አዲስ አበባ:- ህወሓት እጅግ መሰሪ የሆነና ኢትዮጵያዊ ያልሆነ፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የቆመ የፖለቲካ ኃይል መሆኑን የራያ ራዩማ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አገዘው ህዳሩ አስታወቁ። በወንጀል ሊጠየቅ፤ ከፖለቲካ ፓርቲነት ሊሰረዝ፤ በአሸባሪነት ሊፈረጅ እንደሚገባም አሳሰቡ፡አቶ አገዘው ህዳሩ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳመለከቱት፣ ህወሓትን እየዘወሩ ያሉ ሐይሎች ከአስተሳሰባቸው ጀምሮ ኢትዮጵያውያን አይደሉም። በኢትዮጵያ ስም መጠቀም እስከቻሉ ድረስ በኢትዮጵያዊነት አብረው መቆየት የሚፈልጉ ናቸው፤ እነሱ መጠቀም እና በስልጣን መቆየት ካልቻሉ ኢትዮጵያን ለእነሱ ስጋት በማትሆን መንገድ መስራትና አፈራርሶ መሄድ ይፈልጋሉ።
ለዚህም የራሳቸውን ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ፣ የሚሊተሪና የፀጥታ አቅም አዳብረው መጠቀም እስከቻሉ ድረስ አብረው ለመቆየት ችግር የለባቸውም ያሉት ሊቀመንበሩ፣ ራሳቸው መጠቀምና ሌላውን በሚፈልጉት መንገድ ማሽከርከር ካልቻሉ ኢትዮጵያን አፍርሰው መልሰው ለእነሱ ስጋት እንዳትሆን አድርገው መሄድ ፍላጎታቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
“ህወሓት ለህዝቡም አይጠቅምም፤ እጅግ መሰሪ የሆነና ኢትዮጵያዊ ያልሆነ፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የቆመ የፖለቲካ ኃይል ነው። ስለዚህ ከዚህ ጋር የሚተባበር ኢትዮጵያዊ መኖር የለበትም ብዬ አምናለሁ። ይሄን የምለውም እኛ ከስር መሰረታቸው ስለምናውቃቸው ነው። ምናልባት ሌላው ህዝብ ግፍና በደሉን ብቻ ነው የሚያየው፤ እኛ ግን አስተሳሰባቸውንም ጭምር እናውቃለን “ብለዋል ።
የትግራይን ህዝብ ጨምሮ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ላይ ሆኖ የነዚህን ሰዎች ህልውናቸውን ማሳጠር እንዳለበት ያመለከቱት አቶ አገዘው፣ ለመላው ህዝባችን የሚጠቅመው አንድነቱ፣ ኢትዮጵያዊነቱ እና የጋራ ተጠቃሚነቱ እንደሆነ አስታውቀዋል።
ከእኩልነትና ከኢትዮጵያ አንድነት የሚገኘው ትርፍ እጅጉን የገዘፈ እንደሆነ በአጽዕኖት የተናገሩት ሊቀመንበሩ፣ ከህወሓት የገንጣይና ነጣይ ባህሪ አንጻር /ምን አይነት ስነልቡና እንደሆነ ባላውቅም/ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ከህወሓት የፖለቲካ ጥቅም አገኛለሁ ብሎ የሚዶልት፤ የሚያሴር የፖለቲካ ሃይል ተግባር በጣም አስገራሚ እንደሆነ አመልክተዋል።
“እነዚህ ሰዎች ባልጠበቁት ሁኔታ ያውም በማይታመን መልኩ በፈጣሪ እርዳታ ከመሃል የኢትዮጵያ ክፍል ተገልለው ወደ አንድ ዳር እንዲሰበሰቡ ሆኗል። እነዚህ ሰዎች ደግሞ መልሰው ስልጣን መያዝ አይችሉም። ከዚህ አንጻር ፍላጎታቸውን ለመፈጸም ብዙ ሞክረዋል። ዙሪያውን ሄደው ኢትዮጵያን ለማመስ ያላደረጉት ጥረት የለም።
ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፤በጋምቤላ፣ በሶማሌ ሁሉ ሞክረዋል፤ በደቡብ አሁንም እየሞከሩ ነው፤ በኦሮሚያም ሙከራ አለ። ››ሲሉ አብራርተዋል።
እነዚህ ሰዎች ተፈጥሮ ፍትህን፣ እኩልነትን፣ ነጻነትን፣ ኢትዮጵያዊነትን እና በኢትዮጵያ ማዕቀፍ የፈለገው የፖለቲካም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ችግር ቢኖር፤ በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ፍትሃዊ ያልሆነውን አሰራር እየታገልክ ኢትዮጵያዊነትን እንደ አንድ ምሰሶ ይዘህ ኢትዮጵያን ማቆየት የሚል ህልም እንደሌላቸውም አስታውቀዋል።
ለውጡና የለውጡ ሀይል የሚያቀነቅነው ከእነሱ አስተሳሰብ በተቃራኒው ነው ያሉት ሊቀመንበሩ፣ ኢትዮጵያዊነትን እንደ አንድ ምሰሶ የያዘ መሆኑን ገልጸዋል። ይህ ሀይል የፈለገው አይነት የፖለቲካ ችግር ቢኖር በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ መፈታት አለበት የሚል አቋም እንዳለው ጠቅሰው፣ እነሱ ግን በልዩነት ላይ የተመሰረተ፣ በብሄር ብሄረሰቦች መካከል ተቃርኖ እንዲኖር ማድረግ ነው። ሌላው ቀርቶ የእነሱ ህልውና የሚረጋገጥ የሚመስላቸው ራሳቸውን የበላይና ሁሉን ነገር አድራጊና ፈጣሪ አድርገው በመመልከት፣ በመሳልና በዛው ልክ በመግለጽ ነው ብለዋል። ይህንንም በአብነት ሲጠቅሱ ጎንደርና ጎጃም እንዲሁም ወሎና ጎንደር የጋራ ነገር የለውም ብለው እንደሚስቡም አመልክተዋል።
“ይልቁንም እኛ ነን አንድ ያደረግነው ብለው ነው የሚያስቡት። ኦሮሞን አንድ ያደረግነው እኛ ነን ብለው ነው የሚያስቡት። ከዚህ በመነሳትም ነው አሁን ላይ እነዚህን አካባቢዎች ለማፈራረስና እንደፈለገን ለመበታተን ምክንያቶች አሉን ብለው በማመን ይሄን ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምረዋል ብለዋል።
በዚህ ደረጃ ኦሮሞን አንድ አድርጋችሁ፤ አማራን አንድ አድርጋችሁ ነው ለስጋት የዳረጋችሁን ብለው የሚወቅሷቸው ኃይሎች እንዳሉም ሊቀመንበሩ ተናግረዋል። ስለዚህ ቀድሞ አስተሳሰባቸው የተመሰረተው በማህበረሰቦች መካከል ተቃርኖ በመፍጠር በሚፈጠር የፖለቲካ ልዩነት የእነርሱን እድሜ ማራዘም እንደሆነም አስታውቀዋል።
“ የትግራይ ህዝብ ገና ለውጡ ከመምጣቱ በፊት በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ እነዚህ ሰዎች ሲሰሩት በነበረው ግፍና በደል ምክንያት ከእነሱ ጋራ በአቻ መንገድ እየታየን በየትኛውም ቦታ የመንቀሳቀስና ሄደን የመስራት ስጋት እየተፈጠረብን ነው የሚል ምሬት ነበረው።
ልጆቻችንንና አገራችንን አጥብበውብናል የሚል አስተሳሰብ በትላልቆቹ ሰዎች ዘንድ ነበረ። ››ያሉት ሊቀመንበሩ፣ አሁንም ቢሆን ህወሓት ለትግራይ ህዝብ እንደማይጠቅም አስታውቀዋል። ይልቁንም የህወሓት ህልውና እየጨመረ በሄደ ቁጥር የትግራይ ህዝብ በህወሓት ዓይን እየታየ የበለጠ ተጎጂ እየሆነ ነው የሚሄደው”ብለዋል።
የትግራይ ህዝብም ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር አንድነቱን አጥብቆ እነሱን መታገል አለበት፤ በእውነተኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኩልም እያየን ያለነው ውጣ ውረድ ሊወገድ፤ አንዳንዶቹም ወደ ህወሓት በመጠጋት ህልውናቸውን ለማቆየት እየሂዱበት ያለው መንገድ ሊታረሙ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ከዚህ ባለፈ ህወሓት የተወሰኑ ወራት በቆየ ቁጥር የኢትዮጵያ ፖለቲካ በሽታ እያመረቀዘ እንዲሄድ ማድረግ ነው ያሉት ሊቀመንበሩ፣ ህወሓት በምንም ሃይል በኢትዮጵያውያን አንድነት መጥፋት ያለበት ነቀርሳ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
“ይሄ ብቻም ሳይሆን በወንጀልም ሊጠየቅ፤ ከፖለቲካ ፓርቲነትም መሰረዝ፤ በአሸባሪነትም መፈረጅ ያለበት የፖለቲካ ፓርቲ ነው። ለዚህ አስፈላጊ ከሆነ የመረጃ ማሰባሰብ ስራ ቢሰራ የፈጸሙት ተግባር ከእነዚህ ሰዎች ጋር እንኳን ዜግነት ሰውነት መጋራት ሁሉ እስኪቀፍህ ድረስ ህውሃት እጅግ በጣም የክፉዎች ስብስብ ነው። ››ሲሉም ተናግረዋል። የዚህ ስብስብ መጥፋት ለኢትዮጵያ ህዳሴ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያውያን አንድነትና አብሮነት አንድ ትልቅ ነቀርሳ እንደመንቀል ነው ብለዋል።
አዲስ ዘመን ነሐሴ 26/2012
ወንድወሰን ሽመልስ