September 1, 2020
1 min read

ነውርና ፀያፍ (ዘ-ጌርሣም)

ሰው በሰውነቱ ሊኖር ከተገባው
ከነውርና ፀያፍ ዕርቆ ሲገኝ ነው

ሲሰርቅ መብቱ
ሲገድል ኩራቱ
ሲዋሽ ባህሉ ነው
መኖሪያው እንጀራው

የነውርን ትርጉም ከማንም ካልሰማ
መስታወት ፊት ቆሞ ራሱን ካላማ
ነውር ሆኖት ውድቀት
ፀያፍ በቁም መሞት
አይቀርም ማለፉ እንደተወለደ
ቀን ለቀን አጋልጦት ካልቆየ እንዳበደ

በህብረተሰቡም ስም ይወጣለታል
መፀየፍ የማይችል ነውረኛ ይባላል

ማታለል ሌላውን
ማደንቆር እራስን
ከመሰለው ብልጠት
ብቻውን ይቀራል ስትገለጥ ዕውነት

ፀያፍና ነውርን ጅል ያጌጥበታል
የኋላ የኋላ አንገት ያስደፉታል
ነውርን ተረድቶ መፀየፍ ላልቻለ
አዘቅት ይከተዋል እያንከባለለ

ሰው በዓይን ይፀየፋል
ቆሻሻ በአፍንጫ በሽታ ይለያል
የነገር ትኩሳት በምላስ ይለካል
በጤናማ አዕምሮ ለሚዛን ይቀርባል
ፀያፍ ወይም ነውር መሆኑን ይነግራል

ሰው በሰውነቱ መኖር ከተገባው
ከነውርና ፀያፍ ዕርቆ ሲገኝ ነው

አለብለዚያማ ሰው መባሉ ቀርቶ
ክብርና ሞገሱን በቁም ተቀምቶ
መኖር ሊጀምር ነው እሱም ጫካ ገብቶ
ኑሮውን ተላምዶ ከአውሬ ተጎራብቶ

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop