February 5, 2023
12 mins read

መልእክተ-አንቃእድዎ ! ጤና ይስጥልኝ፤ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ

መርሐጽድቅ መኮንን እሰኛለሁ፡፡

የከበረ ሠላምታዬን እያስቀደምኩ ከሁሉ በፊት እንደምን አሉ ማለት ይኖርብኛል፡፡
ቸሩ እግዚአብሔር ይመስገን፤ እኔ ለጊዜው ደህና ነኝ፡፡

የርስዎን አእምሯዊ የጤንነት ሁኔታ ግን በእጅጉ መጠራጠር ከጀመርኩ ውዬ አድሬያለሁ፡፡ በርግጥ ይህንን የምናገረው በተሰበረ የሀዘን ልብ እንደሆነ ከወዲሁ ልገልጽልዎ እወዳለሁ፡፡

abiy dividerክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር

በሀገራችን አማካሪ የሌለው ንጉስ፣ ያለአንድ ዓመት አይነግስ የሚል ቱባና እድሜ-ጠገብ ብሂል እንዳለ አውቃለሁ፡፡

በርግጥ ይህ አባባል በቁሙ ሲነገር እርስዎን አይመለከት ይሆናል፡፡ የመንግሥት ሥልጣን ከጨበጡና ስርአተ-ዘውድ አከል በሆነ መንገድ በይፋ ከነገሱ እኮ አምስት ዓመት ሊደፍኑ የቀሩዎ በጣት የሚቆጠሩ ወራት ብቻ ናቸው፡፡

ያም ሆኖ ምከረው ምከረው፣ እንቢ ሲል መከራው ይምከረው እንዲሉ አቢይ አህመድ ፈጽሞ ተመክረው የሚድኑ ሰው አይደሉም፡፡ በኔይቱ አቅም እንኳ ስንት ጊዜ ልመክርዎ ሞክሬያለሁ፡፡ እርስዎ ግን ለመስማት የሚወዱትን ብቻ እየመረጡ የሚሰሙ ግብዝ ሰው ይመስሉኛል፡፡

ይልቁንም ለቅርብና ለሩቅ አማካሪዎችዎ ሳይቀር አለቅጥ የበዛ ንቀትና እብሪት እንደተጣባዎ ለመገመት እደፍራለሁ፡፡ ለዚህም በየጊዜው ለተሳሳቱ ውሳኔዎች እየተዳረጉ እንደመጡና ይህም በውጤቱ መንግሥትዎን ወደገደል አፋፍ እንዳስጠጋው የምሬን እያዘንኩ ልነግርዎ እፈልጋለሁ፡፡

ብወድም ባልወድም መሪዬ ለመሆን በቅተዋልና እንደአንዳንድ አድር ባይ ባለሟሎችዎ ይወዱት ይሆናል ብዬ የምገምተውን ብቻ በመጻፍ ያለአግባብ እያሞጋገስኩና እንደቅርብ የሀይማኖት አማካሪዎችዎ በሀሰተኛ ትንቢት ልብዎን እየሰቀልኩ ላታልልዎ ፈጽሞ አልፈልግም፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር

ከተራዘመ ዳተኝነት በኋላ ዝምታዎን ድንገት ሰብረው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን ውስጥ የተፈጠረውን ክፍፍልና በህልውናዋ ላይ ያንዣበበውን አደጋ በተመለከተ ጥር 23 ቀን 2015 ዓ.ም አመሻሹ ላይ በሀገሪቱ ራዲዮና ቴሌቪዥን ብቅ ብለው የሰጡትን የአይመለከተኝም ማብራሪያ አይሉት ማደናገሪያ ዲስኩር እንደብዙዎች ሁሉ አልወደድኩልዎም፡፡ እርሱ ከትክክለኛው መስመር የወጣ፣ መንግሥታዊ ኀላፊነትን የዘነጋ፣ ለሕጋዊ ተቋማት ልእልና ተገቢውን ክብር የነፈገ፣ የአንድ ወገን አድልዎ የተጠናወተውና ሌላው ቀርቶ በቀላሉ ሊታረሙ ይችሉ በነበሩ አያሌ የፍሬ-ነገር ህጸጾች የተሞላ ዲስኩር ነበር፡፡

በርግጥ በጸላኤ-ሰናያት የቅርብ እገዛ የተደረሰ የሚመስለውን ያንኑ ሀተታ-መናፍስት የጥቃቱ ቀጥተኛ ሰለባ የሆነችው የራሷ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ በብርሃን ፍጥነት ተከታትሎ በዝርዝር የተቸውና ሳይውል ሳያድር ህዝባዊ ቅቡልነት ያሳጣው ስለሆነ ጉዳዩን እንደገና አንስቼ ከዚህ በላይ ላቆስልዎ አልሻም፡፡

ሆኖም መንግሥትዎ እንደሚረዳው አደጋው ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ የዚያ መርዘኛ ዲስኩርዎ ውጤት ሕገ-ወጡንና አፈንጋጩን ቡድን ለከፋ ጥፋት አነሳስቶ በተከታዮቹ ወሮበሎች አማካኝነት ለተቀጣጠለው አመጽና ግርግር ነዳጅ ሆኖ በማገልገሉ በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ ቤተ-ክርስትያኗ ያለአግባብ ተደፍራለች፣ በሮቿ እየተገነጠሉ ንዋየ-ቅድሳቷ ተዘርፏል፣ ቅርሶቿ በእሳት ጋይተዋል፣ ወድመዋልም፡፡

የአርሲ-ነገሌንና ሻሸመኔ ከተሞችን ጨምሮ በአንዳንድ ስፍራዎችማ የቤተ-ክርስትያኒቱን ደህንነት ለመከላከል የወጡና ሕጋዊ ይዞታዎቿን ከጥፋት ለመታደግ የሞከሩ መሳሪያ ያልታጠቁ ምእመናን ከመንግሥት የጸጥታ ሀይሎች በተተኮሰ ጥይት እየተደበደቡ ውድ ህይወታቸውን ተነጥቀዋል አካላዊ ጉዳትና ስቃይ የደረሰባቸውም ብዙኃን ናቸው፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሆይ

በተለየ መልኩም ቢሆን እርስዎም ሆኑ ቤተ-ሰብዎ ሀይማኖትን የምትለማመዱ ይመስለኛል፡፡ የእምነትዎ መሰረትም ሀዲስ ኪዳን እንደሆነ እገምታለሁ፡፡

እንዲያ ከሆነ ደግሞ የቆመ የመሰለው ሁሉ እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ ሲል ሀዋርያው ጳውሎስ አብዝቶ የተጠበበበትን ዝነኛና ዘመን ተሻጋሪ መልእክት ደጋግመው እንዳነበቡ አምናለሁ፡፡

እነሆ ሁለቱም በመንታ እግሮቻቸው ለጊዜው ጸንተው የቆሙ ይምሰልዎ እንጂ የሚወዱት ዙፋንዎ ለውድቀት፣ የሚመሯት ሀገርዎ ደግሞ ለመፍረስ በአደገኛ ሁኔታ ተቃርበዋልና እንደእኩያን ጠላቶቻችን ፍላጎትና ምኞት ሂደቱ ተቀላጥፎ ለአስከፊው ፍጻሜ ከመዳረጋችን በፊት ከዚህ በታች የተመለከቱትን እርምጃዎች በድፍረት እንዲወስዱ ዛሬም እንደገና ከተቀበሉኝ በታላቅ ወንድምነት አለበለዚያም በተራ ዜግነት አቋም እመክርዎታለሁ፣ እማጸንዎታለሁም፡፡
(ምክር ሠናይ ለኩሉ ዘይገብራ) ተብሎ ተጽፏልና፡፡

1.ጥር 23 ቀን 2015 ዓ.ም ምሽት ላይ እሳት ለብሰው፣ እሳት ጎርሰው የሰጡትን ማብራሪያ እንዳለ ይጠፉና በይፋ ወጥተው ቅድሥት ቤተ-ክርስትያንና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ምእመናኗን በተለይ፣ መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ በአጠቃላይ ይቅርታ ይጠይቁ፤
2.አጥር ሰብሮና ቅጥር ጥሶ ወደመኖሪያ ቤትዎ የገባን ሌባና ወንበዴ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ተከላክሎ ከመመለስ ወይም በተመጣጣኝ ሀይል ይዞ ለፍርድ ከማቅረብ በስተቀር የተሻለ አማራጭ እንደሌለ አውቀው ቅዱስ ሲኖዶሱንና የቤተ-ክርስትያኒቱን ቀኖና ተላልፎ ያፈነገጠውን ቡድን አባላት ለኀላፊነትዎ በማይመጥንና የመንግሥትዎን ገለልተኝነት ከባድ ጥያቄ ውስጥ በሚያስገባ የተለሳላሺነት አቀራረብ ለማሸማገል የሚያደርጉትን የቀቢጸ-ተስፋ እንቅስቃሴ እባክዎ ያቁሙ፤
3.በአፈንጋጩ የቀድሞ ሊቃነ-ጳጳሳት ስብስብ ሕገ-ወጥ ስምሪትና በኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ፖሊስና የጸጥታ ሀይሎች ድጋፍ የሚካሄደውን የአብያተ-ክርስትያናትና አህጉረ-ስብከቶች ጽ/ቤቶች ወረራና የጠራራፀሃይ ዝርፊያ ያለተጨማሪ መዘግየትና የባሰ ጥፋት በማስቆም ሕግና ስርአት ወደነበረበት ሁኔታ እንዲመለስ ለተጠቀሰው ክልላዊ መስተዳድር ቀጭንና የማያዳግም ትእዛዝ ያስተላልፉ፤
4.የማይናወጥ ሕገ-መንግሥታዊ ኀላፊነትና ግልጽ የሆነ አለም-አቀፋዊ ግዴታ እያለበት በጊዜው ሕጋዊ ከለላ ካለማድረጉና ጥበቃ ካለመስጠቱ የተነሳ መንግሥትዎ ያሳየውን የበዛ ዳተኝነት ተጠቅመው በቅድስት ቤተ-ክርስትያኒቱና በንጹሃን ምእመናኖቿ ላይ የነፍስ ግድያና ውንብድናን ጨምሮ የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶችን የፈጸሙና የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ያደረሱ ወገኖች ሁሉ በሀገሪቱ ሕግ መሰረት ደንበኛው የወንጀል ምርመራ እንዲጣራባቸውና ሥልጣን ባለው ፍርድ ቤት ተከሰው ተመጣጣኝ ቅጣት እንዲወሰንባቸው ለክቡርነትዎ በቀጥታ ተጠሪዎች ለሆኑት ለፌደራል ፖሊስ ኮምሽንና ለፍትሕ ሚኒስቴር የማያወላውል የስራ መመሪያ ይስጡ፤
5.ሕገ-ወጡ ቡድን ከማእከላዊው ቅዱስ ሲኖዶስ እውቅናና ፈቃድ ውጭ የራሱን ኤጲስጶጶሳት ከሾመና ከዚኅ የተናጠል አድራጎቱ የተነሳ ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም በውግዘት እንዲለይ ከተደረገ በኋላ የየአካባቢውን ማሕበረ-ሰብ በማነሳሳትና ወራሪዎችን በማሰማራት በቤተ-ክርስትያኒቱም ሆነ በምእመናኖቿ ላይ የደረሰው ህልፈተ-ህይወት፣ አካላዊ ጉዳትና ቁሳዊ ውድመት በወጉ ተጣርቶ ተገቢው ካሳ እንዲከፈል ይዘዙ፡፡

ማስገንዘቢያ
ለዚህ የጉዳት ካሳ ክፍያ እርስዎ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ብቻ ሳይሆን በጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዛዢነት ጭምር የሚመሩት ማእከላዊ መንግሥት በእጅ-አዙር ተጠያቂ ሲሆን ቀዳሚው ኀላፊነት ግን በቀጥታ የሚወድቀው በኦሮምያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ላይ ይሆናል፡፡

አመሰግናለሁ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
Go toTop