃለው አዲስ ክልል የመሰረቱት። እንደገና ለማስታወሰ፤ የዐማራውን ሕዝብ ጉረሮ ለማነቅ ቁልፍ የሆኑትን መሬቶች መንጠቅ አስፈላጊ ሆኖ የማየው በዚህ ምክንያትም ጭምር ነው።
ተንኮለኛውን ህወሓትን ከታላቁ ከትግራይ ሕዝብ መለየት ተገቢ ነው።
በመግቢያው ላይ እንዳስቀመጥኩት፤ ነፍሱን ይማረውና ዶር አምባቸው መኮንን ወደ አሜሪካ መጥቶ በነበረበት ወቅት ትንሽ ላናግርህ ብየ አንድ ምክር ሰጥቸው ነበር። ህወሕት የዐማራውን ክልል ሰርጎ ገብቶበታል በሚል ጀምሬ፤ እኔ ግን የምመክርህ ትኩረትህ ከህወሃት ላይ እንዲሆን አይደል። ሌላውን ሁሉ ነገር ወደ ጎን ትተህ የትግራይ ሕዝብ ከዐማራው ሕዝብ ጋር እንዲወያይ አድርግ የሚል ነበር። በተጨማሪ፤ የዐማራውና የኦሮሞው ሕዝብም ጠንካራ ግንኙነት እንዲያደርጉ አምናለሁ በሚል ሹክ ብየው ነበር። እሱም “ይኼ ጥሩ ምክር ነው። አደርገዋለሁ። አንተም ወደ አገርህ መጥተህ እንወያይ አደራ” ብሎኝ ነበር።
የህወሓትን መሰሪነትና አጥፊነት በጥልቀት ካሰቡበት መሪዎች መካከል የመጀመሪያውን ደረጃ እሱ ይዞት ነበር። ምን ይሆናል ሳይታሰብ ይህን ቅንና አስተዋይ መሪ አጥተናል። ይህን ያስታወሰኝና ፎቶግራፉን በዚህ ሰንድ ላይ ለማስገባት የፈለግሁት ዛሬ የወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ጠለምት፤ ሰቲት ሁመራ፤ ራያና አዜቦ፤ ጉዳይ ተስፋ የሚሰጥ ሁኔታ ስላየሁ ነው።
የማይረሳው ዶር አምባቸው መኮነን
መተከል ለምን ከዐማራው ክልል ተነጠቀ?
ህወሓት የዐማራውን ሕዝብ ያስጨነቀውና ያሳደደው በጎንደርና በወሎ ብቻ አይደለም። መተከልን ከዐማራው ክልል ነጥቆ ወደ ቤን ሻንጉል ጉሙዝ በማጠቃለሉም ጭምር ነው።
ይህ አዲስ ሰው ሰራሽ ክልል ሌሎችም የተፈጥሮ ኃብቶች አሉት። የፀሐይና የነፋስ ኃይል በስፋት መኖራቸው ስትራተጂክ መሆኑን ያጠናክራል። ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ ሥልጣን ከመያዙ በፊት በዚህ አካባቢ የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪዎችን በውስጡ ይዛ ነዋሪዎቹን በሰላምና በአብሮነት ተከባብረው ይኖሩባት የነበረች አካባቢ ናት የእልቂት አውድማ የሆነችው። እልቂቱን በተከታታይ የሚያካሂዱት ነዋሪዎቹ ናቸው ለማለት አልችልም። ከጀርባ ሆነው ተንኮሉን ከሚሰሩት ላይ ትኩረት ቢደረግ ይሻላል። ዋናው ተንኮለኛና አጥፊ ህወሕት ነው። ሌላው ደግሞ ኦነግ ሽኔ ነው። በዚህ ክልልና በወለጋ የተፈጸመው ወንጀል ሽብርተኞች የፈጸሙት ወንጀል መሆኑን መቀበል ያስፈልጋል። አንዱ በትግራይ ሕዝብ ስም፤ ሌላው በኦርሞ ሕዝብ ስም። አቋማቸው ግን አንድ ነው። የሚፈጽሙት ወንጀል እየተናበቡ ነው። ለወደፊቱ ነዋሪው ሕዝብ እንዳይጠቃ ከተፈለገ የነዋሪውን አቅም፤ የመከላከል ኃይሉን ማጎልመስ ወሳኝ ነው። ይህን ለማድረግ የሚችለው የፌደራሉ መንግሥት ነው። የክልል ባለሥልጣናት ፈተናውን አላለፉም። ተንኮለኛው ማነው? የሚለው መመለስ አለበት።
ሽብርተኞች ወንጀለኞች ናቸው፤ ጨፍጫፊዎችና አገር አጥፊዎች።
አካባቢው የሽብርተኞች ምሽግ መሆኑን ከኢትዮጵያ የህልውናና የብሄራዊ ጥቅም አንጻር ላቅርበው። ይህ አካባቢ የሕዳሴ ግድብ በሚገኝበትና ግብጽ፤ ህወሓት፤ ኦነግ ሽኔና ሌሎች ጸረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች ትኩረት የሰጡት መሆኑ እየታወቀ የፌደራል መንግሥት መከላከያ ኃይል የት ነበር? ክልሉ ከዐማራው ክልል አጠገብ ስለሆነ የዐማራው ክልል ዐመራርስ ምን አቋም አሳይቷል? በተለይ ትኩረት ሊሰጥበት የሚገባው የፖሊሲ ጥያቄ፤ የክልሉ አመራር የችግሩ አካል መሆኑ ነው። መሪዎቹ በሙስና፤ በጥላቻና በሌላ የተበከሉ ከሆኑ ችግሩ መፍትሄ አይኖረውም። አመራሩ በየደረጃው መጽዳት አለበት። የማያሻማ ጠንካራ እርምጃ ከተወሰደ ሰላም ሊሰፍን ይችላል።
እነዚህ ባለሥልጣናት ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ከተካሄዱት የሚዘገንኑ እልቂቶችና መፈናቀሎች ምን ትምህርት ቀስመው ነበር? ለነዚህ ጥያቄዎች እኔ መልስ የለኝም፤ ግን አስቡባቸው።
በዐማራው ስም የሚደረጉ አንድ አንድ ክስተቶች ይገርሙኛል። ለምሳሌ የምጠቅሰው ትዝብት አለ። በመተከል አካባቢ የተካሄደው እልቂት ከመፈጸሙ በፊት የተከሰተው ሁኔታም የሚከተለው ነው። የኦሮሞው ክልል ፕሬዝደንት አቶ ሺመልስ አብዲሳ አብዛኛውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ያስገረመውና ያስደነገጠው ንግግር በታሪክ ሲጠቀስ ይኖራል። “የዐማራውን መንግሥት ዐባይን ተሻግረን ሰባብረነዋል…ያመታት ስራችን ውስጥ ለውስጥ እየሰራን ነው…ብልፅግናን የመሰረትነው እኛው ነን…ለመግዛትና ለመጨቆንም በሚያመች መንገድ እየሰራን ነው…” ወዘተ፤ ወዘተ፤ ወዘተ
የአንድ ክልል መሪ እንደዚህ ብሎ ለመናገር ያስቻለው ሁኔታ ምንድን ነው? “ዐባይን ተሻግሮ” ምን ሰራ? በማን ላይ? እውነት የብልጽግና ፓርቲ የበላይ ኦህዴድ ነው? “ለመግዛትና ለመጨቆን በሚያመች መንገድ እየሰራን ነው…በቤኒ-ሻንጉል ጉሙዝ የኦሮሞው ቋንቋ ተናጋሪው 37 በመቶ ሆኗል…አማርኛ” እየቆረቆዘ ነው ሲል የሚገዛውና የሚጨቆነው ማነው? በማን? ሽመልስና ፓርቲው ምን አይነት ኢትዮጵያን ለመመስረት እየሞከሩ ነው? ይህ የተረኝነት ሂደት ነው። መሰረታዊውን ችግር የሚያባብስ፤ ከድጡ ወደ ማጡ የሚያመራ።
በእኔ እምነት ይህ ብሂል ለኢትዮጵያና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፈተናና አደጋ ፈጣሪ ነው። ለግብጾች ግን እልል የሚያስብል ነው። የዐባይ ወንዝ የተደበቀ “ቦምብ” የያዘ ነው የሚለው ሲያነጋግር ቆይቷል። በዐማራውና በአገው ሕዝብ ላይ የተካሄደው እልቂት ቦምቡ እየፈነዳ መሆኑን ያመለክታል። የችግሩ እምብርት ግን የተጸነሰው ኢህአዴግ ሥልጣን ሲይዝና አገሪቱን በክልል ሲሸነሽናት ነው።
የመተከል ወረዳ ከጎጃም ክፍለ ሃገር ተነጥቆ ወደ ቤኒ-ሻንጉል ጉሙዝ እንዲቀላቀል የተደረገበት ምስጢር ግልፅ እየሆነ ሄዷል። ህወሓት የፈለገው የጎንደርን መሬቶች ነጥቆ “ከታላቋ ትግራይ” ጋር ካዋቀረ በኋላ ወደ ምእራብ ከሱዳን ጋር ወሰኑን ለመቀየስና ወደ ደቡብ ደግሞ ለራሱ ክልል የሚጠቅም አካባቢ ለመፍጠር ነበር። አልተሳካለትም። ህወሓት ከሥልጣን ከወረደና በመቀሌ ከመሸገ በኋላ ተተኪው ኦህዴድ የኦሮሞን ክልል ለማስፋፋት ባለው እቅድ መሰረት ቤኒ-ሻንጉል ጉምዝን ለመጠቅለል ያሰበ ይመስላል የሚሉ ታዛቢዎች አሉ። ለማስታወስ ያህል፤ በቀለ ገርባ የወሎን መሬት የኦሮሞ አካል ነው ብሎ ነበር። ሸመልስ አብዲሳ ደግሞ 37 በመቶ የሚሆነው የቤኒ-ሻንጉል ጉሙዝ ነዋሪ ኦሮሞ ነው ብሏል። እነዚህ ሁሉ ሲከሰቱ በክልሉ ለሚኖረው ለዐማራውና ለአገው መብትና ህልውና ማን ተከራክሯል? የሚያዋጣው አማራጭ በዜግነት መብት ተጠቅሞ መኖር ብቻ ነው።
ባጭሩ ለማለት የምችለው፤ ለም መሬቶችና ወንዞች ስልት በተሞላበት ደረጃ ከዐማራው እጅ ሲነጠቁ እየተመለከትኩ መሆኑን ነው። ለዚህ ነው፤ የአማራውን ጉረሮ ለማነቅ የሚደረግ እቅድ አለ የምለው። በዚህም በዚያም ስገመገም የማያሻማው ሃቅ ዐማራው መፈናፈኛ እያጣ መሆኑ ነው። መሬትና ንብረት የሌለው ሕዝብ ጉረሮው ታነቀ ማለት ነው።
አንድ መሰረታዊና ያልገባኝ ጥያቄ አለና ላቅርበው። ከላይ ያነሳኋቸውን መሰረታዊ ጥያቄዎች በመጠየቅ ፋንታ የዐማራው ብልጽግና ፓርቲ ያደረገው ምንድን ነው? ወደሚለው ልመለስና ባጭሩ ላቅርበው።
እኔን የገረመኝና ያስደነገጠኝ፤ አቶ ሽመልስ አብዲሳ የተናገረው ሁሉ ለኢትዮጵያና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የማይመጥን መሆኑ ነው። ይህ ግለሰብ፤ ቢያንስ ቢያንስ መላውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ ጠይቆ ከስልጣኑ ይውረድ በማለት ፋንታ የዐማራው ብልፅግና ፓርቲ አለቃዎች ያደረጉት ወደ ባህር ዳር ጋብዘው “ካባ” አለበሱት። ካባ የክብርና የዝና ምልክት ነው። ይህን ካባ ሲያለብሱት የሰጡት ምልክት ምንድን ነው?
በእኔ እምነት “አይዞህ፤ ያደረግኸውን እንጋራለን፤ ከአንተ ጋር ነን፤ ቀጥልበት፤ አንተ የኛ ጀግና ነሕ” ማለታቸው አይደለም? ካልሆነ የዐማራ ብልጽግና መሪዎች ለዐማራው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ምክንያታቸውን በይፋ ይግለጹ።
የዚህ የካባ ሽልማት አሉታዊ ውጤት ምንድን ነው?
አንዱና ሊያሳስበን የሚገባው ውጤት በዐማራው ሕዝብ ላይ ለሚካሄደው እልቂት ግብዓት ሊሆን ይችላል የሚለው ነው። ሌላው፤ የዐማራው ሕዝብ በተደጋጋሚ ከሚኖርበት መሬትና ንብረት እንዲወገድ ሲደረግ ለሞት፤ ለስደትና ለድህነት መዳረጉ የማይቀር መሆኑ ነው። ለምሳሌ፤ በቤኒ-ሻንጉል ጉሙዝ የኦሮሞው ተናጋሪ እየጨመረ ሄዷል የሚለው ብሂል፤ የአማራው ግን እየቀነሰ ሊሄድ ይገባል የሚል ምልክት ሊሰጥ ይችላል። ይህ የዜሮ ድምር (Zero sum game) ሂደት ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ሕዝብ አያዋጣም። ሌላውን ሁሉ ችላ ብንለው ግብጾች የሚፈልጉትን ያገኛሉ የሚለውን እናስተናግደው። ግብጾች ከሁሉ በላይ የሚፈልጉት አገር ወዳድ ሕዝብን ማጋጨት፤ ቢቻል እርስ በእርስ እንዲጨራረስ ማድረግ ነው። ይህን ስል አገሩን የሚወድ ዐማራው ብቻ ነው ማለቴ አለመሆኑን አስመርበታለሁ። አገር ወዳድ ለእኔ ትርጉም የሚሆንበትን መስፈርት ከላይ አቅርቤዋለሁ።
ልክ በዘመነ ህወሓት ይደረግ እንደ ነበረው አንዱ ኃይል “አሳዳጅ፤ ሌላው ደግሞ ተሰዳጅ” የሆነባት ኢትዮጵያ ራሷን የምታጋልጠው ለጠላቶቿ መሆኑ ግልጽ ነው። ይህ ደግሞ የተለመደ እየሆነ ነው። ህወሓት መራሹ ኦነግ ሽኔ የዐማራ ህጻናትን፤ የዐማራ ወጣት ሴቶችን፤ አናቶችን ወዘተ በተደጋጋሚ ደፍሯል፤ አዋርዷል፤ ገድሏል፤ አፍኗል፤ ከቀያቸው አባሯል። “ነፍጠኛና ትምክህተኛ” የሚለው የህወሓትና የብአዴን ብሂል ልክ እንደ ወንጀለኛነት የተለመደ ሆኖ ስር እንዲሰድ ወይንም እንዲሰርፅ ተደርጓል። ጃዋር እልቂት አካሂዶበታል። ታዲያ በዚህ ሁኔታ ዐማራው የት እንዲኖር ይፈለጋል፤ ጨረቃ ላይ?
ወደ ኋላ ሄጀ ትዝ የሚለኝ፤ ዋለልኝ መኮንን የግራ ክንፉንና የጣልያን ፋሽት ምሁራንን ትርክት ሸምድዶና ያለ አግባብ ተጠቅሞ ለብአዴን፤ ለህወሓት/ትህነግ፤ ለኦነግና ለሌሎች የዘውግ የፖለቲካ ፓርቲዎች አገር አፍራሽና ሕዝብን ከሕዝብ የሚያናክስ ቅርስና ውርስ አበርክቶ አልፏል። ከእነዚህ ሁሉ ጉዳቱን ያባባሰው የኃይል ቅንጅትና ለብዙ ንጽህ ኢትዮጵያዊያን፤ በተለይ ለዐማራው ዘውግ አባላት እልቂትና የግዙፍ ኃብት ውድመትና ብክነት በሃላፊነት መጠየቅ ያለበት ጀግናውን፤ አገር ወዳዱንና ኩሩውን የዐማራውን ሕዝብ በተከታታይ ያስጨፈጨፈው ህወሓትና የፈለፈላቸው የዘውግ ፓርቲዎች ናቸው። የዐማራውን ሕዝብ “ነፍጠኛና ትምክህተኛ” ብሎ በፕሮግራሙ የወነጀለው ሁሉ ለእልቂቱ ተጠያቂ ነው።
ለዐማራው ሰቆቃ ዋናው ተጠያቂ ማን ነው? ብሎ መጠየቁ አግባብ አለው።
የዐማራውን ተከታታይ እልቂት በተናጠል አላየውም። ይህ የሚዘገንን ዘውግንና ኃይማኖትን ትኲረት ያደረገ እልቂትና ውድመት (Genocide and the destruction of huge investments) በተለይ የዐማራው ተከታታይ እልቂትና ጉረሮ መታነቅ፤ ዙሮ ዙሮ ኢትዮጵያን ልክ እንደ ዩጎስላቭያ እንደሚያደርጋት ማሰብ የእያንዳንዱ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት የሚያምን ግለሰብና ስብስብ ሃላፊነት ነው። ሁኔታው ባለበት ከቀጠለ ግን፤ ቢያንስ ቢያንስ ኢትዮጵያ እንደ ሶርያ፤ የመን፤ ደቡብ ሱዳን፤ ሶማልያ መሆኗ አይቀርም፤ ሆናለችም የሚሉ እየበዙ ሄደዋል።
በዐማራው ሕዝብ ላይ በተደጋጋሚ ሲካሄድ የቆየው እልቂት፤ የስነ ልቦና ጦርነትና ጥቃት፤ የተቋማት፤ የኃብትና የንብረት ውድመት፤ መፈናቀል ወዘተ የሚያስታውሰኝ በግራኝ ሞሃመድ ወረራ ዓመታት የተካሄደውን የሃገራችን የኢትዮጵያን መፈራሰስ ታሪክ ነው። ይህን በሚመለከት ወጣቱ የታሪክ ተመራማሪና ምሁር ሃብታሙ መንግሥቴ ተገኝ በቅርቡ ያሳተመው “በረራ፤ ቀዳሚት አዲስ አበባ፤ 1400-1887 ዓ. ም” የሚለው በመረጃዎች የተደገፈ መነበብ ያለበትን መጽሃፍ ነው።
በተጨማሪ፤ መምህር ታየ ቦጋለ “ሱፍ በለበሱ እብዶች የተበከለች ኢትዮጵያን” እንታደጋት ያለውን አስታውሶ፤ የዘውግ የበላይነት፤ ጠባብ ብሄርተኛነት፤ ጽንፈኛነት፤ ሽብርተኛነት፤ የዘውግ ተረኛነት የሚያስከትሉትን አገር አፍራሽ አደጋዎች ለዐማራው ሕዝብ ህልውና ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ቀጣይነት ስንል ቆራጥነት የምናሳይበት ወቅት ዛሬ ነው። ባለፈ እልቂትና ውድመት፤ ባለፈ ድርጊት መጮሃችን ብቻ በቂ አይደለም። ይህንማ እያደረግን መልሰን መተኛታችን ወይንም ማንቀላፋታችን የዓለምን ሕዝብ ትዝብት አስታጋብቶልናል።
በግራኝ ዘመን የሆነው ትምህርት ሊሆነን የሚገባበት መሰረታዊ ምክንያት በዚያ ወቅት የተለያዩ ወረራዎች ተጨማምረውበት ሃያ ስምንት የሚሆኑ ዘውጎች፤ ባህላቸው፤ ማእረጋቸው፤ ታሪካቸው፤ ቋንቋቸውና ሌላው መለያቸው ሁሉ የውሃ ሽታ ሆኗል። ጃዋርና ተከታዮቹም ያካሄዱትና አቅደውት የነበረው የእልቂት ጥሪ ተመሳሳይ ነው። ዛሬ በዐማራው ዘውግ ላይ የሚካሄደው እልቂት ካልቆመ ይህ ዘውግና ኃይማኖት ተኮር እልቂትና የበላይነት ፖለቲካ ማንንም እንደማይምር ማስተዋል ያስፈልጋል።
ጎንደሬው ያሰማው መፈክር፤ “ዐማራን እየገደሉ ኢትዮጵያን መግዛት የከሰረ ፖለቲካ ነው” የሚለው አግባብ አለው፤ ትክክል ነው፤ የሚሰማ ካለ። ዛሬ ይህች ረዢም ታሪክ ያላት፤ ወንድማማችነትን/እህትማማችነትን ፍትህን፤ እውነተኛ እኩልነትንና ዲሞክራሳዊ ስርዓትን ተቀብላ በዘውግ ካድሪዎች ሳይሆን፤ በሞያተኞች የምትተዳደር ሕብረ-ብሄራዊት ኢትዮጵያን ብንመሰርት አገራችን በፍጥነት የበለጸጉ አገሮች ከደረሱበት ደረጃ ላይ ትደርሳለች። ይህ ተስፋ እንዳለ ሆኖ፤ ከፍተኛና አደገኛ ሰው ሰራሽ መሰናክሎች በግልጽ ይታያሉ።
ለማጠቃለል፤ ምክር ብጠየቅ ምን እላለሁ?
ከላይ ያቀርብኳቸው ምክሮችና ሃሳቦች እንዳሉ ሆነው፤ በተጨማሪ የሚከተሉትን እንድናስብባቸው እጠቁማለሁ።
- ዋናውና መሰረታዊው የዐማራው ሕዝብ ፈተና በስሙ የሚነግዱት ግለሰቦች፤ ስብስቦችና ፓርቲዎች የግለሰባዊነት፤ የመንደርተኛነት፤ የጎጠኛነት፤ የሆዳምነት፤ ለመተባበር የሚታየው ንፉግነት፤ የስነ-ምግባርና የሞራል ዝቅተኛነት፤ የማይበገር የፖለቲካ ሆነ የማህበረሰብ ተቋም ለመመስረት መሰናክል መሆናቸውን አስበንበት መፍትሄ እንፈልግ፤ አማራጮች እናቅርብ።
- የዐማራውን ህልውና ጥያቄና መተኪያ የሌላትን ኢትዮጵያን እንደ ሃገር ከማስቀጠል እና ኢትዮጵያዊነትን እንደ የዜግነት መለያዎች በጋራ ሆኖ ከመታደግ አቅማችን ጋር የተቆራኙ ሆነው አያቸዋለሁ። የዐማራውን ሕዝብ ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያዊነት ለይቸ አላያቸውም። በመላው ኢትዮጵያ የሚኖረውን የዐማራውን ሕዝብ መታደግ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ከመታደግ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳላቸው አሳስባለሁ (The fate of the Amhara is organically linked to the fate of Ethiopia and Ethiopianness).
- የህብረ-ብሄራዊ ፖለቲካ ድርጅት አቅም ግንባታና የመረጃ መለዋወጥ ስራዎች ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው የምንል ሁሉ፤ በጋራ ሆነን የዐማራውን ሕዝብ የህልውና ጥያቄ ነጥለን ለብቻው እንዳናያቸው አደራ እላለሁ። የዐማራው ሕዝብ መሬትና ንብረት ሲነጠቁ የሚያሳየው ክስተት የዐማራው ሕዝብ ጉረሮ መታነቁን (Economic Strangulation) የሚያመለክት የፖለቲካ ውሳኔ መሆኑን በማያሻማ መልኩ አሳይቻለሁ። ይህ ሁኔታ ደግሞ ኢትዮጵያንም እያዳከምናት ነው የሚለውን መሰረታዊ ሃሳብ እንድናስተናግድው አሳስባለሁ። የወልቃይት፤ የጠገዴ፤ የጸለምት፤ የሰቲት ሁመራ፤ የዋልድባ፤ የራያና አዜቦ፤ የመተከል ችግሮች መፈታት ለሰላም፤ ለሕግ የበላይነት፤ ለእርጋታና ለዘላቂ ልማት ወሳኝ ነው።
- ጦርነቱን እንደ አዲስ ምእራፍ አየዋለሁ። በኢትዮጵያ ቀጣይነት እምነት ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ የማህበረሰብ፤ የኃይማኖት፤ የሞያ፤ የሴቶችና የወጣቶች ተቋማትና ስብስቦች የዐማራውን እልቂት በተናጥል ከማየት ይልቅ ለሃገራችን ለኢትዮጵያ የማስቀጠል ወይንም ልክ እንደ ዩጎስላቭያ እስክትሆን ችላ ብሎ ከማዘን ይልቅ የሚታየውን አደጋ አብሮና ተባብሮ የሚታይበት ሁኔታ ባስቸኳይ እንዲፈጠር ጥሪ አደርጋለሁ።
- በዘውግና በቋንቋ የተመሰረተው ሕገ መንግሥትና የክልል አስተዳደር ለዐማራውና ለሌላው ሕዝብ እልቂት፤ መፈናቀል፤ ለአገራችን አለመረጋጋት፤ ለህገወጥ ድርጊቶችና ለውንብድናዎች ተከታታይ መንስኤ መሆኑ በማያሻማ ደረጃ ታይቷል። ይህ ሕገ መንግሥትና የክልል አስተዳደር በባለሞያዎች ተጠንቶ ለኢትዮጵያ ተመጣጣኝ የሚሆን አማራጭ ረቂቅ ሕዝብ እንዲወያይበትና ድምጽ እንዲሰጥበት አደራ እላለሁ። አለያ፤ ምርጫም ቢካሄድ ከመተካካት ውጭ መሰረታዊ ለውጥ አይቻልም። ፍትህ አይኖርም። ልማት በሚፈለገው ደረጃና ፍጥነት ሊካሄድ አይችልም። የዓለም ሕዝብ እየታዘበን፤ ሌሎች ጥቁር አፍሪካዊያን እየናቁን መሄዳቸው አይቀርም። በብሄር፤ ብሄረሰብና ሕዝቦች ሰበብ የተዋቀረው ሕገ መንግሥትና የክልል አስተዳደር ስርአት በህወሓት መራሹ ኢህአዴግ ለ 28 ዓመታት ተሞክሮ አልሰራም። ጥገና ሳይሆን መሰረታዊ ለውጥ አስፈላጊ ነው።
- የኢትዮጵያ 115 ሚሊየን ሕዝብ ችግር “በፌደራሊስትና በአሃዳዊ ኃይሎች” የፖለቲካ ልሂቃን መካከል በሚደረግ የተተኪነት ግብግብና የገመድ ጉተታ ትግል መሆኑ የዓለምን ሕዝብ እያስገረመውና እያስደነገጠው መሆኑን መረዳት አስፈላጊ ነው። እነዚህ የዘውግ ልሂቃን ኃይሎች በሕዝብ ስም ሕዝቡን እያስጨነቁትና እያስገደዱት ነው። ፍትሃዊ ሊሆን የሚችለው ከላይ በተራ ቁጥር አራት ያቀረብኩትን ምክር ማስተናገድ ነው። ስር ነቀል ስር ዓታዊና መዋቅራዊ ለውጥ ይደረግ።
- በዚህ አጋጣሚ ባልደራስና መኢአድ ያካሄዱት የአንድነት ስብበሰባ፤ የፈጠሩት ህብረ-ብሄር ፓርቲና የአንድነት ጥሪ ለሌሎች ተመሳሳይ ፓርቲዎች ፈር ቀዷል። እኔ የምመክረው፤ ኢታዮጵያንና የኢትዮጵያን ሕዝብ ከፊታቸው ላይ ከተደቀነው አደጋ ለመታደግ አስቸኳይ የብሄራዊ መግባባት፤ እውነተኛ የእርቅና የሰላም ውይይት ጥሪ እንዲደረግ አደራ እላለሁ።
- የኢትዮጵያን ችግር ልንፈታው የምንችለው ራሳችን ብቻ ነን። ፈረንጆች አይፈቱልንም። የዐማራውና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ደህንነት ከኢትዮጵያ ደህንነት ጋር የተያያዘ ሆኖ አይቸዋለሁ። ዐማራውንና ሌላውን እየጨፈጨፉ ኢትዮጵያን ለመታደግ አይቻልም።
- በመጨረሻ፤ ህወሓትና ኦነግ ሽኔ የሚያካሂዱትን የእልቂትና አገርን የማፍረስ አጀንዳ መታገል፤ ከአገር ወዳዱና ለአገራችን ከሚሞትላት መከላከያ ኃይል ጋር አብሮ መቆም የወቅቱ ታሪካዊ ግዴታችን ነው። የእነዚህን አመጻዊያን/አሸባሪ ኃይሎች የተቋም፤ የገንዘብ፤ የውጭ ግንኙነት መረብና ሰንሰለት የመስበር ወይንም የመበጣጠስ እድል ተከፍቷል። ይህ እድል እንዳይባክን ከፈለግን፤ እየተናበብን የምንሰራበት ታሪካዊ ወቅት ዛሬ ነው።
የተከበረችና የተባበረች ኢትዮጵያን እንታደጋት!!
Novemberr 5, 202