ፖለቲካና ስደት
(ወለላዬ ከስዊድን)
መቼም እኔና አንቺን ሲፈጥረን
ጉዳችሁ አይለቅ ያለን ነን
ይሄው ደግሞ ተሰደንም
ልንስማማ አልደፈርንም።
ሳትሰሚኝ አጣጥመሽ
እኔም ያንቺን ሳላውቅልሽ
መግባባቱ እንዳቃተን
በየአቅጣጫው ተበታትነን
ስንፋተግ ዕድሜ ገፋን።
እውነታውን ስንሸሸው፣ መወያየት ስንፈራ
ቀለብ ሆነን ሀሜት ጉራ።
በይ ተይው ግዴለም፣ ድሮውንም ሲፈጥረን
ጉዳችሁ አይለቅ ያለን ነን።
ለነገሩ ትተነውስ ወዴት ልንደርስ
ግደለሽም እኛው ደፍረን እንዋቀስ
የዕለት የዕለቱን ትተነው
ዘላቂውን እንመርምረው።
የጋራ ችግራችንን ተነጋግረን
በጋራ እንፈታለን እያልን
በአፍ ብቻ ስንወተውት
ከልብ አጣን ስምምነት።
ስለሀገሬ ስለሀገርሽ
አንቺም ስሚኝ፣ እኔም ልስማሽ!
የማተያት፤ የማልተዋት
የጋራችን አንድ ሀገር ናት።
ታዲያ ይሄንን እያውቅን
በድርጅት ተከፋፍለን
እላይ ላዩን ታጋይ መስለን
ውስጥ ለውስጥ ተሸዋውደን
“በእከክልኝ ልከክልህ” ተዘማምደን
እንኳን ካለው ከጎናችን
ጸበኛ ሆ’ን ከህሊናችን።
የጠላታችንን ጠላት፣ ወዳጅ ማድረግ
እንቢ ብለን በማፈግፈግ
እሱ ራሱ ተስፋ እንዲቆርጥ
እንጥራለን ለመበጥበጥ
ይሄን አውቀን በአዲስ መንፈስ
ካልፈታነው ያለንን ቀውስ
ከቶ አንችልም የትም ልንደርስ።
ከአፍ ብልጠት ሳትቆጥሪብኝ
ማነህ? ብለሽ ሳታይብኝ
እንደ አባቶች በእርጋታ፣ እንደ እናቶች በጽሞና
ተወቃቅሰን እንቃና
ህዝብ ማለት እኮ-እኔና አንቺ ነን
ሀገርም ማለትም እኛ ነን።
ሀገር ሀገር ብንላት
በምላሳችን ጫፍ ለጥፈናት
አናድናትም ከጥፋት
እስቲ እንተወው አልልሽም ይሄንንስ
ትተነውስ ወዴት ልንደርስ?
ሌላ ሀገር እኮ ቢኖሩት
ያስጨንቃል የራስ እጦት
አዎን! ችሎ ማደር ይባላል
ችሎ ማደር ይቻላል
ሀገር ካልኖረ ችሎ፣ ታድሮስ የት ይገባል?
ይሄው! በትግሉ ጎራ ብንኮለኮልም
እኔና አንቺ ጠርተን አንጠራም
እርስ በእርስ ተቆራቁዘን
ተኮራርፈን ተሰዳድበን
ስም መግደያ ሰይፍ መዘን
ስንቱን ጥለን ጨፈጨፍነው
ስንቱን ሰቅለን አወረድነው
እኔና አንቺ ከመጣብን
ምን ያስዋሻል እንደዚህ ነን።
በይ! እንፍታው በንግግር
እንድንድን ከዚህ ችግር
እስከመቼ ተፈራርተን
ተባባሉ መባል ጠልተን
እውነታውን አንሸፍን
ድንገት እንኳን ቢሆነን ፈውስ
ተገጣጥመን እንዋቀስ።
አንዴ ወጥተን ሥልጣን ላይ
የልጅ ልጆች እዛው ሳናይ
እኔና አንቺን የሚነካን
ወያኔ ነው ውረድ ካለን።
የኔና ያንቺ ሥልጣን አቅም
ከልጆች መብት ብዙ አያንስም
ብናጠፋስ ማን ተናግሮን
እንዳላየ ነው የሚያልፈን
ይሄን ይሄን ካላረምን
ገዚው ፓርቲ የሚበልጠን
ልብ ብለን ካስተዋልነው
በሚንስትር ብቻ እኮ ነው።
እንተወው አልልሽም ይሄንንስ
እኔና አንቺው እንዋቀስ
መወቃቀስ ለህሊናው ላደረ ሰው
እንደ እንቆቆ መዳኒት ነው
ይሄን አውቀን አምነንበት
መራሯን ቃል እንጨልጣት
ካለን ሕመም ለመፈወስ
ደግመን ደግመን እንዋቀስ
ግድ የለሽም ገጽታሽን አታጥቁሪ
አንገትሽን አታዙሪ
ለሰው ያሉትን – ለኔ ብሎ መስማት
ይጠቅማል እንጂ የለውም ጉዳት።
በይ! እንግዲህ እንዋቀስ፣ ብለን ካልን
ስህተታችን ካስተማረን፤
ትንሽ ሲገኝ የምንኮራ
ወሬ ሰምተን የምንፈራ
በገዢና ተገዢ አይነት
በኔ አውቃለሁ ግትርነት
በተበለጥኩ ምቀኝነት
ተተብትበን ምንራኮት
የጠራ አቋም ያልጨበጥን
የማንፈትሽ ውስጣችንን
እኛን ጥለን ሌላ ምንጥል
በግማሽ ልብ ምንታገል
መወያየት አስፈርቶን
አሉባልታ የተጫነን
ምን ያስዋሻል፣ እኔና አንቺ እንደዚህ ነን።
ወለላዬ ከስዊድን
[email protected]