ካንዳንድ ወዳጆቼ ጋ ሳወራ ፣ ” ግን ሄኖክ በትግሉ ተስፋ ቆርጠሃል ማለት ነው ? ” የሚል ጥያቄ ይጠይቁኛል ። እኔ ሲጀመር መቼ ተስፋ አድርጌ አውቃለሁ ? “ያለውን ትግል ከማዳፈን አብሮ ሆኖ ስህተቱን ማረም ነው የሚሻለው” የሚል መልካም አስተያየቶችም ደርስውኛል ። እርግጥ ያ ቢሆን ማን ይጠላል ? ሳይማር ያስተማሩን ገበሬ አባቶቻችን ፣ ሳይሰሙ ስሙን የሚሉ ልጆች ወለዱ ። ሳይታገሉ ፣ የሚያታግሉ ወንዶች ልጆች አባቶች ሆኑ ። የነሱ ስቃይ በምን እና በማን ይገለጽ ? አፈር ፈጭተው ሰው ያደረጉን እኛ የነሱ ልጆች ፣ ወሬ ፈጭተን ፣ ሰው ልናደርጋቸው አሰብን ። እኛ ያባቶቻችን ልጆች ነን ? ።
ሄኖክ ተስፋ አትቁረጥ ይሉኛል ። ተስፋ የሚያስቆርጥ ምን አዲስ ነገር ? ተስፋ የሚሰጥስ ነገር አለን ? እኛ ስለ ተስፋ እናውቃለን ? ተስፋ ያለው ሕዝብ እኮ ቢያንስ እምነት አለው ? ቢያንስ ተስፋ ያለው ሕዝብ ጽናት አለው ። ተስፋ ለመቁረጥም ሆነ ተስፈኛ ለመሆን ምን አዲስ ነገር አለና ።
ስለ እውነት እኛ ኢትዮጵያኖች ተስፋን አልረሳነውምን ? እስራዔላውያኖች ከግብጽ ወደ ከነዓን ሲጏዙ ተስፋ የሆናቸው መጏዛቸው እኮ አይደለም ፣ ተስፋ የሆናቸው ሀገር እንዳላቸው ማወቃቸው ነው ። ስንቶቻችን ነን ሀገር እንዳለን ትዝ የሚለን ? የምናውቀው ? አንድ ቀን እንገባለን ብለን የምናስበው ? እኛ ተስፋን ረስተነዋል ፣ ምክንያቱም ተስፋ እኛን ስለረሳን ።
አንዳንዴ መከራችን ሲደራረብ ፣ ሃዘናችን ሲበረታ ፣ ፊታችንን ወደ እግዚአብሔር እናዞራለን ፣ ጥሩ ነገር ነበር ግን እሱን እንኳ ለይስሙላ ( ለፋሽን ) የምናደርግ ሰዎች ነን ። በእውነት እምነት እኛን ያውቀናል ? እኛ ክርስቲያኖ ነን እንዴ ? እስላሞች ነን እንዴ ? ነን የምትሉ የክርስቲያን ወይም የሙስሊም ባህርይ ምን መምሰል እንዳለበት መጽሐፍ ቅዱሱንና ቁርዓኑን አገላብጡ ። ከዚህ አንጻር እኛን እግዜሩ አያወቅንም ማለት እችላለሁ ።
ድረስ አምላክ ፣ አረ የት ነህ
ብንማጸን ብንለምንም
አትሳሳቱ ሰዎች እግዜር እኛን አያውቀንም !
የገዳማት ሀገር እኛ
የግዮን ወንዝ መገኛ
የማህሌት መዝሙር ምንጭ
የበገና አውታሮች እጅ
ብለን እልፍ ብናወራ
ወሬያችን ምንም ላይሰራ
እግዜር እኛን አያውቀንም
የሚመስለኝ ይሄ ነው ። እና በትግሉ ተስፋ ቆረጥክ ለምትሉ ፣ ተስፋ አርጋችሁ ነበር እንዴ ? ሳያዩ የሚያምኑ ብጹአን ናቸው ፣ ያዩትን ማገናዘብ እና ራሳቸውን መጠየቅ ያልቻሉ ግን ፣ በአሁኑ አጠራር ( ወይም አገላለጽ ) ተስፈኞች ናቸው ማለት ነው ። የ ካልሃሪ በርሃ ላይ ዝናብ ይዘንባል ብሎ ተስፋ ማድረግ ስህተት አይደልም ፣ ግን እንዲህ አይነት ተስፋ ጥቅሙ ምንድን ነው ?
Source: Henok Yeshitela fb