አውስትራሊያን ከኢትዮጵያ ጋር የማመሳሰል ሕልም

 መስከረም 8 2013

ከታክሎ ተሾመ

 

አውስትራሊያ ቀለመ ብዙ አገር  ናት። ከ200 በላይ  ቋንቋ  የሚናገሩባት በዝንቅ ማኅበረሰብ የተመሰረተች፤በጥሬ ማዕደኗ፤ ወንድ ሴት ሳይል የሰዎች የተፈጥሮ ሰብአዊ መብት የተከበረባት አገር ማን ትባላለች ብሎ ለሚጠይቅ  መልሱ አውስትራሊያ  ናት ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል።

 

አዎ እርግጥ ነው አውስትራሊያ በስደት የምኖርባት አገር ናት፤ ከዚህ በፊት ዴሞክራሲ የሚባል ነገር ስላላየሁ  ከዚህች አገር ውጭ ዴሞክራሲ ያለ መስሎ ስላልታየኝ  ወደድኳት፤ ተመችታኛለች። መፋቀርና መቻላል  ስላለ ብዙ እድሎችና ሕይወትን የሚለውጡ አጋጣሚዎች  የተመቻቹ  ናቸው።

 

አውስትራሊያን  ጥሩ  አገርና  መልካም ሕዝብ ያሰኛት የተለያዩ ምክንያቶች  አሏት። አውስትራሊያ ራሷን  የቻለች አገር  ከመሆኗ  በፊት  እርግጥ ነው ብዙ ጦርነቶች  ተካሂደውባታል።  ይሁን እንጂ ራዕይ ባላቸው ሰዎች አማካኝነት ከችግር  ተላቃ  ዴሞክራሲ የሰፈነባት አገር ለመሆን የቻለቸው  ሌበርና ሊበራል  የተሰኙ ሁለት አንጋፋ ፓሪቲዎች  በመፈጠራቸው  ነው። ሁለቱ  ፓርቲዎች  የየራሳቸውን  የፖለቲካ ፕሮግራም ይዘው  ሲከራከሩ ከዚህ ቀደም የሰሩት ሥራ እየተገመገመ  ሕዝቡ የሚበጀውን  ይመርጣል።

 

በአውስትራሊያ የፌደራሊ ምርጫ ሲደረገ  ጦርሰራዊት፤ ፖሊስ ወይም ደህንነት የሚባሉ በየምርጫ ጣቢያው  አካባቢ ድርሽ አይሉም። የአውስትራሊያ ዜጋ ሁሉም የሚበጀውን ፓርቲ የመምረጥ ኃላፊትም ሆነ ግዴታ አለበት። መስከረም 7 ቀን 2013 ቅዳሜ  ከጧቱን 8 ሰዓት  ጀምሮ እስከ ምሽቱ 6 ሰዓት ድረስ  ምርጫ ተካሂዷል።  በዚህ ወቅት ለውድድር  የቀረቡ፤ የአውስትራሊያ ሌበር ፓርቲና የአውስትራሊያ ሊበራል ፓርቲ በዋናነት ሲወዳደሩ እንዲሁ አናሳ የሚባሉ 1 ናሽናል ፓርቲ 2  ግሪን ፓርቲ  3 የግል ተወዳዳሪዎች 4  ዩናይትድ ፓርቲ  የመሳሰሉት ለውድድር  ቀርበው  ነበር። ከ2007  እስከ  2013 ዓ.ም ድረስ  የአውስትራሊያ  የሠራተኞች ፓርቲ ሌበር ሥልጣን ላይ  ነበር። ነገር ግን መስከረም 7 ቀን 2013 ዓ.ም በተደረገው ምርጫ ከምሸቱ 8.45 ሰዓት ላይ ተቃዋሚ  የነበረው  የአውስትራሊያ ሊበራል ፓርቲ 88 ድምጽ ሲያገኝ ሌበር ፓርቲ 54  ድምጽ አግኝቶ የሥልጣን ባለቤት ለመሆን በቅቷል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሴት የሁላችንም እናት በመሆኗ ሠላምን እና ዳቦን አጥብቃ ትሻለች - መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ 

 

ከላይ እንዳልኩት በምርጫ ወቅት የሳጥን ስርቆት አልነበረም፤ ሥልጣን ላይ የነበረው ሥልጣን አለቅም ብሎ ጦር አላዘመተም። እንዲያውም አሸናፊውን እንኳን ደስ ያለህ በማለት ወደፊት እየተመካከሩ አገርና ሕዝብ ለመምራት ቃል ኪዳን በመግባት የእለቱ ምርጫ  ተጠናቋል።

 

ይህንች አጭር ጽሁፍ ላቀርብ የተገደድኩበት ምክንያት የአውስትራሊያው ምርጫ በኢትዮጵያ መቼ ይሆን የሚደገም የሚለው ጥያቄ  ስላስገደደኝ  ነው። እርግጥ ነው፤ አንድ አገር  እንደ አገር ሲቆረቆር ብዙ ውጣ ውረዶችን  ማለፍ ግድ  እንደሚለው  ይታወቃል። ከታሪክ  መረዳት  እንደሚቻለው አገራችን ኢትዮጵያ ከዓለም ቀደምት መሆኗን ነው የሚነግረን። ነገር ግን ረጅም  እድሜ  ብታስቆጥርም ከአብራኳ በሚፈጠሩ መንግሥታት ሕዝቦቿ  በነፃነት እንደ ዜጋ እየኖሩ አይደለም።

 

ኢትዮጵያ ከዓለም የሚወዳደሩ ምሁራን ልጆች እንዳሏት አይካድም። ነገር ግን አገርና ሕዝብን ለመታደግ የታደለች አገር  አይደለችም። በመሆኑም  በየጊዜው  እስር፤ ስደትና ሞት የዘወትር እጣ ፈንታችን  ሆኗል። ይሁን እንጂ ችግሮችን አስወግዶ ዴሞክራሲያዊ የሆነ በሕዝብ የሚመረጥ መንግሥት ለማምጣት ረጅም  ዓመታት የተለያዩ ትግሎች ተካሂደዋል። ለትግሉ ስኬት አለመበቃት የተለያዩ ምክንያቶች እንዳሉ አይካድም።  ከፓለቲካ ድርጅት  መሪዎች  እስከ ግለሰቦች ድረስ ያለውን ብሎም ከሕይወታችን ጋር በንፅፅር ማስቀመጡ ተገቢ  ይመስለኛል።

በመጀመሪያ ደረጃ ዓላማን  በትክክል በመረዳት ወደየትኛው መስመር ነው የምንጓዝ፤ የምንታገለው ለጐጂ ወይስ ለጥሩ ዓላማ የሚለው ተለይቶ ከታወቀ  ትግሉ ትርጉም ያለውና የተሟላ  ይሆናል። ይህ ማለት የትግሉ ዓላማና የጉዟችን አቅጣጫ ከታወቀ ሕዝቡ ሊከተል ይችላል። ከተለያዩ ዓለም ትግሎች ተሞክሮ መረዳት እንደሚቻለው  ትግላቸው ውጤት ከማምጣቱ በፊት  ብዙ እልህ አስጨራሽ ትግልን ማለፍ ይጠበቅባቸው ነበር።  በመሆኑም  በደቡብ  አፍሪካ፤ በሰሜን  አሜሪካና በሌሎች አገራት ለነፃነት የታገሉ ድርጅቶች ለአሸናፊነት የበቁት  ሽንፈትንና  ተስፋ  መቁረጥን በፀጋ  መቀበልን  ባለመፈለጋቸው  ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  (ለትውስታ) አቡበከር አህመድ ከመታሰሩ በፊት ከራድዮ ፋና ጋር ያደረገው ቃለምልልስ - [ሊደመጥ የሚገባና አዲሱን የወያኔ ሴራ የሚያጋልጥ]

 

ከዚህ በፊት የተደረጉ ትግሎች በድርጅቶችም ሆነ በግለሰቦች ላይ አስደሳችና አሳዛኝ ገጠመኞችን ተመልሰን ስንቃኝ ብዙ ትምህርቶችን መቅሰም  ይቻላል። ለአገራችውና ለሕዝባቸው ሲሉ ከዚህ በፊት የተሸነፉ ፓርቲዎች በችግሮች ተስፋ  ሲቆርጡ  አንዳንዶች  ዛሬም ድረስ  የሚችሉትን  ያህል  እየተፈረጋገጡ  ይገኛሉ።

 

 

በአገራችን የተፈጠሩ በርካታ ተቃዋሚ ድርጅቶች በውስጥና በውጭ  እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ ስንቶች ናቸው መሰናክሎችን ማለፍ የሚችሉ ብለን ስንጠይቅ በጣት የሚቆጠሩ ሆነው እናገኛቸዋለን። በመጀመሪያ ደረጃ  ይጠንክሩም  ይኩሰሱ  አገር ቤት ውስጥ  የሚንቀሳቀሱ  ድርጅቶች የለውጥ ተስፋ እንደሚሆኑ እገምታለሁ።

 

ከላይ ከተጠቀሱት  የተስፋ ፓርቲዎች በተጨማሪ በውጭ የተሰባሰቡ ጅርጅቶችም እንዲሁ የአጋዥነት ግዴታ  እንዳለባቸው ብዙዎች ሲናገሩ እየተደመጠ ነው። እርግጥ ነው በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ከጉልበት እስከ ገንዘብ ድረስ የሚችለውን ያህል ለአገሩ እያበረከተ መሆኑን ማንም አይክድም። ነገር ግን  አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች እርስ በርሳቸው በሚያደርጉት ፍክቻ  ትግሉ ወጥነት ኑሮት ስኬታማ እንዳይሆን መሰናክል መፍጠሩ አልቀረም።

 

ዋናው ነገር ግን ትግሉ ስኬታማ ሊሆን የሚችለው አገር ቤት በሚደረገው ትግል ስለመሆኑ አምንበታለሁ፤ ብዙዎችም አባባሌን  የሚስማሙበት ይመስለኛል። እነዚህ የአገር ቤት ተቃዋሚ ድርጅቶች ለአገራቸውና ለሕዝባቸው  መብት  መከበር  ሲሉ ብዙዎች የእሳት ረመጥ እስከ መሆን ደርሰዋል። እስር፤ ግርፋት ቢደርስባቸው የጀመሩትን ሰላማዊ ሕዝባዊ ተቃውሞ ትግል ከግብ ለማድረስ ቆርጠው መነሳታቸውን  በአንደበታቸው  እየሰማንና  ተግባራቸውን  እያየን  ነው።

 

እርግጥ ነው የአገር ቤት ድርጅቶች ለመስዋዕትነት መዘጋጀታቸው ቢያስደስትም የጀመሩት ትግል ውጤት እንዲያመጣ ከተፈለገ  ማበረታቻ  ያስፈልጋቸዋል። ይህ ሲባል  በስደት የተበተነው ትውልደ ኢትዮጵያዊና የፖለቲካ ድርጅቶች በሞራል፤ በገንዘብ፤ በዲፕሎማሲ፤ አገር ቤት ገብቶ አብሮ  መታገልን ግድ ይላል። እያንዳንዱ ለአገሩና ለሕዝቡ ሲል የራስ ተነሳሽነት ስሜት  ካለውና ከልብ የሚታገል ከሆነ ውጤታማ  ይሆናል። ብሎም የድርጅት መሪዎች ተነሳሽነታቸውም ቢሆን ዘላቂነት ይኖረዋል። ለዚህ ደግሞ ኃይል ሊሆን የሚችለው እምነት መሆኑ  አያጠያይቅም።  ስለሆነም እያንዳንዱ ኃላፊነትን መቀበል ሲጀምርና ወደ አንድ መመጣት ሲችል የትግሉ አቅጣጫ  ይስተካከላል ብሎ  በድፍረት  መናገር ቢያስ  ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የገንዘባችን ዋጋ ስንት ነው?

 

ከመግቢያየ ላይ  እንዳልኩት አውስትራሊያ  ዛሬ ከደረሰችበት የእድገት ደረጃ ከመድረሷ በፊት ብዙ ፈተናዎችን እንዳለፈች ከአውስትራሊያ ቤተ መጽሃፍት ውስጥ ገብቶ የታሪክ መጽሕፍቶችን ለሚያገላብጥ አስቀያሚና አስደሳች ታሪካቸው በሚገባ ተቀምጧል።  መስከረም 7 2013  በአውስትራሊ የተካሄደውን  የመንግሥት  ምርጫ በቅርበት ማየት ብቻ ሳይሆ  ተሳትፊ  እንዳየሁት ከሆነ  ተሽናፊው ለአሸናፊው ሥልጣኑን በሰላም አስረከቧል።

 

ከላይ ይህን ካልኩ ዘንዳ  ከምርጫ በኋላ   ቤቴ ቁጭ ብየ ቴሌቭዝኝ እየተመለከትኩ እግሬን ሳይሆን አእምሮየን  ኢትዮጵያ አድርጌ ጉደኛዋ አገራችንስ በምን ላይ  እንደምትገኝና የ1997 ቱ  ምርጫ ተመልሸ ስቃኝ አዘንኩ፤ ተከዝኩ እርር ትክን አልኩ። እርግጥ ነው ሃዘኔ ግን ተስፋን  ያዘለ ነው። ምክንያቱም ከዚህ ቀደም በተናጥል ይደረግ የነበረው ትግል አሁን፤አሁን በተቀናጀ መልክ  ሰላማዊ ሕዝባዊ ትግል ለማካሄድ  መስማማታቸውን እየሰማን ነው። ስለሆነም  ተስፋ ጥሩ ነው “ቸር  ተመኝ በጐ “እንድታገኝ ይሉየል በአውስትራሊያ ያየሁት  የሰላም የሥልጣን ዝውውር በኢትዮጵያም ይደገማል የሚል የተፍሳ  ስንቅ ተሸክሜአለሁ።

 

ሁሉም ፊቱን ወደ ሰላም እንዲያዞር ኃያሉ ልዑል እግዜአብዜ ይርዳን።

1 Comment

Comments are closed.

Share