የትግራይ ህዝብ ራሱን ከውጭ ወደ ውስጥ እንዲህ ቢያይ?

June 28, 2011

(ከገለታው ዘለቀ) ሕወሃት ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ወዲህ ለነጋሪ ከማይመቹ ክስተቶች መካከል አንዱ የትግራይ ህዝብ በዚህ መንግስት ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ ተጠቅሙዋል የሚሉ ወገኖች ቅሬታ ሲሆን በተቃራኒው ይህን ጉምጉምታ የሚቃወሙ ወገኖች ደሞ የተጠቀመው አብዛኛው የትግራይ ህዝብ ሳይሆን ጥቂት የትግራይ ተወላጆች ናቸው በርግጥ እነዚህ ጥቂት ግለሰቦች በትግራይ ህዝብ ስም እየነገዱ ስለሆነ የትግራይ ህዝብ ያላግባብ እየተጠቀመ እንደሆነ ሊያስመስለው ይችላል ብለው ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከራሉ::

ዛሬ ይህችን ደብዳቤ ለመላክ ያነሳሳኝ ጉዳይ ለነዚህ ወገኖች ፍርድ ለመስጠት አይደለም::ማነኝና::መነሻዬ የሃገራችንን መጻኢ እድል ለማሳመር እውነት እውነቱን ተነጋግረን ፈውስ ለማውረድ የሚያስችለንን የግል አስተያየት ለመሰንዘር ነበር::በ ዚህች አጭር ደብዳቤ የትግራይ ህዝብ በተለይ ተጠቅሙዋል የሚሉ ወገኖች ራሳቸውን ከውጭ ወደ ውስጥ እንዲያዩ እንዲሁም የትግራይ ወገኖችም ራሳቸውን ከውጭ ወደ ውስጥ እንዲያዩ የፍቅር አሳብ ለማቀበል እሞክራለሁ::

የትግራይ ህዝብ ራሱን ከውጭ ወደ ውስጥ እንዲህ ቢያይ?

የትግራይ ህዝብ ላፍታ ወጣ ብሎ እነዚህ ያላግባብ እየተጠቀምክ ነው የሚሉትን ኢትዮጵያዊ ወንድሞቹን ሲያይ ጥያቄያቸው የቅናት አለመሆኑን በሱ መጠቀም አይናቸው ደም የለበሰ አለመሆኑን ይረዳል::ይልቁን የወንድሞቹ ጥያቄ የፍትህ ጥያቄ መሆኑን ይገነዘባል::ላፍታ ወጣ ብሎ ራሱን በኦሮሞዎች,ባማሮች,ባኙዋኮች በሌሎቹም ወገኖቹ ቦታ አስቀምጦ እነዚህ ወገኖቹ ምን ሊሰማቸው እንደሚችል መረዳት ይችላል::

እውነቱን እንነጋገር ከተባለ እነዚህ ወገኖች ብዙ ናቸው::ጥያቄአቸውም ኢትዮጵያ ሃገራችን ብዙህ በመሆኑዋ ይህንን ተፈጥሮዋን የሚያስተናብር ፍትህ ከመፈለግ የመነጨ ነው::የትግራይ ህዝብ ያላግባብ ተጠቀመ ብለው እንዲያዝኑ ያደረጋቸው አንዱ መነሻ ሰፊ በሆነቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ባህር በሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት ውስጥ በፖለቲካ ስልጣኑም ሆነ በንግዱ በከፍተኛ የበላይነት የትግራይ ሰዎች ተቆጣጥረውት መታየታቸው ነው :: ንብረትነቱ የትግራይ ህዝብ መሆኑ ባቶ ስብሃት ሳይቀር ከተመሰከረለት ከኤፈርት ጀምሮ እስከ ባልትና ቤቶች ድረስ የትግራይ ሰዎች ጎልተው ይታያሉ::እንዳንድ የትግራይ ሰዎች ያለ ቀረጥ ይነግዱ ሁሉ እንደነበር ይታዎቃል::በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ከታችኛው ጀምሮ እስከ ላይ መኮንኖች ድረስ ዋና ዋና ቦታዎች በትግራይ ሰዎች እጅ ነው::ከገቢያቸው የማይመጣጠን ኑሮ የሚኖሩትም በአብዛኛው እነዚሁ የትግራይ ልጆች ናቸው::በዘጠና ሰባቱ ምርጫ ዋዜማ የቅንጅት መሪዎች የመንግስትን ስታትስቲክስ ዋቢ አድርገው ሲከራከሩ እንዳየነው ትግራይ በትምህርት,በጤና,በኢንፍራ ስትራክቸር,በአጠቃላይ የማህባራዊ አገልግሎት ተቋማት ግንባታ ከኦሮሚያ በጅጉ ይበልጣል::የራሱ የህወሃት የፖለቲካ እምነት በብሄር መብት ላይ የተመሰረተ ሆኖ ግን በተግባር በጣም ጥቂት የሆነው የትግራይ ህዝብ ዋናዎቹን የፖለቲካ ስልጣኖች መቆጣጠራቸው ኦሮሞውን ወይም አማራውን ቢያስከፋው ትክክል ነው ይላል ትግራይ ራሱን ከውጭ ወደ ወስጥ ሲያይ::ትግራይ ላፍታ ወጣ ብሎ ራሱን ከውጭ ወደ ስውጥ ሲያይ እነዚህ የትግራይ ህዝብ ተጠቀመ የሚሉ ወገኖች ትግራይ ያላግባብ ተጠቅሙዋል ብለው አፋቸውን ሞልተው ለመናገር የሚችሉብትን መንገድ እንዲህ ያየዋል::እነዚህ ወገኖች ትግራይ ተጠቅሙዋል ለማለት እኮ የትግራይ ህዝብ በሙሉ ሃብታም ሆኖ ማየት አይጠበቅባቸውም::እንዲህ አይነቱ ሁኔታም በተግባር አይገጥምም::የትግራይ ህዝብ ያላግባብ ተጠቅሙዋል ለሚሉ ወገኖች ጥያቄ ምላሹ የትግራይ ህዝብ ሳይሆን ጥቂት የትግራይ ሰዎች ናቸው የተጠቀሙት ሲባል ስንት ሰዎች ማለት ነው ?የትግራይ ህዝብ ራሱ በቀጥር ትንሽ አይደለም ወይ? ብሎ እንደገና ይጠይቃል በመቶዎች? በሺዎች? ወይስ ሚሊዮን ይጠጋል?ይላል ::በዛች ሰፊ አገር እና ህዝብ ወስጥ በንግዱም በስልጣኑም ጎልተው ከታዮ ቀላል የማይባሉ የትግራይ ሰዎች ያላግባብ እየተጠቀሙ ነው ማለት ነው::እንደው ቀጥር መድፈር ጥሩ አይደለም እንጂ ወደ ሚሊየን የሚጠጋ ሰው በንግዱና በተለያዩ ድጎማዎች የትግራይ ሰዎች ከሌላው ኢትዮጵያዊ በተለዬ እየተጠቀሙ ከሆነ የትግራይ ህዝብ ደሞ ወደ 6% ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የትግራይ ህዝብ ተጠቅሙዋል ለማለት ይቻላል እኮ::እነዚህ ያላግባብ የተጠቀሙ ሰዎች እኮ ዞሮ ዞሮ ያንኑ ቤተሰባቸውን ነው የሚጠቅሙት::በ ኢትዮጵያ አማካይ የቤተሰብ መጠን ወደ 6 ሰው ከሆነ የትግራይ ህዝብ በጃዙርም ቢሆን ተነካካ ብለው ሊደመድሙ ቢችሉ አይፈረድባቸወም::

ትግራይ ራሱን ከውጭ ወደ ውስጥ ሲያይ እንዲህ የሚጠይቁትን ሰዎች እስቲ ትግራይ ተጠቅሟል የምትል ከሆነ የተጠቀሙትን ሰዎች ስም ዝርዝር ጥራልኝ ብሎ አይሳለቅበትም::ይህ ህዝብ እኮ ከአፍ ወደ ጆሮ በሆነ የመረጃ ዘዴው ለሃያ አመታት ያከማቸው እውነት ነው::ሁሉም በየቀበሌው ያየውን በየ ንግድ ቦታው ያየውን በየ መስሪያቤቱ ያየውን ኢፍትሃዊነት በየማህበራዊ አጋጣሚው እያነሳ ሲያወጣው እና ሲያውርደው ቆይቶ በልፍ ምስክሮች ያረጋገጠው ሃቅ ነው ይላል::

የትግራይ ህዝብ ላፍታ ወጣ ብሎ ከውጭ ሆኖ ራሱን ሲያይ የነዚህን ወገኖቹን ሃዘን ሊረዳው ይችልና አሃ የነዚህ የወንድሞቼ ጥርጣሬ ያስኬዳቸዋል ስሜታቸውም መራራ ተቃውሞአቸውም ገባኝ ይልና ለፍትህ ከሌሎቹ ወገኖቹ ጋር ይታገለል::የወገኖቹን ጥያቄም ሜዳ ላይ አይጥልም::ትክክል ነው የታሪክ አጋጣሚ ሆነና እንዲህ አይነት ሰዎች ከቀበሌዬ ወጡ? ብሎ ይቆጫል ከቁጭትም አልፎ በየ ማህበራዊ አጋጣሚው ከሌላው ወገኑ ጋር ሲገናኝ የሌላውን ወገኑን መራራ ተቃውሞ መረዳቱን ሲገልጽ እና ማትቡን ሲያሳይ ለሌሎች ወንድሞቹ ፈውስ ይስባል::

ሌላውም ህዝብ ራሱን ከውጭ ወደ ውስጥ እንዲህ ቢያይ?

በተለይ በትግራይ ህዝብ ላይ ቅሬታ ያደረባቸው ወገኖች ላፍታ ወጣ ብለው ራሳቸውን በትግራይ ቦታ አስቀምጠው ቢያዩ መልካም ነው::እነዚህ ከልባቸው ያዘኑ ወገኖች አሁን በዚህ ታሪካዊ ጊዜ የትግራይ ህዝብ ባለፈበት የህይዎት ልምድ ባልፍ ምን ይሰማኝ ነበር? እነዚህ ከአንድ ሰፈር የፈለቁ ሰዎች ከትግራይ መመንጨታቸው ቀርቶ ከኔ ቀበሌ ቢሆኑስ? የትግራይን ህዝብ አንዴ የንግስናው ተራ የኛ ነው ሌሎች ተቃዋሚዎች ሁሉ የሚቃወሙህ ያንተን ንግስና ተራ ንቀው ወይም ላንተ መገዛቱን ጠልተው ነው የአስተዳደር ትችት ሲሰነዘር ደሞ እየው ተመልከት አስተዳደሩን የሚቃወሙት ያንተን የተፈጥሮ የማስተዳደር ችሎታ መናቃቸው ወይም አስተዳደር አትችልም ማለታቸው ነው በኢኮኖሚው ትንሽ አልፎልህ ቢያዩ አይናቸው በቅናት ቀልቶ ነው እያሉ ትግራይን እየጠላለፉ ግራ ግብት እንዳደረጉት ይህ ሁኔታ በኔ ቀበሌ ሆኖ ቢሆን አንድ አይነት ታሪክ ይሆን ነበር ብልው ያስባሉ::እነዚሁ ወገኖች ላፍታ ከውጭ ወደ ውስጥ ራሳቸውን ሲያዩ እንዲህ ይላሉ::የትግራይ ህዝብ ስጉ ነው ርህሩህም ነው::በመሆኑም እነዚህ ብልጣ ብልጥ ከወንዙ የፈለቁ ልጆቹ ይህን የዋህ ስሜቱን ተጠቅመውበታል::አንዳንዴ ብናጠፋም ልጆችህ ነን ምን ታረገናለህ? የወለዱት የት ይጣላል? ብለው የወላድ አንጀቱን ያላውሱታል:: አንዳንዴ በበረሃ በንጹህ ልቦና ለፍትህ የሞቱትን ልጆቹን እያስታወሱ ገራገር ልቡን ግራ አግብተዋል::የአስተዳደር ብልሹነት ጥያቄ ሌላው ኢትዮጵያዊ ሲያነሳ በትግራይ በኩል ህፍረት እንዲሰማው በደመ ነፍስም እንዲከላከል የሚያደርግ ስነ ልቦና ለመፍጠር እነዚህ የህወሃት መሪዎች ለብዙ አመት ሰርተዋል::በዚህም የትግራይ ህዝብ ልቡ በሃዘን ተመቷል::

ሌላው ህዝብ ራሱን ከውጭ ወደ ውስጥ ሲያይ እንዲህ ይላል::የትግራዩ ወንድሜ በርግጥ ትንሽ በኢኮኖሚውና በማህበራዊው ተቋማት ተጠቅሟል ይሁን እንጂ በዚህ መንግስት ተለይቶም ተጎድቷል::ስለ ምን የዚህ የወንድሜ ጉዳቱ ሳይታየኝ ጥቅሙ ጎልቶ ታየኝ? ብሎ ልቡ ይራራል::

ይህ መንግስት ትግራይን የመጨረሻው መደበቂያ አድርጎ ስለወሰደ ከሌላው ኢትዮጵያዊ በላይ አፈና አለበት::ህይወቱ በስጋት እንዲሞላ ሆኑዋል::ባንድ በኩል ለውጥ ከመጣ ከዚህ በፊት በወያኔ ጊዜ ስትጠቀም ነበር ብሎ ኦሮሞው ይሁን አማራው ይጨርስሃል እያሉ ስጋት ፈጥረውበታል::በመሆኑም እነዚህን ጥቂት እያሳዩ ከሌሎች ወንድሞቹ አቆራርጠው ከቤቱ እንዲቀመጥ እያደረጉት ያሉትን ሰዎች በሆዱ እየረገም የሆዱን በሆዱ ይዞ ተቀምጧል:: የሚመጣውን ለውጥ ለመደገፍ ዋስትናም የማጣት ስሜት እንዲኖረው አርገውታል::ይላል ራሱን በትግራይ ቦታ አድርጎ የሚያየው ወገን::ይህ ወገን ትግራይን ሲረዳው ጥቅሙን ብቻ ሳይሆን ጉዳቱን ሲያይለት እና በየማህበራዊ አጋጣሚው መረዳቱን ሲገልጽለት ፈውስ በነፍሱ መፍሰስ ይጀምራል::

የፈውሱ ቀንዲል ካህናት

ከላይ ያነሳነው የፈውስ አሳብ ወደ ተግባር የሚቀርበው በአጠቃላይ በህዝብ ደረጃ በጅምላ ሲታሰብ ሳይሆን ሃላፊነት የሚሰማቸው እና የታችኛው ህዝብ መከራና ስቃይ የሚያማቸው የፖለቲካና የሲቭክ ማህበራት መሪዎች እና አባላት በመጀመሪያ ራሳቸውን ከውጭ ወደ ውስጥ ማዬት ሲጀምሩ ነው::እነዚህ በህዝብ ልብ ውስጥ ያሉ ሌሂቃን/ባንድም በሌላም መንገድ በ ህብረተሰቡ ውስጥ ተጽእኖ ያላቸው/ ከፒራሚዱ ከታችኛው ክፍል ስላለው ህዝብ ሲሉ እልህና በነገር መቆራቆስ ትተው መረዳዳት/understanding each other/ ሲያሳዩ የታችኛው ህዝብም ይቀበላል::በመሆኑም በትግራይ በኦሮሞ በአማራ ውዘተ.ያሉ የሃይማኖት አባቶችም ሆኑ ምሁራን ይህንን የፈውስ አሸንዳ ወደ ህዝቦቻቸው መዘርጋት አለባቸው::ሃቅን እየሸመጠጡ ልዩነትን ከማስፋት ይልቅ እውነታዎችን እየተቀበሉ የሃገርን መጻኢ እድል ለማበጀት አብረው መታገል ግድ ይላቸዋል::ለብዙህ ኢትዮጵያ የሚበጃት ፍትህ በመሆኑ ለጋራ ጥቅም ይህ ትውልድ ለፍትህ መታገል አለበት::ፍትህ ንጉሳሽን ፍትህ አሳላፊ ፍትህ አስተናባሪ ሲሆን የሁላችን ልብ ሊያርፍ ይችላል::ይህ ደሞ መለኮት የሚሰራው ከኛ አቅም በላይ የሆነ አይደለም::በሃገራችንን የታሰረውን ፍትህ መልቀቅ ብቻ ነው::ነጻ ፍርድ ቤት ነጻ ፖሊስ ነጻ ፕሬስ ወዘተ.ማቋቋም እንችላለል::

እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ

ገለታው ዘለቀ

Geletawzeleke@gmail.com

Previous Story

No to "Grand Coalition" with the EPRDF

Next Story

Ethiopian rebels: We handed over two aid workers we were holding

Latest from Blog

አዲስአበባ ተኩስ ተከፈተ “ለመደራደር ዝግጁ ነን” አረጋ ከበደ | አብይ አደገኛውን ካርድ መዘዙ | አዲሱ አዋጅና የቀረበበት ተቃውሞ “የሞተም ሰው ንብረት ይጣራል | ጌታቸው ያጋለጠው ጸብ

አዲስአበባ ተኩስ ተከፈተ “ለመደራደር ዝግጁ ነን” አረጋ ከበደ\  አዲሱ አዋጅና የቀረበበት ተቃውሞ “የሞተም ሰው ንብረት ይጣራል አብይ አደገኛውን ካርድ መዘዙ ጌታቸው ያጋለጠው ጸብ

ከመጠምጠም መማርን እናስቀድም!

;በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com) አብዛኛው አንባቢ ተገንዝቧል ብዬ እንደምገምተው ሕዝብ ለቡና ቲራቲም፣ ለግብዣ፣ ለበዓል፣ ለሰረግ፣ ለሐዘን፣ ለእድር፣ ለእቁብ ለውይይትና ለሌሎችም ማህበረሰባዊ ጉዳዮች ሲገናኝ የሚበዛው አድማጭ ሳይሆን ተናጋሪ  ወይም ደግሞ ለመናገር  መቀመጫውን ከወንበር ወይም
Go toTop