July 11, 2013
24 mins read

ዲሲ 2013 – ክንፉ አሰፋ

ክንፉ አሰፋ

      ስለ ኢትዮጵያውያን ብዙ የሚያውቁ ፈረንጆች ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ጠንቀቆ ማወቅ በጣም አስቸጋሪ እና ከባድ እንደሆነ ይናገራሉ። “ስለ ሕዝቡ ለመጻፍ የሚፈልግ አንድ ሰው ኢትዮጵያ በገባ ማዕግስት አንድ መጽሃፍ ሊጽፍ ይችላል፤ ይህ ሰው ሳምንት ሲቆይ አንድ መጣጥፍ ይጽፋል፣ ወር ሲቆይ ግን የሚጽፈው ይጠፋበታል።” ይላሉ። ይህ አባባል በከፊል ትክክል ይመስለኛል። ኢትዮጵያ የብዙ ባህል፣ የብዙ ቋንቋና የበርካታ እምነት ሃገር ስብስብ በመሆንዋ ታሪኳን ጠለቅ እያልን ለማወቅ በሞከርን ቁጥር ሊወሳሰብ ስለሚችል እጅግ ብዙ ጥናት ማድረግ ይገባል ለማለት ነው። ጸሃፊው ለረጅም ጊዜ በቆየ ቁጥር የሚጽፈው ጠፍቶት ሳይሆን ግራ ተጋብቶ መጻፉን ያቆማል።

በያዝነው የበጋ ወር፡ ዲሲ ላይ ያጋጠመኝ ችግር ይኽው ነበር። ስለ-30ኛው የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን ስፖርት ፌስቲቫል በበርካታ ርዕሶች ዙርያ ለመጫጫር ፈለግኩ። ነገር ግን በርዕሶቹ ላይ ጠለቅ እያልኩ ስሄድ ግራ በመጋባት ላለመጻፍ ወስኜ ነበር። የአትላንታው ዳዊት ከበደ ኢ.ኤም.ኤፍ. ላይ በሚጽፋቸው ገጠመኞች ለማብራሪያው እኔን እየጠቃቀሰ ‘ሼም’ አስያዘኝ። በበአሉ መክፈቻ እለት የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት እና የህዝብ ግንኙነቱ ፋሲል አበበ በር ላይ አግኝተውን ሞቅ ያለ ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ፋሲል አበበ፣  ‘…አንተ ሳትኖር ይህ በዓል አይደምቅም።’ ያለኝም ታወሰኝ። ከዚህ ቀደም ፌዴሬሽኑን እየተቸን የጻፍናቸውን በማንሳትም ወደፊት ገንቢ ትችት እንድናቀርብ አበረታች ሃሳብ ነበር። አሁንም የታዘብኩት ነገር አለ። ይህንን ወደኋላ እመለስበታለሁ።

30ኛው የሰሜን አሜሪካ ስፖርት ፌስቲቫል እንደተጠናቀቀ ወዳጆቼን ሸኛኝቼ ዲሲን መቃኘት ያዝኩ። በዲሲ ያለ ኢትዮጵያዊ ልዩ ነው። በዲሲ ከማህበራዊነት ይልቅ ግለኝነት በስፋት ይንጸባረቃል። እዚህ የግል ነገር ይበዛል።

የግል ንግድ፣ የግል ራዲዮ፣ የግል ጋዜጣ፣ የግል ፓርቲ፣ የግል ቤተ-ጸሎት፤ … አዎ የግል ቤተ-ክርስቲያን። በዚህም ቤተ-ክርስትያን የሙሴ ጽላት ያለበት ታቦት አለ። የግል ታቦት። የሚገርመው ታዲያ በዚህ ሃላፊነቱ ባልተወሰነ የግል ቤተ-ክርስቲያን ምእመናን እየሄዱ መሳለማቸው፣ ማስቀደሳቸውና ምጽዋት መክፈላቸው ብቻ አይደለም፣ የቤተ-ክርስቲያኑ አገልጋይ ቄስ ከተገኘ ተከፍሎት ይቀድሳል፡ ከሌለ ደግሞ ቅዳሴው ለምእመናኑ በቴፕ እንዲተላለፍ ይደረጋል።

አሜሪካ የእድል ሃገር ናት (ላንድ ኦፍ ኦፖርቹኒቲ) የሚባለው እንዲህ አይነቱን እድልም ይጨምራል ማለት ነው። ታዲያ አንዳንድ የዲሲ ነዋሪ ኢትዮጵያዊ ባልጠፋ ጸሎት ቤት ወደግሉ ቤተ-ክርስቲያን እየሄደ የሚሳለመው ለምን ይሆን? ትሉ፡ይሆናል። ይህ የኔም ጥያቄ ነው። መልስ የሚሰጠኝ ግን አላገኘሁም።  በግምቴ ካልተሳሳትኩ ገሚሱ በፍርሃት ሌላው ደግሞ በአንጃነት የሚሄድ ይመስለኛል። አንጃ የሚለውን ቃል በመጨረሻ የወዳጄ ሼክስፒር ታሪክ ላይ አነሳዋለሁ።

በዲሲ የግል ራዲዮ ያለው ሰው በጣም ነው የሚፈራው። በራዲዮ የሚደረግ ዘመቻ አንድን የንግድ ተቋም ከምድረ አሜሪካ የማጥፋት ሃይል እንዳለው ተገንዝቤያለሁ። እጅግ ደማቅ የነበረው የአቦነሽ አድነው (አቢቲ) የባህል ምሽት ቤት እንዲዘጋ የአንዲት ሰዓት  የራዲዮ ዘመቻ ብቻ በቂ ነበር። አቢቲ በደረሰባት አደጋ አቤት የምትልበት አጣችና እንባዋን ወደ ፈጣሪዋ ፈነጠቀች። አሁን ምሽት ቤትዋን ዘግታ፥ ዘፈኑንም ትታ መንፈሳዊ መዘምራን ሆናለች።

ኤፍ.ኤም. ራዲዮዎችን በጅምላ መንቀፉ ተገቢ አይደለም። ገንቢ እና እጅግ በጣም ድንቅ የሆነ ስራ እያከናወኑ ያሉ የራድዮ  ጣቢያዎች  እንዳሉ ሁሉ፡ አፍራሽ የግል ጣቢያዎች በህብረተሰቡ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ መፍጠራቸው በግልጽ ይታያል። በዲሲ፥ አንድ ኤፍ.ኤም. ጣቢያ ያለው እና ጥሩ ተናጋሪ ሰው ራሱን የቻለ መንግስት ሊሆንም ይችላል።

ጭብጨባ፤ ሌላው የታዘብኩት የዲሲ ኢትዮጵያውያን ህብረተሰብ ባህርይ ነው። መድረክ ላይ ያለ አንድ ተናጋሪ በጭብጨባ ይጀምርና በጭብጨባ ታጅቦ ከመድረክ ይወርዳል። አንዳንዴም የሚናገረውን አረፍተ-ነገር ገና ሳይጨርስ ይጨበጨብለታል። በሄድኩባቸው ስብሰባዎች ሁሉ ይህ ነገር አጋጥሞኛል። ማጨብጨብ ለተናጋሪው የሞራል ድጋፍ መስጠት ይረዳል። ሲበዛ ግን ያስፈራል። ተናጋሪውንም ወደማይፈልገው ትእቢተኝነትና ስሜታዊነት ይገፋፋዋል። ፈረንጆች ሲጨበጨብላቸው በጣም ይፈራሉ። እነሱ እንደሚሉት፥ ሰዎች አንድን ሰው ሲያደንቁና ሲያጨበጭቡለት፤ ለዚያ ሰው ስራ እየሰጡት ነው። ከሰውየው ብዙ የሚጠብቁት ነገር እንዳለ ማመላከቻ መልዕክት።  በምክንያት ሳይሆን ይልቁንም በስሜት የሚደረግ ጭብጨባ ግን አደጋ አለው።  የሚጨበጨብላቸው ስዎች ታዲያ በዚህ አይነቱ ሞብ ከመኮፈስ ይልቅ የበለጠ ስራ ለመስራት ቢተጉ ይበጃቸዋል። በጭብጨባ ብቻ እየተካቡ ሰማይ ላይ የደረሱ ሰዎች ከጊዜ በኋላ ካሉበት ስፍራ ሲፈጠፈጡ ከቀድሞ ተሞክሮ አይተናል።  ክርስቶስን በቤተልሄም እያጨበጨቡና ቄጠማ እያነጠፉ የተቀበሉት ሰዎች ግዜው ሲደርስ ራሳቸው “ይሰቀል! … ይሰቀል!” ብለው ተነሱበት። ሕዝብ በብዙ ምክንያቶች ስሜታዊ ይሆናል። ይህንን ሞብ ለማስቆም ይከብዳል።

***

     

ወደ 30ኛው የኢትዮጵያ ስፖርት እና ባህል ዝግጅት ልውሰዳችሁ። በዓሉ እስካሁን ከነበሩት ዝግጅቶች ሁሉ እጅግ የደመቀና፡ ኢትዮጵያዊነትን የተላበሰ ነው ከማለት ውጭ የምጨምረው የለኝም። ታዲያ በዚህ ደማቅ እና ግዙፍ ዝግጅት አንዳንድ እንግዳ ነገሮች ቢኖሩ አይደንቁንም። አንዳንዶቹ ችግሮች በቀላሉ ሊፈቱ የሚችሉ ነበሩ።

 

አርብ እለት የኢትዮጵያ ቀን ሲከበር ሼክ ሱለይማን ነስረዲን የተሰኙ የሙስሊም እምነት ተወካይ ንግግር አድርገው ነበር።  በሜዳው የነበረውን ሕዝብ ከዳር እስከዳር ያነቃነቀ ንግግር። ሼክ ሱለይማን ስለ ሙስሊም እምነት ብቻ ሳይሆን ስለ ክርስትና እምነትም ሰብክዋል፡ በተለይ ደግሞ ስለ ክርስቶስ እናት ስለ ቅድስት ማርያም ብዙ ብለዋል።   በበዓሉ መክፈቻ ላይ ያልነበሩ ሰዎች ግን አንዳንድ ጥያቄዎች ማቅረባቸው አልቀረም፡ “ሼኩ ሁለቱንም እምነት ወክለው ነው እንዴ እዚህ የተገኙት?” “የክርስትና እምነት ተወካይስ ለምን አልተጋበዙም?” የሚሉ ጥያቄዎች።

የክርስትና እምነት ተወካይ ያለመገኘትን በተመለከተ መልሱ ቀላል ነው። የበዓሉ  መክፈቻ ላይ የክርስትና እምነት አባት ተጋብዘው ሲናገሩ የሙስሊም ተወካይ ተረስተው ነበር። በሙስሊም ምዕመናን ጥያቄ መሆኑ ነው ሼክ ሱለይማን ነስረዲን በአምሰተኛው ቀን እንዲገኙ የተደረገው። ይህ እንግዲህ የዝግጅቱ አንደኛ ጉድለት መሆኑ ነው።

ከነጋዴው መብዛት አንጻር ይከሰት የነበረው የኤሌክትሪክ ሃይል መቋረጥ ሌላው ሊገታ ይችል የነበረ ችግር ነበር። በተለይ የኢትዮጵያ ቀን ሲከበር የሙዚቃ መሳሪያው ለበርካታ ጊዜ መቆራረጡ የህዝቡን ስሜት በእጅጉ ጎድቶታል። በርካታዎችም ሜዳውን እየለቀቁ ወጥተዋል።

የፕሬስ ካርድ አለማዘጋጀት፡ በየአመቱ ሊቀረፍ ያልቻለው የፌዴሬሽኑ ችግር ነው። በርካታ ጋዜጠኞች በዚህ ምክንያት ሲጉላሉ አይተናል። ከፌዴሬሽኑ አመራር ጋር ከዝግጅቱ በፊት በዚህም ጉዳይ ላይ ተወያይተን መፍትሄ ተገኝቶለት የነበረ ቢሆንም ተግባራዊ ግን አልሆነም። ለፌዴሬሽኑ ህልውና የሜዲያው ሚና ቀላል እንዳልሆነ ያውቁታል። እነሱ ለፕሬሱ ከሚሰጡት አክብሮት ጋር ግን አይመጣጠንም።  ዘንድሮ ይባስ ብሎ በሺዎች የሚቆጠር ህዝብ ሜዳ መግባት አልቻለም። ሜዳው ሞልቶ ሳይሆን ያንን ሁሉ ህዝብ (ከ40 ሺህ በላይ) ለማስትናገድ ፌዴሬሽኑ ቅድመ-ዝግጅት ስላላደረገ ነበር።

አርብ እለት የኢትዮጵያ ቀን ሲከበር ቀድሞ ፕሮግራም ላይ ያልነበረው ጃ ሉድ ዘው ብሎ መድረክ ላይ ተገኘ። ከመድረኩ ፊትለፊት ጢም ያለውን ህዝብ ሲያይም ገራ ገባው። የባንዱ ሙዚቃ እየሄደ ነው። ጃ ሉድ ማይኩን ያዘና “ቬኑስ እንገናኝ ተብዬ ነበር የመጣሁት። … እኔ አላውቅም።” አለና የሞት ሞቱን የርግብ አሞራ… ማለት ጀመረ። ህዝቡ ግን እንኳን ሊጨፍር ራሱንም አልነቀነቀም ነበር። ጃ ሉድ ትንሽ ሃይ እንደነበር ያስታውቃል። የዚያኑ እለት የነበረው ኮንሰርት አዳራሽ ሙሉ ሰው ሲጠብቀው ጃ ሉድ የውሃ ሽታ ሆኖ ቀረ።

እንደዚህ አይነት በርካታ እንግዳ ነገሮችን ታዝበናል። ለግዜው ፈገግ ሊያደርጉን ቢችሉም ችግር መሆናቸው አልቀረም።

በእርግጥ ፌደሬሽኑ ከተገንጣዩ ቡድን ጋር የገባው እሰጥ እገባ ብዙ ጊዜውንና ጉልበቱን ወስዶበታል። ሙሉ ትኩረቱን በ30ኛ አመት በዓል ላይ አለማድረጉ ዝግጅቱ በጥቂቱም ቢሆን መደናቀፉ አልቀረም። የዘንድሮውን በዓል ለየት ያደረገው ሕዝቡ በእልህ እና በቁጭት እንደዘመቻ በመረባረብ ዝግጅቱን ማሳመሩ ነው። ዘንድሮ በዚህ አልፏል። ወደፊት ግን ፌደሬሽኑ ቁጭ ብሎ ማሰብና ብዙ መስራት ይጠበቅበታል። በሙያው የተካኑ ቋሚ ሰራተኞችን ቀጥሮ ማሰራት ካልቻለ ችግሮቹ አሁንም ለ30 አመታት ይቀጥላሉ።

***

      ፌዴሬሽኑን በፖለቲከኝነት ለሚከሱ ወገኖች የምለው አለኝ። ሃገር ወዳድነት ፖለቲከኝነት አይደለም። በሰው ሰራሽም ሆነ በተፈጥሮ ክስተት ወገን ሲጎዳና ለአደጋ ሲጋለጥ እርዳታ ማድረግ ሰብአዊነት እንጅ ፖለቲከኝነት አይደለም። ወገኖቻችን በፖለቲካና በመንፈሳዊ እምነታቸው ምክንያት ያላግባብ ሲሰቃዩ ዝም ብሎ መመልከትም በአንጻሩ ሰብአዊነት አይደለም። ደቡብ አፍሪካ በዘረኛው አፓርታይድ ስርዓት ስር ወድቃ በነበረችበት ጊዜ ቤተ-ክርስትያናትም ለዜጎቻቸው መብት እና ነጻነት ይጮሁ ነበር። ታዲያ እነ ዴዝሞንድ ቱቱ ፖለቲከኞች ናቸው?

ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያንን ያሰባሰበ ተቋም ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ አያገባውም ማለት ከግብዝነትም ያለፈ ይሆናል።

ኢትዮጵያ ላይ እንዲጋልቡ የተፈቀደላቸው ባለሃብቶች፡ በድሃው ህዝብ ላይ እስኪደክሙ ሊጋልቡ ይችላሉ። አትላንቲክን ተሻግሮ በዲያስፖራው ላይ መጋለብ እንደማይቻል ግን የዘንድሮው የዲሲ ዝግጅት በቂ ምስክር ነበር። ከ 3,000,000,000 ዶላር በላይ ወጥቶ 700 ሰራተኞች እና ተጫዋቾች በቅጥር የተሰማሩበት የዲሲው አር.ኤፍ.ኬ ስታዲየም ባዶ ነበር። በቃ ባዶ!… ከኢትዮጵያ የተጋበዙ እንግዶች፡ አትሌቶች፣ አርቲስቶችና ታዋቂ ሰዎች ሁሉ እዚያኛው ሜዳ ድርሽ አላሉም። ሁሉም፡ የተገዙ ተጫዋቾችም ጭምር፤ ሜሪላንድ በመሄድ ከኢትዮጵያዊው ጋር በዓሉን  በፍቅር ማሳለፍን ነበር የመረጡት።

ከቅድም አያቶቻችን የወረስነው አረንጓዴ-ቢጫ-ቀይ ባንዲራችንን ይዞ መገኝት በዘመናችን ገዢዎች ወንጀል እንደሆነ ተነግሮናል። ዘንድሮ በዲሲ ያየነው ደግሞ ትንሽ እንግዳ ነገር ነው። የራሱ የገዢው ፓርቲ ደጋፊዎች በንግድ ስፍራዎቻቸው ባለኮከቡን የህወሃት ባንዲራ አውርደው ያልተበረዘውን ባንዲራ ሲሰቅሉ ታዝበናል። በዲሲ አር.አፍ.ኬ. ስታዲየምም ሆነ ተገንጣዮቹ በሚበትኑት ፍላየር ባለኮከቡ ባንድራ አልነበረም። ለግዜው አራዶች መሆናቸው ነው። ለጥቅም ሲሆን ሁሉም በባንዲራችን ይነግዳሉ። ብሄርተኝነት በኢኮኖሚ ጥቅም ይጠፋል ያለው ማን ነበር?…

ሁሉም ግምት ውስጥ የገቡ ይመስላል። እውነታው ግን አንድ ቦታ ላይ ነው ያለው። ገንዘብ ኢትዮጵያዊነትን አላሸነፈውም፣ አልገዛውምም። አንጋፋው ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ ስለዘንድሮው ዝግጅት እንዲህ አለ “የምናውቀው አንድ ድርጅት ብቻ ነው። ነባሩ ፌዴሬሽን። የኢትዮጵያን ህዝብ ለመክፋፈል የሚደረገውን ተንኮል ብልሁ የኢትዮጵያ ህዝብ በመፈቃቀር አክሽፎታል።”… አዲዮስ!

***

      “አንጃ” የሚለውን ቃል ቀደም ብዬ ሳነሳ ወዳጄ ዶ/ር ሼክስፒር ፈይሳ ታወሰኝ። እለተ-አርብ ከኢትዮጵያ ቀን ደማቅ ዝግጅት በኋላ ከሼክስፒር ፈይሳ እና ዳዊት ከበደ ጋር ከግቢ ስንወጣ ሜሮን አሃዱን ከበር ላይ አገኝናት። ሜሮን የአንጋፋው ጋዜጠኛ የአህዱ ሳቡሬ ልጅ ናት። ሼክስፒር የኢትዮጵያዊነት ውርስ እና ቅርስ በሰሜን አሜሪካ ሊቀ-መንበር በነበረ ግዜ በሁለቱ መካከል የተፈጠረ ቅራኔ እንዳለ ብንሰማም እንዲህ የተካረረ ጉዳይ አልመሰለንም ነበር። በመሃል የነበርነው እኔና ዳዊት ግን እንዲታረቁ ገፋፋናቸው። ሜሮን የሼክስፒርን ይቅርታ ጥያቄ አልቀበልም ብላ ብዙ ካንገራገረች በኋላ እኛን በማክበር ለመታረቅ ተስማማች እና ተቃቀፉ።

ከእርቁ በኋላ በጸቡ ዙሪያ መቀላለድ ጀመርን። እኔን ትንሽ ፈገግ ስላደረገኝ ነው እዚህ የምደግምላችሁ።

ጸቡን ያመጣው “አንጃ” የሚል ቃል ያለበት የሼክስፒር ኢሜይል ነበር። “ለመሆኑ አንጃ ማለት ምን እንደሆን ታውቀዋለህ?” ስትል ሜሮን ሼክስፒርን ጠየቀችው። “እኔ ምን አውቅልሻለሁ። ያው ፖሊቲከኞቹ የሚጠቀሙበት ቃል ስለሆነ ነው የጨመርኩት።” ሲል መለሰላት።

ሼክስፒር በሙያው እጅግ የሚደነቅ ችሎታ ያለው ለመሆኑ ብዙዎች ይመሰክሩለታል። ጨዋታና መዝናናትን ይወድዳል። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሀ-ሁ እንጂ ገና አቡጊዳው (shrowdity) ላይ የደረሰ ስለማይመስል ለፖለቲካ የሚሆን ሰው አይደለም።

የሜሮን ኢሜይል ምላሽ አንተ “ግልገል” አንባገነን የሚል ነበር። ሼክስፒር ለፈጸመው ድርጊት ይህ ምላሽ ተገቢ እንዳልነበር ተነጋገርን። በመጨረሻ ግን ግልገል የሚለው ሃረግ ብቻ እንዲነሳ ተስማማን። ሼክስፒርም በዚሁ ተስማማና ወደ ጃኖ ባንድ የምሽት ዝግጅት ተያይዘን አመራን።  … ጃኖዎች መድረክ ላይ በቲቪ እንደምናያቸው ሆነው አልተገኙም።

***

      …በመጨረሻም ዲሲን ተሰናብቼ ወደ ዳለስ አውሮፕላን ማረፍያ አመራሁ። ከበጀት የተከራየሁትን መኪና የተረከበኝ አንድ ሰውዬ ትኩር ብሎ ተመለከተኝና “ኢትዮጵያዊ ነህ?” ሲል በእንግሊዝኛ ጠየቀኝ። “አዎ” ስለው እሱም ኤርትራዊ መሆኑን ነግሮኝ አንድ ስለመሆናችን የሚደሰኩር ወሬ ብጤ ጀመረ – በተኮላተፈ አማርኛ። አዎ አንድ ነን አልኩት በልቤ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንዲህ የሚሉ በርካታ ኤርትራውያን አጋጥመውኛል። የሚገርምው ታዲያ ዛሬ እንዲህ የሚሉን፤ ከአመታት በፊት እኛን ለማናገር እንኳን ይጸየፉ የነበሩ ናቸው። ከኢትዮጵያ ለመለየት 99.9 በመቶ ድምጽ ሲሰጡ ምንም አላልናቸውም ነበር። ዛሬ የአፍሪካዋን ሲንጋፖር ሲጠብቁ ኤርትራችን “ሲንግል ኤንድ ፑር” ሆና መቅረትዋ የቆጫቸው ይመስላል። አዎ! ከትላንት ይልቅ ዛሬ አንድ ነን። ሁሉም ነገር ያልፋል፡ ፍቅር ያሸንፋል!

ላሁኑ በዚህ ላብቃ፡ በሚቀጥለው ጽሁፌ የ”አሲንባ ፍቅር”ን የመጽሃፍ ምረቃ ቅኝትና የመጽሃፉን ግምገማ ይዤ ብቅ እላለሁ።

ሜሪላንድ፡ ጁን 2013

Latest from Blog

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

Go toTop