የድምጻዊት አቢይ ላቀው "ወደመጣሁበት" ፊልም ለዕይታ በቃ

በጥበበሥላሴ ጥጋቡ (ሪፖርተር ጋዜጣ)፡ – ከሦስት ዓመታት በፊት ባዘጋጀችው የመጀመርያውና ብቸኛው ኮንሰርቷ የብዙዎችን ትኩረት ስባ የነበረችው ድምፃዊት አቢ ላቀው
ዘንድሮ ደግሞ በፊልም ተዋናይትነት ብቅ ብላለች:: ከትናንት በስቲያ በብሔራዊ ቴአትር በተመረቀው
‹‹ወደ መጣሁበት›› በተሰኘው ፊልም ከታዳሚዎች
ጋር ተገናኝታለች:: ጐንደር የተወለደችው ድምፃዊት
አቢ የአሥራ ሦስት ዓመት ታዳጊ ሳለች ወደ
አሜሪካ የሔደችው ሲሆን በ2000 ዓ.ም. በአዲስ
አበባ ለሙዚቃ አፍቃሪው እንግዳ ድምፃዊት ሆና
ስትመጣ ‹‹ማን አለ›› በሚለው ነጠላ ዜማዋ
የብዙዎችን ትኩረትና አድናቆት ማግኘት ችላለች::
ይህ ነጠላ ዜማ በቴሌቪዥን እንዲሁም በተለያዩ
ሬዲዮ ጣቢያዎች በተደጋጋሚ ይለቀቅ እንደነበር
ይታወቃል::
ይህ ዜማ የሁለት ማንነቷ ነፀብራቅ እንደሆነ፤
ኢትዮጵያዊ ማንነቷ እንዲሁም የአሜሪካ እድገቷ
ነፀብራቆች በቋንቋዎቹ መገለጻቸውን አቢ
ትናገራለች:: አቢ ይህን ዜማ ከአማርኛ በተጨማሪ
በእንግሊዝኛም ተጫውታዋለች::
አቢ አሁን ወደ ኢትዮጵያ የመጣችው
ሐምሌ አሥራ ስድስት ከድምፃዊው ኬቨን ሊትል
ጋር ለምታቀርበው ኮንሰርት እንዲሁም ‹‹ወደ
መጣሁበት›› በተሰኘውና ለተወነችበት ፊልሟ
ምረቃ መሆኑን ለሪፖርተር ገልጻለች::
እሷ እንደምትለው፣ በ2000 ዓ.ም. ያደረገችው
የመጀመርያ ኮንሰርቷ ከፍተኛ ፍላጐቷ ለሆነው
የፊልም ሥራ በር ከፍቶላታል:: የፊልሙ ፕሮዲዩሰር
በፊልሙ ላይ እንድትተውን ያቀረበላትን ጥያቄ
ድርሰቱን (ስክሪፕቱን) ካነበበች በኋላ አዎንታዋን
ገልጻለች:: በዚህ ፊልም ላይ በመተወኗም እስከ
አሁን በፊልም ተዋንያን ከተከፈለ ክፍያ ትልቅ
የተባለው 150 ሺሕ ብር ሊከፈላት ችሏል::
‹‹ሁሌም ፊልም ለመሥራት እፈልግ ነበር::
የዚህን ፊልም ድርሰት ደግሞ ወድጄዋለሁ::
ክፍያውን በተመለከተ ይህን ያህልም ትልቅ
የሚባል አይመስለኝም:: ቢሆንም ይህን ያህል
ገንዘብ ለመከፈል የመጀመርያ በመሆኔ እድለኛ
ነኝ:: ወደፊት ተዋናዮቻችን ከዚህ የተሻለ ተከፋይ
እንደሚሆኑ ተስፋ አደርጋለሁ፤›› ብላለች::
በፊልሙ ላይ የተጫወተቻትን ገጸ ባሕርይ
ወዳታለች፤ እንዲሁም ቀረፃው የተካሔደባቸው
ቦታዎች የትውልድ ቦታዋን ጨምሮ ባሕር ዳርና
በአዲስ አበባ ያለፈውን የአገር ቤት ሕይወቷ
እንዳስታወሳት ገልጻለች:: በፊልሙ ስለተጫወተቻት
ገጸ ባሕርይ ላቀረብንላት ጥያቄ፣ ‹‹ስለፊልሙ ብዙ
ነገሮችን አሁን መናገር አልፈልግም፤›› በማለት
መልሳለች:: ከትናንትና በስቲያ ለሕዝብ እይታ የበቃው
አቢ የተወነችበት ፊልም የመጀመርያዋ እንደሆነ፤
በቀጣይ ሌሎች ፊልሞችን እንደምታበረክትና
‹‹ይምህ ጅማሬዬ ነው፤›› ብላለች::
ለሙዚቃ ያላት ፍቅር መታየት የጀመረው ገና
ታዳጊ ልጅ ሳለች ቢሆንም አንድም ቀን ሙዚቃን
‹‹ሥራዬ ብዬ›› እይዘዋለሁ ብላ አስባ አታውቅም::
ከሙዚቃ ጋር ያላትን ቁርኝት ‹‹ሙዚቃ ሁሉ ነገሬ
ነው፤ የቅርብ ጓደኛዬ፤›› በማለት ትገልጻለች::
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለች በትምህርት ቤት
ውስጥ በነበረው የሙዚቃ ቡድን ተሳታፊ ብትሆንም
አልቆየችበትም:: ቆይታም የሙዚቃ ትምህርት
መከታተሏንና ሙዚቃ አቀናባሪው ወንድሟ
ሚሊዮን ላቀው የመራት መንገድ ለሙዚቃ ሕይወቷ
አስተዋጽኦ መደረጉን ሳትጠቅስ አላለፈችም::
የመጀመርያ አልበሟ ‹‹ማን አለ››ን ከለቀቀች
በኋላ ነገሮች መስመር መያዝ ጀመሩ:: ከተለያዩ
አካላት የተለያዩ የሥራ ጥያቄዎች ይቀርቡላት
ጀመር:: ከዚያም ተከታታይ የሥራ ጉዞዎችን
ማድረግ ቀጠለች:: በአሁኑ ወቅትም በዓመት
ከአሥራ አምስት እስከ ሃያ ጉዞዎችን
ታደርጋለች::
እያንዳንዱ የሙዚቃ ሥራዋ
እንደሚያስደስታት የምትናገረው
አቢ ከሁለት ዓመታት በፊት በግሪክ
ያዘጋጀችው ኮንሰርት ልዩ እንደነበር
ታስታውሳለች:: የሙዚቃ ኮንሰርቱ ከሁለት
ዓመታት በፊት የተደረገ ቢሆንም አቢ
ግን ከሁለት ቀናት በፊት እንደተከናወነ
ሁሉ የእያንዳንዱ ነገር ትውስታዋ ጉልህ
ነው:: ‹‹በኮንሰርቱ ላይ የነበሩት ጥቂት
ኢትዮጵያውያን ብቻ ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያዊ
ያልሆኑ መብዛታቸውና ዘፈኔን ማወቃቸው
አስደንቆኝ ነበር፤›› በማለት ከሦስት
ዓመታት በፊት ገቢው ለልብ ሕሙማን
ድጋፍ ይውል ዘንድ በተዘጋጀው ኮንሰርት
ላይ ያገኘችው የሕዝብ ምላሽም አስደንቋት
እንደነበር ትናገራለች::
‹‹ሁልጊዜም ለየትኛውም ዝግጅት
ምንም ነገር ጠብቄ አላውቅም:: ይህን
ያህል ሰው ቢገኝ ብዬ የገመትኩት ነገርም
አልነበረም:: እንደ ቁማር ነው::መጨረሻ ላይ ሁሉም ነገር ግልጽ ይሆናል፤›› በማለት በኮንሰርቱ
ላይ የነበረውን ነገር ታብራራለች::
ራሷን አርአያ ሊሆን እንደሚችል ሙዚቀኛ የምትመለከተው
አቢ፣ አንዳንዴ ግጥም ትጽፋለች:: ምናልባት ሌሎች አርቲስቶች
ግጥም ከሰጧት ግጥሙ የፍቅር እንዲሆን ትፈልጋለች::
‹‹ለኔ ዋናውና ትልቁ ነገር ፍቅር ነው:: እናም እስከማውቀው
ድረስ ለኔ ፍቅር ትልቅ ቦታ አለው:: ሙዚቃም ስለፍቅር
መልዕክት ማስተላለፍ መቻል አለበት:: እኔ በመጥፎ ነገሮች ራሴን
አላስጨንቅም:: የማተኩረውም ጥሩ ነገሮች ላይ ነው::››
አስተዳደጓ ትንሽ ከበድ ያለ ሁኔታ ቢኖረውም ከዚያ ሁሉ መጥፎ
አጋጣሚዎች ራሷን እንዳላቀቀች ትናገራለች:: ‹‹ከኢትዮጵያ ለሄደ
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሁሉ ነገሮች አልጋ ባልጋ አይሆኑም::››
እንደምታስታውሰው፣ ትምህርት ቤቷ ውስጥ የነበረችው ብቸኛ
ጥቁር በመሆኗ ምክንያት የዘር መድልዎና መገለል አስተናግዳለች::
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስትገባ ሁኔታዎች እየተቀየሩ መጡ::
ሌሎች ኢትዮጵያውያንም እሷ የምትማርበት ትምህርት ቤት
በመግባታቸው እሷ ለይ የነበረው ብቸኛ አትኩሮት ተቀይሯል::
መድልዎና መገለል ቢደርሱባትም በትምህርት ቤት ቆይታዋ
ከመደበኛ ትምህርት በተጨማሪ ባሉ ሌሎች እንቅስቃሴዎች ላይ
ትሳተፍ ነበር:: ከነዚህም ውስጥ የእጅ ኳስና የሙዚቃ ቡድን
ይገኙበታል:: ‹‹በጊዜው የነበረው ሁኔታ ይረብሸኝ ነበር:: ምንም
እንኳን ከጥቂት ቆይታ በኋላ ብረሳውም በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን
ቤተሰቦቼ ከጐኔ ነበሩ፤›› ብላለች:: አቢ በሕይወቷ ውስጥ ያጋጠማትን
ዘረኝነትም ይሁኑ መጥፎ ነገሮች ዘፈኖቿ ላይ ማካተት አትፈልግም::
ሁሌም የምትዘፍነው ስለፍቅር ብቻ ነው::
‹‹ሙዚቃ መሆን ያለበት አንድና አንድ ነገር ፍቅር ነው፤››
የምትለው አቢ በሁለት ቋንቋዎች ብትዘፍንም በአማርኛ መዝፈን
ምርጫዋ ነው:: ‹‹በእንግሊዝኛ የሚዘፍኑ ብዙ ዘፋኞች አሉ::
የእንግሊዝኛ ዘፈን የሚፈልጉ እነሱን መስማት ይችላሉ:: እኔ መዝፈን
የምፈልገው በአማርኛ ነው:: ውጭ አገር ላሉ ኢትዮጵያውያንም
እንደ አማርኛ መማርያ ይሆናቸዋል፤›› በማለት አቢ ትገልጻለች::
ሙሉ ጊዜዋን ለሙዚቃ ብትሰጥም በስምንት ዓመት የሙዚቃ
ቆይታዋ መሥራት የቻለችው አንድ አልበም ብቻ ነው:: ለዚህም እንደ
ምክንያት አድርጋ የምታቀርበው ባሏት ብዙ ጉዞዎችና ኮንሰርቶች
ምክንያት ነው:: አሁን ግን ያንን ሩጫዋን ገታ አድርጋ 12 ዘፈኖች
ያሉት አንድ አልበም ሠርታ ጨርሳለች::
ለረዥም ጊዜ በቅርቡ ሕይወቱ ካለፈው ይርጋ ዱባለ ጋር
አብራ መዝፈን ብትፈልግም አልተሳካላትም:: ‹‹እኔ ይርጋን በጣም
የማደንቀውና የምወደው ዘፋኝ ነው:: ለብዙ ዓመታትም አብሬው
መዝፈን እፈልግ ነበር:: ግን ሳይሳካ ቀርቷል፤›› በማለት አቢ
ታጠቃልላለች::

ተጨማሪ ያንብቡ:  ድርድር እንጅ ይቅርታ አልጠየቅንም? ስምምነቱ ተጥሷል
Share