ከይርጋ አበበ
ጣሊያናዊው ሮቤርቶ ማንቺኒ በዱባይ ባለሀብቶች የሚመራውን ማንችስተር ሲቲን ከአርባ አራት አመታት በኋላ ሻምፒዮን ባደረጉ በአመታቸው ከክለቡ አሰልጣኝነት ተሰናብተዋል።
ማንችስተር ሲቲ እግር ኳስ ክለብ በይፋዊ ድረ ገጹ ባወጣው መግለጫ አሰልጣኙ በአመቱ እንዲያሳኩ ከተቀመጡላቸው ግቦች መካከል አብዛኛዎቹን ማሳካት አልቻሉም ፤ በዚህም ምክንያትነት ከኃላፊነታቸው ተሰናብተዋል ብሏል።
አሰልጣኝ ሮቤርቶ ማንቺኒ ማንችስተር ሲቲን በቀጣዩ አመት በሚካሄደው የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ተሳታፊ መሆን የሚያስችለውን እድል እንዲያገኝ ቢረዱትም ከተቀመጡላቸው ግቦች መካከል አብዛኛዎቹን አለማሳካታቸው ለስንብታቸው መንስኤ መሆኑን ክለቡ አስታውቋል።
በውድድር አመቱ ክለቡ የቀሩትን ሁለት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችና በአሜሪካ የሚያደርገውን ዝግጅት ምክትላቸው ብሪያን ኪድ እንደሚመሩም በመግለጫው ይፋ አድርጓል።
የክለቡን የአሰልጣኝነት ኃላፊነት ይረከባሉ ተብለው ከሚጠበቁት ታላላቅ አሰልጣኞች መካከል ቺሊያዊው የስፔኑ ማላጋ እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ ማኑኤል ፔሌግሪኒ ግንባር ቀደሙ መሆናቸውን ቢቢሲ በዘገባው አስነብቧል።የስፔኑን ኃያል ሪያል ማድሪድን በአውሮፓውያኑ 2010 በአሰልጣኝነት የመሩት የ59 አመቱ ፔሌግሪኒ ባለፈው እሁድ ከማንችስተር ሲቲ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌላቸው ተናግረዋል።
ማንችስተር ሲቲ እግር ኳስ ክለብ የአሰልጣኝ ሮቤርቶ ማንቺኒን ስንብት ይፋ ባደረገበት መግለጫው አሰልጣኙ ክለቡን በኃላፊነት ከተረከቡ ከአውሮፓውያኑ 2009 ጀምሮ ለሰሩት ስራ ምስጋና አቅርቧል።
«ሮቤርቶ ያስመዘገቧቸው ውጤቶች ማንታቸውን ይገልጻሉ ። ከክለባችን ደጋፊዎች ታላቅ ፍቅርና አክብሮት ማግኘት ችለዋል ። ለክለባችን ቃል በገቡት መሠረት ውጤት አስገኝተውልናል። ከእርሳቸው ጋር መለያየት ከባድ ቢሆንም በዚህ የውድድር አመት ያስመዘገቡት ውጤት ሲመረመር በአመቱ ለማሳካት ከተቀመጠላቸው ግብ አንጻር ዝቅተኛ ሆኖ በመገኘቱ እንዲሰናበቱ ተወስኗል » ብለዋል የክለቡ ሊቀመንበር ካልዱን አል ሙባራክ በመግለጫቸው ።
የ48 አመቱ ጣሊያናዊ ሮቤርቶ ማንቺኒ በአውሮፓውያኑ 2009 ማርክ ሂውዝን ተክተው ክለቡን በኃላፊነት ከተረከቡ በኋላ ማንችስተር ሲቲን የኤፍኤና የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ባለቤት ማድረግ ችለዋል።
በዚህ የውድድር አመት ግን ክለቡ ከሻምፒዮኑ ማንችስተር ዩናይትድ ጋር ሰፊ የነጥብ ልዩነት ያለው መሆኑ፣ አውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ውድድር በጊዜ መሰናበቱና በኤፍኤ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ በዊጋን አትሌቲክ ተሸንፎ ዋንጫ ማጣቱ የአሰልጣኙን ስንብት እንዳፋጠነው ይገመታል።