April 1, 2017
30 mins read

ለሕዝብና ለሀገር፣ ፍቅር እና ክብር ያለው ትውልድ ለመቅረጽ (ከይገርማል)

የሀገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት ስራ መስራት የሚጀመረው ከቤተሰብ ነው። ወላጆች ልጆቻቸው በጥሩ ሥነምግባር ተኮትኩተው እንዲያድጉ ቀዳሚውን ኃላፊነት ይወስዳሉ። ፈላስፋው “ሕጻን ልጅ ከሰጣችሁኝ በፈለግሁት መንገድ ቀርጨ አሳያችኋለሁ” እንዳለው የሰውን ልጅ ባህሪ በሚፈልጉት መንገድ ለመቅረጽ የሚቀለው በሕጻንነት ስለሆነ በቤተሰብ ደረጃ ልጆችን ገርቶ ለሀገርና ለወገን ራሳቸውን አሳልፈው እንዲሰጡ አድርጎ ማሳደግ ይቻላል። ከቤተሰብ ቀጥሎ ትውልድን የመቅረጽ ሀላፊነት የሚወድቀው በዋናነት በት/ቤቶች ይሆናል። በልጆች አስተዳደግ ላይ የማህበረሰቡና የመንግሥት ድርሻም ግዙፍ ነው። በወላጆች ተኮትኩተው በት/ቤት ዳብረው የሚወጡት ወጣቶች ችግር ፈጣሪ ሳይሆኑ ችግር ፈቺ እንደሚሆኑ አምነን በዚያ ላይ አተኩረን መስራት ያስፈልጋል። ሀገራችን በኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ፣ ፖለቲካዊ ዕድገታቸው በሞዴልነት ከምናያቸው ሀገሮች ተርታ እንድትሰለፍ ከተፈለገ የወደፊት ተስፋወቻችንን ከሕጻንነታቸው ጀምሮ ለሀላፊነት የሚበቁ፣ ለፈጠራ የሚተጉ፣ በባህሪያቸው የተገሩ እንዲሆኑ አድርገን ኮትኩተን ማሳደግ ይኖርብናል።

በአጼ ኃ/ሥላሴ ዘመነ-መንግሥት የግብረገብ ትምህርት በአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች ይሰጥ ነበር። ሕፃናት ገና በለጋ ዕድሜያቸው፣ የወደፊቱን የህይወት አቅጣጫቸውን መልክ ለማስያዝ ሲባል፣ በቤተሰብና በማህበረሰብ ዘንድ የሚኖራቸውን ተሳትፎና የሚጠበቅባቸውን ግዴታ በማስጨበጥ በሞራል የተገነቡ የሕዝብ አገልጋዮች ሆነው እንዲቀረጹ ይደረግ ነበር። በዚህም ምክንያት ደርግ ከመምጣቱ በፊት ሕዝባችን ለሀይማኖት እና ለሞራል ትልቅ ከበሬታ ነበረው። ሀገርን መውደድ፣ ለሰዎች ፍቅርና ክብር መስጠት፣ ታላቅን ማክበር፣ ጾም መጾም፣ የሀይማኖት በአላትን ማክበር፣ የተቸገሩትን መርዳት፣ ባህልን መጠበቅና ማበልጸግ የዜጎች የህሊና ግዴታ ሆኖ አስከብሮን አከባብሮን ኖሯል።

ደርግ ከመጣ በኋላ የግብረገብ ትምህርት ከካሪኩለም ተፋቀ። በሶሻሊዝም አስተምህሮ “ሀይማኖት የገዥው መደብ ስልጣን ማስጠበቂያ መሣሪያ ነው” በሚል አማኞችን ከሀይማኖታቸው እና ከእምነታቸው ለማራቅ ብዙ አፍራሽ ተግባር ተፈጸመ። በሰበብ አስባቡ አለመስራት ወደኋላ ለመቅረታችን እንደምክንያት ተጠቅሶ ሰንበትን ጨምሮ የሀይማኖት በአላት እንዳይከበሩ ቁጥጥር በማድረግ የፈሪሀ-እግዚአብሄርን ልጓም አውልቆ በምትኩ ስርአተአልበኝነትን ተከለ። “ፈረንጆች ያደጉት ቀን ሌሊት ሳይሉ፣ በአላትን እናክብር ብለው እጅ እግራቸውን አጣጥፈው ሳይቀመጡ በመስራታቸው ነው” ተብሎ ተሰበከ። (የሚገርመው ግን ፈረንጆች የሚያከብሯቸው በርካታ በአላት ያሏቸው መሆኑ ነው። በጸሀያማው የሀምሌና የነሀሴ ወራት ብዙወች የተለያዩ አካባቢወችን ለመጎብኘት፣ በባህር ዳርቻወች ላይ ለመዝናናት ራቅ ብለው ይሄዳሉ። በጸደይም፣ በክረምትም፣ በጥቢያቸውም የእረፍት ጊዜ አላቸው። የአዲስ አመት መለወጫ፣ ብሄራዊ ቀን፣ ፋሲካ፣ ሱቆች ሳይቀር ተዘግተው ይከበራሉ። ቅዳሜና እሁድ የእረፍት ቀናት ናቸው። ሱቆች የሚከፈቱት ከረፋድ ላይ ነው። ያም ሆኖ ስራቸውን ሳይለግሙ በጥራት ስለሚሰሩ፣ ሕዝባቸውን በሀቅ ለማገልገል፣ ሀገራቸው በዕድገት ጎዳና እንድትገሰግስ ለማገዝ በቁርጠኝነት ስለሚደክሙ ከራሳቸው አልፈው ለሁሉም የሰው ልጆች የሚጠቅም ውጤት አስመዝግበዋል። ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን የሚወዱ ሆነው በመቀረጻቸው፣ የማይሰራን መንግሥት አውርዶ በአዲስ መተካት የሚያስችል ስርአት በመዘርጋታቸው አሁን ካሉበት ደረጃ ለመድረስ በቅተዋል። ሲሰሩ አቅደው ነው፤ ዕቅዳቸውን ለማሳካት ጎትጓች አያስፈልጋቸውም። አስከፊውን የአየር ጸባይ እንኳ በክፉ አይጠሩም። ተፈጥሮ የለገሰቻቸውን ጸጋ እንደሚመች አድርገው የሚጠቀሙ በመሆናቸው “የልብስ እንጅ የአየር ፀባይ መጥፎ የለውም” በማለት በአለባበስ ብርድና ሙቀትን መከላከል እንደሚቻል በማስተማር ፈተናውን ወደመልካም ዕድል ቀይረውታል። መጥፎውን መጥፎ ነው ከማለት ወጥተው መጥፎውን ወደጥሩ ለመለወጥ የሚተጉ በመሆናቸው አሁን ለደረሱበት ስልጣኔ እንዳበቃቸው መገንዘብ ያስፈልጋል። ችግሮችን እያነሱ ማልቀስ ሳይሆን ለችግሮች መፍትሄ በመፈለግ ሁላችንም አሁን ለምንገኝበት የስልጣኔ ዘመን እንዳበቁን ማወቅና ትምህርት መውሰድ ያስፈልጋል።)

እኛ ኢትዮጵያውያን ከስህተታችን ተምረን እጅ ለእጅ ተያይዘን ለሀገር ግንባታ ከተነሳን፣ የነበረውን አፍርሰን ከአልቦ መጀመራችንን አቁመን ያለውን እያረምን እና እያሳደግን መሄድ ከቻልን ሌሎች ከደረሱበት የስልጣኔ ደረጃ የማንድረስበት ምንም ምክንያት አይኖርም። ምንም እንኳን አሁን እየደበዘዘ ቢሄድም ጠንካራ ሠራተኛነት መታወቂያችን ነው። በእጅጉ የሚማርኩ ባህሎች አሉን፦ የባህል አለባበሳችን፣ የእንግዳ አቀባበላችን፣ ለታላቆች የምንሰጠው አክብሮት፣ የተቸገረን የመርዳት ልምዳችን፣ ይሉኝታና ፈሪሀ እግዚአብሔር ያለን መሆናችን ከሁሉም የሚለዩን የምንኮራባቸው ጨርሰው ያልጠፉ መገለጫወቻችን ናቸው። ድንግል የተፈጥሮ ሐብት፣ ታታሪ ህዝብ፣ መልካም ባህል፣ ቀና አስተዳደር፣ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ካለ በሁሉም መስክ ችግር ለመፍታት የሚችሉ ዜጎችን በትምህርት አንፆ ማውጣት ይቻላል፣ ድህነትን እና ኋላቀርነትን ወደታሪክነት መቀየር ይቻላል።

ችግሩ ግን የተሻለ ነገር ለመፍጠር የሚያስተባብር መንግሥት አለመኖሩ፣ ከዘረኝነት እና ከሙስና የጸዳ አሳታፊ ስርአት አለመዘርጋቱ ነው። ይባስ ብሎ የሀገር ሀላፊነት ተሸክሚያለሁ የሚለው መንግሥት የመጥፎ ነገሮች ምንጭ መሆኑ ችግሩ ስር እንዲሰድ አድርጎታል። እኛም ብንሆን ከመልካም ባህሎቻችን፣ ከጥሩ ሥነምግባሮቻችን ባሻገር ያሉ እጅግ አስቀያሚ ልምዶች አሉን። የራሳችንን በጐ ነገር እንደኋላቀር በማየት መጥፎውን ከጥሩ ሳንለይ የውጭውን ባህል እንዳለ ለመውረስ የምናደርገው ነገር የሚያሳስብ ነው። አሁን አሁንማ ይሉኝታን እንደአላዋቂነት የሚያዩ ተችወች በመበራከታቸው አንዳንዱ ‘ምን ይሉኝን’ እርግፍ አድርጎ ትቶ ከባህል እና ከወጋችን ባፈነገጠ መልኩ ልቡ የፈቀደውን ማድረግና መሆን ቀጥሏል። በወያኔው መንግሥት የሚገርም አስተዳደር፣ ሰው ሰውን እና ሀገሩን እንዲጠላ በመቀስቀሱ እንግዳ አክብሮ የመቀበል ባህላችን በዘረኝነት መንፈስ ተሰርዞ አንድነትን ጠልተን ለልዩነት በመትጋታችን የእኛ አይደሉም የምንላቸው ሰዎች ላይ የማግለል፣ አንዳንዴም የማጥቃት እርምጃ ሲፈጸም ይታያል። የነበረን ሰውን በሰውነቱ የማክበርና “የሰው ሀገር ሰዎች ናቸው” ብለን ለእንግዶቻችን ስንሰጥ በነበረው እንክብካቤ ምትክ ከእኛ ዘር የሚሳቡ አይደሉም በማለት አብረውን ለረጅም ዘመን ተመሳስለው የኖሩትን ሰዎች ሳይቀር መጤወች የሚል ስም በመስጠት በክፉ ዐይን ማየት የጊዜው ፋሽን ሆኗል። ዛሬ ዛሬ ‘ለሰው መድሀኒቱ ሰው ነው’ የሚለው ዕውነት በግልባጩ መተርጎምም፣ መተግበርም ተለምዷል።

በዚያ ላይ በድህነት ይኖር የነበረ ሰው በአንድ በሆነ የህይወት አጋጣሚ ከድሀነት ወደሀብታምነት የሚያሸጋግረው ነገር ሲያገኝ የነበረውን ባህሪ ገፍፎ ጥሎ የእኔ ናቸው በሚላቸው ሰዎች ላይ ሳይቀር በንቀትና በዕብሪት የተሞላ ፍጹም ሌላ ስብዕና መላበስ በሀገራችን በብዙ ሰወች ዘንድ ሲዘወተር ይታያል። የዘመድ ወዳጅ ድጋፍ ተችሯቸው፣ እነሱም ያላቸውን ነገር ሳይሰስቱ ሰጥተው በፍጹም ትህትና ይኖሩ የነበሩ ሰዎች እጅግ ፈታኝና አሳዛኝ ህይወት አሳልፈው ለተሻለ ደረጃ የደረሱላቸው ልጆች በሚቸሯቸው ገንዘብ ወይም ጊዜ በከፈተላቸው ዕድል ተጠቅመው ባገኙት ዕድገት ተመጻድቀው በአኗኗራቸው ስታይል ብቻ ሳይሆን በአነጋገራቸው፣ ባካሄዳቸውና በሁኔታቸው በእጅጉ ተለውጠው ድሀን ሲንቁና ሲጠየፉ ማየት እንግዳ ነገር አይደለም። ከድሀ ቤተሰብ ወጥተው ለጎረቤት ተላልከው፣ ከዘመድ ወዳጅ ድጋፍ አግኝተው፣ ተምረው፣ ሕዝብን በእኩልነትና በትህትና ለማገልገል መሀላ ፈጽመው የሚቀጠሩ የመንግሥት ሠራተኞች የገቡትን ቃል ወደጎን ብለው ሕዝብን ሲያሰቃዩ ማየት ተለምዷል።

በሆስፒታሎች ታካሚወችን ማዋረድ፣ ማንገላታት እንደ አሰራር የተወሰደ የተለመደ ተግባር ነው። ሀኪም ቤት ውስጥ መነጫነጭ ወይም መቆጣት ካለበት ያን የሚያደርገው በሽተኛው መሆን ነበረበት። ማለት በህመም የተጎዳ ሰው ሸክሙን መቋቋም አልችል ቢልና የመንፈስ መረበሽና ማስቸገር ቢታይበት የሚፈረድበት አይሆንም ለማለት ነው። እኛ ሀገር ግን የሚፈራውና የሚረብሸው የህክምና ባለሙያው ነው። በስቃይ የተነሳ እርዱኝ እያለ የሚያቃስት በሽተኛ ቢኖር አስታማሚወችና ታካሚወች ላይ የሚጮሁ፣ አውጥቸ ነው የምጥልህ/ሽ ብለው ያዙን ልቀቁን የሚሉ የህክምና ባለሙያወችን ማስተዋል የዕለት ከዕለት ትዕይንት ነው። በችግር ላይ ላለ በሽተኛ እርዳታ እንዲሰጡ የሚጠየቁ የሌሊት ተረኞች “እንዴት ከእንቅልፋችን ትቀሰቅሱናላችሁ?” ብለው ሲቆጡና ሲያንጓጥጡ አይከብዳቸውም። በምጥ ጊዜ የምትጮህን እናት “እግርሽን ስታነሽ ምንም አላለሽ!” እያሉ ማበሻቀጥ፣ ወረፋ ጥበቃ ላይ ያለ ማንገላታትና ማስፈራራት የተለመደ ክስተት ነው።

ፖሊሶች የህዝቡን ሰላምና ጸጥታ ለማስጠበቅ መቀጠራቸውን ረስተው የሰላማዊ ሰዎችን ክብር መግፈፍና ማሰቃየት ተዋህዷቸዋል።ሲጣሩ “ስማ!” ብለው በንቀት ነው፤ ሲሸኙም “ውጣ!” ብለው በእብሪት ነው። መረጃ ለማግኘት የፈለጋቸውን ቢያደርጉ ጠያቂ የላቸውም። በእኛ ሀገር ፖሊስ የህ/ሰቡን ሰላም እና ጸጥታ ለማስጠበቅ የተመሰረተ ተቋም ሳይሆን ህዝቡን በሰበብ አስባቡ ለማሰቃየት የተመሰረተ ቀጪ ኃይል ይመስላል።

ነጮች የፖሊስ አገልግሎት እንዲኖር ያደረጉት ለህዝባቸው በማሰብ ነው። ፖሊሶች ዋናው አላማቸው ህዝቡን ማገልገል መሆንኑን አውቀው ለዚያ የሚሰሩ ናቸው። የሚሰሩት በህግ የተቀመጠላቸውን ማዕቀፍ ተከትለው ነው። ህጋቸው ደግሞ ዘረኝነትን እና አድሏዊነትን አይቀበልም። ሁሉም የሚሰራበት የስራ ክልል ስላለ የሚያገናኝ ቢኖር ተወያይተው ይፈቱታል እንጅ ከተሰጣቸው ኃላፊነት ያፈነገጠ ነገር ሲከሰት አይቀበሉም። በምንም ይሁን በምን ተታለው ወይም ፈርተው መስራት የሚገባቸውን ነገርም ወደጎን አይገፉትም። ፖሊስ ራሱ ከህግ ያፈነገጠ ስራ ከሰራ ይጠየቅበታል፤ ይቀጣበታል። እዚህ ላይ አንድ የሰማሁትን ነገር ማንሳት እፈልጋለሁ። አንዲት ኢትዮጵያዊት ስደተኛ በሆላንድ ጥገኝነት ትጠይቃለች። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ይህች ሴት ቀደም ብሎ ሌላ ሀገር ጥገኝነት ጠይቆ ወደሚኖረው ባለቤቷ እንድትሄድ እና ጉዳይዋ ባለቤቷ በሚኖርበት ሀገር እንዲታይ ታመለክታለች። ጠበቃዋ የሚመለከተውን ክፍል አሳውቆ ባለቤቷ የሚኖርበትን ሀገር ፈቃድ ይጠይቅና ያስፈቅዳል። በዚህም መሰረት ፖሊስ ሴትዮዋ ትኖርበት ከነበረው የስደተኞች ካምፕ አውጥቶ ለአንድ ቀን እስር ቤት ያስገባታል። ይህንን የሰማው ጠበቃ እንደበረረ ሄዶ “ባለቤቴ ወደምኖርበት ሀገር ሄጀ ጉዳየ በዚያው ሀገር ይታይልኝ ብላ ያመለከተችውን ሴት እንደወንጀለኛ እንዴት ታስሯታላችሁ?” ብሎ ተቆጥቶ ፖሊሶችን ወቅሶ እንደሚያስክሳት ቃል ይገባላታል። በሁኔታው የተደናገጠው ፖሊስ ሴትዮዋን ከእስርቤት አውጥቶ እስክትሄድ ድረስ ወደምትቆይበት ቦታ ይልካታል። ሴትዮዋ ከባለቤቷ ጋር እንደተገናኘች ያላግባብ ለአንድ ቀን በእስር ቤት በማደርሽ 425 ዩሮ (ከ10 000 ብር በላይ) ካሳ ተልኮልሻል ተብላ ገንዘቡን ተቀበለች። ህዝብን ከማንገላታት አልፎ ይህን ያህል ረጅም መንገድ ተጉዞ የሰውን መብት ለማስከበር የሚደረግ የህግ ሰዎች ጥረት በሀገራችን አለ?

የእኛ ሀገር የህግ ሰዎች (አንዳንድ የህግ ሰዎች ልበል ይሆን!) ለጥቅም ብለው ወይም ቢያንስ የመንግስት ባለስልጣናትን ፈርተው ፍትህን ሲያዛቡ ይስተዋላሉ። ፖሊሶች ሰላማዊ ዜጎችን ካላግባብ ሲያሰቃዩ፣ ዳኞች በጉቦ፣ በዝምድና እና በፖለቲካ ወገንተኝነት ከሙያ ስነምግባር ውጪ የሆነ ውሳኔ በማሳለፍ ንጹሀንን ለእስር፣ ለስቃይና ለሞት ሲዳርጉ የሚጠዘጥዝ የህሊና ህመም አይሰማቸውም።

በመንግስት መስሪያቤቶች አብዛኞቹ ከጽዳት ሠራተኛና ጥበቃ ጀምሮ እስከ ቢሮ ሀላፊወች ድረስ ያሉት ባለጉዳዮችን በትህትናና በቅን ልቡና ለማስተናገድ ፍላጎቱ የላቸውም፤ ፍላጎት ቢያሳዩም ትህትና በራቀው መንገድ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ አንድ ባለጉዳይ ችግሬን ይፈታልኛል ብሎ ካሰበው ባለስልጣን ፊት ለመቅረብ ለረጅም ጊዜ ደጅ መጥናት ይኖርበታል። ባለጉዳዮች ተፈቅዶላቸው እንዲገቡ ከተደረጉም በኋላ ያለው ሁኔታ እጅግ የሚያሳዝን ነው። በር አንኳኩተው የገቡት ባለጉዳዮች የቢሮ ሰራተኛውን ትኩረት ለማግኘት ድምጽን አጥፍተው ለደቂቃወች መቆም ይጠበቅባቸዋል። የሚሰሩት አጥተው በኮምፕዩተር ላይ ጌም ሲጫወቱ የነበሩት ሰራተኞች ባለጉዳዮች ሲመጡ በስራ የተወጠሩ ለመምሰል ወይም የበላይነትን ለማሳየት በመፈለግ ይመስላል ባለጉዳዩን እንዲቀመጥ እንኳ ሳይጋብዙ እስክርቢቶ ጨብጠው፣ የሆነ ወረቀት ላይ አይናቸውን ተክለው ድምጻቸውን አጥፍተው ሲቀመጡ ቅንጣት ታክል አይከብዳቸውም። የሚበቃቸውን ያህል ካስጠበቁ በኋላ አንገታቸውን ቀና አድርገው አፍጥጠው እያዩ ከተቀመጡበት ወንበር ልክ እንደተቆጣ ድመት በማበጥ “ምን ነበር?” ብለው በእብሪት መጠየቅ የታላቅነት መገለጫ ይመስላቸዋል። ፈረንጆች ጋር እንዲህ አይነት ነገር አይታይም። የመንግስት ሰራተኛ የህዝብ አገልጋይ ነው። ስለዚህ ባለጉዳይ ሲያንኳኳ ከተቀመጡበት ወንበር ተነስተው በሩን ከፍተው በፈገግታ ራሳቸውን አስተዋውቀው ሲያበቁ በትህትና ወደውስጥ እንዲገባ ያደርጋሉ። ባለጉዳዩ “እባክህ ተቀመጥ!” ተብሎ ይጋበዝና “የምረዳህ ነገር አለ?” ተብሎ ይጠየቃል። እነርሱ ዘንድ የሚከበረው ህግ ነው፤ ህጉ ደግሞ ሰውን ያከብራል።

ክፉና ደጉን መለየት የሚያስችል ህሊና ባለቤቶች ሆነን እያለን፣ የህሊናም ይሁን የአካል ጉዳት ምን ያህል እንደሚያም እያወቅን፣ ሰዎች ካለሀጢያታቸው እንዲጎዱ ምክንያት መሆን ተገቢ አይደለም። በእኛ ውሸት፣ ተንኮል፣ አድሏዊነት የንጹሀን እምባና ደም ሲፈስ እያየን እንዴት የሰላም ህይወት ለመኖር እንችላለን? ለሀገራችን እና ለልጆቻችን እናስባለን የምንል ከሆነ የማይጠቅመውን ክፋታችንን ትተን መጪው ጊዜ ብሩህ እንዲሆን ስለፍቅር፣ አንድነትና ሰላም ለማስተማር መሰረት እንጣል። አሁን ያለው መንግሥት የጋራ ሀገራችንን ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር የመሰረት ድንጋይ ለማንጠፍ አሁንም ዕድሉ አለው። በልዩነት አገር አይገነባም፤ በዘረኝነት ፍቅርና አንድነት አይጸናም። እስካሁን የተሄደበት መንገድ ብዙ ጥፋት አስከትሏል። ከስህተቱም፣ ከጥፋቱም፣ ከልማቱም ትምህርት ወስዶ “ለልጅ የልጆቻችን የምናወርሰው ምን መሆን አለበት?” ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። “ብልህ የአመቱን ሞኝ የዕለቱን” አይደል የሚባለው! እናንተ ለዕለቱ ተጠቅማችኋል፤ እየተጠቀማችሁም ነው። ለወደፊቱ የሚሆን ሀብት ንብረትም አከማችታችኋል። ይህ ሁሉ ግን ለልጅ ልጅ የሚተርፍ ሰላምና ደህንነት ያረጋግጣል? በጡንቻ ሳይሆን በጭንቅላት ማሰብ መጀመር ተገቢ ነው።

የመንግሥት አስፈላጊነት የተፈጥሮ ሀብትን፣ የህዝብን ጉልበት እንዲሁም ዕውቀት አደራጅቶ ለሕዝብ ጥቅም እንዲውል ለማድረግ የተመቸ ስርአት ለማስፈን ነው። ይህንን መሰረታዊ መርህ ተግባራዊ ለማድረግ ሕጻናት ከታች ጀምሮ በግብረገብ (Moral) ትምህርት ተኮትኩተው ማደግ አለባቸው። የሙያ ዲሲፕሊንን ለማጎልበት የሙያዊ ሥነምግባር (Professional Ethics) ትምህርት በኮሌጅና በዩኒቨርሲቲ ደረጃም እንደ አንድ የትምህርት አይነት መሰጠት አለበት። የመንግሥት ሠራተኛ ሆነው የሚመደቡ ሰዎች ተቀጣሪ ሆነው ደመወዝ የሚከፈላቸው በዋናነት ሕዝብን በእኩልነት፣ በታማኝነትና በትህትና ለማገልገል እንደሆነ ተምረው መውጣት ይኖርባቸዋል። ጥቅምን ሳይሆን ሕዝብን ማዕከል አድርገው የሚሰሩ በሞራል እና በህግ የተገሩ ዜጎችን መፍጠር ለማህበራዊ ህልውናችን እና ለሀገራችን ዕድገት ወሳኝ ነው። ደመወዝ የሚከፈላቸው ህዝብን ለማገልገል እንደሆነ ማወቅ ብቻ ሳይሆን ህዝብን እና ሀገርን ማገልገል የህይወት ፍልስፍናቸው አድርገው እንዲወስዱ ተደርገው መቀረጽ ይኖርባቸዋል። እንግዳን ወይም ደንበኛን እንዴት መቀበል እንዳለባቸው፣ እንዴት ማስተናገድና መሸኘት እንደሚገባቸው፣ ከእነሱ የሚጠበቀውን በምን ያህል ፍጥነትና እንዴት ማሟላት እንዳለባቸው፣ ከአቀባበልና ከሚጠቀሙባቸው ቃላት ጀምሮ በትምህርቱ ተካቶ በተግባር ትምህርት ተደግፎ ቢቀርብ መልካም ባህሪን እና የስራ ዲሲፕሊንን እንደ ልምድ በመያዝ አሁን የሚታየውን የተበላሸ አሰራር በሂደት ማስተካከል ይቻላል።

ሀሜት፣ አሉባልታ፣ ምቀኝነት፣ ክፋት፣ ተንኮል፣ ድብቅነት፣ ውሸት፣ ማታለል፣ ሙሰኝነት፣ አድሏዊነት፣ ማግለል፣ ማስመሰል፣ የሀገር ፍቅር ማጣት፣ ለሰላምም ሆነ ለዕድገት ጸር ስለሆኑ ከእኛ አልፈው ወደልጆቻችን እንዳይሻገሩ መስራት ያስፈልጋል። ለዕውነት መወገን፣ ችግሮቻችንን በግልጽ ውይይት መፍታት፣ የምናውቀውን ከመደበቅ ወጥተን ላላወቀው ማሳወቅ፣ ጥፋታችንን ሳንሸፋፍን አምነን ለማረም መስራት፣ መጥላትም ሆነ መውደድ መጥፎ ባህሪን/ተግባርን እንጅ ዘርን ወይም ቋንቋን አለማድረግ፣ መጥፎውን የማውገዝ/የመቃወም ጥሩውን የማወደስ/የመደገፍ ባህል ማዳበር፣ ለሰላማችንም ሆነ ለዕድገታችን አስፈላጊ ግብአቶች ናቸው። የሞራል እሴቶች፣ ወጎች እና ባህሎች ለዕድገት፣ ለሰላም፣ ለፍቅር እና ለአንድነት መሰረት እንዲሆኑ መጥፎውን በማረም መልካሙን ማጎልበት ያስፈልጋል። ሀገራችን የራሳችን መለያ ባህሪ ያረፈባት በስልጣኔ ከበለጸጉት ሀገሮች ተርታ የምትመደብ እንድትሆን ሀገር ተረካቢው ትውልድ በስነስርአት ተኮትኩቶና ተገርቶ ሊያድግ ይገባል። የሀገር ፍቅር ስሜት ስናዳብርና ለሕዝብ ስራ ራሳችንን አሳልፈን የመስጠት አላማ ሰንቀን ስንነሳ ያን ጊዜ ተሳስበን መኖር፣ ተያይዘን ማደግ እንችላለን።

Latest from Blog

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop