የችግር መንስኤ መድኃኒት / መፍተሄ አይሆንም !!! – ማላጂ

እንዳለመታደል ሆኖ የ ሽ ዘመን የነጻነት ምድር በሆነች አገር ነጻ አዉጭ ብሎ የስነ መንግስት(ፖለቲካ ድርጅት )  አደረጃጀት መኖር እና ይህን ህጋዊ ብሎ መቀበል እና ማስተግበር  ዕዉን በሆነባት አገር የዜጎች ህይወት እንደዋዛ በማን አለብኝነት ቢቀጠፍ የማያስገርም መሆኑን በኢትዮጵያ ምድር ለዓመታት የታየ እና የተለመደ ሆኗል፡፡

በሶስት ምርኩዞች (ህገ መንግስት፣ ያልተማከለ የህዝብ አስተዳደር እና ምርጫ) እየተገፋ በነጻ አዉጭ  የስነ መንግስት ትግል (ፖለቲካ ድርጅት ) ስም የሚንቀሳቀሱት በቅደም ተከተል( ትህነግ፣ ኦነግ እና ጉምዝ ህዝቦች ነጻ አዉጭ ግንባር ) ከተመሰረቱበት ጊዜ ጀምሮ አስካለንበት ዘመን በብሄራዊ ደህንነት እና የዜጎች የመኖር ተፈጥሯዊ እና ዓለማቀፋዊ ሰባዊ መብቶች ላይ ስለደረሰ ዕልቂት እና ስደት ይህም የጅምላ ጭፍጨፋ ፣ ዘር ፍጅት ፣ የማግለል እና ሽብር ተግባር ካለፉት 25 ዓመታት መማር ባለመቻል እና የህዝብን መከራ አለመጋራት እና መፍትሄ ለመስጠት አለመሞከር በማዕከላዊ ሆነ በአካባቢ አስተዳደር የመንግስት አደረጃጀት እና መዋቅር የህግ ተጠያቂነት ካለመኖሩ የሚከሰት ተደጋጋሚ ሁነት ነዉ ፡፡

በየትኛዉም ዓለም ባለንበት 21ኛ ክ/ዘመን  የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ካልሆነ በቀር የጨቋኝ  እና ተጨቋኝ  ትርክት በመፍጠር የህዝብን ነጻነት እና የብሄራዊ ልዑላዊነት አደጋ በመጣል የሚደረግ የጥቅም እና የስነ መንግስት ስልጣን ትንቅንቅ ከልካይ ማጣት የሚያመላክተዉ ለእነዚህ ከላይ ለተገለፁት ነጻ አዉጭ ድርጅቶች አገር እና ህዝብን የሚጎዳ ማንኛዉም ድርጊት ለማከናወን  ይፋ ፈቃድ እንደተሰጣቸዉ እና ይህም በአገሪቷ ዜጎች ላይ ለሚደርስ የህልዉና  ስጋት በባለቤትነት እና ኃላፊነት ያገባኛል አለማለት መሆኑን የችግሩ መደጋገም እና መሽከርከር ማሳያ ነዉ ፡፡

በምድራችን የሠዉ ልጅ ታሪክ በእኛ አገር የተፈፀመ እና እየተፈፀመ ያለ ኢሰባዊ ድርጊት ( ማግለል፣ ማሳደድ፣ መግደል (በተናጠል፣ በጅምላ እና ለይቶ ማጥፋት/ በዘር ፍጅት)፣ ለባህላዊ እና ዕምነታዊ ዕሴቶች ዕዉቅና እና አክብሮት መንፈግ ( ጅምላ ግድያ እና ቀብር) ወንጀል እና ኃጢያት ሆኖ  ዛሬ በሰዉ ልጆች ካልተወገዘ  ፣ ወንጀለኞች ለግማሽ ምዕተ ዓመታት በአገር እና ህዝብ ላይ ያደረሱት እና እያደረሱ ላለዉ እጅግ ዘግናኝ እና በሰዉ ልጅ የመኖር ታሪክ የማይደረግ እና የማይረሳ ወንጀል ተጠያቂ እና ዋጋ ከፋይ በማይደረጉበት ስርዓት እና አገር ከዚህ በላይ እና ከምትነግሩን በላይ ስለሆነ ፣ እየሆነ ስላለ እና ስለሚሆን ችግር እና መርዶ መደረት መገለባበጥ እንጅ ለዉጥ  አይጠበቅም  ፡፡

በአገራችን አበዉ ነጋሪየ ሠዳቢየ እንዲሉ ትናንት ፍትህ እና ርትዕ ከእኛ በላይ ሲል የነበር ዛሬም ፍትህ እና ርትዕ እያለ ቢያቀነቅን የማይኖር ቃል  እያደር እንደገለባ መቅለል ነዉ ፡፡

ለዉሸት  ለይኩን ዕዉነት እንጅ ሀሰት አይሆንም  ለዕዉነተኛ መፍትሄ እዉነተኛ መንስዔን መንቀስ እንጅ ማድበስበስ ለዓመታት የተለመደ ማባባስ ነዉ ፡፡

የመከራ መንስኤ  በመንከባከብ  እና መፍትሄ በመግፋት እና በማክፋፋት የህዝብን እና አገርን የመከራ ዘመናት ከማደስ እና ከማራዘም  ዉጭ የአገሪቱ ችግር ጅረት በሚነሳበት ምንጭ ዉሃ የችግር  ማንጫ እና ማምለጫ በማድረግ ለሚጥር እና ለሚሞክር  ሁሉ  ካለፉት ሜጋ ስህተት እና ዉድቀት ለመማር ካለመፈለግ የሚመጣ በህዝብ እና አገር ቁስል መርዝ እንደመጨመር ነዉ ፡፡

በአንድ አገር ላይ ሁለት እና ሶስት ደረጃ ያለዉ ትዉልድ እና ዜጋ ለመፍጠር የመሞከር አባዜም በህዝቦች የአብሮነት ትስስር በመቆራረጥ የመደመር ዕሳቤን በተቃርኖ የሚያነብር ይሆናል ፡፡
የአገራችን የዓመታት ችግር መንስዔ እና መፍትሄ በህገ መንግስት ይዘት፣ ትርጉም እና አተገባበር ዙሪያ ስላለዉ መሰረታዊ አወንታዊ ሆነ አሉታዊ እንደምታ አይነኬ አድርጎ የማየት እና የመመካት አባዜ ከልብ በመነጨ ብሄራዊ እና ህዝባዊ ጥምረት፣ ጥረት እና ቁርጠኝነት እስካልተፈታ ጊዜ ድረስ የዘመናት ችግር  በተፈጠረበት ይዘት እና ፍላጎት አግባብ  ይፈታል ብሎ ማሰብ የዜጎችን እና የአገሪቷን ቀጣይ ህልዉና አደጋ ላይ በመጣል  የዓመታት  ሰቆቃ ከማሳነስ እና ከማለባበስ የሚራምድ  አይሆንም  ፡፡

እናም ዞትር መከራ እና ችግር ከመስማት እና ከማየት የችግሩን ምንጭ/ መንስዔ  ማድረቅ ላይ ለመስራት ህብረት ፣ አንድነት ፣ ቁርጠኝነት እና የዓላማ ፅናት መላበስ ብቸኛዉ አማራጭ መሆኑን የእኛ እና የዚህች አገር መጻዒ ፋንታ የሚያሳስበዉ ሰባዊ ፍጡር ሁሉ ሊገነዘብ ይገባል ፡፡

ለሁላችንም   ፡-

አስቀድሞ ከመናገር…..በስራ እና በተግበር መኖር ፣

ከመሳቀቅ ……. ቀድሞ መጠንቀቅ፣

ከመመደናቆር…….መተባበር፣

በሌሎች ከማሳበብ……..ማሰብ፣

ከአፍቅሮ ንዋይ/ ገንዘብ…..መገንዘብ፣

ከማድነቅ…….መጠያየቅ፣

ከመደነቃቀፍ…..መደጋገፍ፣

ከመለፋለፍ ….ንቆ ማለፍ ፣

ካድር ባይነት …… የራስ ማንነት፣

ከይምሰል………ማስተዋል  ፣

ከመለያየት …..አብሮነት ፤  ይሁነን ፤ አሜን  ፡፡

                                                                 

                                                                                                                                     

 

ተጨማሪ ያንብቡ:  የእህቴ መከራ የኔም ነው - ከሞሲት የሻነህ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share