February 15, 2013
31 mins read

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት ዕጩ ፓትርያሪካቸውን አሳወቁ፤ ማህበረ ቅዱሳንስ?

(ዘ-ሐበሻ) ቀደም ባለው ዜናችን ላይ መንግስት 6ኛው ፓትርያርክ አቡነ ሳሙኤልን ምርጫው ሳይደረግ መወሰኑን መዘገባችን ይታወሳል። በመንግስት ተላላኪው አባይ ፀሐዬ ሥር እየሠሩ ነው የሚባልላቸው የፓትርያርክ አስመራጭ ኮሚቴዎችና በፓትርያርክ ምርጫ ላይ የሚሳተፉት ወገኖች እኚህኑ ፓትርያርክ እንዲመረጡ ሽርጉዳቸውን ቀጥለዋል። የሐበሻ የቤተክህነት ምንጮች እንደሚሉት በፓትርያርክ ምርጫ ላይ ድምጽ ይሰጣሉ ከሚባሉት ውስጥ አንዱ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሲሆን ተማሪዎቹ ለ6ኛው ፓትርያርክነት አቡነ ሳሙኤልን አጭተዋል። የፓትርያርክ ጥቆማው ዛሬ እንደሚጠናቀቅ ይጠብቃል ያሉ ምንጮቻችን “በመንግስት ሚድያዎች በፓትርያርክ ምርጫ ይሳተፋል የተባለው የማህበረ ቅዱሳን ፓትርያርክ ማን ይሆን?” ሲሉ ይጠይቃሉ። በዚሁም መሠረት ዛሬ የሁሉም ጥቆማ ስለሚጠናቀቅ መረጃው እንደደረሰን እናቀርባለን።
የሐራ ተዋሕዶ ድረ ገጽን ዘገባ እንደሚከተለው አስተናግደነዋል

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት ዕጩ ፓትርያሪካቸውን አሳወቁ

•ከዘረኝነትና ሙስና የጸዳ አመራር ይሰጣሉ ያሏቸውን አቡነ ሳሙኤልን በዕጩነት ጠቁመዋል
•የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆችም ሊቀ ጳጳሱ በዕጩነት እንዲቀርቡ ጠይቀዋል
•በአስመራጭ ኮሚቴው ላይ የተአማኒነት ጥያቄ ተነሥቷል
•የዕጩ ፓትርያሪክ ጥቆማው በነገው ዕለት ይጠናቀቃል

የስድስተኛው ፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ ባወጣው የምርጫ መርሐ ግብር መሠረት፣ ከካህናትና ምእመናን የዕጩ ፓትርያሪክ ጥቆማ የሚቀበልበት ቀን ነገ የካቲት 8 ቀን 2005 ዓ.ም ከቀኑ 10፡00 ላይ ያበቃል፡፡ ኮሚቴው የጥቆማ ስጡ ጥያቄውን በይፋ ካቀረበ በኋላ በተለይ በአዲስ አበባ አራቱ አህጉረ ስብከት የሚገኙ ዕጩ ፓትርያሪክ ጠቋሚዎቹ የድጋፍ ደብዳቤዎችን ይዘው በተናጠልና በቡድን እየቀረቡ የተዘጋጀውን ቅጽ በመሙላት ዕጩአቸውን እየሰጡ ይገኛሉ፤ ጥቆማው ለዚሁ በተመደበው የፋክስ አድራሻ ጭምር እየተላከ መኾኑ ነው የተነገረው፡፡

ጠቋሚዎች የሚሞሏቸው ቅጾች በዕጩነት ስለሚጠቁሙት አባት ያላቸውን ዕውቂያ (በምንኲስና፣ በአገልግሎት፣ በትምህርት ደረጃ) የሚጠይቅ/የሚለካ ነው ተብሏል፡፡ ቅጹ በጠቋሚዎች ከተሞላ በኋላ የአስመራጭ ኮሚቴው አባላት ተፈራርመው በማኅተም በታሸገው ሣጥን ውስጥ የሚጨምሩት ሲኾን ይኸው ሣጥን ነገ ከቀኑ 10፡00 በኋላ ሁሉም የኮሚቴው አባላት ባሉበት ተከፍቶ የመለየት ሥራ እንደሚሠራ ተገልጧል፡፡ በፋክስ የሚላኩት የዕጩ ጥቆማዎች በምን ላይ ተመሥርተው እንደሚሰጡና የምሥጢራዊነት ጉዳይ ግን አጠያያቂ ኾኗል፡፡

ስለ ስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ በውጭና በሀገር ውስጥ አህጉረ ስብከት የሚገኙ ካህናትና ምእመናን የዕጩ ፓትርያሪክ መመዘኛ መስፈርቱን ዐውቀውና ተገንዝበው በጥቆማው የሚሳተፉበት የብዙኀን መድረክ ሳይፈጠር፣ ባሉትም መድረኰች አንዳችም የቅስቀሳ ሥራ ሳይሠራ በነገው ዕለት የሚጠናቀቀው የዕጩ ጥቆማው ይኹን የምርጫው መርሐ ግብር አጠቃላይ ሂደት በኮሚቴውና በአባላቱ ላይ የግልጽነት፣ የተአማኒነትና የተቀባይነት ጥያቄዎችን እያሥነሳ ማወያየቱን ቀጥሏል፡፡ ጥያቄዎቹ ኮሚቴው ከሚሠራበት የፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንብ ይዘት (መንፈሳዊነት)፣ ካወጣው የምርጫ አፈጻጸም መርሐ ግብር ግልጽነትና ጥድፊያ ጀምሮ እስከ ግሰለብ አባላቱ ማንነት ድረስ የሚዘልቅ ነው፡፡

ይህም ኾኖ ‹‹ምርጫው መካሄዱ ካልቀረ አጋጣሚውና ዕድሉ አይለፈን›› በሚል በተደራጀ አኳኋን ለዕጩ ጥቆማው የተንቀሳቀሱ አካላት መታየታቸው አልቀረም፡፡ በተረጋገጠ መነሻ÷ በጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ለመልካም አስተዳደር እንዲያመች በሚል ለአራት ከተከፈለው የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት መካከል የሦስቱ አህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች የቀድሞውን የሀ/ስብከቱን ረዳት ሊቀ ጳጳስ፣ የአሁኑን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን በዕጩ ፓትርያሪክነት መጠቆማቸው ታውቋል፡፡

ሥራ አስኪያጆቹና ጽ/ቤቶቻቸው በእነርሱ ጥቆማ ብቻ ሳይወሰኑ በአህጉረ ስብከቱ ሥር የሚገኙ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች የጥቆማ ብቻ ሳይኾን የመራጭነት መብት እንዲሰጣቸው አስመራጭ ኮሚቴውን መጠየቃቸው ተሰምቷል፡፡ ጥያቄያቸውን ያዳመጡት የአስመራጭ ኮሚቴው አባላት በተለይም ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ግን ጥያቄው በምርጫ ሕገ ደንቡ ስለመራጮች የተደነገገውን እንደሚፃረር በመግለጽ በቀጥታ ውድቅ እንዳደረጉትና በተግሣጽ እንደመለሷቸው ተገልጧል፡፡

በዛሬው ዕለት በዕጩ ጥቆማው ረገድ የተሰማው ሌላ የተደራጀ እንቅስቃሴ ደግሞ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የመደበኛው መርሐ ግብር ደቀ መዛሙርት ያቀረቡት ነው፡፡ በቁጥር 180 ያህል የኾኑ ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ዓመት የኮሌጁ ደቀ መዛሙርት፣ የስድስተኛውን ፓትርያሪክ ምርጫ በማስመልከት ከትላንት ረቡዕ እስከ ነገ ዐርብ የሚቆይ የሦስት ቀናት የማኅበር ጸሎት እያደረጉ ነው፡፡ ደቀ መዛሙርት ለጸሎት ሱባኤው በተሰባሰቡት አጋጣሚ ስለ ኮሌጁ አስተዳደር እና ስለ መምህራኑ ተወያይተዋል፤ ጥያቄዎችንም አንሥተዋል፡፡

ከጠቅላላ ሕዝቧ ዐሥር በመቶ ብቻ የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት በሚገኝባት የኮፕት ቤተ ክርስቲያን ዘጠኝ የነገረ መለኮት ኮሌጆች እንዳሉ የሚናገሩት ደቀ መዛሙርቱ÷ ከጠቅላላ ሕዝቧ ከግማሽ በላይ ለሚኾነው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ ለሚገኝባት ኢትዮጵያ ሦስት የነገረ መለኰት ኮሌጆች ብቻ በቂ እንዳልኾኑ ተናግረዋል፡፡ ከኮሌጆች የቁጥር ማነስ ባሻገር የሚመደበው በጀትና የሚሰጠው አገልግሎት አለመመጣጠን፣ ለተቋሞቹ የማይመጥኑ መምህራን መብዛት፣ በአቅም የተሻሉ መምህራን ቢኖሩም በቤተሰብና ዝምድና የተሳሰረ ነው ለሚሉት አስተዳደር ጥገኛ መኾናቸውና አካዳሚያዊ ነጻነት ማጣታቸውን ደቀ መዛሙርቱ ይዘረዝራሉ፡፡

ደቀ መዛሙርቱ በጸሎት ሱባኤ ቆይታቸው በኮሌጁ ጉዳይ ብቻ ሳይወሰኑ በአጥቢያ ደረጃ ስላለው የቤተ ክርስቲያን አስተዳደርም አንሥተዋል፡፡ ‹‹በአጥቢያ ደረጃ የቤተ ክርስቲያናችን ሀብትና ንብረት በአምስቱ ከለባት ቤተሰባዊነት የጥቅመኞች ሲሳይ ኾኗል›› ይላሉ ደቀ መዛሙርቱ፡፡ ‹‹አምስቱ ከለባት›› የሚሏቸው የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችን፣ ጸሐፊዎችን፣ ሒሳብ ሹሞችን፣ ቁጥጥሮችን እና ገንዘብ ያዦችን ነው፡፡

ደቀ መዛሙርቱ የፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴውን የሚተቹት በኮሚቴው ከተካተቱት አባላት በመነሣት ነው፡፡ በተለይም ቀድሞ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሳሉ እናውቃቸዋለን በሚሏቸው የአስመራጭ ኮሚቴው ጸሐፊ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጩ ላይ በመተኰር ዘረኝነትን፣ ሙስናንና ብልሹ አሠራርን በማንሰራፋት ይወቅሷቸዋል፡፡ በዚህ አስመራጭ ኮሚቴ አስፈጻሚነት ሊመረጥ የሚችለው አባት የኮሚቴውን ጸሐፊ ከሚወቅሱባቸው ጉዳዮች (ዘረኝነት፣ ሙስና፣ ብልሹ አሠራር) የጸዳ ስለመኾኑም ደቀ መዛሙርቱ ይጠይቃሉ፡፡

አቡነ ሳሙኤል

የኮሌጁ ተማሪዎች ጥርጣሬያቸውን ከኮሚቴው አባላት ወደ መራጮች በማሻገር በተለይም ከየአህጉረ ስብከቱ በየሊቃነ ጳጳሳቱ በሚመራ የአስተዳደር ጉባኤ ስብሰባ ተወክለው ከሚመጡት መራጮች ድምፅን በገንዘብ/በጥቅም ለመግዛት ከፍተኛ ዘመቻ እየተካሄደና ጫናም እየተፈጠረ መኾኑን አስረድተዋል፡፡ ተጽዕኖው በውል ዘርዝረው ካላሳወቋቸው ሊቃነ ጳጳሳትም አካባቢ እንደታየ የሚናገሩት ደቀ መዛሙርቱ ምርጫው መካሄዱ የማይቀር ከኾነ ዘንድ ቀደም ሲል በየመዋቅሩና በየተቋማቱ ከተጠቀሱት የዘረኝነት፣ ሙስና እና ብልሹ አሠራር የጸዳ፤ በበሳል አመራር ሰጪነቱና በአስተዳደር ችሎታው የተመሰከረለት፣ ብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ ግዴታዎቹን በብቃት መወጣት የሚችል ዕጩ ፓትርያሪክ እንዲጠቆም ጠይቀዋል፡ የዕጩውን ማንነትም ወስነው አሳውቀዋል፤ የሚመረጠው ፓትርያሪክ ሊያሟላቸው ይገባል፣ በቀኖና ቤተ ክርስቲያንም የተደገፉ ናቸው ያሏቸውን መመዘኛዎችንም ዘርዝረዋል፡፡

በደቀ መዛሙርቱ የፓትርያሪክ መመዘኛ መስፈርት መሠረት የሚመረጠው አባት፡-
•ባለራእይ ማለትም የቤተ ክርስቲያኒቱን ዓላማ ሁለገብ በኾነ መልኩ ለሁሉም ተደራሽ በማድረግ የሚያስፈጽም፤
•ለሰው ልጆች እኲልነት የቆመ÷ እግዚአብሔር በአርኣያውና በአምሳሉ የፈጠረውን የሰው ልጅ ትንሽ ትልቅ ሳይል በማክበር ፍትሕ በመስጠት ማገልገልና በየትኛውም መንገድ እግዚአብሔር የሰጠውን ነጻነት ከመጥፎ ነገር መጠበቅና ማስጠበቅ የሚችል፤
•በበጎ ሥነ ምግባሩና ትሩፋቱ የተመሰከረለት፤
•የቤተ ክርስቲያኒቱን ዶግማ፣ ቀኖናና ትውፊት የሚጠብቅና የሚያስጠብቅ፤
•የቤተ ክርስቲያኒቱ ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት አጠናክሮ የሚቀጥል፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ክብሯ እንደተጠበቀ ከሁሉም ጋራ በሰላምና በፍቅር እንድትኖር ማድረግ የሚችል፤
•በቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ውስጥ መንግሥትና ሕዝበ ክርስቲያኑ እንዲሁም ልዩ ልዩ ተቋማት መልካም ግንኙነት እንዲኖራቸው የሚያደርግ፣ በየዘርፉ ባለሞያዎችን በማማከር የሚሠራ ሥርዐት መዘርጋት የሚችል፤
•የቤተ ክርስቲያኒቱን ሠራተኞች በሞያቸውና በክህሎታቸው በሚገባቸው ቦታ ማስቀመጥ (The right person at the right place) የሚለውን መርሕ የሚከተል፤
•የአብነት ት/ቤቶች፣ የካህናት ማሠልጠኛዎች፣ መንፈሳዊ ኮሌጆች ተሻሽለውና ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እንዲሁም ተጨማሪ ኮሌጆች እንዲከፈቱ የሚያደርግ፤
•የቤተ ክርስቲያኒቱ ተከታዮች በሚናገሩት ቋንቋ ሁሉ አስተምህሮዋን የሚገልጹ መጻሕፍትን እየተረጎመችና እያሳተመች ማዳረስ እንድትችል የሚያደርግ፤
•የቤተ ክርስቲያኒቱን የገንዘብ አስተዳደር ማእከላዊ በኾነ መልኩ እንደ መንግሥት አስተዳደር ከከተማ እስከ ገጠር ላሉት አብያተ ክርስቲያን በስኬል ደረጃ እንዲዳረስ ማድረግ የሚችል፤
•ለቤተ ክርስቲያኒቱና ለሀገሪቱ የዕድገት ማነቆ እየኾነ የመጣውን ዘረኝነትንና ሙስናን የሚያስቀር ጠንካራ አስተዳደር መዘርጋት የሚችል፤
•የቤተ ክርስቲያኒቱን ንብረቶች ማለትም ቅርሶች፣ የታሪክ ቦታዎች፣ ገዳማት በአጠቃላይ ውድ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አንጡራ ሀብቶቿን በመከባከብ መጠበቅና ማስጠበቅ ብሎም በአግባቡ መጠቀም የምትችልበትን ሥርዐት መዘርጋት የሚችል፤
•የተዘጉ አብያተ ክርስቲያንና ገዳማትን ወደ ህልውናቸው መልሶ አገልግሎት የሚሰጡበትን ሥርዐት መዘርጋት የሚችል፤
•የሉላዊነትን (ግሎባላይዜሽን) ጥቅሙንና ጉዳቱን በመለየት ሃይማኖት፣ ምግባርና መልካም ባህል ላለው ሕዝባችን ማስረዳት የሚችል፤
•ከአገር ውጭ በሥራ ምክንያት በዓለም ዙሪያ ተሰራጭተው ላሉ ምእመናን መንፈሳዊ አገልግሎት የሚያገኙበትን ኹኔታ የሚያመቻች፤

በአጠቃላይ ዘመኑን የሚዋጅ የቤተ ክርስቲያኒቱን እሴቶች የሚጠብቅና ከአሁኑ ትውልድ አንጻርም መግባባት ይቻል ዘንድ ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋራ በአግባቡ መተዋወቅ የሚችል፣ ከዓለም ቋንቋዎች አንዱ የኾነውን እንግሊዝኛን መናገርና መስማት የሚችል መኾን ይጠበቅበታል፡፡

በዚህ የፓትርያሪክ መመዘኛ መስፈርት መሠረት ደቀ መዛሙርቱ [ለፓትርያሪክነት] ለዕጩ ፓትርያሪክነት ይበቃሉ በማለት የጠቆሟቸው አባት÷ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ናቸው፡፡

ደቀ መዛሙርቱ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን ለዕጩ ፓትርያሪክነት [ለፓትርያሪክነት] ያበቋቸዋል ያሏቸውን ብቃታቸውን ዘርዝረዋል፤ እንዲህ ሲሉ፡-
•በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከ60 በላይ አብያተ ክርስቲያን አሳንጸዋል፡፡
•በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፣ በቅ/ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን፣ በአዲሱ ቅ/ሚካኤል፣ በጎፋ ቅ/ገብርኤል፣ በላፍቶ ቅ/ሚካኤል፣ በብሥራተ ገብርኤል፣ በአየር ጤና ኪዳነ ምሕረት፣ በኮተቤ ኪዳነ ምሕረት፣ በአቃቂ መድኃኔዓለም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶችን አስገንብተዋል፡፡
•ወቅታዊ ተጨባጭ ኹኔታዎችን ለማሳወቅ ለመላው አዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት ካህናት በየስድስት ወሩ ሥልጠና እንዲሰጥ አድርገዋል፡፡
•ከፍተኛ ግምት የተሰጠውን የአዲስ አበባን ሀ/ስብከት መንበረ ጵጵስና በሚያስገርም ኹኔታ አሳንጸዋል፡፡
•ከ40,000 በላይ የኾኑ በደቡብ ኦሞ፣ በቤንች ማጂና በቤንሻንጉል ጉሙዝ አካባቢ የሚኖሩ ኢጥሙቃን ወገኖችን አስጠምቀዋል፡፡
•በዲቪዲ እና በቪሲዲ ቁጥራቸው ከስድስት በላይ የኾኑ ትምህርታዊ ሥርጭቶችን ለምእመናን አሠራጭተዋል፡፡
•ከ10 በላይ ወቅታዊ መጻሕፍትን አሳትመው አሰራጭተዋል፡፡ እኒህም፡- ባሕታውያን በዋልድባ ቁጥር 1፤ ረዐይኬ አባግዕዬ፤ ባሕታውያን በዋልድባ ቁጥር 2፤ ሰዶማውያን የኀጢአት ደመወዝ፤ ቤተ ክርስቲያንና አስተዳደር፤ Sodomites and the wage of sin፤ ድህነትና ኢትዮጵያ፤ በኢትዮጵያ የሃይማኖት መቻቻል አለን? ታሪክህን ዕወቅ፤ መሪና አመራሩ፤ ፈለገ አሚን ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሲኾኑ ከሌሎች አካላት ጋራ ተዘጋጅተው የታተሙ መጻሕፍት ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ ሁለት ሺሕ ዓ/ም፤ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዐተ አምልኮ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅርሶች ናቸው፡፡ ከመጽሐፎቻቸው ጀርባ እንደገለጹት ለወደፊት ሊታተሙ የተዘጋጁ መጻሕፍት ደግሞ፡- እውነተኛ መሪ ማን ነው?፤ ቤተ ክርስቲያንን ትጠብቋት ዘንድ ለመንጋውና ለራሳችኹ ተጠንቀቁ፤ ስለ ቤተ ክርስቲያን ማን ይናገር? የሚሉ ናቸው፡፡
•በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና በግብጽ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መካከል ለአምስት ቀን የቆየ ዐውደ ትምህርት እና የልምድ ልውውጥ እንዲደረግና የሁለቱ አገሮች ሰላማዊ ግንኙነት እንዲጠነክር አድርገዋል፡፡
•ለሚማሩና ራሳቸውን ለሚያሻሽሉ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ሁሉ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋሉ፡፡
•ከቻይና ኖሬላ ካምፓኒ ጋራ ከስድስት በላይ ለሚኾኑ የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት አድባራት በአንድ ቢልዮን ብር ሆስፒታልና ልዩ ልዩ ልማታዊ ሥራዎችን ለመሥራት ተፈራርመው ነበር፤ ይህም በቻይናውያን TODAY ጋዜጣ ላይ ለዘገባ በቅቷል፡፡
•የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት በከፍተኛ ደረጃ የሚቃወመውንና ብሎም ለማጥፋት የሚታገልበትን አሳፋሪ ሙስና (ብልሹ አሠራር) እና ዘረኝነት በከፍተኛ ደረጃ በመቃወም ጽኑ አቋም አሳይተዋል፡፡
•ገዳማት ተከብረው እንዲቆዩና በልማት ራሳቸውን እንዲችሉ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ በአጠቃላይ በበሳል አመራር ሰጪነታቸውና በአስተዳደር ችሎታቸው የተመሰከረላቸው አባት ናቸው፡፡ በመኾኑም ይህን ክቡር ዓለም አቀፋዊና ብሔራዊ ሓላፊነት በብቃት ይወጡታል ብለን ስላመንን፣ በተሰጠን ዕጩ ፓትርያሪክ የመጠቆም መብት መሠረት ለስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ ዕጩ ፓትርያሪክ ይኾኑ ዘንድ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የጠቆምን መኾኑን በአክብሮት እንገልጻለን፡፡

በፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንቡ አንቀጽ 7 ንኡስ አንቀጽ 1/ሰ መሠረት÷ ከቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ ኮሌጆች መምህራንና ደቀ መዛሙርት ከእያንዳንዳቸው ሁለት፣ ሁለት መራጮች የሚወከሉ ሲኾን ከሁለቱ አንዱ የደቀ መዛሙርቱ ተወካይ ሌላው ደግሞ የመምህራኑ ተወካይ መኾኑ ተደንግጓል፡፡ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት የካቲት 4 ቀን 2005 ዓ.ም በሦስት ገጽ አዘጋጅተው ለአስመራጭ ኮሚቴው ጽ/ቤት ያደረሱትና ለሐራዊ ምንጮች ያስታወቁት ጥቆማቸው፣ የኮሌጁ መምህራንና የተቀሩት ሁለት ኮሌጆች (ሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ እና መቐለ ቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን) መምህራንና ደቀ መዛሙርት ይስማሙበት ወይም አይስማሙበት አልተረጋገጠም፡፡

ስለ ኮሌጁ ደቀ መዛሙርት ጥቆማ አስተያየታቸውን የተጠየቁ የምርጫው ሂደት ታዛቢዎች እንደተናገሩት፣ በፓትርያሪክነት መመረጥ ስለሚገባው አባት በተማሪዎቹ የተዘረዘሩት መስፈርቶች በራሳቸው ጎጂዎች አይደሉም፡፡ ይኹንና የፓትርያሪኩን ሥልጣንና ተግባራት ከአባታዊና መንፈሳዊ ተግባሩ በላይ አብዝተውና አግዝፈው የተቋማቱን ሚና በመተካት የሚያስቀምጡ ናቸው፡፡ በምትኩ የተዘረዘሩት ሥራዎች በአመዛኙ ዘመን የተሻገራቸውን የቤተ ክርስቲያኒቷን የአመራርና የአስተዳደር ተቋማት በመገንባትና በማጎልበት፤ ተገቢና ትክክለኛ መዋቅር፣ ስትራተጂና ፖሊሲ ዘርግቶ ካህኑንና ምእመኑን በሰፊው በማሳተፍ ሊመለስ ይችላል ያሉት ታዛቢዎቹ፣ በመመዘኛነት የተጠቀሱት ተግባራት በዋናነት ለፓትርያሪኩ ግለሰባዊ(?) ብቃት የሚተዉ ከኾነ የቀድሞው ፓትርያሪክ ዐይነት አስተዳደራዊ ዐምባገነንት፣ ሙስናና ብልሹ አሠራር መንሰራፋቱን እንደሚቀጥል አይጠራጠሩም፡፡

ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል

ታዛቢዎቹ እንደሚሉት፣ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንቡ ከተቀመጠው መመዘኛ መካከል በዕድሜያቸው አነስተኛው መነሻ – 50 ዓመት – ላይ ይገኛሉ፡፡ በጥቆማው የተዘረዘረው የብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የሥራ ፍሬዎችም የተወሰኑት በተጨባጭ፣ የተቀሩትም በዝንባሌ ደረጃ ሐቅ ወይም የሐቅ ጠረን ያላቸው ናቸው፤ ነገር ግን ጥቂቶቹ በተለያዩ አጋጣሚዎች በጉልሕ እየተነሣ ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ ሲነቀፉባቸው የነበሩትን ትችቶች ያላገናዘቡ፣ የተለጠጡና ከራሳቸው ከደቀ መዛሙርቱ መመዘኛዎች ጋራ የሚጋጩ ነጥቦች አልታጡበትም – እንደ ታዛቢዎቹ አስተያየት፡፡

‹‹የተመረጠው ፓትርያሪክ አስቀድሞ ታውቋል፤ ምርጫው ለሽፋን ነው የሚካሄደው›› ስለሚለው ጥቂት የማይባሉ ወገኖችን ትችት በተለያየ መንገድ ከሚወስዱት ታዛቢዎቹ፣ የተወሰኑት÷ የመንግሥትን ፍላጎት ቀዳሚና ዐቢይ መወሰኛ በማድረግ ከሊቃነ ጳጳሳቱ ማንኛቸውም ለፓትርያሪክነት ቢታጩ/ቢመረጡ አብዛኞቹ ፈቃዱን/ተጽዕኖውን ሊጋፉት/ሊቋቋሙት እንደማይችሉ ስላረጋገጠ (በእነርሱ ቀጥተኛ አነጋገር – መንግሥት ጳጳሳቱን ዐውቆ፣ ንቆ ስለጨረሳቸው) የተመረጠው እንዲመረጥ እንጂ ወስኖ ያስቀመጠው የለም ይላሉ፡፡ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ለፓትርያሪክነት እንደሚመረጡ አረጋግጠው ለሚናገሩትም፣ ታዛቢዎቹ÷ ብፁዕነታቸው አንዳንድ አቋሞቻቸው የማይገመትና ለመንግሥትም የሚያስቸግር መኾኑን በመጥቀስ ይኹንታ ማግኘታቸውን ይጠራጠራሉ፡፡ ሌሎችም ብፁዕነታቸው ለውጭ አካላት የማይገመቱ አቋሞች ሊወስዱ እንደሚችሉ አምነውና ይህም በተጽዕኖ አሳዳሪዎች ዘንድ እንደማይወደድ ተቀብለው ሲያበቁ ነገር ግን የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅሞ ተገማች ያልኾኑ አቋሞቻቸውን በማቀብ በቦታው መቀመጣቸውን ሊፈቅድ እንደሚችል ይተነባሉ፡፡

Latest from Blog

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop