ፍራንክ ላምፓርድ – የቸልሲው በራሪ ኮከብ

May 5, 2013

ከይርጋ አበበ

የምሥራቅ ለንደኑ ዌስትሃም ዩናይትድ የክለቡ ታላቅ ውጤት የተመዘገበው በ1997/98 የውድድር ዘመን ሲሆን ውጤቱም 5ተኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀበት ነው። የምእራብ ለንደኑ ቼልሲ ደግሞ ከ50 ዓመት በኋላ ከእንግሊዙ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ጋር የተገናኘው በ 2004/05 የውድድር አመት ነበር።በታላቁ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ያስመዘገበው የመጀመሪያ ታላቁ ውጤቱ የሩብ ፍፃሜ ተፋላሚነት ቦታ ነበር በኋላ ዋንጫውን በአሊያንዝ አሬና ማንሳት ቢችልም።

የሮማን አብራሞቪች ቡድን በሀገር ውስጥ እና በአውሮፓ መድረክ ላለፉት አስር አመታት ጡንቻውን ማሳየት ሲጀምርም ሆነ ዌስትሃም ዩናይትድ የአውሮፓ ማህበረሰብን ኮታ ሲያሳካ በሁለቱም ክለቦች የአንበሳውን ድርሻ መወጣት የቻለው ፍራንክ ጀምስ ላምፓርድ ነበር። አባቱ በተጫወቱበት ዌስትሃም ዩናይትድ ውስጥ በአጎቱ ሃሪ ሬድናፕ ስር እየሰለጠነ ያደገው ፍራነክ ጀምስ ላምፓርድ በ2001 የውድድር ዘመን መባቻ ላይ ከምስራቅ ለንደን ወደ ምእራብ ለንደን በ11 ሚሊዮን ፓውንድ ክፍያ ዝውውር በመፈጸም ሰማያዊ ለባሽ ሆነ።

ስምንት ቁጥር ለባሹ እንግሊዛዊ በኦክቶበር 1995 የውድድር ዘመን ወደ ዌልሱ ክለብ ሰዋንሲ ሲቲ በወሳሱል ተዘዋውሮ ጨዋታዎችን ብቻ በሊበርቲ ስታዲየም ተጫውቶ አንድ ግብ አስቆጥሮ ወደ አሳዳጊ ክለቡ ተመለሰ። ሁለት መቶ አንድ ጎሎችን ለሰማያዊ ለባሾቹ በማስቆጠር የምንግዜም የክለቡ ባለብዙ ጎል የመሀል ሜዳ ተጫዋች የሚል ክብርን የተጎናፀፈ ሲሆን አንድ መቶ ስልሳ አራት ጨዋታዎችን ለፕሪሚየር ሊጉ በተከታታይ በመሰለፍም ባለክብረ ወሰን ነው።

ላምፓርድ በቼልሲ

2001-2004

የመጀመሪያ የቼልሲ ጨዋታውን ያደረገው ኦገስት 19/2001 ከሰሜን ምስራቁ የእንግሊዝ ክለብ ኒውካስትል ዩናይትድ ጋር ነበር። በአለን ሺረር ፊት አውራሪነት የሚመራውን ክለብ ገጥሞ አንድ እኩል በመለያየት የስታንፎርድ ብሪጅ ቆይታውን ፋይል ከፈተ። በእዚህ የውድድር ዘመን በሰላሳ ስምንቱም የቼልሲ ጨዋታዎች ሰልፎ ስምንት ግቦችን ለሰማያዊዎቹ አስቆጠረ። የውድድር ዓመቱን በጥሩ እረፍት ጨርሶ ወደ ሜዳ የተመለሰው የቻርልተን አትሌቲክን መረብ በመድፈር ነው።

የቼልሲን 2002/03 የውድድር ዘመን የመክፈቻ ግብ በእዚህ ሁኔታ አስቆጠረ። በአመቱ መጨረሻ ሩሲያዊው ቢሊየነር ረብጣ ዶላሮችን ይዘው ስታንፎርድ ብሪጅ ሲደርሱ በአንፃሩ የክለቡ የምንግዜም ምርጥ ተጫዋች ጣሊያናዊው ጂያንፍራንኮ ዞላ ከክለቡ ጋር ያለውን ጋብቻ ቀደደው።

ጣሊያናዊው የሮቴሽን ሲስተም ተከታይ አሰልጣኝ ክላውዲዎ ራኒዮሪ ደግሞ ዳሚን ዳፍ ሴቫስቲያን ቬሮን ክሎድ ማኬሌሌ ሄርናን ክርስፖን እና የመሳሰሉትን ከዋክብት ወደ ክለባቸው አስመጥቶ የውድድር ዘመናቸውን ሲጀምሩ እንግሊዛዊው አይደክሜ ፍራንክ ላምፓርድ የወሩ ምርጥ ተብሎ በመስከረምና በጥቅምት ወር ተመረጠ።

«የማይበገሩት» የሚል ስም የተሰጣቸውን የቬንገርን ልጆች ተከትለው ሁለተኛ የወጡት ምዕራብ ለንደናውያኑ ኮከባቸው ፍራንክ የዓመቱ ምርጥ ሁለተኛነት ክብርን ከአርሰናሉ ህያው ቴሪ ዳንኤል ሆነሪ ቀጥሎ ተቀበለ። አስራ አራት ግቦችን ደግሞ ለራኒየሪ ቡድን በማስቆጠር የክለቡ ባለውለታ ሆኖ ዓመቱን አጠናቀቀ።

2004 እስከ 2005

ትእግስት አልባው ሩሲያዊው ከበርቴ አሰልጣኞችን መቀያየር የጀመሩበት ዓመት 2004 የክረምት ወቅት። ወጤት አልባውን ጣሊያናዊ ራኒየሪ በማሰናበት በምትካቸው የቼልሲ ደጋፊዎችንና ተጫዋቾችን ፍቅር ዉጤጣማውን ፖርቹጋላዊ ጆዜ ሞሪኒዮን አመጡ። በፖርቹጋሉ ኃያል ክለብ ፖርቶ ያሳኩትን ውጤት ተከትሎ ስታን ፎርድ ብሪጅ የደረሱት ታክቲካሉ ጆዜ ለፍራንክ ላንፓርድ ምቹ ሆነውለት ነበር የቀረቡት።

በዚህም ልጁ 38ቱንም የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ለ3ኛ ተከታታይ ዓመት በመሰለፍ ዓመቱን ፈፀመ። በውድድር ዓመቱ 19 ጐሎችን ሲያስቆጥር 16 ኳሶችን ደግሞ ጣጣቸውን ጨርሰው ለጓደኞቹ አመቻችቶ አቀበለ። ቼልሲ ከግማሽ ክፍለ ዘመን እልህ አስጨራሽ ትዕግስት በኋላ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ሲያነሳ ከወራት ቀደም ብሎ ደግሞ በካርዲፍ ሚሊኒየም ስታዲየም የራፋዬል ቤኔቴዝን ሊቨርፑልን በማሸነፍ የካርሊን ካፕ ዋንጫን አነሳ።

ለዚህ ሁሉ ውጤት መገኘት የቀድሞ የዌስት ሃም ዩናይትድ ተጫዋች ሚና ከሁሉ የላቀ ነበር። በጠንካራ ምቶቹ በሚያስቆጥራቸው ጐሎች ይበልጥ የሚታወቀው ላምፓርድ ሪ2004/05 የውድድር ዘመን ከዓለም ምርጥ አማካኞች ሊያሰልፈው የሚችለውን ብቃት ማሳየት ጀመረ፡፡

በተለይም በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የመጀመሪያው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ በስታንፎርድ ብሪጅ የፍራንክ ራይካርድን ባርሴሎና አራት ለ ሁለት ሲያሸንፋ ሁለት ጐሎችን በማስቆጠር የነሮናልዲንሆ ጐቾን ቡድን ከሩብ ፍፃሜ ውጪ አደረጉት። በሩብ ፍፃሜ ደግሞ የጀርመኑ ኃያል ቡድን ባየር ሙኒክን ነበር የተገናኙት፡፡

በሚሼል ባላክ የሚመራው ሙኒክ ከሩብ ፍፃሜ በፊት በጥሎ ማለፋ የቬንገርን ቡድን በደርሶ መልስ ሦስት ለ ሁለት አሸንፈው ስለነበር ቼልሲንም በቀላሉ አሸንፎ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ይቀላቀላል የሚል የቅድመ ግምት አሸናፊነት አግኝቶ ነበር።

በሙኒክ ተጀምሮ ለንደን ላይ በተጠናቀቀው የሁለቱ ክለቦች የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ 11 ጐሎች የተቆጠሩ ሲሆን፤የጆዜ ሞሪኒሆ ልጆች ስድስቱን በማስቆጠር የበላይ ሆነው ግማሽ ፍፃሜውን ተቀላቀሉ። የምስራቅ ለንደኑ ልጅ በሁለቱ ጨዋታዎች በኦሊቨር ካን መረብ ላይ ሦስት ጊዜ ጐል ያስቆጠረ ሲሆን በተለይም አንዷ ጐሉ እጅግ ማራኪ ነበረች።

በፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ ለጓደኛው ኳስ ማቀበል አይችልም ተብሎ የተገፋው ክሎድ ማኬሌሌ ያሻገረለትን ኳስ በደረቱ አብርዶ እና ተገልብጦ ሲመታት የመጨረሻ ማረፊያዋ ኦሊቨር ካን ጀርባ ከተወጠረው መረብ ውስጥ ነበር። ከዚች ጐል መቆጠር ሁለት ወራት በኋላ ቦልተን ወንደረስን ሁለት ለባዶ አሸንፎ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ሲያነሱ ሁለቱም ጐሎች በነ ጄይ ጄይ ኦካቻ ቡድን ላይ ያስቆጠረው ይኸው እንግሊዛዊ ነበር። የ2004/05 የውድድር ዓመት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ክብርን ተቀዳጅቶ ዓመቱን ዘጋ።

2005-06

ባለፈው የውድድር ዘመን የዓለም ምርጥ 11 ውስጥ ስሙን ያስመዘገበበትን ምርጥ አቋም አሳይቶ የውድድር ዓመቱን የዘጋ ሲሆን፤በዚህ የውድድር ዓመት ደግሞ 16 የፕሪሚየር ሊግ ጐሎችን አስቆጥሮ የውድድር ዘመኑን ጨረሰ፡፡ የዓለም እና የአውሮፓ ምርጥ ተጫዋችነት ክብርን በባርሴሎናው ብራዚላዊ ጥበበኛ ሮናልዲኒሆ ጐቾ ተበልጦ የብር ዋንጫ አሸናፊ ሆነ።

በዴቪድ ጀምስ 159 ጊዜ በተከታታይ የመሰለፍ ሪከርድን በካሻሻለ በኋላ ታህሣስ 28 2005 ፍፃሜው ሆነ። ከማንቸስተር ሲቲ ጋር በነበረበት ጨዋታ በህመም ምክንያት ባለመሰለፍ። በዚህ የውድድር ዓመት የመጀመሪያዎቹ ወራት ብቻ 12 ጊዜ የተቃራኒ ቡድኖችን መረብ ደጋግሞ ጐበኘ። ብላክበርን ሮቨርስ እና ቼልሲ ያደረጉትን የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ባለሜዳው አራት ለ ሁለት ሲያሸንፍ ሁለት ጐሎች አስቆጥሮ የወጣላቸውን የመሀል ሜዳ ሞተር ጆዚ ሞሪኒሆ እንዲህ ሲሉ ነበር የገለፁት።

ብላክ በርን ሮቨርስን አራት ለባዶ አሸንፈው ሲወጡ ሁለት ግቦችን ያስቆጠረውን ፍራንክ ላምፓርድ ማወደሻ ቃላት ከጆዜ ሞሪንሆ አንደበት የወጣውን ቃል ልናነብ ስንዘጋጅ የቦታ ጥበት ለነገ ብሎን ነበር የተለያየነው ። ጆዜ «የዓለማችን እጅግ ምርጡ አማካይ» ሲሉ ነበር የተናገሩት።
2006-07
የቼልሲ ደጋፊዎች ሚስተር ቼልሲ የሚሉት ግዙፉ እንግሊዛዊ ተከላካይ በደረሰበት ከባድ ጉዳት ከሜዳ መራቁን ተከትሎ የቀድሞው የዌስትሃም ዩናይትድ አማካይ የስታንፎርድ ብሪጁን ክለብ ለረጅም ወራት በአምበልነት መምራት የጀመረበት ዓመት ነበር ። በስምንት ተከታታይ ጨዋታዎች ለሰባት ጊዜያት ኳስ እና መረብን በማገናኘት የቼልሲን ጉዞ አሳመረለት። በቼልሲ ክለብ ታሪክ ከመሃል ሜዳ እየተነሳ ብዙ ግቦችን ለሰማያዊዎቹ በዴቪድ ሞይሱ ኤቮርትን ላይ በማስቆጠር ባለ ታሪክ የነበረውን የዴኒስ ዋይዝን ሪከርድ የሰበረውም ከላይ በተጠቀሰው የውድድር ዘመን ነበር ። የ2007 የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫን ቼልሲ ከማንችስተር ዩናይትድ ላይ ሲነጥቅ በፍጻሜው አይቮሪያዊው ዲዲዬር ድሮግባ ያስቆጠራትን ግብ ላምፓርድ ነበር ጣጣዋን ጨርሶ ያቀበለው። በግሉም በሁሉም የኤፍኤ ካፕ ጨዋታዎች 6 ጊዜ በተጋጣሚ መረብ ላይ አግብቶ የውድድሩ ኮኮብ ግብ አግቢ ሆኗል። ክለቡ ማንቸስተር ዩናይትድን በማሸነፍ የዓለማችንን አዛውንት ውድድር ዋንጫ ሲያነሳ የፈጠረበት ደስታ ጫማውን በስታንፎርድ ብሪጅ ለመስቀል ፍላጎት እንዳለው ተናገረ።
2007-08
ከ1996/97 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በጥቂት ግጥሚያዎች ወደ ሜዳ የገባበት የውድድር ዘመን ነው። 40 ጨዋታዎችን ብቻ ለሰማያዊዎቹ ሲጫወት 24ቱ ብቻ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ያደረጋቸው ናቸው። ምንም እንኳ ከሌሎች ዓመታት ያነሱ ጨዋታዎችን ይጫወት እንጂ በዚህ ዓመት በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች የፈጸማቸው ተግባራት እጅግ ከፍተኛ ነበሩ። ክለቡ በኤፍኤ ካፕ ሁደርስ ፊልድ ታውንን ሦስት ለምንም አሸንፎ ወደ ቀጣዩ ዙር ሲያልፍ ስምንት ቁጥር ለባሹ 100ኛ ግቡን ማስቆጠር ቻለ። 100ኛ ግቡን ሲያስቆጥር ለብሶት የተጫወተውን ማሊያ እና ከማሊያው በታች በጽሑፍ የተሞላውን ቲ-ሸርት ወደ ደጋፊዎቹ ወረወረ።  የቲ-ሸርቱ ጽሑፍ መልዕክትም «አንድ መቶ ግቦች፤ ሁሉም ለናንተ ናቸው፤ አመሰግናለሁ» የሚል ነበር ። እግረ መንገዱንም በየጨዋታው ስሙን እያነሱ የሚዘምሩለትን ደጋፊዎቹን ማመስገኑ ነው። የምዕራብ ለንደኑ ክለብ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ተፋላሚ እንዲሆን የአንበሳውን ድርሻ የተወጣ ሲሆን ፣በተለይም በ2005 መረብ ያልነካች የሉይስ ጋርሺያ ግብ የፈጠረችባቸውን ጸጸት ያስረሳች ግብ በሊቨርፑል መረብ ላይ ማሳረፉ በክለብ አጋሮቹ እና በደጋፊዎቹ ጀግና አሰኝቶታል ።
በቀዝቃዛማዋ ሩሲያ ቼልሲና እስራኤላዊው አሰልጣኝ አብርሃም ግራንት አሳዛኝ ሽንፈትን ሲጎነጩ ፍራንክ ላምፓርድ ግን የመድረኩ ምርጥ አማካይነት ክብርን ለማንም ሳያስረክብ ምርጥነቱን ዳግም ለዓለም አስመሰከረ። በሩሲያዋ ሉዚንክ ስታዲየም ከስድሳ ሰባት ሺ ተመልካቾች በላይ  በተከታተሉት የፍፃሜ ጨዋታ አምበሉ ጆን ቴሪ እና አጥቂው ኒኮላስ አኔልካ የመለያ ፍጹም ቅጣት ምት አምክነው ዋንጫው በአሳዛኝ ሁኔታ ከጃቸው ሲወጣ የጨዋታውን የመጀመሪያ ግብ ማስቆጠር የቻለው እንግሊዛዊው ላምፓርድ ነበር።
2008-09
ኦገስት 13/2008 ከሰማያዊዎቹ ጋር ያለውን ቃል ኪዳን ያጠናከረበትን ፊርማ ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት አራዘመ ። ይህም ሰላሳ ዘጠኝ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ፓውንድ በደመወዝ መልክ እንዲከፈለው የሚያደርግ የውል ስምምነት ነበር። ይህ ደመወዙ በወቅቱ የፕሪሚዬር ሊጉ ከፍተኛ ተከፋይ አድርጎት ነበር። የምሥራቅ እንግሊዙን ሰንደርላንድን አምስት ለምንም ሲያሸንፉ ፍራንክ ያስቆጠራት ግብ 100ኛ የፕሪሚዬር ሊግ ግቡ ሆነች። በሃል ሲቲ መረብ ላይ ከሃያ ያርድ ርቀት መትቶ ያስቆጠራት ግቡ ደግሞ  ለሰማያዊ ለባሾቹ ያስቆጠራቸውን ግቦች ወደ 150 ያሳደገች ግብ ነበረች። በጊዜው የቼልሲ አሰልጣኝ የነበሩት የዓለም ዋንጫ አሸናፊው ሉይስ ፍሊፕ ስኮላሪ ስለ ላምፓርድ ግብ ሲናገሩ በሕይወቴ ካየኋቸው እጅግ በጣም ምርጥ ግቦች አንዷ ነበር ያሉት።  የዓለም ኮኮብ መሆን የሚገባው ተጫዋች ያስቆጠራት ምርጥ ግብም በማለት ነው የተናገሩት። ሃያ ግቦችን አስቆጥሮና በሚሊ ሜትር የተለኩ 19 ኳሶችን ደግሞ ለጓደኞቹ በማቀበል የምንጊዜውም ከፍተኛ ግብ ፈጣሪ ያስባለውን ብቃት ለክለቡ ማበርከት ቻለ።
ስኮትላንዳዊው የማንቸስተር ዩናይትድ ውጤታማ አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ስለ ላምፓርድ ችሎታ እማኝነታቸውን ሲሰጡ ኳሶችን ሳያዛንፍ የሚያቀብል በአማካይ ከሃያ በላይ ግቦችን በያመቱ የሚያመርት ሜዳውን ከጫፍ እስከ ጫፍ አካሎ የሚሮጥ ከሁሉ በላይ ደግሞ ይህንን ሁሉ ሲፈፅም ቀሽም ሸርተቴዎችን በመውረድ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾችን ሳይጎዳ መሆኑ ነው በማለት የተናገሩት ንግግራቸው ብዙዎችን ያስማማ ነበር ። በኤፍኤ ካፕ የፍፃሜ ጨዋታ ላይ በኤቨርተን መረብ ውስጥ የጨመራት ግብ የዓመቱ ሃያኛ ግቡ ናት። ግቧን እንዳስቆጠረ ወደ ማዕዘን መምቻው በመሄድ ባንዲራውን ደጋግሞ በመምታት ደስታውን ሲገልጽ ታይቷል። ይህንን ያደረገው ደግሞ ከ30 ዓመት በፊት በ1979 የውድድር ዓመት አባቱ ፍራንክ ላምፓርድ ሲኒዬር በተመሳሳይ መድረክ ግማሽ ፍፃሜ ውድድር ኤቨርተን ላይ ግብ አስቆጥረው ያደረጉትን ነበር የደገመው። ለሦስተኛ ተከታታይ ዓመት የቼልሲ ኮኮብ በመሆንም በክለቡ ደጋፊዎች ዲዲዬር ድሮግባ እና አምበሉ ጆን ቴሪን አስከትሎ ተመረጠ።
2009-10
በግዝፉ ዌምብሌይ ስታዲየም የፕሪሚዬር ሊጉን ሻምፒዮን ማንቸስተር ዩናይትድን በመለያ ምት አራት ለአንድ በማሸነፍ የኮምዩኒቲ ሼልድ ዋንጫን በማንሳት የውድድር ዓመቱን የከፈተው ቼልሲ በኤድዊን ቫን ደር ሳር መረብ ውስጥ ካስቆጠራቸው ፍፁም ቅጣት ምቶች አንዱን ከፍራክ ላምፓርድ ነበር ያገኘው። በታህሳስ ወር የዓለም እግር ኳስ የበላይ ተቆጣጣሪ ፊፋ የዓመቱ ምርጥ አስራ አንድ ውስጥ ካካተታቸው አስራ አንድ የዓለማችን ከዋክብት አንዱ የቼልሲው ምክትል አምበል ነበር። ላምፓርድ ይህንን ክብር ሲያገኝ ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ ለስድስተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። እንዲሁም ለአምስት ተከታታይ ዓመታት 20 ግቦችን ለሮማን አብራሞቪቹ ክለብ ያስቆጠረውም በዚሁ የውድድር ዘመን መሆኑ ተጫዋቹ ብቃቱ ሳይወርድ ለ10 ዓመታት ክለቡን አገልግሎት የሰጠበት ዓመት ነበር። የካርሎ አንቼሎቲ ቡድን ማንቸስተር ዩናይትድን በአንድ ነጥብ በልጦ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ዋንጫን ሲያነሳ እና አፍሪካዊው ዲዲዬር ድሮግባ 29 የፕሪሚዬር ሊግ ግቦችን በማስቆጠር ኮኮብ ግብ አግቢነቱን ከዋይኒ ሩኒ በሁለት በልጦ ሲቀዳጅ በፕሪሚዬር ሊጉ 37ኛው ሳምንት አንፊልድ ላይ ያስቆጠራት ግብ የላምፓርድን ወሳኝነት ያሳየች ነበረች። በዓመቱ መገባደጃ እንግሊዛዊው ኮኮብ 22 የፕሪሚዬር ሊግ ግቦችን በስሙ በማስመዝገብ ብቸኛው ተጫዋች እንዲሆን አስችሎታል።

2 Comments

    • Dear Kassy,

      Honestly speaking, i don’t think we have many to write about. Instead, it would be better to let them learn from those players like Lampard

Comments are closed.

abune merekoriwos
Previous Story

ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ ለትንሣኤ በዓል ቃለ-ምእዳን አስተላለፉ

photo0977 001
Next Story

የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮችና አባላት አንዷለም አራጌን እንዳይጠይቁ በልዩ ሀይል ተባረሩ

Latest from Blog

አገራችን አሁን ያለችበት እጅግ አጣብቂኝ ሁኔታ (እውነቱ ቢሆን)

በዚህች አጭር ጽሁፌ ሁለት ነገሮች ላይ ብቻ አተኩራለሁ፡፤ በወልቃይትና ራያ መሬቶች ጉዳይና ስለአብይ አህመድ የማይሳካ ቅዠትና ህልም ዙሪያ፡፡ ስለወልቃይትና ራያ፦ እነዚህ ቦታወች ዱሮ የማን ነበሩ? በማን ስርስ ይተዳደሩ ነበር?  አሁንስ የማን ናቸው?? ለምንስ ይህንን ያህል ደም ያፋስሣሉ… ወዘተ ወደሚለው ጥያቄ ከማምራታችን በፊት መሬቶቹ በውስጣቸው ምን ቢይዙ ነው? አቀማመጣቸውና ጠቀሜታቸውስ ምንና

ሳሙኤልም እንደ እስጢፋኖስ!

 በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com) ሳሙኤል አወቀ እንደ ቅድመ አያቶቹ ዝቅዝቅ መታየትን ያልተቀበለና በጥናት የታገለ ከመጀመሪያዎቹ ፋኖ ሰማእታት አንዱ ነው፡፡  ሰማእታትን መዘንጋት አድራን መብላት ነው፡፡ አደራን መብላትም እርምን መብላት ነው፡፡ እርምን መብላትም መረገም ነው፡፡እርማችንን

በትሮይ ፈረስነት የመከራና የውርደት አገዛዝን ማራዘም ይብቃን!!!   

June 16, 2024 ጠገናው ጎሹ በሥልጣነ መንበር ላይ የሚፈራረቁ ባለጌ፣ ሴረኛ፣ ሸፍጠኛና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች መከረኛውን ህዝብ ከአስከፊ ድንቁርና እና ከሁለንተናዊ የመከራና የውርደት ዶፍ ጋር እንዲለማመድ  ከሚያደርጉባቸው እጅግ በጭካኔ  የተሞሉ ዘዴዎቻቸው መካከል ኮሚቲ፣

ኑሮ የከበዳቸው የመንግሥት ሠራተኞች የምሳ ሰዓትን በቤተ እምነቶች እያሳለፉ መሆኑ ተነገረ

ሲሳይ ሳህሉ / ቀን: June 16, 2024 የቤት ኪራይ መክፈል ያልቻሉ ተደብቀው ቢሮ ውስጥ ያድራሉ ተብሏል መንግሥት የሚከፍላቸው ወርኃዊ ደመወዝ አልበቃ ያላቸው የመንግሥት ሠራተኞች የምሳ ሰዓታቸውን ወደ ቤት እምነቶች በመሄድ፣ እንዲሁም ቤት

ህገ መንግስታዊ ዲዛይን ምርጫዎቻችን የትኞቹ ናቸው?

ኤፍሬም ማዴቦ (emadebo@gmail.com ) እኛ ኢትዮጵያዊያን እራሳችንን ስንገለጽ የረጂም ግዜ ሥልጣኔና ታሪክ ያለን፣በነጭ ያልተገዛን፣ከ2000 አመት በላይ ተከታታይ የመንግስት ሥርዓት ያለን፣የሦስቱ ዘመን ያስቆጠሩ አብርሃማዊ ሃይማኖቶች አገር ነን እያልን ነው። ነገር ግን ባለፉት ሃምሳ አመታት
Go toTop