"ከትላንትናዉ ይልቅ ዛሬ እራሴን አብዝቼ አዘጋጃለሁ" ብርቱካን ሚደቅሳ


“ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ወንድሜ ሳይሆን ሲቀር ማየት አይቻለኝም። ወንድሜ ስመ ጥፉ ፣ ግብረ ጥፉ ሊሆን ይችላል። ግን ምንም ማድረግ አልችልም …..ወንድሜ ነዉ። “

“የኢትዮጵያን ቀን ስናከብር የልጆቿን ወንድማማችነትና እህትማማችነት እናወድስ። አባቶቻችን የተዉልንን የአንድነት መንፈስ እንላበስ። ኢትዮጵያዊነታችን የሚያገል ሳይሆን የሚያቅፍ ይሁን። በጥላቻና በጭካኔ ሳይሆን በርህራሄ ይሞላ።”

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በአትላንታ በዚሆች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን ያቀረበችዉ ታሪካዊና ልብ የሚመስጥ፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሊያነበዉና ሊያዳምጠዉ የሚገባዉን ንግግር እንደሚከተለዉ ለአንባቢያን አቅርበናል፡

“በጣም በጣም ደስ ትላላችሁ። እንኳን ለዚህ ቀን አበቃን። እንኳን ለዚህ አደረሰን። በእናንተ መካከል መገኘት በጣም ያስደስታል። ፍቅራችሁ በጣም ያስደስታል። በጣም አመሰግናለሁ።

ከሁሉም አስቀድሜ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ የስፖርት ፌዴሬሽን በዚህ በርካታ ኢትዮጵያዉያንን በሚያሰባስብ ታላቅ ፌስታ ላይ በክብር እንግድነት እንድገኝ ላደረገልኝ ግብዣ ክፍተኛ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

በመቀጠልም በዚህ የተሰባሰባችሁም ይሁን በዚህ ያልተገኛችሁ ኢትዮጵያዉያን አገራችን የብልጽግናና የፍትህ አገር ሆና ለማየት በሚደረገዉ ትግል፣ ለአመታት ያደረጋችሁትን አስተዋጾ በዚህ አጋጣሚ ላደንቅ እፈልጋለሁ። ከዚህም በላይ ባሳለፍኩት የ19 ወራት አስቸጋሪ ወቅት ላደረጋችሁልኝ ሁለገብ ድጋፍ ያለኝን ምስጋናና አክብሮት በትህትና ልገልጽ እወዳለሁ። እናንተም ሆናችሁ በአገራችን የሚኖረዉ ነጻነት ወዳጅ ኢትዮጵያዉዊ ከምገምተዉ በላይ ወዳችሁኛል። ይገበኛል ብዬ ከማስበዉ በላይ አክብራችሁኛል። ፈጣሪ ያክብርልኝ። ይህንን ዉለታችሁን ለመመለስ የምሞክረዉ ለአገሬ ያለኝን መልካም ሃሳብ፣ ለአገሬ ያለኝ የፍትህና የብልጽግና ምኞት፣ ደግሜ በማደስ ብቻ ነዉ። ይህንን አላማ ለማገልገልም ከትላንትናዉ ይልቅ ዛሬ እራሴን አብዝቼ አዘጋጃለሁ።
ይህ መድረክ ስፖርትና ኢትዮጵያዊ ባህልን የሚመለከት መድረክ በመሆኑ በረጅም ንግግር አላሰለቻችሁም። ነገር ግን እኛን ሁላችንንም እዚህ ስላገናኘን፣ ስለኢትዮጱያዊነታችን ትንሽ ቃላት ለመወርወር እፈለጋለሁ። ሁላችንም እንደምናዉቀዉ በእዉቀት በስለንና ትልቅ ሰዉ ተብለን፣ በሕይወት አስተሳሰባችን ወይንም በርእዮተ አለማችን ተቃኝተን፣ ለኢትዮጵያ ና ለኢትዮጵያዊነት ከምንሰጠዉ ትርጉም በላይ፣ በእምቦቅቅላችን አዉቀንም ሆነ ሳናዉቀዉ የምንይዘዉ የአገራችን ስእል ቀለማት እጅግ ይደምቃሉ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የጃዋር የሳተላይት ጠለፋና ስለላ ጉድ፦‼

ለዚህም ይመስለኛል ባለቅኔያችን ጸጋዬ ገብረመድህን የአገራችንን ክቡር ሰማእት የአቡኑ ጴጥሮስ የመጨረሻ የሕሊና ክርክር እንድህ ሲል በብእሩ የከተበዉ

“ ከናቴ ማሕጸን አልፌ ፤ ከኢትዮጵያ አልፌ
ከአፈሯ ጠፍጥፌ ጠፍጠፌ፣ ደሜን ከደሟ ጠንፍፌ፣ ከወዟ ወዜን ጠንፍፌ፣
በሕጻን እግሬ ልኬበት፣ በሕልም አጥፋና ከንፌ፣
እረኝነቴ በሰማ በምድር ላይ አሳልፌ
ከጫጩትና ከጥጃ ከግልገል ጋር ተቃቅፌ”

እያለ ይቀጥልና

“ፈረሰ ግልቢያ ሲሸመጥጥ
ከወፎች ዜማ ስቀዳ
ልቤ በንፋስ ተንሳፎ በዋሽንት ዋይታ ሲቀዳ
ያቺን ነዉ ኢትዮጵያ የምላት
እመብርሃን እረሳሻት
ያቺን የልጅነት ምስራች
የሕጻንነት ብስራት
የሳቅ የፍንደቃ ዘመን
የምኞት የተስፋ ብዛት
ያሺ የልጅነት እናት ..”

እያለ ባለቅኔዉ ይቀጥላላል።

በአዲስ አበባ ሰሜን ምስራቅ አካባቢ የምትገኘዉ፣ እኔ ያደኩባት መንደር ብዙዎቻችሁ እንደምታዉቋት አልጠራጠረም። ፈረንሳይ ለጋሲዮን ትባላለች። በዚች መንደር የሚኖሩ የቤተሰብ አባዎራዎች አብዛኞቹ ገቢያቸዉ በወር ከአንድ እና ከሁለት መቶ ብር የማይበልጥ ፣ አገራቸዉን የሚወዱና በዉትድርና ዘመናቸዉን ያገለገሉ ነበሩ። ነበሩ ያልኩት አብዛኞቹ በሞት የተለዩን ስለሆነ ነዉ። ሚስቶቻቸዉ ደግሞ ሌትና ቀን ለቤተሰባቸዉ ኑሮና ደህንነት የሚተክሩ የቤት እመቤቶች ናቸዉ። ድህነት የኑሯቸዉ አካል ነበረን ? አዎን አሳምሮ ነበር። በተለይ እንደ እኔ እናትና አባት ፈጣሪ በአንድ ልጅ ያልወሰናቸዉ ወላጆች የልጆቻቸዉ የአመት ልብስ፣ የእለት ጉርሻ አለማሳጣት፣ ወደ ትምህትር ቤት መላክ፣ ጤንነታቸዉን መንከባከብ ቋሚ ፈተናቸዉና የዘዉትር ጸሎታቸዉ ነበር።

እነዚህ ወገኖች በሕይወታቸዉ ደስታ ያጡ ምስኪኖች ነበሩ ብላችሁ ብታስቡ አይፈረድባችሁም። እዉነቱ ግን እንደዚያ አልነበረም። በሚያስደንቅ ሁኔታ እርስ በርሳቸዉ በፈጠሩት የፍቅር የመተጋገዝ ገመድ እራሳቸዉንና ልጆቻቸዉን በአመታት መካከል አሸጋግረዋል። በዚህ ትንሽ አለም በፈረንሳይ ለጋሲዮን የአንዱ እጦት የሌላዉ እጦት ፤ የአንዱ ሕመም የሌላዉ ሕመም፣ ሐዘንና ደስታዉም እንደዚያ ነበረ። ችግራችንን በፍቅር አሸነፍነዉ። የንዋይ እጦታችንን በሰዉ ሃብት ረታነዉ::

ተጨማሪ ያንብቡ:  ቴዲ አፍሮ በሲያትል የተሳካ የሙዚቃ ኮንሰርት አደረገ፣ በሳንሆዜና በሚኒሶታ ይቀጥላል

ልላዉ የሚገርመኝ ደግሞ የግጭት አፈታታችን ነበር። በግጭት አፈታት ኤክስፐርት የሚመራ ነዉ የሚመስለዉ ብዬ ብናገር ማጋነን አይሆንም።

ሌላ አንድ ነገር ረስቼ .. በዚህ ማህበራዊ መሰባሰብ፣ በዚህ ማህበራዊ መስተጋብር የማንኛዉም ግለሰብ የብሄር ጀርባ እዚህ ግባ እንደሚባል ነገር ተቆጥሮ አያዉቅም።

ይግረማችሁና ከጎሮቤቶቼ አንዱ የአባቴ አገር ልጅ እንደሆነ ያወኩት አባቴ ከሞተ በኋላ ነበር። በአጠቃላይ ይህ የቤተሰቦች ሕብረት የሆነዉ ትልቁ ቤተሰብ ሁሌ ዋጋ የምሰጠዉ አገራዊ ስሜት ቀርጾብኛል። ከዚህ የተነሳ ይመስለኛል አንድ ነገር ማድረግ እጅግ እጅግ የሚያቅተኝ።፡ ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ወንድሜ ሳይሆን ሲቀር ማየት አይቻለኝም። ወንድሜ ስመ ጥፉ ፣ ግብረ ጥፉ ሊሆን ይችላል። ግን ምንም ማድረግ አልችልም …..ወንድሜ ነዉ።

ምን ልትጠይቁኝ እንደምትችሉ አስባለሁ። አሳሪዎችሽን ያካትታል ወይ ? ትሉ ይሆናል። ለዚህም መለሴ አዎን የሚል ነዉ። ከዚህም ተነስቼ ለፍትህ ለነጻነት ለሕግ የበላይነት የሚደረገዉ ትግል ሆነ የሚከፈለዉ መስዋእትነት ለነርሱም የሚደረግ ለነርሱም የሚከፈል መስዋእትነት ነዉ ብዬ ከልቤ አምናለሁ።

ወገኖቼ

የበደሉኝ ሁሉ የበደሉት ይሄ በዘመናት ዉስጥ ያስተሳሰረን ኢትዮጵያዊ ወንድማማችነትን ስላላወቁት ወይንም ሊያወቁት ስላልፈለጉ ነዉ።

በዚች በዉብ ከተማ በአትላንታ የኢትዮጵያን ቀን ስናከብር የልጆቿን ወንድማማችነትና እህትማማችነት እናወድስ። አባቶቻችን የተዉልንን የአንድነት መንፈስ እንላበስ። ኢትዮጵያዊነታችን የሚያገል ሳይሆን የሚያቅፍ ይሁን። በጥላቻና በጭካኔ ሳይሆን በርህራሄ ይሞላ። የኢትዮጵያን መጥፎ ፍሬዎች እየታገልንም እንኳን፣ ልጆቿን አጉድለን አናስብባት። ለሁሉም የሚገባዉን ሰብዓዊ ክብርና ርህራሄ አንንፈግባት።

ከአለማችን ታላላቅ ሰዎች አንዱ የሆነዉ ማህተመ ጋንዲ እንዳለዉ ፍቅር የፈሪዎች ሳይሆን የደፋሮች ተግባር ነዉና ወገኖቻችንን ለማፍቅርር እንድፈር።

ስለሆነም የዛሬዉን ብቻ ሳይሆን የነገዉን አሻግረን አይተን፣ በዉስጥ ሕሊናችን ከተራራዉ ጀርባ ደርሰን፣ ይህች የጨዋና የኩሩ አገር ከዛሬ በላይ እንደሆነች እንረዳ። ዛሬ ቀኗን ስናከብር ከአንገገት በላይ ሳይሆን ከልባችን የኢትዮጵያ ልጆች ወንድማማችነትን አምነንና ተቀብለን፣ የዜጎች ሁሉ የጋራ መኖሪያ የሆነችዉን ኢትዮጵያ በአንድነት እናክብራት፤ እናወድሳት።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአሶሳው ግድያ የታቀደ ስለመሆኑ ተረጋገጠ
Share