ሰለማዊ ሰልፍ መከልከል??? ከአብርሃ ደስታ

ሰማያዊ ፓርቲ’ የተባለ የፖለቲካ ድርጅት ለአፍሪካ ሕብረት 50ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ለማክበር የአፍሪካ መሪዎች በአዲስ አበባ በሚሰበሰቡበት ግዜ የህዝብ ሰለማዊ ሰልፍ እንደሚጠራ ሰምተን ነበር። የሰልፉ ዓላማ ምንድነው? ለምን አስፈለገ? ለምን ለአፍሪካ መሪዎች ማሳወቅ አስፈለገ (አብዛኞቹ የአፍሪካ መሪዎች ሰለማዊ ሰልፍ አይወዱም ወይ አይፈቅዱም ብዬ) የሚሉና ሌሎች ተዛማጅ ጥያቄዎች አንስተን መከራከር ይቻላል።

እነዚህ መከራከርያ ነጥቦች ለግዜው ወደ ጎን ትተን እነኚህ ‘ሰለማዊ ሰልፍ’ የጠሩ አካላት ምን ይሁን ምን የራሳቸው ምክንያት፣ ዓላማና አሰራር ይኖራቸዋል (ድርጅትን ያህል ምክንያት ሳይኖረው፣ አስፈላጊነቱ ሳይታየው የተቃውሞ ሰልፍ በሚከለከልበት ሀገር ሰለማዊ ሰልፍ ይጠራል ብዬ አላስብም)።

መጠየቅ ያለብን ነገር የሰልፉ ዓላማና አስፈላጊነት ሳይሆን (ምክንያቱም ሰልፉ አስፈላጊ ነው ወይ አይደለም ብለን ለመደገፍ ወይ ለመተቸት የሚከለክለን ሕጋዊ አካል የለም) ዜጎች ሰለማዊ ሰልፍ የማድረግ (ለፈለጉት ዓላማ) ሕገ መንግስታዊ መብት አላቸው ወይ የሚል ነው??? የኢትዮጵያ ህገ መንግስት አንቀፅ 30፣ “ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሳሪያ ሳይዝ በሰላም የመሰብሰብ፤ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነትና፤ አቤቱታ የማቅረብ መብት አለው፡፡” ብሎ ይደነግጋል። በሕግ የተደነገገ በተግባር መተርጎም አለበት። የሕግ የበላይነት መረጋገጥ አለበት። ዜጎችም ሕገ መንግስታዊ መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባል።

ዜጎች በሕገ መንግስቱ የተሰጣቸው ‘ሰለማዊ ሰልፍ’ የማድረግ መብት ለመጠቀም ሰልፍ ከመውጣታቸው በፊት የአከባቢው አስተዳደር ማሳወቅ ወይ ፍቃድ መጠየቅ እንደሚኖርባቸው ሕግ ይደነግጋል። የሰለማዊ ሰልፍ ፍቃድ ሲጠየቅ (የተለየ ሁኔታ ካላጋጠመ በቀር) በመንግስት አስተዳደር የሚከለከልበት መንግስታዊ አሰራር የለም። ምክንያቱም ሰለማዊ ሰልፍ ማድረግ የዜጎች መብት መሆኑ በሕገ መንግስቱ ተቀምጧል)።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሃላፊነትና ተጠያቂነት ዜሮ የሆነባትን ኢትዮጵያን እንዴት እንታደጋት? - አክሎግ ቢራራ (ዶር)

ትናንት ማታ እንደሰማነው ታድያ ‘ሰማያዊ ፓርቲ’ ‘ሰለማዊ ሰልፍ’ ለማድረግ የሚያስችለው ፍቃድ እንዲሰጠው ለአዲስ አበባ አስተዳደር ማቅረቡና ጥያቄው ተቀባይነት አላገኘም። መንግስት ሰለማዊ ሰልፍ የማድረግ ፍቃድ ለመከልከል የሚያስችል ስልጣን የለውም (ሰልፉ የሚከለከልበት ልዩ አጋጣሚ እስከሌለ ድረስ)።

መንግስት ፍቃድ መከልከሉ የሀገራችን ሕገመንግስት የጣሰ ነው። መንግስት የራሱን ሕገመንግስት በራሱ ከጣሰ ዜጎች መንግስት የጣሰውን ሕገመንግስት እንዲያከብሩ እንዴት ማስገደድ ይቻለዋል? ዜጎች ብቻ ሕገመንግስቱ ቢያከብሩ እንዴት ዉጤት ማምጣት ይቻላል? በዴሞክራሲያዊ ሀገር ሕገመንግስት የበላይ ሕግ ነው፤ በመንግስትም በዜጎችም መከበር አለበት። ሕገመንግስቱን በመጣስ ኢህኣዴግ የሚመራው የኢትዮዽያ መንግስት ከሕግ በላይ እየሆነ ነው። መንግስት ሕግን በሚጥስበት ሀገር ዴሞክራሲ አለ ማለት አይቻልም። ዴሞክራሲ ከሌለ የኢትዮዽያ መንግስት ‘አምባገነን ነው’ ብንል እንዴት ስሕተት ሊሆን ይችላል?

መንግስት አምባገነን ከሆነ ዜጎች ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚገነቡበት አጋጣሚ ለመፍጠር ብንቀሰቅስ ኃጥያት ይሆናል? መሪዎቻችን ለስልጣን ሲታገሉ ለዴሞክራሲ ግንባታ ብንታገል መልካም አይደለምን? ሰለማዊ ሰልፍ ማድረግ ህዝቦች ሓሳባቸውንና ያላቸው ቅሬታ (በመንግስት ይሁን በሌላ) የሚገልፁበት መድረክ እስከሆነ ድረስ የዴሞክራሲያዊ አሰራር መገለጫ ይሆናል ማለት ነው።

ሰለማዊ ሰልፍ ማድረግ የዴሞክራሲ መገለጫ ከሆነ ታድያ ለምን ሰለማዊ ሰልፍ እንፈራለን? ሰለማዊ ሰልፍ ባለመፍቀድ የህዝብን ብሶት ያቃልላል ያለው ማነው? ህዝብን ማፈን የህዝብን ቅሬታ እንዲጨምር እንደሚያደርግና ህዝቡ ሌላ አማራጭ (ሰለማዊ ያልሆነ መንገድ) ተጠቅሞ ፀረ መንግስት ሊነሳ እንደሚችል ኢህኣዴጎች ከደርግ አገዛዝ ትምህርት አለመቅሰማቸው ግርም ይለኛል። ሰለማዊ መንገድ መዝጋት የሃይል ወይ የዓመፅ መንገድ መክፈት ማለት ነው።

እኛ የምንፈልገው ግን የዓመፅ መንገድ ሳይሆን ሰለማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲኖር ነው። ኢትዮዽያ በሃይል ስልጣን የመያዝ የብዙ ዓመት ልምድ አላት። እስካሁን ድረስ የኢትዮዽያ ገዢዎች ስልጣን የያዙት በሃይል ነው። ባለስልጣናቱ (ሰዎቹ) ይቀያየሩ እንደሆኑ እንጂ ፖለቲካዊ አገዛዛቸው ተመሳሳይ ነው፤ ስልታቸው ጭቆና ነው። የሚገለገሉበት ስልጣን ከህዝብ ተውሰው የያዙት ሳይሆን በጠመንጃ አፈሙዝ የነጠቁት ነው፤ ለዚህም ነው ለስልጣናቸው እንጂ ለህዝብ ነፃነት ግድ የሌላቸው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የብሄር እኩልነት!

ሰለማዊ ሰልፍ የምንፈራበት አንድ ምክንያት ሊኖር ይችላል። ይሄም ‘ሰለማዊ ሰልፉ’ እንደስሙ ‘ሰለማዊ’ ላይሆን ይችላል። መፍትሔው ግን ቀላል ነው። በሕገ መንግስቱ የተቀመጠ ‘ሰለማዊ ሰልፍ’ ነው። ሰዎቹም የጠሩት ‘ሰለማዊ ሰልፍ’ ነው። ፍቃድ የተጠየቀው ‘ለሰለማዊ ሰልፍ’ ነው። መንግስት ይሄንን ፍቃድ መስጠት ነበረበት። ሰልፉ ሰለማዊ መሆኑ ቀርቶ የዓመፅ መንፍስ ከታየበት ‘ሕገ ውጥ ሰልፍ’ እየሆነ ነው ማለት ነው። በዚህ ግዜ መንግስት ‘ሕገመንግስቱን ለማስከበር’ ጣልቃ ሊገባ ይችላል። ‘ሕገ ወጥ ድርጊት’ የፈፀመ አካል ካለ ወደ ሕግ ቀርቦ በሕግ ይፈረዳል። (የሕግ የበላይነት ይከበራል)።

ገና ለገና ‘ዓመፅ ሊቀሰቅሱ ይችላሉ’ በሚል ስጋት (ይህን ያልኩበት ምክንያት መንግስት ዓመፅ ፈርቶ ካልሆነ በቀር ሰለማዊ ሰልፍ የማይፈቅድበት አሳማኝ ምክንያት ስላልመጣልኝ ነው) ሰለማዊ ሰልፍ መከልከል የዜጎች መብት መጣስ ስለሆነ አግባብነት የለውም። ባጭሩ መንግስት በሕገወጥ ተግባር ተሰማርተዋል ማለት ነው።

ሰለማዊ ሰልፍ መጥራት የመብት ጥያቄ እንጂ የአቋም ጉዳይ አይደለም።

ዓፈና ዓመፅን ይወልዳል።

4 Comments

  1. the so called eprdf they only know to write theory not practical ways of doing things. they are cruel and savage thugs.

  2. You are Denkoro man; dedeb, if you do not need permission then why you need government in the first place? Denez

  3. Madam Lemlem, it is good to be a person of your name. I do not understand what kind of mistake the writer made. The article is written in simple language even you to understand with out difficulty.

  4. If the right to peaceful demonstration is guarantied by the constitution, then one does’nt need to ask for permission. One has only to notify beforehand. Ok, Lemlem?

Comments are closed.

Share