በፍቅር ልንወድቅ የሚገባ ከማሸነፍ ወይስ ከትግል አይነት።  (ዳዊት ዳባ)

December 22, 2014

dawitdaba@yahoo.com

ዳዊት ዳባ

አምርረህ ልትታገልበት የሚገባ በቂ ምክንያት ካለ አላማው አንድና አንድ “ማሸነፍ” የሆነ ትግል እንጂ የትግል አይነት የሚባል ነገር የለም። አዎ ያለው ትግል ነው። ቢቸግር ነው እንጂ ችግሩ “አይነት” የሚለው ቃል ችግር ሆኖ አይደለም። ትግሉ ላይ ሲሆን አጠቃቀማችንና አረዳዳችን ግን በጣሙኑ  ግራ ያጋባል።  “ምግብ” ለሚለው ያጋራ መገለጫ ስር ጨጨብሳ፤ ሙዝ ፤ ወተት የመሳሰሉ ምግቦች እንዳሉ ለማሳያት  ሳይሆን   የጣሳ፤ ፅጌሬዳንና የሚዳቋን ዝምድና ለማሳያት መከራ የምናይበት እየመሰለ ነው።

ቂጣ መጋገርያ የስንዴ ድቄት ብቻ ላለው ሰው ዱቄቱ ግሉቶን የሚባል የሚያወፍር ንጥረ ነገር ስላለው አትብላ ተርበህ ሙት ተብሎ አይመከርም። እንዲሁ ወርጅብኝ እየወረደበትና  ለመረረው ህዘብ በዚህ ወይ ባዛ ብቻ ካልታገልክ ብሎ መጨቅጨቅ ግብዝነት ነው። ለማንኛውም  በዚህ ወይ በዛ አይነት የትግል ዘርፍ ብቻም የተገረሰሰ ጨቋኝ አገዛዝም የለም። የቅርብ ጊዜውን የአረቡን አቢዬት ብንወስድ እንኳ ቱኒዝያውያን አንድ ቀን ተነስተው አደባባይ ሄደው ስለተቀመጡ ብቻ ለውጥ አልመጣም።  በትንሹ ማደራጀት ፕሮፓጋንዳና ቅስቀሳ፤ አልታዘዝ ባይነትና ከስርአቱ ሰዎች ውስጥ በጥምዘዛም ይሁን በማጋግባባት ወይ በማሳመን ወደ ህዝብ ወገንተኛነት መገልበጥ ነበረበት። እነሱም ይስሩት ውጫዊ አካል ሰራው ለወጥ የለውም አስፈላጊው ስራ ተሰርቷል። መሳርያ ያስታጠቀው ክፍል አሊን አልታዘዝህም ባለበት ሁኔታ ስላልተተኮሰ ብቻ  መሳርያ ያልነበረበት ፍፁም ሰላማዊ ነበር ማለትም አይቻልም። እንዲሁ ደርግ ስልጣንን ሰላማዊ በሆነ ህዝባዊ እንቢተኛነት ብቻ  ከፊውዳሎች አልቀማም። ወያኔም ከጫካ እየገደለ ቢመጣም መሳርያ ብቻ በራሱ አሸናፊ አላደረገውም። ማወቅ ያለብን ለወያኔ አይነት ስርአት የምንጥልህ በሰላም፤ በአመፅ ወይ በመሳርያ ነው ስላልነው እንዴት አንዱን ካንዱ ለይቶ ወይ የተሻለ መወገጃዬ ነው ብሎ እንዲያስብና እንዲራራ አንጠብቃለን።

በአለማወቅም ይሁን አልዞረልን እያለ ይህው ላለፉት ሀያ ሶስት አመታት ‘ማሸነፍን” ፍፁሙ የሆነ  መፍትሄ፤ አስፈላጊና የሚቻል ከማድረግ ይልቅ ይህን ወይ ያንኛውን የትግል አይነት  ተቀባይ ለማድረግ የምናጠፋው ሁለንተናዊ ጉልበት እጅጉኑ የገዘፈ ነው።  አርእስቱ ልንፅፍበት፤ ልንናገርበና ልንቀሰቅስበት  ሁሌም አዲስና ተፈላጊ አድርገን ወስደነዋል። ምሁራን፤ መሪዎች፤ የድርጅት ሰዎች፤ ፀሀፊዎች፤ ጋዜጠኞች፤ ተሰሚነት ያላቸው ሰዎች  በዋና አስጀማሪነት አጠንክረው ይሳተፉበታል። ባህታዊ መፍጠር ተችሏል ባይባልም ሀያ አራት ሰአት ሙሉ ለአመታት ይሄንኛው የትግል አይነት ካልሆነ እራሳቸውን የሚሰቅሉ በሚመስል ምሬት የሚሰብኩ ጥቂቶች ተፈጥረዋል። ከዚህ ሁሉ ድካም በሗላ ግን የተገኘው ውጤት አይደለም ይህን ወይ ያንኛውን የትግል አይነት በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ ፍፁም ተቀባይ ማድረግ አይደለም   በቀጥታ ተጎጂ የሆነውን አብዛኛውን ዜጋ እንኳ ትግሉ ላይ የድርሻውን እንዲያደርግ ማስቻል አልተቻለም። በሰላም ሲባል በመሳርያ ካልሆነ፤ በመሳርያ ሲባል በሰላም ካልሆነ ብለው ለአፍ ማውራት ዘመንኛ ሆኗል። በአጠቃላይ ግን ህዝቡ ግራ እንዲጋባና ከትግሉ እንዲሸሽ በማድረግ ደረጃ አስተዋፆ አለው ማለት ይቻላል።  ትግሉ ላይ  ተሳታፊ ከሆነው የበዛው ዜጋ ከዛም ከዚህም ወገን ያለውን ሰምቶ ሰምቶት ከጉሮሮው አልወርድ ብሎታል። ስለዚህም እየነፈሰበት እንዳለ ሰንበሌጥ ወዲያና ወዲህ ይንገላወዳል።

ለወትሮው ሰላማዊ፤ የሀይልና በህዝባዊ እንቢተኛነት የትግል ዘርፎች መሀል ነበር ማወዳደሩ። አንዱን ካንድ በማነጻጸር አንዱን የትግል አይነት መጥፎ በማድረግ ያንኛውን ተመራጭ የማስመሰል ስብከት የሚሰራው። ዛሬ ይህ አዚም እድገት አሳይቷል።  የትኛውንም አይነት የትግል እንቅስቃሴና ለትግሉ አስፈላጊ የሆኑ ስራዎች ህዝብን በአዳራሽ ሰብስቦ ከማዋየት አንስቶ፤ ሰልፍ፤ ዲፕሎማሲ፤ ቅስቀሳና ፕሮፓጋንዳ፤ የገንዘብ አቅም መገንባት፤ ምርጫ፤ ማእቀብ፤ ሜዲያ  እያላችሁ ቀጥሉ ሁሉም ላይ ለተቃውሞ እንዲያመች ማነፃፀርያ ይበጅለትና  አመክንዬና ተግዳድራቶች በመደርደር ታሪክና ተመክሮ እየታጠቀሰ በጭራሽ የማይቻል ነው እንባላለን።

የግዜው ፋሽን ከሆነችውና ዘናጯ ጠብ ማጫር [confrontational] ከምትለው ጀምረን፤ ስናሸንፍ የምናደረገው አልን እንጂ የምንታገለው ለዲሞክራሲ ብቻ ይመሰል ታገሱ ሂደት ነው። ከኤርትራ አብዳችሗል። የምን በየኢንባሲው መጮህ ነው። ውጬ ያላችሁ ተቆርቋሪ ዜጎች ከበርገር ከተረፋችሁ ገንዘብ እርዱ። ይህን ምርጫ የሚባል እቃቃ ጫወታ ተዉን አንስማው። በአገር ቤትም በውጪም ያለው ተደምሮ ትግል ውስጥ በአመት የሚንቀሳቀሰው የገንዘብ አቅም አንድ ሚሊዬን እንኳ በማያደርስበት ሁኔታ የደሀ ነገር ሆኖ የሀያ ቢሊዮን እናለቅሳለን። አንድ ደረቅ እንጀራ በአምስት ብር እየገዛ በሚኖርበት ዘመን የትኛውንም አይነት ትግል ለማካሄድ ምን ያህል ውድ ሊሆን እንደሚችል አይዞርለትም። ትግል እያካሄዱ ያሉ ድርጅቶች በሙሉ ለብሪቱ ነው ብሎ ይደመድማል።ደርጎች ወታደሮች ስለነበሩ አሁን መሳርያ የያዘውን ለውጡ ላይ ሊኖረው ስለሚችለውን ድረሻ ገና ሲነሳ የወታደር ነገር  ቱ በሉ የሴጣን ጆሮ እንዳይሰማው። በሀይል የሚመጣ በጭራሽ ዲሞክራሲያዊ ሊሆን አይችልም ድምድም፤ እያስፈቀድክ በመሰለፍ ምንም አታመጣም ፋይዳ ቢስ አርፈህ ተቀመጥ። ስላወራህና ስለቸከቸክ እየተጋልኩ ነው ብለህ እንዳታስብ። ዛሬም ነገም እንትና ይፈታ  አንስማ። ሙስሊሙ፤ ኦሮሞው፤ ክርስቲያኑ፤ ጋንቤላው፤ አማራው መብቴን ሲልና ሲፈጅ እሰይ ሲሉ ጮቤ ባደባባይ  መርገጥ ሁሉ ተጀምሯል። እታገላለው የሚለው ዜጋ ሆነ ድርጅት ሁሉ እርግጠኛ ተሆኖ ለስልጣን ነው ይባላል።  መዘርዘሩ ደከመኝ ላቁመው። አስፈሪ ግዙፍ ክስም ይጨመርበታል አሸባሪ ፤ ሚኒሊካዊያን፤ ከሀዲ፤ ህዝብ አስጨራሽ፤ የህዝብን ትግል አስመች፤ ቀልባሽ፤ ጀሀዲያዊያን፤አጎብዳጅ፤ ያለፈ ስርአት ለማምጣት፤ ተሞዳማጅ፤ ወያኔ፤ ጎጠኛ የመሳሰሉ።  ተሸማቆ እንዲያቆም ቅርቃብ መምታት መሆኑ ነው። የበዛው ህዝብ ደግሞ ሁሉንም ያዳምጣል። ይሰማና ይደምራል፤ ያጣፋል፤ ይቀንሳል። በመጨረሻ የሚያገኘው ውጤት ዚሮ ይሆንበታል። ትግል አያስፈልግም የሚል ስለሆነ እጁን አጣጥፎ ዝም ብሎ እያየ ነው።

እዚህ አፍራሽ ድርጊት ላይ ድርሻ የለኝም የሚል እኔንም ጨምሮ እጁን ያውጣ። ሁላችንም አጠንክረን ይዘንዋል። የበዙትን ባላንጣዎቻችን ያቀብሉናል። እኛ ደግሞ እንረቃቅበታለን። እንቀጣቀጥበታለን። ድርጅቴ ቀላል የማይባል አስተዋፆ አለው።  ዋናው ችግር ግን እራሱ ትግል የሚባለው ነግር ላይ ያለ የተዛባ አመለካከት ነው። የትግል ትንሽ የለውም፤ ባለው ተጨባጭ እውነታና ተግዳድራቶች ውስጥ ውጤት እንዲኖረው ማድረግ መቻል አለመቻል እንጂ አይሰራም የሚባል  የትግል አይነትም የለም። ተጋዳድራቶች ሳይኖሩት የሚደረግ የትግል አይነትም የለማ። ካለም ያ ትግል አይባልም ። በእርግጥ የትኛውም የትግል አይነት ምርጫዬና ሀላፊነቴ ብሎ የያዘው ባለቤት ይፈልጋል። ለምሳሌ ከምርጫው መታቀብ ተመራጭ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር ይችል ይሆናል። ይህ የትግል አይነት ግን ባለቤት የለውም። ባለቤት ስለሌለው ደግሞ ቦይካት ቦይካት የሚለውን ድምፅ እዚህና እዚያ ይሰማል እንጂ እንዴት? ጥቅሙ? ውጤቱ ለመሳሰሉት ጥያቄዎች ላይ አይደለም ለዜጋው በቅርብ ትግሉ አካባቢ ላለውም ምንም የሚጨበጥ ነገር ማስያዝ አልተቻለም። ተችሎም ቢሆንም ለለውጥ የሚታገል ክፍል  ሁለት የማይደጋጋፉና ሊቀናጁ የማይችሉ የትግል አይነቶችን ባንዴ አያካሂድም። ምክንያቱም ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። የማይደጋገፉ ከሆነ በሁሉም ዜጋ ዘንድ ተቀባይ ማድረግ ማስቻል ላይ እርግጠኛ ሳይሆኑ ማንሳት በራሱ አዳካሚ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ በያምንበትም አዘግይቶት የበዛው ወዳለበትና ሊሆን ወደሚችለው መጠቅለል ከማሸነፍ እንጂ ከትግል አይነት ፎንቃ የማይዘው ብልህ  ታጋይ መገለጫ ነው።

ጎበዝ ምንድን ነው የነካን። ማሸነፍን ለምን ፈራን?። እያንዳንዱን የትግል አይነት እራሱን በቻለ ሁኔታ ትግሉ በሚካሄድበት ነባራዊ  ሁኔታና ባሉት ተግዳድራቶች ውስጥ ስኬታማ ማድረግ የሚቻልበትን መንገድ ላይ መጨነቅና መጠበብ ለምን አልቻልንም?። ያሉ ጥረቶችን ማገዝ ማበረታት ትተን ሰበበኛ ለምን ሆንን?። በተመሳሳይ ሊሰራባቸው የሚገቡ ቁም ነገሮችን  እየመዘዝን ስኬታማ የሚሆኑበትን መንገድ ላይ መመራመር ማጥናት ሰርቶ ማሳያት ለምንድን ነው ያቃተን?። ሁሌ ንፅፅርስ ጤናማ ነው ወይ?። ለዚህ ሁሉ ችግር ፍቱን የሆነው መፍትሄ እኮ በተናጠል ስኬታማ ማድረግ መቻሉ ነው። እያንዳንዱ የትግል ዘርፍ በተናጠል ስኬታማ ለማደርግ ስንጀምር ደስ እያላቸው ብዙዎች ድርሻ ያደርጋሉ። አሳምረን ልንሰራዋና ውጤታማም መሆን እንደምንችል ኢሳት ማሳያ ነው።መፍትሄው ይህ ነው ስል ግን ሁሉ የሚያውቀው ስለሆነ ኢሳትን ተጠቀምኩ እንጂ ተጠንቶና በትንሹ ተሞክሮ እንደሚሰራ የተረጋገጠለት መንገድ ስለሆነ ነው።

መረጃ መሰብስብ የጀመረ አካል አለ። በርቱ የሚሰኝና ልንረባረብበት የሚገባ ድንቅ ጥረት ነው። ትግሉ ላይ ልንሰራቸው ከሚገቡ ጉዶይች አንዱ ነበር። ለጊዜው ወና አላማ ያደረገው ወንጀል የሚሰሩትን ለመክሰሻ መረጃ መሰብሰብ ቢሆንም ለትግሉ ልንጠቀምበት እንድንችል ዝም ብለን ሁሉንም አይነት መረጃ እንላክላቸው። በየመንደሩ በየቀበሌው ያሉትን የገዛዙ ሰዎችና ደጋፊ ናቸው የምንላቸውን እንኳ አንድ እንዳናስቀር። መርሳት የሌለብን ትግሉ ላይ የሚያስፈልገን የበዛው መረጃ ሚስጥር የልሆነ ዜጎች በቀላሉ ሊያገኙት የሚችሉ ሞሆኑን ነው።

ያዳሩ ሰልፍ ለጊዜው አልተሳካም። ስለዚህ አይቻልም ተብሎ አይተውም። ለረጅም ጊዜ ሰልፍ የሚባል ነገር የማይቻል ስለመሰለና ስለተባለ ሳናስችለው አለቀረንም። አሁንም እንዴት የሚለው ላይ አይምሯችንን ካሰራን መላ አናጣም። እርግጠኛ ነኝ በብዙዎች አይምሮ ውስጥ ይህ ጉዳይ ማጨት ጀምሯል። በቅርብ ደግሞ ይወለዳል። ጉጀሌው ከኛ ውስጥ ወንድሞቻችን ወስዶ የእማሆይን እጅ ጠምዝው ለመስበር የማያራሩ አውሬ አድርጓቸዋል። ይህን በማውገዝ ብቻ የምንተወው መሆን የለበትም። አብዝተን ልንሰራበትና ልንቀይረው የሚገባ ጉዳይ ነበር። አሁንም ድፍረት እንዳይሆን እንጂ በውጪ ካሉት ድርጅቶች ሊሰሩበት ፍላጎቱ ካላቸው ትሰራለች ብዬ አብዝቼ የማንኩባትና የቀመርኳት መላ አለች ልልክላቸው ደስተኛ ነኝ። መነሻ ሀሳብ ትሆናለች። የመሀበራዊ ሳይንስና የስነ አይምሮ ምሁራኖቻችን መሰርያ የያዘውን በቅርብ ከሚያውቁ ጋር ቲም መፈጠር አለባቸው።

አገር ውስጥ ሆነው በግልጽ የሚታገሉ  የምንታገለው በሰላማዊና ህጋዊ በሆነ መንገድ ብቻ ነው ሲሉ ማንም ይረዳዋል። ያም ሆኖ እንደቀጣይ መንግስት  የትምህርት ፖሊሲ ይዘው ነው ምረጡን የሚሉት። በተመሳሳይ አገዛዙ የመብት ጥያቄ ያነሱ ዜጎችን አሸባሪ ብሎ ጦርነት ውስጥ የገባበትን አገራዊ ጉዳይ ላይ የተሻለ አማራጭ ሰርተው ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሰላማዊ መፍትሄ እንዳለውና በቀላሉ ተፈፃሚ ሊያደርጉት የሚችሉ መሆኑን ለመራጩ ማሳየት ከቻሉ የተለየና የተሻላ አማራጭ አላቸው ብሎ ይወስደዋል። ይህው መሳርያውን እርግፍ አድርገን እንጥላለን። ይህው አገር ውስጥ ገብተን በሰላማዊ መንገድ እንታገላለን ያሉበትና የተስማሙበት ደብዳቤ ብለው ለህዝብ ማሳየት ከቻሉ ደግሞ ግሩም አድርገው ስራ ሰርተው ገብተዋል ማለት ነው።  ምርጫው ላይ ፊት የሚደፈጥጥና ህሊና አስቶ የሚጥል ቡጢ ሰነዘሩ ይሆናል። ከዚህ በላይ ማሳጣትም ባዶ ማስቀረትም የለም።

እጠይቃለው። የግንቦት ሰባት ንቅናቄ የዚህ አይነት አንድምታ ያለው ለላማዊ ተጋዬች እውቅና የሚሰጥ ደብዳቤ ተደራድሮበት አይደለም ሳይጠየቅ ቢያስገባ የሚጎዳው እንዴት ነው?። የሚጠቀምበትን ግን አስር ገፅ መዘርዘር እችላለው። ይህ ጥያቄ ግን ለግንቦት ሰባት ብቻ አይደለም። ለተከለከሉ፤ አሸባሪ ለተባሉ በሀይልም ሆነ በተለየ የትግል አይነት በድብቅም ሆነ በግልፅ ትግሉ ላይ አስተዋፆ ለሚያደርጉ ድርጅቶች ሁሉ ነው። ዳውድ ኢብሳ ፍቃደኛ ሆኖ ካላደረገው ይገርመኛል። ትግሉን እናስፋው ሀሳባችንን ግን ማሸነፍ ላይ እንሰብስበው እባካችሁ።

 

 

 

 

 

2 Comments

  1. በሁሉ አቅጣጫ ለኢትዮጵያ ነፃነት ዋጋ እየከፈሉ ላሉ ወገኖች ገንቢና እርስ በእርስ ሳይጠላለፉ ትግላቸዉን በማራመድ ዕይታቸዉ ዉጤት ላይ ያነጣጠረ መሆን እንዳለበት እዉነታን በማስረገጥ ያቀረብከዉ ትንታኔ ወቅታዊ በመሆኑ ልትመሰገን ይገባል (God job) !!

  2. ሰላም!
    ወንድማችን ያንሳሃቸውን ነጥቦች መተግበር ያለባቸው ነገሮች ሲሆኑ አሁን አሁን ግን እጅግ ተጠናውቶን ያለው ነገር ስግብግብነት በቀላሉ መክበር ከነዚህ ጋር ተያይዘው ከመጡ ዋነኛው ነገር እንደ ዜጋ ለአንዲት ሃገር ማሰብ ና መቆርቆር አቅቶን ይታያል ይህ ሲባል ግን ሁሉኑም ለማለት አይደለም አሉ ቀን ከለሊት ቀና ደፋ የሚሉ አምላክ ይርዳቸው :: ካነሳሃቸው ነጥቦች ውስጥ ሁሉም አይነት ትግል ትግል ነው ያልከው እውነትነት አለው ሁሉም ሰው ሃገሩን ነጻ ለማውጣት መነሳት ያለበት አሁን ነው ይህ ሲባል በተለያዩ መንገድ ሃገሩን መርዳትማለት እንድሆነ ግልጽ ነው ይህ ግን በቀላሉ እንዲተገበር አቅጣጫን ማሳየት ያስፈልጋል እንዴት መርዳት እንዳለብን ወዴት መሄድ እንዳለብን መንገድ ሁሉ ያሰብንበት ያደርሳል ማለት አይደለምና ዴቭ እናመሰግናለን ቤተሰቦችህን እግዚያብሔር ይባርክልህ!!! ሰላም!

Comments are closed.

Previous Story

Hiber Radio: የባህርዳሩ ጉዳይ ልዩ ዘገባና ቃለምልልስ… የአንዳርጋቸው ባለቤት አቤቱታ… በሃረር ቤተክርስቲያን ሊፈርስ መሆኑ… ሌሎችም

2007 election
Next Story

የህዝብ ታዛቢ ሆነው ከተመረጡት ውስጥ አብዛኞቹ የኢህአዴግ አባላት መሆናቸው ተገለጸ

Latest from Blog

የአበባው ታደሰ እና የአረጋ ከበደ ፍርጠጣ | ስለአማራ ክልል ከነዋሪዎች የተሰማው | አበባው ጉ’ድ ሆነ – “አበባውን ሳትይዙ እንዳትመጡ”|“በባህርዳር ተከበናል፣ ከፍተኛ አዛዦች ተመተዋል” | “ፋኖ መንግ’ስት ሆኗል” ጄ/ሉ |

የአበባው ታደሰ እና የአረጋ ከበደ ፍርጠጣ አበባው ጉ’ድ ሆነ – “አበባውን ሳትይዙ እንዳትመጡ”|“በባህርዳር ተከበናል፣ ከፍተኛ አዛዦች ተመተዋል”| “እጅ ከመስጠት ውጭ አማራጭ አይኖረንም” ፊ/ማ “ፋኖ መንግ’ስት ሆኗል” ጄ/ሉ |

ከውጭ በተላከ ገንዘብ ሀብት አፍርቶ የተላከበትን ደረሰኝ ያላቀረበ ንብረቱ እንዲወረስ የሚደነግግ አዋጅ ቀረበ

ዮሐንስ አንበርብር በጥፋተኝነት ላይ ያልተመሠረተ ንብረት የመውረስ ድንጋጌም በአዋጁ ተካቷል አዋጁ የሚፀድቅ ከሆነ 10 ዓመት ወደኃላ ተመልሶ ተፈጻሚ ይሆናል ከውጭ በተላከ ገንዘብ ሀብት አፍርቶ የተላከበትን ደረሰኝ ያላቀረበ ሰው ወይም ሊታወቅ ከሚችል ገቢው በላይ ሀብት አፍርቶ ምንጩ ሕጋዊ መሆኑን ማረጋገጥ ያልቻለ ሰው፣ ንብረት በመንግሥት እንዲወረስ የሚፈቅድ ድንጋጌ የያዘ
Go toTop