የኢትዮጵያ የፖለቲካ ተጨባጭ እውነታ ዋልታዎች – አንዱዓለም ተፈራ

አንዱዓለም ተፈራ – eske.meche@yahoo.com

ሐሙስ፣ ነሐሴ ፳፫ ቀን ፳፻፲፩ ዓ. ም. (8/29/2019)

 

በሀገራችን የለውጥ እንቅስቃሴ ከተጀመረ ወዲህ፤ የለውጡ የፖለቲካ ሂደት ግልጥ የሆነ ቅርጽና ምንነት ይዞ መውጣት ተቸግሮ ቆይቷል። በአንድ በኩል የለውጡ ባለቤት፣ መሪ ኃይልና ለውጡን ፈላጊው ክፍል፤ በሌላ በኩል ለውጡ የመጣበትና አንዲለወጥ የተፈለገው ክፍል የተዘበራረቀበት ሁኔታ አይሎ ነበር። ይህ የሀገራችን የፖለቲካ ምሕዳር በብዥታ ሞልቶት ነበር። ይሄ ያልጠራ ብዥታ፤ ለውጥ ፈላጊውን ወገን ወደ አንድ ለማሰባሰብና ለውጡን ትርጉም ሠጥቶ ወደፊት ለማስቀጠል አስቸጋሪ አደረገው። በሌላ በኩል ደግሞ፤ ለውጡን የሚቃወመው ክፍል ተለይቶ ወጥቶ፤ በለውጥ ፈላጊውና ለውጡን በሚቃወመው ክፍል ግልጥ መስመር እንዳይኖር አግዶታል። በዚህ ያልጠራ ወቅት፤ በሀገራችን ብዙ ትርጉም የለሽ ፍጅት ተከስቷል። የለውጥ አይቀሬ ሂደት ነው ተብሎ ሊታለፍ የማይገባው ዕልቂት ተካሂዷል። ለረጅም ጊዜ የታመቀው ብሶትና በደል፤ በትክክል መልስ እንዳያገኝ አግዷል። ይልቁንም በብዥታው ምክንያት፤ የለውጡን ፈላጊዎች ሰፈር በማደናበር፤ በለውጥ ፈላጊውና ለውጥ ተቃዋሚው መካከል ሊደረግ የሚገባውን ግብግብ፤ በለውጥ ፈላጊዎች መካከል እንዲሆን በማድረግ፤ ለከፍተኛ ጉዳት ሀገራችንን ዳርጓታል። ባሁኑ ወቅት፤ እስካሁን የቆየው ያልጠራ ብዥታ፤ በሂደት እየበሰለና እየለዬ መጥቷል።

 

ለብዥታው መንስዔ የነበረው፤ ለለውጡ ሂደት የተሠጠው መሽከርከሪያ ጉዳይ ነው። በለውጥ ሂደት፤ ሁለት ጉዳዮች አሉ። አንደኛው ለውጡ ያስፈለገበት ጉዳይ ነው። ሌላው ደግሞ ለውጡ የማያስፈልግበት ጉዳይ ነው። የነዚህ ሁለት ጉዳዮች እውነትነትና ገሀድነት ነው ለውጡን ለውጥ የሚያደርገው። ይህን ጉዳይ ከግለሰቦች ጋር አያይዞ መንዳት፤ ለውጡን ትርጉም ያሣጣዋል። እከሌ ወይን እነእከሌ ስለፈለጉ ለውጡ አልመጣም። የእስካሁኑ ጉዳዮችን አረዳዳችን፤ ለዚህ ብዥታ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርጓል። ግለሰቦች የለውጡ መከፋፈያ ዋልታ አይሆኑም። ግለሰቦች በግል እምነታቸውና ፍላጎታቸው፤ በሥልጣን ላይ ተቀምጦ ከመመራት አኳያ ብቻ ሳይሆን፤ ያዋጣናል አያዋጣንም? ዛሬ ጠንክሬያለሁ ወይንስ ደክሜያለሁ? በሚል የፖለቲካ ስሌት፤ ሊገለባበጡ፣ የተለያዬ ገፅታ ሊያሳዩ ስለሚችሉ፤ በቋሚነት የፖለቲካ ዋልታ ሆነው ሊወሰዱ አይገባም። የዋልታዎቹ መተክላዊ ሥር፤ የፖለቲካው መሽከርከሪያ ተጨባጭ እውነታው ነው። አሁን በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ የሚያሽከረክሩት ዋልታዎች ነጥረው ወጥተዋል። ለውጡ በነበረው ሀቅና ያንን ሀቅ ለመለወጥ በሚፈልገው ወገን መካከል መሆኑ፤ በግልጥ እየታዬ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ስለ አማራ መደራጀት [ ክፍል ፩]

 

የፖለቲካ ሂደቱን ነፋስ ስንመዝነው፤ ባጠቃላይ የለውጡ ምንነት ሃሳብ፤ በፖለቲካው መድረክ ላይ ቦታውን ይዟል። የዚህ ሃሳብ ግልጥነት፤ የፖለቲካ እንቅስቃሴውን ለማወቅ ወሳኝ ነው። ለውጡ የሚሽከረከረው በምን ሂሳብ ነው? የዚህ የለውጥ ኃይል ስብስቡ የት ላይ ነው? ተጠቃሚዎቹ እነማን ናቸው? ለውጡ እንዳይካሄድ የሚለው ሃሳብ ማዕከሉ ምንድን ነው? በዚህ ዙሪያ ያለው ኃይል ስብስቡ የት ላይ ነው? የዚህስ ጉዳይ ተጠቃሚው ክፍል የትኛው ነው? እኒህ አስፈላጊ ጥያቄዎች ናቸው። ለነዚህ ጥያቄዎች የምንሠጣቸው መልሶች፤ ለውጡን ለመረዳት ያስችሉናል።

 

በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ቡድን የሚመራው ክፍል፤ ለውጡ መደረግ የለበትም ብሎ ሽንጡን ገትሮ፤ ለማዕከላዊው መንግሥት ተቋማዊ ተቃርኖ ፈጥሯል። ይህ አካል፤ በፈለገው መንገድ ለሃያ ስድስት ዓመታት ሲገዛ፤ ራሱ ሕግ አርቃቂና ሻሪ፣ ራሱ ሕግ አስፈጻሚና አጉዳይ ነበር። የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይሆን ይህ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ነበር ዋናው የሀገራችን ሕልውና ትንፋሹ! እናም የተካሄደው በሙሉ ለዚህ አካል የተገዛ ነበር። አሁን ይህ አካል መቀሌን ምሽግ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ነው። መሽከርከሪያ መንጠልጠያ

 

ሃሳቡ፤ ሕገ-መንግሥቱ ይከበር። ሕገ-መንግሥቱ ትክክል ነው። ሕገ-መንግሥቱ በትክክለኛ መንገድ ነው የተበጀው። ሕገ-መንግሥቱ ፍትኅ አስከትሏል። የነበረው የአስተዳደር ዘይቤ ትክክለኛ ነው። እየተካሄደ ያለው ለውጥ ሕጋዊ አይደለም። ያን መልሰን ለማንገሥ አንገታችንን እንሠጣለን! ብሏል። የዚህ አባሪ የሆኑ ጽንፈኛ አክራሪዎች፤ እንዲያውም ያለፈው ሥርዓት የጎደለው ነገር አለ! ኢትዮጵያን ሽንሽኖ ወደፊት ጠቅልሎ መሄድ ነበረበት! እስከሚሉት ጽንፈኞች ድረስ በዚሁ ሰፈር ተሰልፈዋል። ይህ ሰፈር፤ የዳበረ መዋቅር አለው። የተጠራቀመ ገንዘብ አለው። ገንዘቡን ተጠቅሞ ሀገራችንን እንዳትራጋ ለማድረግ ሌት ተቀን እየሠራ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  " አእምሮ  የጎደለው  ሰው  ድርጊት ፣  ልክ እንደ  እንስሳ  ነው  ፡፡ የወያኔም አመራሮች ድርጊት እንዲሁ ፡፡ " መኮንን  ሻውል  ወልደጊዮርጊስ

 

በሌላ በኩል ደግሞ፤ የነበረው የፖለቲካ ፍልስፍና፣ የአስተዳደር መመሪያውና በተግባር የታየው ሂደት፤ የሀገራችን ሕልውና አደጋ ላይ የጣለና ዘለቄታዊ ጉዳት ያስከተለ ነው! ይህ መቆም አለበት! የሚለው ክፍል ነው። ይህ ክፍል ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለበትን ለውጥ፤ አሁንም ሕይወቱን ሠጥቶ፤ ለውጡን ወደፊት ለማስኬድ ቆርጦ ተነስቷል። በዚህ ክፍል፤ አለሳልሰን ኢሕአዴግን እንቀይረው ከሚሉት አንስቶ፤ የለም ኢሕአዴግማ ለውጡ የመጣበትና የለውጡ ምክንያትም ስለሆነ፤ እንዳለ መቀየር አለበት! እስከሚለው ጽንፍ ድረስ የተሰለፉበት ይገኛሉ።

 

ነጥረው የወጡ ሁለት የለውጡ እንቅስቃሴ ዋልታዎች መኖራቸው፤ ጠቅላላ የፖለቲካ ሂደቱን ለመረዳት ያስችለናል። ብዙ ዋልታዎች ሲኖሩ፤ ወደፊትም ሆነ ወደኋላ መሄዱ አስቸጋሪ ስለሚሆን፤ ባለንበት መርገጡ ላይ ትዳር እንመሠርታለን። ያን አግብተን፤ መዳከሩን የኔ እንለዋለን። እናም ይሄን ግልጥ እየሆነ የመጣውን የሁለት ዋልታዎች እውነታ ተቀብለን፣ ጎራችንን ለይተን እየተጠቃለልን፣ የለውጡን ሁለት የተለያዩ ሰፈሮች ትርጉም ባለው መንገድ መሳተፍ፤ ለያንዳንዳችን ተገቢ ይሆናል። እኔ የለውጡ ደጋፊ ነኝ። ለውጡ እኔ በምለው ብቻ መንቀሳቀስ አለበት ብዬ፤ የራሴን ትርጉምና መለኪያ ሰቅዬ፤ እንዴት ሲባል ብዬ አልፎክርም። ኢሕአዴግን አለሳልሰን እንቀይረው ከሚሉት አንስቶ፤ የለም ኢሕአዴግ ካልተቀየረ ሞቼ እገኛለሁ አስከሚሉት ድረስ ያለነው ያንድ ወገን ነን። የዚህ ወገን ሕልውና የሚቆመው፤ ማዕከላዊ የለውጡ ምንነትና ለውጡ ሊያስከትል የሚገባው ውጤት ናቸው። በዚህ ላይ ግልጥ የሆነ ስምምነት በማበጀት፤ ጎራችንን አሁን ማጠናከር አለብን። ይህ ወሳኝ ነው። ከዚህ ባነሱ ጉዳዮች ላይ የየራሳችንን ትኩረት ጠምደን፤ ይሄን ዋናውን የለውጥ መሽከርከሪያ ወደኋላ ካልነው፤ አደጋው ገሃድ፤ ውጤቱ አስከፊና ባለቤቶቹም እኛው ነን።

 

ዋሽንግተን ዲሲ ላይ፤ ትግሬዎች ተሰባስበው ለውጡ ለኛ አይደለም፤ እየጎዳን ነው፤ ምን ሲባል አንድ ትግሬ ለእስር ይዳረጋል! ብለው ፎክረዋል። አልፈው ተርፈው አንድ ዓለም አቀፍ አሰባሳቢ ድርጅት አቋቁመው ተነስተዋል። መቀሌ ላይ የስብሰባ ዝግጅት አድርገው፤ ለውጡን ለመዋጋት ተማምለዋል። በዚህ ቦታ ጽንፈኛ የኦሮሞ አክራሪ ግለሰቦች ተገኝተዋል። መገኘት ብቻ ሳይሆን፤ የስብሰባውን ማጠንጠኛ ሃሳብ ደግፈው ቆመዋል። ይህ ቡድን ሀገራችንን አደጋ ላይ እንድትወድቅ ተግቶ እየሠራ ነው። መቀሌ ውስጥ ተቀምጠው፤ የትግራይ አስተዳደር ፈልጌ አጣኋቸው በሚል የማፌዝ መልስ፤ የፌዴራሉን ትዕዛዝ አላስፈጸመም። በሌሎች አካባቢዎች ግጭቶች እንዲኖሩ፣ ገንዘብ እየረጨ ነው። በዐማራና በኦሮሞ፣ በኦሮሞና በሶማሌ፣ በሲዳማና በወላይታ እንዲሁም በሌሎች ኢትዮጵያዊያን መካከል ስምምነት እንዳይኖር የቻለውን ሁሉ እያደረገ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  እግር መሳም፤ የጭራቅ አሕመድ እግር መዘርጠጫ ዘዴ

 

እኒህ ሁለት የለውጡ ዋልታዎች፤ በውስጣቸው ብዙ የየራሳቸውን ግቦችና የእንቅስቃሴ መንገዶች ያነገቱ ንዑስ ክፍሎች አሏቸው። እኒህን በሚቀጥለው የዚህ ጽሑፍ ተከታይ ክፍል አቀርባቸዋለሁ። እዚህ ላይ በሁለቱ አውራ ዋልታዎች ላይ እናተኩር። በኢሕአዴግ የሥልጣን ርከን ውስጥ የነበረው ለውጥ ፈላጊው ክፍል የያዘው ሃሳብና የኢትዮጵያ ሕዝብ የያዘው የለውጥ ሃሳብ፤ ተቀራራቢ እንጂ አንድ አይደለም። በተቀራራቢነቱ አኳያ፤ በአንድ ጎራ መሰለፍ ይችላሉ፤ ችለዋልም። ሁለተኛውን ክፍል እቀጥልበታለሁ።

Share