የሚጠብቀኝ አይተኛም፣ አያንቀላፋም። የሚል ታዋቂ የክርስትያኖች መዝሙር አለ። በዘማሪ ይልማ የተዘመረ። መነሻው የዳዊት መዝሙር ሆኖ አምላኬና ፈጣሪዬ የዘወትር ጠባቂዬ ነው ለማለት የሚዘመር ነው። ከቅርብ አመታት ወዲህ ይህ መዝሙር ተዘውታሪነቱ እየጨመረ መጥቷል። እኔ ግን አዝማቹን ባደመጥኩ ቁጥር ሌላ ሁለት የተለያዩ አንድምታዎች እየሰማሁበት ተቸግሪያለሁ። እነዚህ ሁለቱም አንድምታዎች በመዝሙሩ ላይ የተጠቀሰውን ሰማያዊ ጠባቂ ሳይሆን ምድራዊ ጠባቂን የተመለከቱ ናቸው። ነገሩ እንዲህ ነው።
በግብርና ኑሮ አዝመራ ጠባቂና ጦጣ ጠባቂ አለ። አዝመራ ጠባቂው አዝመራውን ከአደጋ የሚከላከል ለአዝመራው ደህንነት ጥበቃ የሚያደርግ ነው። ጦጣ ጠባቂው ደግሞ ጦጣው ሰብል ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የሚያባርር እና የሚያሳድድ እንጂ ለጦጣው ደህንነት ጥበቃ የሚያደርግ አይደለም። ሁለቱም ግን ጠባቂ ነው ስማቸው።
በኢትዮጵያ ከሺህ ዘመናት በላይ በዘለቀው ሥርዓተ መንግሥት እና የቤተክህነት አስተዳደርና አስተምህሮ ምክንያት በክርስትያኑ ሕብረተሰብ ውስጥ መንግሥትን የማመን እና በመንግሥት ላይ የመታመን በጥልቅ የሰፈነ ከፍተኛ ዝንባሌ አለ። ባለፉት ሃምሳ አመታት በተለይ ግን ይህን አመኔታ የሚመጥን መከታ ክርስትያኑ ሕዝብ አግኝቷል ወይ? የሚለውን ጥያቄ መልስ ሁላችንም እናውቀዋለን። በተቃራኒው መንግሥት የተባለው ሕዝቡ ላይ የተቀናጀና ቀጣይነት ያለው አደጋ የከሠተ ነው። የመንግሥት መገናኛ ብዙኃንም በፋሺስት አምሳል የሐሰትና የፕሮፓጋንዳ ወሬ መናኛ ከሆኑ ዘመናትን አስቆጥረዋል። ይሁን እንጂ ሕዝቡ አሁንም መንግሥት ይጠብቀኛል እና መንግሥት አይዋሽም የሚለውን አመኔታና ዝንባሌ ጨርሶ አልተወም። ስለዚህ መንግሥት እንቅልፍ አጥቶ ይጠብቀኛል የሚል ከረጅም ሀገረ መንግሥትነት የፈለቀ ሥር የሰደደ አመኔታ አለ ማለት ነው። በተዋሕዶ እምነትና ምእመናን ባለፉት ሦስት መንግሥታት የደረሰው ግን ከዚህ አመኔታ በተቃራኒው ነው።
ስለዚህ ዘመናትን በተሻገረው የተዋሕዶ ፍጅት ምክንያት “የሚጠብቀኝ አይተኛም” የሚለው ተደራቢ ሁለተኛ ስሜት የሚነበብበት ሆኗል። ይህ ንባብ የሚገለጸው ደግሞ መንግሥትን ከአደጋ ጠባቂ አድርጎ በመውሰድ አይደለም። ይልቁንም ሕዝቡ ይጠብቀኛል ብሎ የሚያስበውን የመንግሥት አካል እንደ ድመት ሕዝቡን ደግሞ እንደ ዓይጥ በመሳል የሚገለጽ እንጂ። የተዋሕዶ ልጆች ያ እኛን ይጠብቀናል ብለን እምነትና ተስፋ የጣልንበት ምድራዊ መንግሥት ያለ እንቅልፍ ሲያሳድደን ኖሯል። እውነትም አይተኛም። አንድ ስለ ድመት ሰምታ የማታውቅ ግልገል ዓይጥ ድመትን አይታ ለእናቷ ሄዳ ስለውበቱ አጫወተቻት የሚል የልጆች ተረት አለ። የተዋሕዶ እምነት ተከታይ ወላጆች ደግሞ ልክ እንደ ዓይጧ ስለ ውርዬ አልነገሩንም። ስለዚህ ውርዬን ስናይ አቤት ጢሙ ማማሩ፣ ዓይኑማ ቁልጭ ቁልጭ ሲል፣ አወይ ጽዳቱ፣ ያረማመዱማ ግርማ ሞገስ እያልን እናደንቃለን። ድምጹንም እናደንቃለን። አጥፊያችን እንደሆነ አልለየንምና። የጥፋት ድምጹን የለዩትም ጥቂቶች ነቅተው እንዳይሸሹ የድመት ድምጹን በነቡቺዬ ቋንቋ ስለለወጠው ቡፍ! ቡፍ! ሲል ሀገር ሰላም ብለው ሲወጡ እያነቀ ይፈጃቸዋል።
የሚጠብቀን አይተኛም። እስኪ ለውጡ ከመጣ በጄኖሳይዳዊ ጭፍጨፋ ሳይሆን የተናጠል ጥቃት በሚመስል የተፈጁትን የተዋሕዶ ልጆች እንመልከት፡፡ ከታዋቂ ሰዎች ግድያዎች ብዙኃኑ የተዋሕዶ ልጆች የተቀጠፉበት ነው።
የኦርቶዶክስ ታዋቂዎች ግድያ በአቢይ አህመድ ኢትዮጵያ፤ ከፊል ዝርዝር ለናሙና
ስም | አሟማት* | ሥልጣን/ ሞያ | የተቀበሩበት ሥፍራ | |
1. | ሌተናል ኮሎኔል አስፋው አያሌው | በሽመልስ አብዲሳ ዘቦች ተደብድቦ የተገደለ** | የመከላከያ ደህንነት ኃላፊ | ቤ/ክ ዳንግላ፣ ጎጃም |
2. | ኢንጂነር ስመኘው | አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በጥይት ተመትቶ የተገደለ*** | የሕዳሴው ግድብ ዋና መሐንዲስ | ቤ/ክ አዲስ አበባ |
3. | ሃጫሉ ሁንዴሳ | በኦነግ ነፍሰ ገዳዮች የተገደለ (መንግስት እንዳለው) | ዘፋኝና የኦሮሞ ብሔርተኛ ቀስቃሽ | ኢየሱስ ቤ/ክ አምቦ |
4. | ሰሎሞን ታደሰ | በኦነግ ነፍሰ ገዳዮች የተገደለ (መንግስት እንዳለው) | የቡራዩ ፖሊስ ኮሚሽነር | ቤ/ክ አዲስ አበባ |
5. | ጄነራል አሳምነው ጽጌ | በመንግሥት ወታደሮች የተገደለ | የአማራ የደህንነት እና የልዩ ኃይል ኃላፊ | ቤ/ክ ላሊበላ፣ ወሎ |
6. | ጄኔራል ሰዐረ መኮንን | በመንግሥት ወታደሮች ተገደለ ተብሎ የሚታመን | የመከላከያ ቺፍ ኦፍ ስታፍ | ቤ/ክ መቀሌ፣ ትግራይ |
7. | ዶ/ር አምባቸው መኮንን | በመንግሥት ወታደሮች ተገደለ ተብሎ የሚታመን | የአማራ ክልል ፕሬዚደንት | ቤ/ክ ጋይንት |
8. | ምግባሩ ከበደ | በመንግሥት ወታደሮች ጥይት ቆስሎ የሞተ ተብሎ የሚታመን | የአማራ ክልል አቃቤ ሕግ | ቤ/ክ ጎጃም |
9. | እዘዝ ዋሴ | በመንግሥት ወታደሮች ተገደለ ተብሎ የሚታመን | የአዴፓ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል | ቤ/ክ ጎንደር |
10. | ኮለኔል ገዛኢ አበራ | በመንግሥት ወታደሮች ተገደለ ተብሎ የሚታመን | በጡረታ ላይ የነበረ የመከላከያ ባለሥልጣን | ቤ/ክ ትግራይ |
11. | በአካል አለልኝ | በመንግሥት የጸጥታ አባሎች ተገደለች ተብሎ የሚታመን (በዳንጎቴው ግድያ) | በኢትዮጵያ የዳንጎቴ ዋና ጸሐፊ | ቤ/ክ አዲስ አበባ |
ከ2010 እስከ 2012 የተገደሉ የተዋሕዶ ክርስትያን ባለሥልጣናት/ ታዋቂ ሰዎች ከፊል ዝርዝር
* የትኞቹም ግድያዎች በገለልተኛ አጣሪ ያልተጣሩ የተለያየ ዘገባ የተሰጠባቸው ናቸው። **የሟች ወንድም ለአዲስ ድምጽ ከሰጠው ምስክርነት
*** የፖሊስን አሳፋሪ “ራሱን ነው የገደለው” የሚል ሪፖርት ተራ ዜጎችም፣ ኤክስፐርቶችም አጣጥለውታል
የሞቱ ሰዎችን ዘውግ መግለጽ ተመራጭ ባይሆንም ዘመኑ ነውና ሟቾች የኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግሬ ወይም ውሕድ ማንነት የነበራቸው ሲሆኑ እዚህ ልናሰምርበት የምንፈልገው ሁሉም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች የነበሩ መሆኑን ነው።
ጠ/ሚ ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ባደባባይ ግድያ የተፈጸመባቸውን ከፍተኛ ባለሥልጣናትና ታዋቂ ሰዎች ዝርዝር ስንመለከት ሁሉም ለማለት በሚያስደፍር ደረጃ የተዋሕዶ እምነት ተከታዮች መሆናቸውን እናስተውላለን። ከግድያዎቹ አሳዛኝ ወንጀልነት በተጨማሪ ነገሩን አሳሳቢ የሚያደርገው በኢህአዴግ/ ብልጽግና ከፍተኛ የሥልጣን እርከኖች የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን ቁጥር መጀመሪያውንም እጅግ አናሳ መሆኑን ስንታዘብ ነው። ይህ ኩነት የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን፣ የኢትዮጵያ የሰብኣዊ መብት ድርጅትና የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ተሟጋች ድርጅቶች ጉዳዩን እንዲመረምሩ ያስገድዳል። እነዚህ ግድያዎች እየተፋፋመ የመጣው የኦርቶዶክስ ጄኖሳይድ አካል መሆን አለመሆናቸውን ሊከታተሉ ይገባል። እርግጥ ወቅታዊው የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ዝንባሌ አሳፋሪ ነው። የጥፋቱ ተባባሪ እንጂ ተቆርቋሪ በማያስብላቸው ደረጃ አምኔስቲ ኢንተርናሽናል እና ጄኖሳይድ ዋች የተባሉት ያወጧቸው ሪፖርቶች ኦነግ ጽፎ የሰጣቸው ነው የሚመስሉት። ዞሮ ዞሮ እንዴትና ለምን እንደዚህ ያሉ የታዋቂ የተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ያደባባይ ግድያ ከዚህ በፊት ባልታየ መልኩ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ሁለት አመታት ሰማይ ሊነካ እንደቻለ መጠየቅ የግድ ይላል።
የጣልያንን ሺዎች ካህናት እና የሚሊዮን ምእመናን ጭፍጨፋ ትተን በእኛው ባለሥልጣናት አባ ሃናን በመግደል ሀ ያለው የተዋሕዶ ልጆች ፍጅት፣ ፓትርያርክ ቴዎፍሎስን በማነቅ አቡጊዳ**** ብሎ የኤርትራ የትግራይ የዋልድባ ካህናትን በመጨፍጨፍ ወንጌልን ዘልቆ አሁን አጠቃላይ ምእመናን የመፍጀት መዝሙረ ዳዊትን እየደገመ ይገኛል።
በዚህ ሁለት አመት ብቻ ስንት የተዋሕዶ ልጆች ረገፉ? ከጉሙዝ ጠረፍና ከኦጋዴን ቀበሌዎች አንስቶ መሐል አዲስ አበባ ቤተክርስትያን ውስጥ በጥይት እስከተደፉት ድረስ የንጹሐን ደም አልጎረፈም? ጠባቂያችን ያልናቸው ከአደጋ ጠበቁን? እስኪ በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጉምዝ ዘንድሮ ሰኔ ከገባ የተደረገውን የተዋሕዶ ጄኖሳይድ ብቻ እንመልከት። መከላከያ፣ ልዩ ኃይል፣ ከንቲባ፣ ምንትሴ፣ ጠባቂያችን ብለን የምንወስዳቸው ናቸው? አልተኙም ነው አልተኙልንም የምንለው?
ታድያ “የሚጠብቀኝ አይተኛም” ከሚለው “የሚጠብቀኝ አይተኛልኝም” የሚለው ንባብ ጎልቶ አይሰማበትም?
ለገዢዎቻችን ልቡና እንዲሰጥልን እንጸልይ።
እንደ ዝንጀሮ የሚጠብቀን ሳይሆን እንደ አዝመራ የሚጠብቀን ይስጠን።
****ሀ ሁ ፊደል፣ አቡጊዳ፣ ወንጌል እና መዝሙረ ዳዊት የጥንቱ የቤተክህነት ሥርዓተ ትምህርት የመጀመሪያ ደረጃ ተከታታይ የትምህርት እርከኖች ናቸው።