ወገኖቻችንን ለዘመናተ የጨረሰው አደገኛው ዘንዶ፡-የኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት – ሰርጸ ደስታ

የኢትዮጵያውያን ደም ሲገበርለት የኖረው የሕወሐት ኢህአዴግ ታላቅ ጣዖት ሕገ ምንግስት ከዚህ በኋላ ተነኮታኩቶ መሬት ወድቋል፡፡ ብዙዎች ሕገ መንግስቱን ለመናድ በሚል ለጣዖቱ ተገብረዋል፡፡ አምላኪዎቹ ቀን ከሌሊት ይዘምሩለታል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ከምንም በላይ ጠላቱ ይሄ ጣዖት እንደሆነ የገባው ሰሞኑን ነው፡፡ እስከዛሬ እስኪ እናክብረው በሚል ጠጋ ሲሉት ዜጎችን እየጠለፈ ወደሞትና ጉሮኖ የሚያሰገባው ይህ አደገኛ የሕወሐት ኢሕአዴግ አምላክ ዘንዶ (ሕገ-መንግስት) ሰሞኑን ጎንደር ላይ ክፉኛ ቆሰለ፡፡ አምላኪዎቹ መጨረሻ እነሱኑ እንዳይውጣቸው ፈርተው አሁንም ሊላ ግብር ሊያቀርቡለት እጅግ እየተሯሯጡ ነው፡፡ ግን አይመስለኝም፡፡ ዘንዶው መጨረሻ የሚውጠው ሲያጣ ወደ አምላኪዎቹ መዞሩ እውን እየሆነ ይመስላል፡፡ ጎንድር ሁለተኛ እንደይመለስባት አድርጋ አድምታዋለች፡፡ ሌሎችም ብዙዎች አሁን ስልቱን የነቁበት ይመስላል፡፡ በኦሮምያ ብዙ ከዘንዶው ጋር ግብግቡ ቀጥሏል፡፡ ትንሽ የስትራቴጂ ለውጥ ማድረግ የሚያስፈልግ ይመስላል፡፡ ስልቱን ከጎነድሬዎቹ መማር ነው፡፡ ጎንደሬዎቹ ጠመንጃ ስላላቸው ብቻ አይደለም፡፡ በጣም የተቀናጀና ሰፋ ያለ ጉልበት እንዲኖራቸው በጥንቃቄ ነው ድል የተቀዳጁት፡፡ ጎደር ሁሉም አንድ ነው፡፡ ጎደሬዎቹ ኮሌኔል ደመቀን ለጎንደር ፖሊሶች አደራ ሲሰጡ ፖሊሶቹ ኮሌኔሉን ለዘንዶው አሳልፈው እንደማይሰጧቸው ለሕዝቡ ቃል ገብተውዋል፡፡ ሕዝቡም አልተጠራጠረም፡፡ የዘንዶው ሎሌዎች ብዙ ለፍተዋል፡፡ እንዲህ አይነቱ አንድነት በኦሮምያ እስካሁን ልናየው ልናየው አልቻልንም፡፡ አሁን ግን ለኦሮምያ ባለስልጣናትም ይሁን ፖሊሶች ኋላ ተመልሶ ይህ አደገኛ ዘንደዎ እንዳይውጠን ብለው ለራሳቸው ማሰብ ከቻሉ ራሳቸውን ሕዝቡን ይዘው ይከላከሉ፡፡

በአማራ ክልል ኮሚኒኬሽን ባለስልጣን ቀልድ ይሁን የምር አላውቅም ግን ጎንደር ላይ የአምላካችንን ፍላጎት የሚጻረሩ መልክቶች ተላለፈዋል ብለውናል፡፡ የሚያስቀው ይህ ዘንዶ ከሚጠላቸው መልዕክት ተብሎ ባለስልጣኑ ከተናገሩት አንዱ የኢትዮጵያ የነጻነት አርማ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ አላማችን ነው፡፡ መቼም ጉድ ሳይሰሙ መስከረም አይጠባም አሉ፡፡ አንድ ከምን እንመጣ የማይታወቅ ለዘንዶው እንዲስማማው ተብሎ የኮከብ ቆጣሪዎች ደብተሮች የነገሯቸውን ትልቅ ኮከብ በሰነደቅ አላማችን ላይ ለጠፈው ለዘመናት የሕዝቦችን እኩልነት የሚገልጽ ነው ብለው አጃጃሉን፡፡ እስኪ ይህን ኮከብ አስተውሉት አንድነትን የሚያሳየው የቱ ጋር ነው፡፡ ይልቁንስ ሕዝብን ከሕዝብ በዘር በእምነት እየከፋፈሉ መሆኑን አሳምሮ ይናገራል፡፡ ጠነቋዮቻቸውንም አማክረው ይህን ምልክት ሲያቀርቡለት     ዘንዶው ከራማዬ ወዶት ተቀበሏቸዋል፡፡ እና አቶ ንጉሱ (የአማራው ኮሚኒኬሽን) ራስዎን ቢያድኑ ይሻልዎታል፡፡ ሌላው ዘንዶው እንዳይነኩበት የሚፈልጋቸው ልዩ አምላኪዎቹ (የጣዖቱ ካህናት) በጎንደሬዎቹ የማስጠንቀቂያ መልዕክት ተላልፎላቸዋል፡፡ በእርግጥም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕዋት የሻቢያ ተላላኪ እንደሆነ አሳምሮ ያውቀዋል፡፡ ጎንደሬዎቹ ለዘመናት የተደበቀውን እውነት አደባባይ አወጡት፡፡ የተጠቀሱትም ግለሰቦች በትክክል ሕዝብ ማንነታቸውን አሳምሮ ያውቀዋል፡፡ እውነታው ይሄ ነው፡፡ አቶ ንጉሱ ሕዝብ አይሳሳትም፡፡ የተሳሳቱት እርሶ ነዎት፡፡ ወይም አዚም አርገውብዎት ነው፡፡ ይልቁንም አይፈሩበት ጎንደሬው ነጻነትዎን እያወጀልዎት ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት 60 በመቶ ቡና አብቃይ አካባቢዎች ከአምራችነት ውጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተመራማሪዎች ይፋ አደረጉ

ሌላው ብዙ የትግራይ ተወላጆች አካባቢ ከመቼውም በላይ በአሁኑ ወቅት ለዘንዶው ካሕናት ያላቸውን ወገንተኝነት እያሳዩ ይመስላል፡፡ ከአሁን በኋላ ምንም ሰበብ አይኖራችሁም፡፡ ጎንደሬዎቹ ሁሉንም ናቸው፡፡ ዘር፣ እምነት ምናምን አልያቸውም ሁሉም ጎንደሬዎች ናቸው እንጂ፡፡ ብዙ ጊዜ ብዙ ተመክራችኋል፡፡ አልሰማችሁም፡፡ አሁን ግን ጨው ለራስ ስትል ጣፍጥ አለዚያ የሚላችሁ ጊዜ እንዳይመጣ እፈራለሁ፡፡ ከዘንዶው ራቁ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ተቀላቀሉ ብዬ እመክራለሁ፡፡ አሁንም የዘንዶውን ካሕናት የሀሰት ትንቢት እየሰማችሁ ዘንዶው የመሰናበቻው ራት እንዳያደርጋችሁ፡፡ አባይ ጸሐዬ፣ ጀነራል ጻድቃን፣ ኮሌኔል አበበ በፎረሸ ስብከታችሁ ዳግም እናንተ ለምታመልኩት ዘንዶ ኢትዮጵያውያን ጭዳ አይሆኑም፡፡ ምን ይሻላል ብላችሁ ሌሎቹንም የዘንዶው ካሕናት ሰብሰብ አድርጋችሁ ምን አልባት የምትተርፉ ከሆነ ራሳችሁን አድኑ፡፡

ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት በዘንዶው ላይ ይነሳ! እስከዛሬ በተገበረለት ወገኖቻችን ይብቃ! የዘንዶው አምላኪዎችም እራሳችሁን ወደ ሕዝብ ማሸሽ የምትችሉበት ጥቂት ሰዓታቶች አሏችሁ፡፡ ከሕዝብ የዘረፋችሁት ሐብት ንብረት እያላችሁ እዛ ስትንደፋደፉ ዘንዶው የመጨረሻ እራቱ እንዳያደርጋችሁ!!!

 

እግዚአብሔር ለኢትዮጵያና ሕዝቦቿ የብርሀን ዘመን ያምጣ!

 

አሜን

 

ሰርጸ ደስታ

 

 

 

 

Share