June 10, 2013
35 mins read

አዲስ ጉዳይ መጽሔት፡ “የመጀመሪያው ድምፅ” ዕድሎቹና ፈተናዎቹ

(ይህ ጽሁፍ ዛሬ አዲስ አበባ ላይ ታትሞ በወጣው አዲስ ጉዳይ ላይ የታተመ ነው። የዘ-ሐበሻ አንባቢዎችም ለምን ይቅርባቸው በሚል የቀረበ ነው።)
“የመጀመሪያው ድምፅ”
ዕድሎቹና ፈተናዎቹ

ባለፈው እሑድ በሰማያዊ ፓርቲ የተጠራውና ከምርጫ 97 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሔደው ታላቅ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ በሺሕ የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች አዛውንቶች፣ ጎልማሶች፣ ወጣቶችና ታዳጊዎች ጭምር ተሳትፈውበት በሰላም ተጠናቋል፡፡ የተቃውሞ ሰልፉን የሀገር ውስጥና በርካታ የውጭ ሚዲያዎች ሰፊ ሽፋን ሰጥተው ዘግበውታል፡፡ ነገር ግን የዚያኑ ዕለት ማታ መንግሥትን ወክለው በተናገሩት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል እና በማግስቱ በፋና ሬዲዮና በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የቀረቡት የኢህዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሬድዋን ሁሴን የተቃውሞ ሰልፉ ‹‹የፓርቲውን ፀረ ሕገ መንግሥታዊ እንቅስቃሴ ያጋለጠ ነው›› የሚል ትችቶች አቅርበዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም መንግሥት በሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና እና አባላት ላይ ዘመቻ የከፈተ በሚያስመስለው መልኩ የሰነዘራቸው አስተያየቶች ክስ ሊመሰርትባቸው ነው የሚለውን በስፋት የሚነገር ወሬ አጠናክረውታል።

የተቃውሞ ሰልፉ መነሻና መድረሻ

የሰማያዊ ፓርቲ ግንቦት 17 ቀን 2005 ዓ.ም በአፍሪካ ኅብረት ጽሕፈት ቤት ፊት ለፊት ተቃውሞ ሰልፍ እንዲደረግ ሕዝባዊ ጥሪ አስተላልፎ ነበር። የተቃውሞ ሰልፉን ለማድረግ የታቀደው የአፍሪካ ኅብረት 50ኛ ዓመት በዓሉን በሚያከብርበት ዕለት ነው። ዕለቱን ፓርቲው ለተቃውሞ ሰልፍ የመረጠበትን ምክንያት ‹‹የኢትዮጵያን ሕዝብ ብሶትና አፈና ለዓለምአቀፉ ኅብረተሰብ ይበልጥ ግልጽ በማድረግ በኩል ቀኑ አስተዋጽኦ ቀኑ የሚኖረው በመሆኑ ነው፡፡›› በማለት ገልጾ ነበር፡፡ ለ ሦስት ቀናትም ሕዝቡ ጥቁር እንዲለብስ ጥሪ በማድረግ በሰላማዊ ሰልፉ ዕለት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማኅበረሰቡ ተቋማትና ኢትዮጵያውያን ሁሉ በሕጋዊውና ሰላማዊው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ ቢያቀርብም የተቃውሞ ሰልፉን ማሳወቂያ ደብዳቤውን የሚቀበል ሰው ሳያገኝ መቅረቱን አስታውቋል። ሰማያዊ ፓርቲ ደብዳቤ የሚቀበለኝ ባላገኝም ሰልፉን ከማድረግ አልመለስም የሚል መግለጫ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም የዚያኑ ዕለት ምሽት በመገናኛ ብዙኀን የቀረቡት የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ‘የፀጥታ ኃይሎች እጥረት ስላለና መንግሥት በዚህ ወቅት ለፓርቲው ሰልፍ ጥበቃ ማድረግ ስለማይችል’ ፓርቲው ሰልፉን ከሳምንት በኋላ ማድረግ እንደሚችል በማሳወቃቸው በሳምንቱ እሑድ ዕለት የተቃውሞ ሰልፉ ሊከናወን በቅቷል፡፡

የተቃውሞ ሰልፉን ከጠራው ከሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት መነሻቸውን ያደረጉት በሺሕ የሚቆጠሩት የተቃውሞ ሰልፈኞቹ በአራት ኪሎ በኩል ወደ ፒያሳ በማቅናት በችርችል ጎዳና አድርገው ወደ ተቃውሞ ሰልፉ ማሳረጊያ ኢትዮ—ኩባ ወዳጅነት መንገድ አቅንተዋል፡፡ የተቃውሞ ሰልፈኞቹ ሥርዐት በተሞላበት መንገድ የተለያዩ መፈክሮችን እያሰሙ፣ በኅብረ ዝማሬ ‹‹ሰላማዊ ነን ተቀላቀሉን›› በማለት ግራና ቀኝ ቆሞ የተቃውሞ ሰልፉን ይከታተል የነበረውን ሕዝብ የሰልፉ ተሳታፊ እንዲሆን ሲጋብዙ ነበር፡፡

የተቃውሞ ሰልፈኞቹ በአራት ኪሎ በሚገኘው የድል ሐውልት አደባባይ፣ ራስ መኮንን ድልድይ ፣ መሐል ፒያሳ ደጎል አደባባይ፣ ቸርችል ጎዳና እና የተቃውሞ ሰልፉ ማብቂያ በነበረው ኢትዮ —ኩባ ወዳጅነት ወይም የጥቁር አንባሳ ድላችን ሐውልት በሚገኝበት ሥፍራ ላይ ጥያቄያቸውን በስፋት አስተጋብተዋል፡፡ በሥፍራው ተገኝቶ እንደታዘበው ዘጋቢያችን ከሆነ ለጥበቃ በቦታው ላይ በርካታ ፖሊሶች የነበሩ ቢሆንም ሰልፈኞቹ ያለምንም መተረማመስም ሆነ አንዳችም ግጭት ውስጥ የሚያስገባ ነገር ሳይፈጽሙ ‹‹ፖሊስ የሕዝብ ነው!›› የሚለውን መፈክር በማሰማት ከመነሻው ግንፍሌ አካባቢ እስከ ተቃውሞ ሰልፉ ማብቂያ ኢትዮ—ኩባ ወዳጅነት ድረስ ብዙ ሺሕ ሰዎች የተሳተፉበት ነገር ግን ምንም የተለየ ብጥብጥ ያልተሰማበት የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደው ለማጠናቀቅ በቅተዋል፡፡

የተቃውሞው ሰልፍ ገጽታ

እሑድ ዕለት በተከናወነው የተቃውሞ ሰልፍ፤ “የኅሊና እስረኞች የሆኑት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና ጋዜጠኞች እንዲፈቱ፣ ሰዎችን በዘራቸው እየለዩ ከሚኖሩበት ይዞታቸው ማፈናቀሉ እንዲገታ፣ መንግሥት በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ መግባቱን እንዲያቆም እና በሙሰኞች ላይ እርምጃ እንዲወስድ” የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎች ቀርበዋል።

በተቃውሞ ሰልፉ ላይ ተሳታፊው ሕዝብ ብሶቱን በስፋት ያሰማ ሲሆን፤በዕለቱ ከተንጸባረቁት መፈክሮች መካከል ‹‹የፖለቲካ እና የኅሊና እስረኞች በአስቸኳይ ይፈቱ!››፣ ‹‹በጥፊ በርግጫ አይገዛም ሀገር››፣ ‹‹መንግሥት የለም ወይ››፣ ‹‹ወኔ የሌለው የሀገር ሸክም ነው፡፡››፣ ‹‹ፍትሕ እያሉ ቃሊቲ ገቡ››፣ ‹‹ውሸት ሰለቸን!››፣ ‹‹ተከብረሽ የኖርሽው ባባቶቻን ደም (2) እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውደም!››፣ ‹‹የኑሮ ውድነት ያጎበጠው ትከሻችን እረፍት ይሻል!”፣ “ሕገ መንግሥቱን የሚጻረሩ አፋኝ ዐዋጆች ይሻሩ፤ ይሰረዙ!›› “በሕገ መንግሥቱ የሌለውን የሃይማኖት ጣልጋ ገብነት እናወግዛለን!” የሚሉ እና ሌሎችም መሰል የሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብትን የሚጠይቁ መፈክሮች ተስተጋብተዋል፡፡

የተቃውሞ ሰልፉ ተሳታፊዎች እጃቸውን በማቆላለፍ ታስረናል ምልክት ያሳዩ ሲሆን ‹‹ሰላማዊ ነን ተቀላቀሉን! ›› በማለትም ሌሎች ግራ እና ቀኝ ቆመው የነበሩ ሰዎችን ለተቃውሞው ሰልፍ ጋብዘዋል፡፡ በሺሕ የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የተሳተፉበት የተቃውሞ ሰልፍ በኢትዮ ኩባ ወዳጅነት አደባባይ የሰማያዊ ፓርቲ ተወካይ፣ የሕግ ምሁሩና ፖለቲከኛው ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም፣ ከቤኒሻንጉል የተፈናቀሉ ወገኖች ተወካይ እና ሌሎችም ንግግር ካደረጉ በኋላ ተጠናቋል፡፡ በሥፍራው ከነበሩ ሪፖርተሮቻችንና ከተሳታፊዎቹ በደረሰን መረጃ መሠረትም ምንም ዓይነት ሁከት አለመከሰቱ ታውቋል፡፡
ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም‹‹በዚህ በ21ኛው ክ/ዘመን ሰዎች በሌላው ዓለም ሙሉ ነጻነታቸውና ዴሞክራሲያዊ መብታቸው ተጠብቆላቸው ሕይወታቸውን ሲመሩ፤በእኛ ሀገር ግን የየዕለቱ ወሬ ‘እከሌ ታሰረ’፣ ‘እከሌ ዕድሜ ልክ ተበየነበት’ የሚል ነው›› በማለት ምሬታቸውን ለተሳታፊው ያሰሙ ሲሆን ይሄ ነገር መለወጥ አለበት ብለዋል፡፡

በጥቅሉ በተቃውሞ ሰልፉ ላይ “የጋዜጠኝነት ሙያቸውን በአግባቡ በመወጣታቸው የተወነጀሉ ጋዜጠኞች ከእስር ይፈቱ፣ በቅርቡ በቤንሻንጉል ክልል እንግልት የደረሰባቸው የአማራ ክልል አርሶ አደሮች ጉዳይን መነሻ በማድረግ የሀገሪቱን ዜጎች በዘር ለይቶ ከመኖሪያ ቀዬያቸው ማፈናቀሉ የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው፣ በአሸባሪነት ተጠርጥረው የታሰሩ የፖለቲካ መሪዎችና የሕዝበ ሙስሊሙ የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ይፈቱ፣ የኑሮ ውድነት የሚቀረፍበት ፖሊሲ ይቀረጽ፣ ተዘዋውሮ የመሥራት ነጻነት ይከበር፣ ሕገ መንግሥቱን የሚቃረኑ አፋኝ አዋጆች ይሰረዙ፣ በሙሰኞች ላይ ተገቢ እርምጃ ይወሰድ፣ ውሸት ሰለቸን(የመንግሥት ሚዲያን የሚያወግዙ)’’ ሐሳቦች በስፋት ተንጸባርቀዋል፡፡

የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ትኩረትን ያገኘው የተቃውሞ ሰልፍ

በታላላቅ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች “ከስምንት ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የተቃውሞ ሰልፍ ተካሔደ” የሚል ሐሳብ የያዙ በርካታ ዜናዎችን የዘገቡ ሲሆን፤ሮይተርስ የተቃዋሚ ሰልፈኞቹ አኀዝ ዐሥር ሺሕ እንደሚደርስ ገምቷል፡፡ በበይነ መረብ ላይ ይሄው ጉዳይ የአፍሪካ ኅብረትን አከባበር ተከትሎ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ የላቀ ሽፋን የተሰጠው ሲሆን፤በጉግል የመረጃ ማፈላለጊያ ላይ በኢትዮጵያ የተካሔደውን የተቃውሞ ሰልፍ አስመልክቶ የዜና መረጃ ለማግኘት የሚሞከር ሰው በ0.21 ሰከንድ ውስጥ ብቻ ከ1 ሚሊዮን 919 ሺሕ በላይ መረጃዎች ከጉግል ይቀርቡለታል፡፡ ይሄ በበይነመረብ ላይ መረጃ በዚህ መጠን የማግኘት ልኬት የተቃውሞ ሰልፉ ምን ያህል ሰፊ ትኩረት እንዳገኘ የሚጠቁም ነው፡፡

በዋነኛነት እንደ ቢቢሲ፣ አሶሲየትድ ፕሬስ፣ አልጀዚራ፣ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ፣ ቪኦኤ፣ ዋሽንግተን ፖስት፣ አፍሪካን ሪቪው እና ኤቢሲን የመሳሰሉ ታላላቅ የሚዲያ ተቋማት ለተቃውሞ ሰልፉ ሰፊ የሆነ ሽፋን ሰጥተው ዘግበዋል፡፡ አሶሺየትድ ፕሬስ ‹‹በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ለተቃውሞ አደባባይ ወጡ፡፡ መንግሥት ጋዜጠኞችን፣ አራማጆችን (አክቲቪስቶችን)፣ የሙስሊሙ ማኅበረሰብ አመራሮችን ካልፈታ እንዲሁም ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጣረሱ ሕጎች ካልተሻሩ በቀር ተቃዋሚዎቹ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ሌላ የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚጠሩ አስጠንቅቀዋል፡፡›› በማለት ሰፊ ሽፋን ለጉዳዩ ሰጥቷል፡፡

የቢቢሲው የአፍሪካ የፖለቲካ ተንታኝ ሪቻርድ ሐሚልተን የተቃውሞ ሰልፉን ለማካሄድ በኢትዮጵያ በኩል መንግሥት መፍቀዱ መልካም እርምጃ መሆኑን በማውሳት ለተቃውሞ ሰልፉ ፍቃድ መገኘት ከቀድሞው የሀገሪቱ መሪ ይልቅ አዲሱ መሪ ተቃውሞን ለማድመጥ የተሻለ ታጋሽ መሆናቸውን ያሳያል የሚል ሰፊ ትንታኔ አቅርቧል፡፡ ይሁን እንጂ ከመንግሥት በኩል የተሰጠው የተቃውሞ ሰልፉ ምላሽ ግን ከፖለቲካ ተንታኙ ሪቻርድ ግምት በተቃራኒው የሆነና የተቃውሞ ሰልፉን ያዘጋጀውን ፓርቲ የሚወነጅል ሆኗል፡፡

ዓለም አቀፍ ሚዲያ ተቋማቱ በጥቅሉ ሰልፉ ከምርጫ 97 በኋላ የተካሔደ የመጀመሪያው ሰልፍ መሆኑን ካተቱ በኋላ በተለይ የኢትዮጵያ መንግሥት የፀረ- አሸባሪነት ሕጉን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን፣ ጋዜጠኞችንና ፖለቲከኞችን ለመወንጀል ይጠቀምበታል በሚል ተደጋጋሚ ክስ እንደሚያቀርቡበት በማስታወስ እንደ ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች ጥበቃ ኮሚቴ (CPJ) መረጃ ከሆነ ሀገሪቱ ኤርትራን በመቅደም በርካታ ጋዜጠኞችን ከአፍሪካ በማሰር በአንደኝነት ደረጃ ለመቀመጥ መቃረቧን ጠቁመዋል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ በሃይማኖት አክራሪነት አጀንዳ መወንጀል

በሰማያዊ ፓርቲ የተጠራው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ምንም እንኳን ብዙዎች ከገመቱት ውጪ ከተጠበቀው በላይ ብዙ ሺሕ ሕዝብ ታድሞበት፣ ያለአንዳች ችግር በሠላም መጠናቀቁ ቢታወቅም፣ የተቃውሞ ሰልፉ ከተደረገበት ቀን አንሥቶ በተለይ ከመንግሥት ሚዲያዎች ዐይን ያወጣ ሊባል የሚችል የወገንተኝነት አዘጋገብ ተስተውሏል። ይህም በቦታው ጉዳዩን የታዘቡ ሰዎች የመንግሥት ሚዲያዎች ወገንተኝነትና እውነትን አጣምሞ የማቅረብ አካሔድን እንዲተቹ አድርጓቸዋል።
ዘገባዎቹ በምስል በታገዘ አቀራረባቸው የተቃውሞ ሰልፉን ገጽታዎች ቆንጽሎ በማቅረብ አንድ ጉዳይ ላይ ብቻ ያተኮሩ እንዲመስሉ ለማድረግ ጥረዋል። የተቃውሞ ሰልፉ ፀረ ሕገ መንግሥታዊ አካሔድ መሆኑን በመግለጽ በተለይም ከገዢው ፓርቲ አመራሮች እና ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር የተደረጉ ቃለ ምልልሶች የተቃውሞ ሰልፉ ዓላማውን የሳተ እና ሃይማኖትና ፖለቲካን የቀላቀለ ነው ወደሚል ሰፊ ትችት ወስዶታል፡፡ ነገር ግን የተቃውሞ ሰልፉ በተካሔደበት ዕለት ምንም እንኳን በርካታ ሙስሊሞች ተሳታፊ ቢሆኑና ቅሬታቸውን በዚህ አጋጣሚ ለማሰማት ቢሞክሩም በሺሕ የሚቆጠሩ የሌሎችም ሃይማኖት ተከታዮች በተቃውሞ ሰልፉ ላይ ተገኝተው የሚቃወሙባቸውን ጉዳዮች ይፋ አደርገዋል፡፡ ምንም እንኳን የተቃውሞ ሰልፈኞቹ በሃይማኖት ቢለያዩም በሐሳብ አንድ መሆናቸውን ለመጠቆም ‹‹እዩ ተመልከቱት፣ የሕዝቡን አንድነት›› የሚልን ኅብረ ዝማሬ በማሰማት ሙስሊሞች፣ ክርስቲያኖች ሆነ ሌላም የተለየ አመለካከት ያላቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በተቃውሞ ሰልፉ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ሆኖም ግን ‹‹የሃይማኖት አክራሪነትን አጀንዳው አድርጎ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሰማያዊ የፖለቲካ ፓርቲ ፀረ ሕገ መንግሥታዊ እንቅስቃሴው ዛሬ በጠራው ሰልፍ ተጋልጧል፡፡›› ብሎ ኢህአዴግ እንደሚያምን የግንባሩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሬድዋን ሁሴን ለፋና ራዲዮ አስታውቀዋል። አያይዘውም በሰልፉ በአብዛኛው የተንጸባረቀው የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ይፈቱ እየተባለ መስተጋባቱ፣ ፓርቲው ሕገ መንግሥቱን በመጣስ በሃይማኖት እጁን መክተቱና በሕግ የበላይነት አምናለሁ እያለ በፍርድ ቤት ጉዳያቸው የተያዘባቸው ሰዎች በሁካታ ይፈቱልን ማሰኘቱ ተጠያቂ ያደርገዋል ብለዋል አቶ ሬድዋን።

የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት በበኩላቸው ከኢህአዴግ በኩል የቀረበውን ክስ አስመልክቶ ከአዲስጉዳይ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ በተለይ አቶ ሬድዋን ሰማያዊ የፖለቲካ ፓርቲ የሃይማኖት አክራሪነትን አጀንዳው አድርጎ ሲንቀሳቀስ የነበረ ነው ሲሉ ለሰጡት አስተያየት ምላሻቸውን እንዲህ ሲሉ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹አቶ ሬድዋን ፓርቲውን ከመክሰስ በተጨማሪ በሰልፉ ላይ የተገኙት ሰዎች ቁጥር ከአንድ ሺህ እና ሁለት ሺህ አይበልጡም ብለው ተናግረዋል፡፡ ይሄ በዐይን የታየ ጉዳይን ሆን ብሎ ለማንቋሸሽ የተካሔደ ነገር ነው፡፡›› ብለዋል። አያይዘውም ‹‹ከዚህ ውጪ የሕዝቡን የተቃውሞ ሰልፍ ለማንቋሸሽ እየተደረገ ያለው ሙከራ የሚያሳየው ኢትዮጵያን የሚመሩት መሪዎች ምን ያህል ከሕዝቡ እንደተራራቁ ነው፡፡›› በማለት ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል። ኢንጂነር ይልቃል ፓርቲው ላይ የቀረበውን ውንጀላ እንደማይቀበሉት ነው ያሳወቁት፡፡ ‹‹ኢህአዴግ ግራ ዘመም አስተሳሰብን የሚያራምድ በመሆኑ ሁሉንም ነገር መቆጣጠር ይፈልጋል፡፡ በዚህ የተነሣም የእስልምና ሃይማኖትንም የራሱን ሰዎች አስቀምጦ በሚፈልገው መንገድ ለመንዳት ፈልጓል፡፡ ነገር ግን ለእውነትና በሐቅ ለሃይማኖታቸው የቆሙትን እንዲሁም ለፓርቲው አናደገድግም ያሉትን አሸባሪ ብሎ እየጠራቸው ነው፡፡ በእርግጥ እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ እውነትን የተናገሩ ጋዜጠኞች፣ ሕዝቡን ማስተባበር የቻሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም አሸባሪ እየተባሉ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ትክክለኛ ሰው የሚባለው ለጥቅም ብሎ ከኢህአዴግ ጋር የሚኖር እና የሚዋሽ ብቻ ነው፡፡›› በማለት ተናግረዋል፡፡ በፓርቲው በኩልም “ከኢህአዴግ ውንጀላ በተቃራኒ በሃይማኖት ውስጥ ችግር አለ እስከተባለ ድረስ ና የታሰሩ ሰዎች እስኪፈቱ ድረስ ትግሉን እንቀጥላለን” ሲሉ ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡

የኢህአዴግና መንግሥት መንታ ምላሽ

የኢህአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሬድዋን ሁሴን የተቃውሞ ሰልፉን ‘ፀረ ሕገ መንግሥታዊ ነው’ ብለው እንደፈረጁት ሁሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማልም ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ በጠራው ሰልፍ የተንፀባረቁት መፈክሮችና ቅሬታዎች ሕገ መንግሥቱ በፖለቲካና በሃይማኖት መካከል ያስቀመጣቸውን የልዩነት መስመር የጣሱ ናቸው፡፡ የሰልፉ ተሳታፊዎች በሽብርተኝነት ተጠርጥረው የተያዙና ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ያሉ ግለሰቦች ይፈቱልን ብለው ያቀረቡት ጥያቄ የሕግ ሥርዐቱን መሠረት ያልጠበቀ ነው፡፡›› በማለት የተቃውሞ ሰልፉ ሂደት ትክክል አልነበረም የሚል አንደምታ ያለው ውንጀላ አቅርበዋል።

ሰማያዊ ፓርቲ የጠራው የተቃውሞ ሰልፍ ግንቦት 25 ቀን 2005 ዓ/ም በአዲስ አበባ ከተካሔደ በኋላ ከኢህአዴግ ፓርቲም ሆነ ከመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የተገኘው ምላሽ ተመሳሳይ ነበር፡፡ ከሁሉም ረገብ ያለ አስተያየት የሰጡት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትሩ አቶ በረከት ስምዖን ናቸው፡፡ ሚኒስትሩ በተለይ ከአሶሺየትድ ፕሬስ ለቀረበላቸው ጥያቄ ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጠቀማቸው ምንም ቅሬታ እንደሌላቸው ይፋ አድርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ ‹‹የተቃውሞ ሰልፈኞቹ ወንጀል ሠርተው የታሰሩ ሰዎች ይለቀቁ ማለታቸው ግን ሥነ ምግባር የጎደለውና ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡›› ሲሉ ምላሽ ተናግረዋል፡፡ የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ ለሚለው በአስር ሺሕ ለሚቆጠሩት ሰልፈኞች ጥያቄም ‹‹የፖለቲካ እስረኞች የሉም፡፡ ወንጀል ሠርተዋል ተብለው የተከሰሱ ሰዎች ብቻ ናቸው በእስር ላይ የሚገኙት›› በማለት ምላሻቸውን የሰጡት ሚኒስትሩ አቶ በረከት ወደፊትም ተመሳሳይ የተቃውሞ ሰልፍ ቢካሔድ ቅር እንደማይላቸው ለኤፒ ገልጸዋል፡፡

በመንግሥት በኩል ‹‹ሰልፈኞቹ ያቀረቡት ጥያቄ የሕግ ሥርዐቱን መሠረት ያልጠበቀ ነው፡፡›› የሚለውን ወቀሳ መሠረት በማድረግ የተቃውሞ ሰልፉን የጠራው የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል አስተያየታቸውን ለአዲስጉዳይ ሲሰጡ ‹‹በእኛ በኩል ኢህአዴግ እያደረገ ያለው የተቃውሞ ሰልፉን ማጥላላት አሁንም ፓርቲው የመማር ዕድል እንደሌለው ማሳያ ነው›› ብለዋል፡፡ ኢንጂነር ይልቃል አክለውም ‹‹እኛ እኮ ‘ኢህአዴግ እንደ ፓርቲ የሀገር ጉዳይ የሚሰማው ነው፡፡ ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ጊዜ ያሻዋል’ በሚል ነበር በዛ ሁሉ ሕዝብ ሀገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ እንዲያውቀው ጥያቄ ያቀረብነው፡፡ ነገር ግን የፖለቲካ መሻሻል እንዲያደርግ በዚህ ሁሉ የሕዝብ ቁጥር ጥያቄ መቅረቡን አምነውና የኢትዮጵያ ሕዝብ የተከበረ መሆኑን አውቀው ማጥላላቱን ትተው ምላሹን ቢያስቡበት ነው የሚሻለው፡፡›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በተለይ ሰማያዊ ፓርቲ የጠራውን የተቃውሞ ሰልፍ ተከትሎ በመንግሥት የተሰጠውን ማስፈራሪያ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና የሕግ ባለሙያዎች ውድቅ አድርገውታል፡፡ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አንድ ታዛቢ መንግሥት በፍርድ ቤት ጣልቃ የማይገባ ከሆነ ‹‹ስለምን ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ከተያዘ ተጠርጣሪዎች ጋር የሚገናኝ እና እነርሱን ወንጀለኛ አድርጎ የሚያስፈርጅ “አኬልዳማ” እና “ጀሃዳዊ ሃራካት” የሚል ዶክመንተሪ ፊልም አሠርቶ ለዕይታ ቀረበ?፤ የመጀመሪያው “አኬልዳማ” ስሕተት ቢሆን እንኳን ስለምን ይሄን ዓይነቱን በሕግ የሚያስጠይቅ ጥፋት ሕግ አስከባሪው “ጀሃዳዊ ሃራካት”ን በመሥራት በድጋሚ ሌሎች ተጠርጣሪዎች ላይ ሠርቶ ሕጉን ጣሰ”? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

የተቃውሞ ሰልፉ በተካሐየደበት ዕለት በአካል ተገኝተው ንግግር አድርገው የነበሩት ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም የተቃውሞ ሰልፉ በመንግሥት ባለሥልጣናት መወንጀሉን ተከትሎ ለአዲስጉዳይ በሰጡት አስተያየት ‹ሕዝቡ ከ8 ዓመታት በሁዋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀዳጀው መብት መሆኑን ገልጸው፣ ሕገመንግሥቱን የጣሰው መንግሥት እንጅ ፓርቲው ወይም እርሳቸው አለመሆናቸውን ተናግረዋል። በተመሳሳይ መልኩ ሁለት ታዋቂ ሕግ ባለሙያዎች መንግሥት ያቀረበውን ውንጀላ ውድቅ አድርገውታል። የድምፃችን ይሰማ የሙስሊም አመራሮችን የፍርድ ቤት ጉዳይ የያዙት አቶ ተማም አባቡልጋ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው ተቃውሞአቸውን የማሰማት መብት እንዳላቸው ገልጸዋል። “የእኛ ደንበኞች የሕገመንግሥት መብታቸው በመጣሱ አመለካከታቸውን በተቃውሞ ማቅረባቸው መብታቸው ነው” ያሉት አቶ ተማም፣ ሕገወጥ የሚሆነው ሰዎች ለምን መብታችሁን ገለጻችሁ ተብለው እንዲሸማቀቁ መደረጋቸው ነው ብለዋል።
የታሳሪዋ ጋዜጠኛ ርእዮት ዓለሙ አባት፤ አቶ ዓለሙ ጎቤቦ በበኩላቸው ሕግ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግን እንደማይከለክልና በፍርድ ቤት ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ አለመኖሩን ገልጸው መንግሥት ሕዝቡን ለማስፈራራትና ሐሳቡን እንዳይገልጽ ለማድረግ የወሰደው እርምጃ ሊሆን ይችላ ብለዋል፡፡

‘የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ላይ ክስ ይመሠረታል’ ስለተባለው ጉዳይ

ግንቦት 25 በተካሐየደው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ሬድዋን ‹‹ፓርቲው ያዘጋጀውን ሰላማዊ ሰልፍ ላልተፈለገ ዓላማ አውሎታል፡፡ በሰልፉ በአብዛኛው የተንጸባረቀው የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ይፈቱ እየተባለ መስተጋባቱ፣ ፓርቲው ሕገ መንግሥቱን በመጣስ በሃይማኖት እጁን መክተቱና በሕግ የበላይነት አምናለሁ እያለ በፍርድ ቤት ጉዳያቸው የተያዘባቸው ሰዎች በሁካታ ይፈቱልን ማሰኘቱ ተጠያቂ ያደርገዋል፡፡›› በማለት አስተያየታቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ ገብተዋል የሚል ክስ ሊመሠረትባቸው ነው የሚል ወሬ በስፋት እየተሰራጨ ነው፡፡ ስለ ክሱ ጉዳይ ምንም የሚያውቁት ነገር አለመኖሩን የጠቆሙት ኢንጂነሩ ‹‹ ኢህአዴግ እኛን ማሰር ከፈለገ መክሰስ አያስፈልገውም፡፡ ሰብስቦ ሊያስረን ይችላል፡፡ ይሄን እኛ ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡ እኛ የክስም ሆነ የእስር እርምጃው ያን ያህል አያሳስበንም፡፡ ከዚህ ይልቅ እኛን የሚያሳስበን የሀገሪቱ ሁኔታ ነው፡፡ የወጣት ሥራ አጡ ቁጥር፣ የዜጎች አላግባብ መታሰር፣ ለሁለት ዓመታት ያለአግባብ በሃይማኖታቸው ነጻነት ውስጥ ጣልቃ የተገባባቸው ዜጎች ጉዳይ ነው እኛን በእጅጉ የሚያሳስበን…›› ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡

brother africa ethiopia
Previous Story

ስለቤቲና የወሲብ ጉዳይ – ኣብርሃ ደስታ (ከመቀሌ)

EthiopiaBlueNileFalls
Next Story

የአባይ ኢትዮ-ግብጽ ጦርነት ወይንስ የነፃነት ትግላችን!

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop