በፀጋው መላኩ
በኢትዮጵያ በነዳጅ ፍለጋና ምርመራ ሥራዎች ከተሰማሩት ቱሎ እና አፍሪካ ኦይል ከተባሉ ሁለት ኩባንያዎች ጋር የሚሰራጩ የቻይናው ‘‘BGP Inc’’ የተባለ ኩባንያ አሁን ሥራውን እያከናወነበት ካለው የደቡብ ኦሞ ዞን ወደ ኬኒያ ድንበር የፍተሻ መሳሪያዎቹ (ማሽኖቹን) በማንቀሳቀሱ በአካባቢው ያለው የሁለቱ ሀገራት ድንበር መዘጋቱን የብሉምበርግ ዘገባ አመላከተ። በአካባቢው የሚንቀሳቀሱት ከባድ ማሽኖች ቦታው አስቸጋሪ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ቀናትን ይወስዳሉ ተብሎ ይጠበቃል። የፕሮጀክቱ ኃላፊዎች በአካባቢው የተወሰኑ ሜትሮች ርቀት ያላቸውን ጉድጓዶች በመቆፈር የናሙና ጥናቶችን (Sesmic Studies) ለማከናወን የኬኒያንና ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር በንግግር ላይ መሆናቸውን ዘገባው ያመለክታል።
ኩባንያው በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ከባድ ማሽኖችን ቆፍሮ ማሽኖችን ወደ ኢትዮ-ኬኒያ ድንበር እያንቀሳቀሰ መሆኑ የታወቀ ሲሆን ከዚሁ ጋር በተያያዘ በደቡብ ኦሞ ዞን አቅጣጫ ያለው የሁለቱ ሀገራት አዋሳኝ ድንበር መዘጋቱ ታውቋል። እንደ ብሉምበርግ ዘገባ በኦሞ ወንዝ አካባቢ ተከትሎ ባለው የኢትዮ ኬኒያ ድንበር እስከ 10 ቢሊዮን በርሜል የሚደርስ የነዳጅና የጋዝ ክምችትን ይዟል ተብሎ የሚገመት መሆኑን ዘገባው ጨምሮ አመልክቷል። ቶሎ እና አፍሪካ ኦይል የተባሉ ሁለት ታላላቅ አለም አቀፍ የነዳጅ ፈላጊና አውጪ ኩባንያዎች በሁለቱ ሀገራት ድንበሮች አካባቢ በዚህ ዓመት 11 የነዳጅ ጉድጓድ ቁፋሮዎችን ለማካሄድ እቅድ ያላቸው መሆኑ ዘገባው አመልክቷል።
በኬኒያና በኡጋንዳ ነዳጅን ያገኘው ቱሎ የተባለው ኩባንያ በደቡብ ኦሞ ዞን የነዳጅ ፍለጋን እያከናወነ ሲሆን ብዙም ሩቅ ባልሆነ ጊዜ ውስጥም ውጤቱን ያሳውቃል ተብሎ ይጠበቃል። በዚሁ ጉዳይ ያነጋገርናቸው በማዕድን ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ባጫ ፉጆ በሀገሪቱ ነዳጅ መገኘቱ ከተረጋገጠ ይፋዊ በሆነ መንገድ በመንግስት የሚገለፅ መሆኑን ገልፀው ይሁንና እስከ አሁን ባለው ሁኔታ ኩባንያዎቹ በየሦስት ወሩ ለሚኒስቴር መስሪያቤቱ ሪፖርት በማቅረብ ከሚደረገው ሙያዊ ትንተና ውጪ የተሰጠ ይፋዊ መግለጫ የሌለ መሆኑን አመልክተዋል።n
(ምንጭ፡- ሰንደቅ ጋዜጣ 8ኛ ዓመት ቁጥር 390 ረቡዕ የካቲት 20 ቀን 2005 ዓ.ም )