“በኢንቨስትመንት ስም የሚፈጸም የመሬት ነጠቃ፤ በኢትዮጵያ” ጥናት ትርጉም ይፋ ሆነ (ሊያነቡት የሚገባ)

May 15, 2013

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን)
ግንቦት 5፣ 2005ዓም

በኢንቨስትመንት ስም የአገር ሃብትና ትውልድን እየበላ ስላለው የመሬት ነጠቃ አስመልክቶ የኦክላንድ ተቋምና ድርጅታችን ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ በጋራ ያዘጋጁት ጥናታዊ ዘገባ ይፋ ሆነ። የጋራ ንቅናቄያችን ዋና ዳይሬክተር ጥናቱ በትክክለኛ ጭብጥ ላይ ተመስርቶ እንዲዘጋጅ ለህይወታቸው ሳይሳሱ መረጃ በመስጠት ለተባበሩ ዜጎች “ታላቅ ክብር ይሁንላችሁ። አሁን አትታወቁም። ግን ከቶውንም አትረሱም። ክብር ለማትታወቁት ግን ለማትረሱት የአገር ጀግኖች” በማለት ምስጋና አቅርበዋል።
ኢህአዴግን በደፈናው መቃወምን ዓላማው ያላደረገው ይህ ጥናታዊ ዘገባ ዜጎችን ካደጉበት፣ ከኖሩበት፣ ከቀያቸው፣ ከህልውናቸው፣ ከርስታቸው፣ ወዘተ ያለ አንዳች ውይይት፣ ምክክርና ንግግር በማፈናቀል ለውጪ ኩባንያዎችና ለራሱ ለባለጠመንጃው አገዛዝ ሰዎችና ባለሟሎች መሬት ማከፋፈሉን በማስረጃ ያሳያል። የራሱ የኢህአዴግ አካላትም በሪፖርቱ ውስጥ በአግባቡ ድምጻቸው ተካትቷል። የሚጠቀሙባቸው አዋጆችና ህጎችም አልተዘለሉም።
“የውጪ ባለሃብቶችና ኩባንያዎች ወደ አገር ውስጥ መግባታቸው ለቴክኖሎጂ ዝውውር፣ በአገሪቱ ያለውን የምግብ እጥረት ለማስወገድ ይረዳል” የሚሉ ምክንያቶች እያቀረበ ያለው ኢህአዴግ በተግባር ሲፈተሽ ተግባሩና ዓላማው ምን እንደሆነ የሚያመለክተው ጥናቱ የስርዓቱ ሰለባዎች፣ የኢህአዴግ ባለስልጣናት፣ ኢንቨስተሮች፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ክፍሎች፣ የቅርብ ምስክሮች፣ የተለያዩ ከዓለምአቀፍ ተቋማት የተገኙ መረጃዎች፣ አገዛዙ ራሱ ይፋ ያደረጋቸው መረጃዎችና ለጥናቱ አስፈላጊ የተባሉ አኻዞች የተካተቱበት በመሆኑ እውነታውን ህዝብና ማናቸውም ወገኖች እውነቱን ለመረዳት ያስችላቸዋል ተብሎ በጉልህ ታምኖበታል።
በምሳሌ ለማሳያነት የተጠቀሰው የሳዑዲ ስታር ኩባንያ የሚያመርተውን ሩዝ ደብረዘይት በገነባው ተቋሙ አማካይነት ሩዙን የመለየትና ለኤክስፖርት የማዘጋጀት ስራ ይሰራል። የተመረጠውና መለኪያውን የሚያሟላው ሩዝ ኤክስፖርት የሚደረግ ሲሆን፣ ደቃቃውና በሚሊሜትር ተለክቶ ለኤክስፖርት ደረጃ የማይበቃው አገር ቤት እንዲቀር ይደረጋል። ከዚህ አንጻር እንኳ ቢታይ የመሬት ኢንቨስትመንት የተባለው ዓለም ጠንቅቆ ለሚያውቀው የአገራችን የምግብ እጥረት ችግር መፍትሄ ሊሆን አይችልም። በጥናቱ ዝርዝር ጉዳዩ አለ።
ኢህአዴግ በፖለቲካው ውድማ ላይ ቆሞ የሚያወራውና በተግባር የሚሆነውን እውነት ከሰለባዎቹ አንደበት በመቅዳት ሊስተባበል በማይችልበት ደረጃ ያቀረበው ጥናት፣ ዜጎች ከቀያቸው ከመፈናቀላቸው በፊት ምክክርና የስነልቦና ዘግጅት እንዲደረግ ጊዜ እንደሚሰጥ በህግ የተደነገገ ስለመሆኑ፣ ነግር ግን እውነታው የተገላቢጦሽ መሆኑንን ጥናቱ በማስረጃ ያትታል። ዜጎች ነገ ስለሚሆነው እንኳ ሊያውቁ በማይችሉበት ደረጃ ማለዳ ካረፉበት ሲነቁ ዶዘር ማሳቸውን፣ የጓሮ አትክልታቸውን፣ የኑሯቸው መሰረት የሆነውን ደናቸውን፣ ቤታቸውን ሲጠርግ እንደሚያዩ እነዚሁ መከረኞች ለህይወታቸው ሳይሳሱ መናገራቸውን ጥናቱ ትኩረት ሰጥቶ አቅርቦታል።
የመሬት ካሳ እንኳ ባግባቡ የማያገኙት ወገኖች በራሳቸው አንደበት፣ በግብር የደረሰባቸውንና ከፊት ለፊታቸው ያለውን አደጋ አስመልክቶ በዝርዝር ሚዛናዊ በማድረግ ያቀረበው ጥናት ኢህአዴግ ለማስተባበል ከፈለገ በዜናና በተራ ጩኸት ሳይሆን በመረጃ የተደገፈ፣ ሁሉንም ወገኖች ያካተተ ሚዛናዊ ሪፖርት ካቀረበ ብቻ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) በማስተባበያነት እንደሚቀበለው አስቀድሞ ለመግለጽ ይወዳል።
በአገርና በግለሰብ ደረጃ መረጃ ለማዳረስ፣ በተመሳሳይ ኢህአዴግ የሚያሰራጨውን የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ማጋለጥ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰቱን ማሳየት፣ የተሳሳተውን ፖሊሲ ማስቀየር ዋናው የጥናቱ ዓላማ ነው። በጥናቱ በቀረበው ጭብጥ መሰረት የዓለም ባንክ፣ ወዳጅ አገሮች፣ አበዳሪ አገሮች ፖሊሲ አውጪዎች ወዘተ አካሄዳቸውን እንዲመረምሩ ለማስቻል ሰፊ ስራ የተሰራ መሆኑንን በዚህ አጋጣሚ እንጠቁማለን። በተለያዩ አጋጣሚዎች የተለያዩ የውጪና የአገር ውስጥ ሚዲያዎች እንደዘገቡት ሰፊ ስራ የተሰራ ቢሆንም፣ በዋናነት የጉዳዩ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ምን እየተሰራ እንደሆነ ሲረዳ ትግሉን ማቅለል፤ ውጤቱንም ማቅረብ ይቻላል የሚል እምነት አለን።
በዚህና በሌሎችም ተዛማጅ ምክንያቶች በከፍተኛ የሃላፊነት ስሜት፣ ረዥም ጊዜ ተወስዶ የተሰራው የትርጉም ሰራ ሰውን የሚያክል ክቡር ፍጥረት ከማደሪያው እንዲወጣ ተደርጎ እንዴት ወደ ጉድጓድ እንደሚወረወር ለመጪው ትውልድ በታሪክነት፣ አሁን ላለነው በመረጃነት፣ ከሁሉም በላይ ከጩኸትና ከመረጃ አልባ ክስ የምናገኘው ጥቅም አለመኖሩን በመረዳት አቋቋምን ለማስተካከል ይረዳል፣ ታላቅ ምሳሌም ይሆናል ብለን እናምናለን።
ጥናቱን በማሰራጨትና ዜጎች እጅ እንዲደርስ በማድረጉ በኩል የሁሉም ወገኖች ያልተቆጠበ ጥረት እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ለመግለጽ እንወዳለን። በዚህ አጋጣሚ እናወጣዋለን ብለን ካሰብንበት ጊዜ በማለፍ ተጨማሪ ሳምንታት በማዘግየታችን ታላቅ ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡ በአገራችን ካለው የመረጃ አፈና አኳያ የጥናቱ መጠን ሰብሰብና አጠር ባለ መጠን በኢሜይል እንደሚሰራጭ ሆኖ በአዲስ መልክ ሲቀናበር ተጨማሪ ሳምንታትን መውሰዱ የግድ ሆኗል፡፡
የጋራ ንቅናቄያችን ጽሁፉን የማሰራጨቱ ስራ በጨዋነት፣ ለጽሁፉ ባለቤቶች (ለእንግሊዝኛው የኦክላንድ ተቋም ለአማርኛው ደግሞ አኢጋን) አስፈላጊውን እውቅና በመስጠት እንዲሆን በዚህ አጋጣሚ አበክረን እንሳስባለን። ከመሬት ነጠቃ በላይ የከፋ ወንጀል የለም። ዜጎችን በምድራቸው ወደ ባርነት የሚያሸጋግረው የመሬት ነጠቃ የአገሪቱን ሃብትና ንብረት እየበላ ነው። ይህንን ወደር የሌለው ወንጀል ለማጋለጥ፣ ለመታገል፣ ለመቃወምም ሆነ ተዛማጅነት ያላቸው ተግባራት ለማከናወን ለሚፈልጉ ተቋማት፣ ግለሰቦችና ሚዲያዎች ይረዳ ዘንድ (Land Grab – http://landgrabsmne.wordpress.com) የሚባል ብሎግ እንዲሁም በፌስቡክ Land Grab/መሬት ነጠቃ መከፈቱን ለማሳወቅ እንወዳለን። በቅርቡ የሚሻሻለው ይህ ብሎግና የፌስቡክ ገጽ ከመሬት ወረራ ጋር በተያያዘ ሁሉም ዓይነት ማስረጃዎች የሚታተሙበት ስለሚሆን መረጃ ለሚፈልጉ ወገኖች ሁሉ መልካም አጋጣሚ ይሆናል። [gview file=”https://zehabesha.info/wp-content/uploads/2013/05/Final-Amharic-Understanding-Land-Investment-Deals-in-Africa-Ethiopia.pdf”]
በኢሜይል ለማግኘት የሚፈልጉ በሙሉ በሚከተለው አድራሻ (media@solidaritymovement.org) ቢጠይቁን በቀጥታ የምንልክ መሆናችንን እናሳውቃለን፡፡
በመጨረሻም የጋራ ንቅናቄያችን ዋና ዳይሬክተር ለተርጓሚው ከሁሉም በላይ ግን የስርዓቱ ላንቃ ስር ሆነው የህይወት ዋጋ በመክፈል መረጃ ለሰጡት ወገኖች የአክብሮት ምስጋና አቅርበዋል። አቶ ኦባንግ በመልዕክታቸው “በቦታው ላይ ሆናችሁ ለህይወታችሁ ሳትፈሩ ይህንን መረጃ የሰጣችሁ ሁሉ የአገር ጀግኖች ናችሁ፤ አሁን አትታወቁም። አሁን ልንገልጻችሁ አንችልም። ጊዜና ወቅት ጀግንነታችሁን እስኪገልጹት ግን አትረሱም። ልትረሱም አትችሉም። ብዙ ባይነገርላችሁና ባይዘመርላችሁም ታላቅ ስራ ሰርታችሁዋልና ክብር ይሁንላችሁ” ብለዋል፡፡
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ
የሚዲያና ሕዝብ ግንኙነት ግብረኃይል
*********************************************************************************************************
ለዚህ ደብዳቤ ምላሽም ሆነ ለተጨማሪ መረጃ ዋና ዳይሬክተሩን ለሚዲያ ክፍሉ (media@solidaritymovement.org) በመጻፍ ወይም ድረገጻችንን (www.solidaritymovement.org) በመጎብኘት ለመረዳት ይችላሉ፡፡

[gview file=”https://zehabesha.info/wp-content/uploads/2013/05/Final-Amharic-Understanding-Land-Investment-Deals-in-Africa-Ethiopia.pdf”]

3183
Previous Story

ቃለምልልስ የሶማሊያውን ክልል ፕሬዚዳንት ምስጢራዊ ቪድዮዎችን ለአደባባይ ካበቃው አብዱላሂ ሁሴን ጋር

cover 6
Next Story

“በኢንቨስትመንት ስም የሚፈጸም የመሬት ነጠቃ፤ በኢትዮጵያ” ጥናት ትርጉም (117 ገጾች – ጥብቅ ምስጢር)

Latest from Blog

አገራችን አሁን ያለችበት እጅግ አጣብቂኝ ሁኔታ (እውነቱ ቢሆን)

በዚህች አጭር ጽሁፌ ሁለት ነገሮች ላይ ብቻ አተኩራለሁ፡፤ በወልቃይትና ራያ መሬቶች ጉዳይና ስለአብይ አህመድ የማይሳካ ቅዠትና ህልም ዙሪያ፡፡ ስለወልቃይትና ራያ፦ እነዚህ ቦታወች ዱሮ የማን ነበሩ? በማን ስርስ ይተዳደሩ ነበር?  አሁንስ የማን ናቸው?? ለምንስ ይህንን ያህል ደም ያፋስሣሉ… ወዘተ ወደሚለው ጥያቄ ከማምራታችን በፊት መሬቶቹ በውስጣቸው ምን ቢይዙ ነው? አቀማመጣቸውና ጠቀሜታቸውስ ምንና

ሳሙኤልም እንደ እስጢፋኖስ!

 በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com) ሳሙኤል አወቀ እንደ ቅድመ አያቶቹ ዝቅዝቅ መታየትን ያልተቀበለና በጥናት የታገለ ከመጀመሪያዎቹ ፋኖ ሰማእታት አንዱ ነው፡፡  ሰማእታትን መዘንጋት አድራን መብላት ነው፡፡ አደራን መብላትም እርምን መብላት ነው፡፡ እርምን መብላትም መረገም ነው፡፡እርማችንን

በትሮይ ፈረስነት የመከራና የውርደት አገዛዝን ማራዘም ይብቃን!!!   

June 16, 2024 ጠገናው ጎሹ በሥልጣነ መንበር ላይ የሚፈራረቁ ባለጌ፣ ሴረኛ፣ ሸፍጠኛና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች መከረኛውን ህዝብ ከአስከፊ ድንቁርና እና ከሁለንተናዊ የመከራና የውርደት ዶፍ ጋር እንዲለማመድ  ከሚያደርጉባቸው እጅግ በጭካኔ  የተሞሉ ዘዴዎቻቸው መካከል ኮሚቲ፣

ኑሮ የከበዳቸው የመንግሥት ሠራተኞች የምሳ ሰዓትን በቤተ እምነቶች እያሳለፉ መሆኑ ተነገረ

ሲሳይ ሳህሉ / ቀን: June 16, 2024 የቤት ኪራይ መክፈል ያልቻሉ ተደብቀው ቢሮ ውስጥ ያድራሉ ተብሏል መንግሥት የሚከፍላቸው ወርኃዊ ደመወዝ አልበቃ ያላቸው የመንግሥት ሠራተኞች የምሳ ሰዓታቸውን ወደ ቤት እምነቶች በመሄድ፣ እንዲሁም ቤት

ህገ መንግስታዊ ዲዛይን ምርጫዎቻችን የትኞቹ ናቸው?

ኤፍሬም ማዴቦ (emadebo@gmail.com ) እኛ ኢትዮጵያዊያን እራሳችንን ስንገለጽ የረጂም ግዜ ሥልጣኔና ታሪክ ያለን፣በነጭ ያልተገዛን፣ከ2000 አመት በላይ ተከታታይ የመንግስት ሥርዓት ያለን፣የሦስቱ ዘመን ያስቆጠሩ አብርሃማዊ ሃይማኖቶች አገር ነን እያልን ነው። ነገር ግን ባለፉት ሃምሳ አመታት
Go toTop