ያ ስምንተኛው ሺ ሳይደርስ ሳይመጣ፣
ሕዝብ ቆሞ እያየ ከዘራ እሳት በላ!
ራሱ ተቃጥሎ ሲባል ሰው ያሞቃል፣
እሳቱን አጥፍቶ በብርድ ሕዝብን ግድል፡፡
እንደ ሻማ በሪ ብርሃን ሲለው ሰው፣
ከዘራ ጨለማ ዳፍንት ሆኖ አረፈው፡፡
ተድሮም ከዘራ ጠማማ ቆልማማ፣
ቀጥ ብሎ እማይሄድ አንገቱን የደፋ፡፡
ወዶ ገብ ዘብ ሆኖ ለአብዮት ጥበቃ፣
ለወግ ያበቃውን ያማረ ሕዝብ ከዳ!
ታቻምና በወኔ ሲፎክር ዋለና፣
እግሩን ሽቅብ ሰቅሎ ሃይ ሎጋው አለና፣
ዘፈኑን ዜማውን ዛሬ ቀየረና፣
ሽመሉን ጨንገሩን ስብስብ አረገና፣
“ዳንሱን አስተካክል!” አለ አሽከር ከዘራ!
”ከዘራ አትመኑ”ን አልሰማ ያለ ሰው፣
ተእጁ ሲያፈተልክ እውነቱን ተረዳው፡፡
የሕዝብ ወዝ መጦ ስንት ትከሻ መልጦ፣
ተአብዮት እጅ ገባ ተማረጉ ወርዶ፡፡
ስትጓዝ የኖርከው ከዘራውን አምነህ፣
ተጅህ አልገኝ ሲል ዛሬ ምንድን ዋጠህ?
ስንቱን ሶታ ወጣት እየቆለመመ፣
በእሳት ወስጥ ከዘራ ሲማግደው ኖረ፡፡
ያን ሁሉ ሾተላ በረመጥ አቃጥሎ፣
አቃጣዩ እንዳይነድ ባስነሳው ቃጠሎ፣
እሳቱን አጠፋው ለአብዮት አግዞ፡፡
ጉደኛው ከዘራ ይሉኝታውን ጥሎ፣
ሲጎተት ይውላል ላንዳጅ ምርኩዝ ሆኖ!
ብንመክር ብንዘክር ጭራሽ አልሰማኻን፣
ከዘራ እርካብ እንጅ እግር አይሆን ብለን፡፡
ትናንትና ጪልፋ ወጣት መቆልመሚያ፣
ዛሬ እግር ማረፊያ እርካብ መወጣጫ!
ተዘርዝሮ አያልቅም ኃጥያቱ ከዘራ፡፡
አመሉ ታሪኩ የሚያመለክተው፣
ውሻ በበላበት ልምድ እንደሚለው፣
ከዘራም ለሳበው ምርኩዝ መሆኑን ነው፡፡
እግር ቂጡን ገጥሞ ተአብዮቱ ጋራ፣
ወዝ ተመምጠጥ አልፎ ከዘራ እሳት በላ!
በላይነህ አባተ ([email protected])
ሰኔ ሁለት ሺህ አስራ አንድ ዓ.ም.