November 27, 2015
7 mins read

ከመጠምጠም መማር ይቅደም | መስፍን ወልደ ማርያም [ፕሮፌሰር]

ኅዳር 2008

በፌስቡክ የምንሰባሰበው ለመወያየት፣ አንዱ ከሌላው እንዲማር፣ መረጃዎችን በነጻነት እንድንለዋወጥ፣ ይህንን ሁሉ በማድረግ ራሳችንን ለማሻሻል፣ የእኛ መሻሻል እየተራባና እየተባዛ የአገርና የሕዝብ መሻሻል እንዲሆን፣ ከተቻለንም ከአገራችንና ከሕዝባችን አልፈን የምንታይ የዓለም አካል እንድንሆን መስሎኝ ነበር፤ ሳየው በዚያ መንገድ ላይ ያለንና ፌስቡክን ለበጎ ዓላማ እየተጠቀምንበት ያለን አይመስለኝም፤ ስለዚህ ወይ መታረም፣ አለዚያም በፌስቢክ ጊዜ ማጥፋቱን መተው ምርጫ ሊሆንብን ነው፡፡

ምናልባት 99.99% በእኔ ሰፈር ያሉ የፌስቡክ ተሳታፊዎች ወደፌስቡክ የሚገቡት ለመናገር ነው፤ መናገር የህልውናቸው ምስክር ወይም ማረጋገጫ አድርገው የሚወስዱት ጥቂት አይደሉም፤ ካልተናገሩ የሌሉ ይመስላቸዋል፤ ዋናው ነገር መናገር ይሆንና የሚናገሩት ነገር ወይም ጉዳይ ሌላው ቀድሞ ከተናገረው ጋር የሚያያዝ (የሚቃወመው ወይም የሚደግፈው) ሳይሆን ፈጽሞ ወደተለየ ጉዳይ ውስጥ ገብቶ አዲስ ርእስ መክፈት የተለመደ ነው፤ የአብዛኛው ፍላጎት ማስተማር ወይም ማሳወቅ ነው፤ ማስተማር ወይም ማሳወቅ ቀላል ነው፤ መናገር የሚችል ወይም ፊደሉን አውቆ መጻፍ የሚችል ማስተማር ይችላል፡፡

የትምህርት ቤት ጓደኛዬ በጃንሆይ ዘመን ትልቅ ሚኒስትር ነበር፤ በደርግ ዘመን ለብዙ ዓመታት ታስሮ ሲወጣ ሥራ አልነበረውም፤ ችሎታውን ስለማውቅ በዩኒቨርሲቲ እንዲያስተምር አመቻቸሁለትና ማስተማር ጀመረ፤ ከጥቂት ወራት በኋላ ስንገናኝ ‹‹እኔ ማስተማር ቀላልና እረፍት የሞላበት ሥራ ይመስለኝ ነበር፤ ለካ አንቅልፍ የሚያሳጣ ነው! እዝናናለሁ ባልሁ ቁጥር አንድ ክፍል ሙሉ ተማሪዎች ተሰብስበው ዓይኖቻቸውን እያቁለጨለጩ ምን እንደማስተምራቸው ሲጠብቁ ይታዩኛል! እረፍት ይነሡኛል!›› አለኝ፤ ከአንድ ዓመት በኋላ ማስተማሩን ተወ፤ ኅሊና ላለው ሰው ማስተማር ቀልድ አይደለም፤ ያደክማል፤ ለማስተማር መማር ያስፈልጋል፤ ለማሳወቅ ማወቅ ያስፈልጋል፤ ከመማር ይልቅ ማስተማር፣ ለማወቅ ከመጣር ይልቅ ለማሳወቅ መጣር የሚቀልለው ሰው የእውቀት ሰው አይደለም፤ ሌላ ሥራ ቢመርጥ ይሻለዋል፡፡

ሳያውቁ ለማሳወቅ አደባባይ መውጣት ከችኮላ ወይም ከስንፍና፣ ከትዕቢት ወይም ከግዴለሽነት የሚመጣ ነገር ይመስለኛል፤ ውሎ አድሮ ይጎዳል እንጂ አይጠቅምም፤ በአደባባይ መናገር ወይም መጻፍ የመጨረሻው መጋለጥ ነው፤ በአደባባይ መናገርና መጻፍ በሕዝብ ፊት መጋለጥ መሆኑን ብዙ ሰዎች አያውቁም፤ በአንጻሩ ደግሞ ብዙ ሰዎች ይህንን መጋለጥ ፈርተውትና ሸሽተውት የሚርቁት አሉ፤ መጋለጥን ፈርተው ዓይኖቻቸውን ዘግተው፣ ጆሮዎቻቸውን ደፍነው፣ አፋቸውን ለምግብና ለመጠጥ በቀር የማይጠቀሙበት፣ ዝምታ ወርቅ ነው እያሉ ወርቅ የሚሸምቱበት ብዙ ናቸው፤ ከሕዝብ ጋር እየተጓዙ፣ በሕዝብ መሀል እየኖሩ የሕዝብ ጉዳይ (ፖሊቲካ) አይመለከተንም የሚሉ የማሰብ ችሎታቸውን ህልውና ይጠራጠሩ፤ የማሰብ ችሎታ ከሌለ የማወቅ አምሮት ወይም ምኞት የሚኖር አይመስለኝም፤ የማወቅ አምሮት በሌለበት የማሳወቅ አምሮት ጎልቶ ሲወጣና ሲደናበር ማየት በጣም የተለመደ እየሆነ ነው፤ ፌስቡክ የሚባለው መድረክ የመደናበሪያ መድረክ እየሆነ ነው፡፡

የማሰብ ችሎታው የሌላቸው ሰዎች ከሁለት አንዱን መንገድ በመምረጥ፣ ወይም በሁለቱም መንገዶች በመጠቀም ይሳተፋሉ፡– የማያውቁትን ለማሳወቅ በመሞከርና በዘለፋ! የማያውቁትን ለማሳወቅ መሞከርና ዘለፋ የባሕርይ ግንኙነት አላቸው፤ አሁን እዚያ ውስጥ አንገባም፤ በተለያዩ መስኮች፣ በተለያዩ ጉዳዮች፣ በተለያዩ የእውቀት ጥበቦች በሚያሰራጩት ፍንጥቅጣቂ በአእምሮና በመንፈስ ለመበልጸግ በመጣር ፈንታ በአጉል ትዕቢትና ፉክክር፣ በማይጠቅም ዘለፋና ማስፈራራት የፌስቡክን መድረክ ማበላሸትና ማርከስ ወደኋላ ይጎትተናል እንጂ ወደፊት አያራምደንም፡፡

መሠረታዊ የማሰብ መነሳችን ሳንገነዘብ የማሰብ ትርምስምስ ውስጥ እንገባና መውጣት ያቅተናል፤ ለምሳሌ በእውቀትና በእውነት መሀከል ያለውን ልዩነት ሳንገነዘብ እምነትን ስንሞግት የራሳችንንም ሆነ የሌላውን ጊዜ እናጠፋለን፤ እውቀትን በሙግት ለማጣራት ሲመጡብን ደግሞ ቶሎ ወደእምነት እንዞራለን፤ አጉል መሽከርከር ውስጥ እንገባለን፤

እንዲያው በሆነ ባልሆነው፣ ባወቅነውም ሆነ ባላወቅነው የመጣልንን ሁሉ መዘርገፍ አዋቂ አያሰኝም፤ ጎበዝ አያሰኝም፤ ብልህ አያሰኝም፤ ግን ባለጌ ያሰኛል፤ ባለጌ ነጻነትን አያውቅም፤ ለባለጌ ስድነት ነጻነት ይመስለዋል፤ ነጻነት ባለቤቱ ያጠረው ገደብ ወይም ወሰን አለው፡፡

Latest from Blog

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

Go toTop