Sport: ሆዜ ሞሪንሆ በቸልሲ ዳግም ይነግሱ ይሆን?

ከይርጋ አበበ
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2004 የፖርቹጋሉን ግዙፍ ክለብ ፖርቶ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግና የፖርቹጋል ሱፐር ሊግ ዋንጫዎችን ካስገኙለት በኋላ በሩሲያዊው ከበርቴ ሮማን አብራሞቪች የተያዘውን ቼልሲን ማሰልጠን ሲጀምሩ በዓለም ላይ ካሉ የስፖርቱ ተከታታዮች ጋር በስፋት ተዋወቁ – ጆዜ ሞሪንሆ።
ክለቡንም በአራት ዓመት ቆይታቸው ሰባት የተለያዩ የዋንጫ ድሎችን ያስገኙለት ሲሆን በተለይም ክለቡ ከ1950 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ እንዲቀዳጅ ማስቻላቸው በክለቡ ደጋፊዎችና ተጫዋቾች እንዲከበሩ አደረጋቸው። በምዕራብ ለንደኑ ክለብ አራት የውድድር ዘመናትን ካስቆጠሩ በኋላ ከክለቡ ባለቤት ሮማን አብራሞቪች ጋር መስመማት አለመቻላቸው ነበር ከቼለሲ ጋር የነበራቸውን እህል ውሃ ያሳጠረው።
በተለይ የ2007/08 የውድድር ዘመን የቼልሲ መጥፎ የውድድር ጅማሮ የአብራሞቪችን ፊት ያጠቆረ ነበር። ከቼለሲ እንዲሰናበቱ ምክንያት በነበረው የቪላፓርኩ የአስቶንቪላና የቼለሲ ጨዋታ በወቅቱ በማርቲን ኦኒየል ይሰለጥን በነበረው አስቶን ቪላ የደረሰባቸው ሽንፈት በስታንፎርድ ብሪጅ የሚኖራቸውን ቆይታ አሳጠረባቸው። በዚህ ጊዜ ቼልሲ በደረጃ ሰንጠረዡ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ነበር።
ከቼልሲ ጋር የነበረቸውን የውል ፊርማ ከቀደዱ በኋላ ወደ ጣሊያን አቅንተው የማሲሞ ሞራቲውን ኢንተር ሚላን በኋላም የስፔኑን ግዙፍ ክለብ ሪያል ማድሪድን በማሰልጠን ይታወቃሉ። በጣሊያኗ የፋሽን ከተማ ክለብ ቆይታቸው የጣሊያንን ሴሪአ፣ የጣሊያን ዋንጫና ግዙፉን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ክብር መቀዳጀት ችለዋል።
በተደጋጋሚ ጊዜ በቼልሲ ያላጠናቀቅኩት የቤት ሥራ አለኝ እያሉ የሚናገሩት ፖርቹጋላዊው የአምሳ ዓመት ጎልማሳው ሞሪንሆ ባለፈው ሳምንት ለምዕራብ ለንደኑ ክለብ አራት ዓመት በክለቡ የሚያቆይ ኮንትራት ተፈራርመዋል።
በ2007 መስከረም ወር ላይ ከክለቡ ሲሰናበቱ ሃዘናቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው በአደባባይ ዕንባቸውን ሲረጩ የታዩት ፍራንክ ላምፓርድና አምበሉ ጆን ቴሪ ከአምስት ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ ቀድሞ አሰልጣኛቸውን በማግኘታቸው ደስታቸው ከፍተኛ ሆኗል።
ራሳቸውን ስፔሻል ዋን ወይም ልዩው ሰው ብለው የሚጠሩት የቀድሞው የፖርቶ አሰልጣኝ ሞሪንሆ በ2004 ለቼልሲ እንደፈረሙ በመጀመሪያ ዓመት የእንግሊዝ ቆይታቸው በ38 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታቸው አንድ ጊዜ ብቻ ተሸንፈው ዘጠና ሰባት ነጥብ ሰብስበው ያነሱት ዋንጫ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ በከፍተኛ ነጥብ የተገኘ ዋንጫ ነው።
አሰልጣኙ ጨዋታን ከማሸነፋቸው በተጨማሪ ከመገናኛ ብዙሀን ጋር ያላቸውን አቀራረብ እንግሊዛውያን ጋዜጠኞች ይወዱላቸዋል። ለዚህም ነው የጆዜ ሞሪንሆን ወደ እንግሊዝ መመለስ አስመልክቶ የቢቢሲ ስፖርት ዘጋቢ ጎርደን ፋርኩየር ሚዲያው ያጣውን ተጽእኖ ፈጣሪ አገኘ ሲል የተናገረው።
ከመገናኛ ብዙሀን ጋር ያላቸውን አቀራረብ የእንግሊዝ ሚዲያዎች የሚወዱላቸው አወዛጋቢው አሰልጣኝ በጣሊያንና በስፔን ቆይታቸው ከጋዜጠኞች ጋር የነበራቸውን ግንኙነት አልወደዱትም ነበር።
ጆዜ ከሚታወቁበት አወዛጋቢ አስተያየታቸው መካከል ከተቀናቃኝ ክለብ አሠልጣኞች ጋር የሚፈጥሩት የቃላት ጦርነት ነው። በተለይ ከቀድሞው የሊቨርፑል አሰልጣኝ ራፋኤል ቤኔቴዝ፣ ከፈረንሳያዊው የአርሰናል አሠልጣኝ አርሰን ቬንገር እና ከማንቸስተር ሲቲው ሮቤርቶ ማንቺኒ ጋር የነበራቸው እሰጥ አገባ ለመገናኛ ብዙሀን ጥሩ የወሬ ጮማቸው ነበር።
ቼልሲ በ2005/06 የውድድር ዘመን በተከታታይ ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉን ዘውድ ሲደፋ ክለቡ ሰማኒያ ሚሊዮን ፓውንድ መክሰሩን አስመልክቶ አርሰን ቬንገር «ሰማኒያ ሚሊዮን ፓውንድ ከስሬ ቡድኔ ዋንጫ ከሚያነሳ ራሴን ሰማኒያ ሚሊዮን ማይል ከሚርቅ ባህር ብወረውር ይቀለኛል» ብለው ለሰጡት አስተያየት ፖርቹጋላዊው ለባላንጣቸው ሲመልሱ «የራሱን ስራ አቁሞ ሰው የሚሰራውን ለማየት ከቤቱ ስውር ካሜራ የገጠመ» ብለው ነበር የመለሱት።
በሮማን አብራሞቪች ስር ቼልሲን ማሰልጠን የቻሉ አሰልጣኞች፡
ሩሲያዊው ባለፀጋ የምእራብ ለንደኑን ክለብ እ.ኤ.አ. በ2003 ሃምሌ ላይ ጠቅልለው ከገዙበት ጊዜ ጀምሮ አስር አሰልጣኞች በክለቡ ተፈራርቀዋል። ከዚህ ቀጥሎ የተጠቀሱት አሰልጣኞች ቼልሲን ላለፉተ አስር ዓመታት ያሰለጠኑ ናቸው። ከእነዚህ አሰልጣኞች መካከል ግን እንደ ሞሪኒሆ በደጋፊዎች የተወደደና ውጤታማ አሰልጣኝ የለም፡፡
1.ክላውዲዮ ራኒየሪ ከመስከረም 2000 –
ግንቦት 2004
2. ጆዜ ሞሪንሆ ከግንቦት 2004 – መስከረም
2007
3. አብርሃም ግራንት ከመስከረም 2007 –
ግንቦት 2008
4. ሉይስ ፍሊፕ ስኮላሪ ከሃምሌ 2008 –
የካቲት 2009
5. ጉስ ሄዲኒክ ከየካቲት 2009 -ግንቦት
2009
6. ካርሎ አንቼሎቲ ከሰኔ 2009 – ግንቦት
2011
7. አንድሪ ቪያስ ቦአስ ከሰኔ 2011 –
መጋቢት 2012
8. ሮቤርቶ ዲማቲዮ ከመጋቢት 2012 –
ህዳር 2012
9. ራፋኤል ቤኔቴዝ ከህዳር 2012 –
ግንቦት2013
10. ጆዜ ሞሪንሆ በደጋሚ ከሰኔ 2013 –

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሁለት እግርና አንድ እጅ አልባዋ የዋና ሻምፒዮን

1 Comment

Comments are closed.

Share